ኢትዮጵያዊ አብሮ መኖሩ፣ አንተ ትብስ አንተ ብሎ ተቻችሎ፣ አንዱ ላንዱ ክንዱ እንጂ ደመኛው ሳይሆን፤ በቤተሰብ መካከል አልያም በጎረቤት ችግር ሲፈጠር አንተም ተው አንተ ተው ተባብሎ በሽማግሌ ሰላም የሚያወርድ፤ የተፈጠረውን ችግር ሁሉ ረስቶ እንደቀድሞ ለመሆን የሚችል ቅን ልብ ያለው ህዝብ ነው።
ልጆቹን እንኳን ሳይሰስት ለእህት ለወንድሙ ከዛም ራቅ ብሎ ላመነበት እንዳንተ እንዳንቺ አድርገሽ አሳድጊ ይጠቅምሻል፤ ትጠቅምሻለች ብሎ ለመስጠት የማይሳሳ ለየት ያለ የመተሳሰብ ባህል ባለቤት ነው ።ይህ ከፍቅር የሚመነጭ አብሮነት ለብዙ ዓመታት አብረን እንድንኖር ዓለም እንደ ብርቅ እንዲያየን ስለ እኛ እንዲያስብና እንዲመራመር ያስገደደ ሃቅ ነው።
ዛሬ ይህ ሁሉ አደጋ ውስጥ ገብቶ ለእኛም ለአለምም ግር በሚያሰኝ ችግር ውስጥ ወድቀን እንገኛለን ፤ ወንድም በወንድሙ ላይ እየጨከነ ያለበት መንገድ ከሰው ልክ የሚያወጣን እየሆነ ነው። ለምን በአግባቡ ልንጠይቀውና ምላሽ ልንሰጠው የተገባ ጉዳይ ነው ።
የትናንት ታሪካችን ሩህ ሩህ ልብ ያለን፣ ካለቀሰ ጋር አብረን የምናለቅስ፣ ሳይኖረን የምናካፍል፣ ለእኛ ይቅርብን ብለን የሌሎችን ችግር ለመድፈን የማንሳሳ ነበር። ይህ ወርቃማ እሴታችን የት ሄደ?
ምናልባት መሰልጠን መሰይጠን ሆኖብን ይሆን? በወንድም እህቶቻችን ላይ እንድንነሳ ያደረገን? ወይስ እምነቱም ባህሉም ሁሉንም ጣልነውና የተጫነብንን የስግብግብነትና የራስ ወዳድነት መንፈስ ተግተን በአደባባይ ሰከርን? ያለንበት ሁኔታ፤ እየሄድንበት ያለው መንገድ ሁሉም ግራ የሚያጋባ፤ ከእኛ ኢትዮጵያውያን ፍጹም የማይጠበቅ ለማመን የሚያስቸግር ሆኗል።
በእርግጥ አሻባሪው ሕወሓት ባለፉት 30 ዓመታት የጫኑብን የዘር ፖለቲካ ለዚህ እንዳበቃን ለመናገር የሚከብድ አይደለም፤ ስለምን ግን ይህንን መርዝ በዚህ ደረጃ ተጋትነው? ቡድኑ በቀደደልን እኩይ መንገድስ ለምን በዚህ ደረጃ ፈሰስን? ።
እንደ እኔ አንድ ሰው አገሩ የተወለደበት ሳይሆን ያደገበት ፣ንብረት ያፈራበት፣ ቤተሰብ መስርቶ ወግ ማዕረግ ያየበት ነው።የእኛ የኢትዮጵያውያን ኑሮም እንደዛው ነው። ሰሜን የተወለደ ምናልባት እድገቱና ኑሮው ቤተሰቡን የሚመሰርተው ወይም የመሰረተው ደቡብ ሊሆን ይችላል።ይህ ሰው ታዲያ በዘሩ ምክንያት ችግር ደረሰበት ተብሎ ሲነገር መስማትን ያህል ከባድ ዜና ከወዴት ይገኛል።
ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት እያልን ደጋግመን እንናገራለን፤ አዎ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት፤ ያውም ሁሉም የየራሳቸው መገለጫ ያላቸው ባህላቸው፣እንግዳ አቀባበላቸው፣ ጋብቻ ስርዓታቸው፣ የችግር አፈታት ዘዴያቸው (ሽምግልናቸው) ኸረ ስንቱ ሁሉም የየራሱ ውብ ባህልን የያዘ ነው።
ከዚህ ውስጥ ደግሞ ለእኔ ኦሮሞና ባህሉ እጅግ ይለይብኛል ።ሰው አክባሪነት፣ ልምላሜ ወዳድነት፣የልጅ ፍቅር፣ እንኳን የወለደውን ሰው የወለደውን ተቀብሎ ከልጁ በላይ አሳድጎ ወግ ማዕረግ የሚያደርስ፤ ተካፍሎ አካፍሎ መብላትን የሚያውቅ፣ በገዳ ስርዓት የራሱን ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መስርቶ ለአገር ተምሳሌት በሆነ መልኩ የሚኖር ድንቅ ህዝብ ነው።ዛሬ ግን እያየን ያለነው ነገር እውነት የኦሮሞ እናት ማህጸን ያፈራቻቸው ሰዎች ናቸው፤ አገርን በዚህ ልክ ማቅ እያለበሱ ያሉት ያስብላል።
በገዳ ሥርዓት መሰረት ወንድም ወንድሙን መግደል አጸያፊ በመሆኑ ወንድሙን የገደለ ሰው ከጎሳው ተለይቶ ሰባት ወንዝ ተሻግሮ እንዲኖር እንደሚደረግ አባ ገዳዎች ይናገራሉ፡፡ታዲያ ዛሬ ወንድም እህቶቻቸውን ህጻናትን ሳይቀር በግፍ በማያውቁት ነገር እየገደሉ ያሉት የሰው አውሪዎች ላይ ምን ዓይነት ፍርድ ነው የምንጠብቀው? እንጃ ማሰብ ራሱ ይከብዳል።
በኦሮሞ ባህል እርስ በእርስ መታኮስ ከገዳ እሴቶች ጋር የሚጣረስም እንደሆነ ነው አባገዳዎቹ የሚናገሩት፡፡ በስርዓቱ መሰረት የማስታረቅ ስራዎች ካልተሰሩ በስተቀር ገዳይ ወደ ኅብረተሰቡ እንደማይቀላቀልም ይነገራል ።በኦሮሞ ስም የሚታገል ሁሉ ለገዳ ሥርዓት እሴቶች በመገዛት ራሱን ከዚህ አይነት አፀያፊ ድርጊት ሊያርቅ እንደሚገባም ነው አባገዳዎች የሚናገሩት፤ ታዲያ እነዚህ አውሬዎች ወንድሞቻቸውን እየገደሉ ስለ ምን ሊያወሩ ይችላሉ?
ይህ የክፋት ተግባር በእኛ መካከል መፈጠሩ ያሳዝናል ግን ደግሞ ተፈጥሯል ምንም ማድረግ አይቻልም፤ አሳሳቢው ጉዳይ ግን ከዚህስ በኋላ ሞትን እየተለማመድን መኖር ወይንስ እነዚህን ሰው በላ ቡድኖች አጥፍቶ ሁሉም በአገሩ የትም ሆኖ መኖር እንዲችል ማድረግ? ይህ ሊመለስ የሚገባው ወሳኝ ጥያቄ ይመስለኛል።
አሁን ባለው ሁኔታ ኅብረተሰቡ በሠላም እጦት እየተቸገረ ነው፤ ሠላም ለማስፈን ሁሉም በመነጋገር ለሠላም እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን በማስወገድ መፍትሄ ማስቀመጥ የግድ ነው። ኅብረተሰቡም ሠላም እንዲመጣ የበኩሉን ሁሉ ሊወጣ ይገባል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ወጋችን ነው።ለተፈጸሙ ሰብዓዊ ጥቃቶች ፍትህ መስጠት፣ መሰል ጥቃቶችም እንዳይደገሙ ጥንቃቄ ማድረግ ከመንግስት የሚጠበቅ ለነገ ይደር የማይባል ጉዳይ ነው።
አባቶቻችን ለአያሌ ዓመታት በሰላም አብረው በመኖር አገር እንዳስረከቡን ከታሪክ ተምረናል፣ እኛም ወግ ደርሶን ለማየት ችለናል፤ አሁን ላይ ግን የተለየየ ታረጋ የለጠፉ ግለሰቦች የፖለቲካ ትርፍ ፍለጋ ምንም በማያውቁ ንጹኃን ዜጎች ደም እየቆመሩ፤ በዚህም ብዙ ዋጋ እያስከፈሉን ነው።
ዜጎች በማንነታቸው ብቻ የነዚህ ቆማሪዎች ሰለባ እየሆኑ ነው። በአገሪቱ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን ተለዋዋጭ ባህሪ በመያዝ በሁሉም አካባቢ እየደረሱ ነው።ይህንን ሰንኮፍ ከላያችን ላይ ነቅሎ መጣል ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ ነው።
የጠላቶቻችን ዓላማ ስስ ብላታችንን በማጥናት በተለይ በማንነት እንድንጨራረስና እንድንበተን ተግተው መስራት ነው፤ ከዚህ አንጻር ሰሞኑን የሆነው ነገር በቂ ማሳያ ነው። የጥቃቱ አድማስ ብቻ ሳይሆን አሳቃቂነቱም ከፍ ብሏል።
ይህን ሁኔታ ፈጥኖ መቆጣጠር ያስፈልጋል። “ሳይቃጠል በቅጠል” እንደሚባለው ችግሩን በማያዳግም ሁኔታ ለማስወገድ መንግስት የጀመረውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ በተጠናከረና በተናበበ መልኩ ሊያስቀጥለው ይገባል። በዘመቻው የሚገኘውን ውጤትም በየጊዜው ለህዝብ ማስታወቅ ይጠበቅበታል ።እስካሁን ለጠፋው የሰው ሕይወት ፍትህ ለናፈቀው ህዝብ ፍትህን ማረጋገጥ ቀጣይ አጀንዳ ሊሆንም ይገባል።
የወቅቱ ዋነኛ ስራ መሆን ያለበት የተጀመረውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ በማጠናከር ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ያሉ ዜጎችን መታደግ ነው። መላው ህዝብ በተለይም ጥቃት በሚካሄድባቸው አካባቢ የሚገኙ ዜጎች ዘመቻውን ባላቸው አቅም ሁሉ መደገፍ ይኖርባቸዋል።
በእምነት
አዲስ ዘመን ሰኔ 22 ቀን 2014 ዓ.ም