የሰኔ ወር እንደ አሁኑ የበጀት መዝጊያ ከመሆኑ አስቀድሞ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ወሩ ምን አዲስ ነገር ያመጣልን ወይም ያመጣብን ይሆን ብለው በማሰብ “ምን ያመጣ ሰኔ ?” እያሉ ሲተርቱ ይሰማል። በተለይ ሰኔ እና ሰኞ ከገጠሙ ደግሞ ዘንድሮ በአገራችን ከፍተኛ ችግር ሊመጣ እንደሚችል በእርግጠኝነት ሲናገሩ ይስተዋላሉ።
በነገራችን ላይ ሰኔ እና ሰኞ ገጥመው ኢትዮጵያ አንድም ጊዜ ሰላም ሆና አታውቅም።የኢትዮጵያን ታሪክ በደንብ አገላብጠው ያልተመለከቱ አንድ አንድ ሰዎች ግን የሰኔ እና ሰኞ መግጠምን ችግር ያመጣል የሚለውን ፍራቻ አባቶቻችን እንዲሁ የሚሉት አፈታሪክ አድርገው ይቆጥሩታል።ለጉዳዩ የኢትዮጵያን ታሪክ አገላብጦ ማየት ተገቢ ይመስለኛል ።
አሁን አሁን ግን ሰኔ እና ሰኞ ባይገጥሙም እንኳን በወርሐ ሰኔ በራሱ ኢትዮጵያ በመከራ ማዕበሎች እንድትናጥ የተፈረደባት መስሎ እየታየ ነው።በዚህ ወር ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ፈጽሞ ሊረሷቸው የማይችሏቸው በርካታ አስከፊ የመከራ ማዕበሎች ተፈራርቀዋል። ይህን ስል በርካታ አመክንዮችን በማቅረብ እንጂ እንዲሁ በግብዝነት በመሆኑ በርካታ ማስረጃዎችን በማቅረብ አሳያለሁ።
የሰኔ ወር በመጣ ቁጥር ኢትዮጵያ አያሌ መከራዎች በላይዋ ላይ እየፈሰሱ አላስቆም አላስቀምጥ ሲሏት ተመለክተናል። ይህ ማለት ግን የሰኔ ወር ለኢትዮጵያ ምን መልካም ነገር አስገኝቶላት አያውቅም ማለት አይደለም።ነገር ግን የሰኔ ወር በመጣ ቁጥር ኢትዮጵያ በርካታ መከራዎች በላይዋ ላይ እንደ አሸን እየፈላ እንደአገር ለመቀጠል ስትቸገር ተመልክተናል።
ከጥንት ጅምሮ የሰኔ ወር በኢትዮጵያ ላይ ይዟቸው የመጣቸውን መከራዎች በታሪክ ተመልክቼ ሁሉንም ማቅረብ ባልችልም እንኳ የተወሰኑትን በወፍ በረር ላስቃኛችሁ ወደድኩ።
አንደኛ … የሰኔ ወር እና የኢትዮጰያ ሃዘን … ጀግናው ዘርዓይ ደረስ በአገረ ጣሊያን ለሞት ያበቃው በሰኔ ወር በተፈጠረ አንድ ክስተት ነበር። መቼም ሁሉም ሰው አንድ አይሆንምና ዘርዓይ ደረስ ደግሞ ማን ነው? የሚል አይጠፋ ይሆናል።ስለሆነም ስለጀግናው ዘርዓይ ደረስ ትንሽ ልበላችሁ።
ጀግናው ዘርዓይ ደረስ በኤርትራ ክፍለ አገር ሀማሴን አውራጃ ውስጥ አዝጋ በምትባል መንደር በ1908 ዓ.ም ተወለደ።ኢትዮጵያ በጣሊያን ፋሽስት ነፃነቷ ተደፍሮ በነበረበት ወቅት በወርሐ ግንቦት በ1937 ዓ.ም እ.አ.አ በኢጣሊያ ዋና ከተማ ሮማ ለአስተርጓሚነት ለመስራት ሄደ። ዘርዓይ ደረስ ወደ ኢጣሊያን ለማቅናት ምክንያት የሆነው ደግሞ ብዙ ኢትዮጵያውያን በእስረኝነት ወደ ኢጣሊያ ተወስደው ስለታሰሩና ታሳሪዎቹ ደግሞ ጣሊያንኛ ስለማይችሉ እነሱን በአስተርጓሚነት ለመርዳት ነበር። ዘርዓይ ደረስ ትግሪኛ፣ አማርኛ እና ኢጣሊያ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ የሚናገር ምርጥ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ነበር።
በዶጋሊ ጦርነት ያለቁትን 500 ገደማ ኢጣሊያውያን ለማሰብ ኢጣሊያውያን ሰኔ 7 ቀን 1938 ዓ.ም በሮም ፒያሳ አደባባይ ተሰባሰቡ። ዘርዓይ ደረስም ወደ አደባባዩ እንዲመጣ ጥሪ ተደርጎለት ስለነበር ወደ ግብዣው ቦታ መጣ።
ወጣቱ ዘርዓይ ደረስም ወደ አደባባዩ በመጣ ጊዜ ራስ አሉላን አባ ነጋ በ1871 ዓ.ም በዶጋሊ ጦርነት ጀብዱ የፈፀሙበትን ጎራዴ ወገቡ ላይ ታጥቆ ነበር።በሮም ፒያሳ አደባባይ ጣሊያኖች በዶጋሊ ያለቁባቸው ወገኖቻቸውን ለማሰብ በወጡ ጊዜ በዶጋሊው ጦርነት ወገኖቻቸው ለወሬ ነጋሪ እንኳን ሳይተርፉ እንደ አገዳ የታጨዱበትን የእራስ አሉላ አባ ነጋን ጎራዴ መያዝ ምን የሚሉት ድፍረት ነው? ዘርዓይ ግን አድርጎታል።
ይህ በእንዲህ እያለ የኢጣሊያ ወታደሮች በሁለተኛው ዙር ወረራ ከአገራችን ኢትዮጰያ ሰርቀው የወሰዱትን የይሁዳ አንበሳ ሐውልት በሮም አደባባይ ሲዘባበቱበት ተመለከተ።በዚህም አላበቁ የኢትዮጵያዊያን ኩራት የሆነውን አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን ከመሬት ጥለው እየረገጡ ሲሳለቁበት አየ።በዚህም ክፉኛ በገነ! አንዳች ነገር ሰውነቱን ወረረው! ዘርዓይ ራሱን መቆጣጠር አቃተው።ንዴት በተቀላቀለበት ኢትዮጵያዊ ወኔና አልደፈር ባይነት ግርማ በወገቡ የያዘው ጎራዴ ከሰገቡ አወጣው። አውጥቶትም አልቀረ በአገሩ ሰንደቅ ዓላማ የሚቀልዱትን እና በሞአ አንበሳው ሐውልት የሚሳለቁ ጣሊያኖችን ለ50 ዓመታት በሚያውቁት ጎራዴ አናጋራቸው ! እንደ ገብስ ነዶ ወቃቸው።
ለክብረ በዓሉ የተሰባሰቡ ጣሊያኖችም የዘርዓይን እሳት የሚተፉ እጆች በተመለከቱ ጊዜ ብርክ ያዛቸው።የቻሉት እሮጠው አመለጡ። ያልቻሉት ደግሞ በራስ አሉላ ጎራዴ በዘርዓይ ክንድ ዳግም ተወቁ። በመጨረሻም ጣሊያኖችም ይህን ጀግና ተረባርበው ያዙት።አሰሩትም። ለህልፈት ተዳረገ።ይህ የሆነው በወርሐ ሰኔ ነው። ለዚህ ጀግና ኢትዮጵያዊ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ የጦር መርከብ በስሙ እንዲሰየምለት ተደርጓል።
ሌላው የሰኔ ወር የኢትዮጵያን መከራ የሚጠራ ወር መሆኑን ለማሳያ በሁለተኝነት ያቀረብኩት ታሪክ በዘመነ ኃይለስላሴ የተፈጠረ አንድ ኩነት በወፍ በረር በመዳሰስ ነው። በዘመነ ኃይለስላሴ ኢጣሊያ ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን በወረራ ለመያዝ ባደረገችው ጦርነት በኢትዮጵያውያን ላይ በአለም የተከለከለውን የመርዝ ጋዝ ለጦርነት ተጠቅማ በርካታ ኢትዮጵያውያንን በአሰቃቂ ሁኔታ ገደለች።ይህን ተከትሎ ንጉሱ ወደ ጄኔቭ ሄደው በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ በሚያስረዱ ጊዜ ጣሊያን የፈጸመቸውን ግፍ እንደጥሩ ነገር የቆጠሩ ጽንፈኛ ነጮች በኢትዮጵያውያን የሰቆቃ ጩኸት ጨፈሩ፤ ተዝናኑበትም። ኢትዮጵያውንም ለአምስት ዓመታት በችግር እየተወገሩ እንዲያልፉ ተፈረደባቸው።ይህ ግፍ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመው በፈረንጆች አቆጣጠር 1936 ወርሐ ሰኔ ነበር ።
የሰኔ ወር በኢትዮጵያ ጥፋት ጠሪ ወር እንድለው ያስገደደኝ ሌላው የታሪክ ገጠመኝ ደግሞ በሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም የተደረገው መፈንቅለ መንግስት ነው።ይህ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱ እስከዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ እና በኢትየጵያውያን ላይ መከራን በመከራ እየደራረበ ወደፊት መራመድ እንዳይችሉ ያደረገ ክስትተ ይመስለኛል። ይህን ስል በኢትዮጵያ ንጉሳዊ ስርዓት መቀጠል ነበረበት ለማለት አይደለም።ፈጽሞ እንዲሆንም አልመኘውም። ነገር ግን በወጉ ያልተደራጁ እና የኢትዮጵያን የወደ ፊት እጣ ፈንታ መወሰን የማይችሉ በማርክሲሳዊ እና ሌኒናዊ ንድፈ ሃሳብ ብቻ አብደው ራሳቸውን እንደ አዋቂ የቆጠሩ ቁሞ ቀሮች የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በደንብ ሳያገናዝቡ በእውር ድንብር አብዮት አመጣን በሚል ተደጋጋሚ የሞኝ ዘፈን ራሳቸውን እያታለሉ ኢትዮጵያን ወደ ጥፋት ገደል ለመጣል እና ወደ ገደሉ መሳብ አንድ ብለው የጀመሩበት በዚች ዕለት አድርጌ እቆጥረዋለሁ።
እንደሌሎች አገራት ህዝባቸውን ከጭቆና እና ከባርነት ያላቀቀ መፈንቅለ መንግስት ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያውያን አብዮቱ ፈነዳ የተባለበትን ቀን እንደ ብሄራዊ ቀን እንደሚያከብሩት ለአፍታም አያጠራጥርም።ነገር ግን አብዮቱ ከመጣ በኋላ አብዮቱን የሚመሩት ሰዎች አገሪቱን ለመምራት በራሳቸው አጀንዳ አፍላቂ መሆን ሲገባቸው ከሌሎች አገራት አጀንዳ እየተቀበሉ ከኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ተጻራሪ ህግጋትን እና መመሪያዎችን በማውጣት እና እራሳቸውን ብቻ የለውጥ ሐዋርያ አድርገው በመቁጠር ተፎካካሪ ሃይሎችን ደግሞ ጸረ ለውጥ በማስመሰል ያሳስራሉ፤ ይገድላሉ፤ ያሳድዳሉ።ይህ አካሄድ ደግሞ ኢትዮጵያን ከአብዮቱ ጀምሮ ጦርነት እንዳይለያት ያደረገ ዐብይ ምክንያት ሆኖ እናገኘዋለን።ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጥቁር ቀን መጀመሪያ ስለመሆኑ አብዮቱን በሁለት ስንኝ እንዲህ ስል ለመግለጽ ተገድጃለሁ…
አብዮት አመጣን ብለው የተኩራሩ፣
ስንዴን ለወፍ ጥለው እንክርዳድን ዘሩ።
ከላይ ከተጠቀሱት ኩነቶች በተጨማሪ የሰኔ ወር ይዞ የሚመጣቸው ጦሶች ኢትዮጵያን ለዘመናት ቀፍድዶ መላወሻ የሚያሳጣ ችግር ስለመሆኑ ሌላው ማሳያው ደግሞ በቅርቡ ሰኔ 24 እስከ ሰኔ 28 ቀን 1983 ዓ.ም በአገራችን የተፈጠረው ነገር ነው።በእነዚህ ቀናቶች የሽብር ቡድኑ ሕወሓት በሚያሽከረክረው ኢህአዴግ እና መሰል ተላላኪዎቹ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም የጥፋት ጥንስስ መጠንሰስ የጀመሩበት ጊዜ ነው።ይህ ማለት በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያን በዘር የከፋፋለ ስርዓት ተዘርግቶ አሁን ኢትዮጵያ ለገባችበት ሰቅጣጭ የዘር በሽታ የዳረገን የሽግግር መንግስት ምስረታ የተከናወነበት ወቅት ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም በእነኝህ ቀናቶች የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ራስ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት በእነዚህ ቀናቶች ነው። በሽብር ቡድኑ ራስ የተወሰኑ በርካታ ውሳኔዎች እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያን አላራምድ ያሉ ችግሮችን ተፈጥረዋል።ሌላው የሰኔ ወር መከራ ጠሪ ወር መሆኑን ማሳያው ደግሞ በወርሃ ግንቦት 1997 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በአዲስ አበባ የተፈጠረው አለመግባባት በጉልህ ተጠቃሽ ነው።የምርጫ ሄደቱን ተከትሎ በአጋጠመ ችግር ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሰላም መደፍረስ ተከሰተ።በዚህም የበርካታ ንጹሃን ወገኖቻችን ደም በከንቱ የፈሰሰ። በርካቶችንም ያለ ጧሪ ቀባሪም አስቀረ፡፡
በሰኔ ወር ከተፈጸሙና ኢትዮጵያን ጥቁር ማቅ ካለበሱ ከስተቶች ደግሞ አንዱ ሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ለመግደል የተደረገው ሙከራ ነው።በዚች ቀን አሸባሪው ሕወሓት እና የጥፋት አሽከሮቹ በጎነጎኖት የክፋት ጉንግን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል እረጅም ርቀት ሄደዋል።
ከናይሮቢ እስከ አዲስ አባባ በተዘረጋው የጥፋት ተልእኮ አገርና ህዝብ ዋጋ ከፍሏል። አሸባሪ ሀይሎቹ በመስቀል አደባባይም በመገኘት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመግደል በአገሪቱ ሁከት እና አለመረጋጋት በመፍጠር ለውጡን ለማደናቀፍ ሞክረዋል።
ቦምብ በመወርወር የሄዱበት የጥፋት መንገድ አገርና ህዝብን ሊያስከፍል የሚችለው ዋጋ የከፋ እንደነበር ለመገመት አይከብድም። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋፊዎች ከጥፋት ሃይሎች ጋር ግብግብ ገጥመውና ከፍ ያለ ዋጋ ከፍለው ሴራውን መቀልበስ ችለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመደገፍ የወጡ ንጹሃን በጨካኞች ሴራ ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል። በዚች ዕለት የደም ጥመኞች በንጹሀን ደም የደም ጥማታቸውን ተወጥተዋል።ኢትዮጵያም ጥቁር ማቅ ለብሳለች።
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ደግሞ ኢትዮጵያን ከአሸባሪው ሕወሓት መራሹ ኢህአዴግ የጥፋት መንጋጋ ፈልቅቀው ያወጡ የአማራ ክልል ጉምቱ ፖለቲከኞች እና ለውጥ ዘዋሪ ልጆች በጥፋት ሃይሎች በግፍ የተገደሉበት ቀን ነበር።እነኝህ ለውጥ ዘዋሪዎች ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ብዙ ተስፋ ጥለውባቸው ነበር።ነገር ግን የፖለቲካ ሴራ ከሰኔ ወር አመጣሹ የጥፋት ልክፍት ጋር ተባብረው ባመጡት የጥፋት እሳት በሚዘገንን አኳኋን ተበሉ። ለውጡን በተፈለገው ልክ ያስቀጥላሉ የተባሉ ወንድሞቻችን ለአገራቸው ያለሙት ህልም መሬት ላይ አውርደው ሳይተገብሩ ከእነ ህልማቸው ላይመለሱ ወደማይቀረው አለም ሊሸኙ ግድ ሆነ።
ሰኔ 21 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ ሌላ የጥፋት ድግስ በኢትዮጵያ ተከስቶ ነበር።በዚህች ቀን አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በጨካኞች ተገደለ።ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ጋር በተያያዘ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁከት ተፈጠረ።
እንደሚታወቀው ሰኔ 21 ቀን 2012 ዓ.ም ከራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም ውጭ ለኢትዮጵያ ለአንድ ጊዜም እንኳን ተጨንቀው የማያውቁ የራስ ወዳድነት ልክፍት በሽታ የተጠናወታቸው የፖለቲካ ቁማርተኞች በአርቲስቱ ሞት የተሰማንን ሃዘን ለማዘን ሳይፈቅዱልን ቀሩ።በርካቶች እንዲገደሉ፤ ለዘመናት ያፈሩት ሃብት ንብረታቸው እንዲወድም፣ ከመኖሪያ ቀያቸው በጎሳቸው ተመርጠው እንዲፈናቀሉ ተደረገ።አንዳንድ ከተሞች ሙሉ በመሉ ወደሙ። በሃዘን ላይ ሌላ ልብን የሚያቆስል ሃዘን አከናነቡን።በዚህች ቀን በግብዞች ግብታዊ እርምጃ በርካታ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ንብረቶቻቸው ሙሉ በሙሉ እንዲዘረፉ እና እንዲቃጠሉ ተደረገ።በሰኔ ወር አይለፍልሽ የተባለች የምትመስለው ኢትዮጵያም እጅጉን ተከፋች።በጥቁር ደም ተለወሰች ።
አሸባሪው ሕወሓት ዳግም ወረራ የፈጸመበትን እና በሰሜኑ አገሪቱ ክፍል ከፍተኛ ግፍ እንዲፈጽም በር የከፈተውን ወረራ የጀመረው በወርሐ ሰኔ 2013 ዓ.ም ነው። በዚህ ወረራ አሸባሪው ሕወሓት ህዝባዊ ማዕበል በመፍጠር ከመቀሌ እስከ ጣርማ በር፣ ከአበርገሌ እስከ ደብረታቦር፣ ከማይጠብሪ እስከ ጭና የደረሰ ውጊያ አደረገ።በዚህም በርካታ ኢትዮጵያውያን መስዋዕት ሆኑ።በርካታ የመንግስት እና የግል ድርጅቶች ወደሙ።ከዚህ ወረራ ጋር ተያይዞ በእስከዛሬዋ ቀን ድረስ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለች ትገኛለች።
የዘንድሮው ሰኔ ደግሞ ምን ያመጣ ይሆንተብሎ ሲፈራ … «የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል» እንዲሉ በጋምቤላ ክልል የተጀመረው ጸረ ኢትዮጵያ ጉዞ ወደ ወለጋ ተሸጋግሮ የአለምን ህዝብ ከጫፍ እስከጫፍ ያሳዘነ እና ያስቆጣ ተግባር ተፈጸመ።በርካታ ንጹሃን በግፍ ተገደሉ።ይህ የግፍ ጭፍጨፋ ኢትዮጵያ ብቻ አይደለም የአለምን ህዝብ አስለቀሰ።ዛሬም እያስለቀሰ ነው። በተለይም ከለውጡ ማግስት የተሞከሩ ሴራዎች በታሰበው መንገድ ተሳክተው ቢሆን አገራዊ ፈተናዎችን የቱን ያህል ሊሆን እንደሚችል ማሰብ አይከብድም። ለዚህም ታሪካዊ ጠላቶቻችንና የነሱ ተላላኪ የሆኑ ባንዳዎችን ማሰብ ተገቢ ነው። አገሬ ከሰኔ ወር መግባት ጋር ተያይዞ ከሚፈጠሩ የጥፋት ማዕበሎች ፈጣሪ አብዝቶ እንዲጠብቅሽ ምኞቴ ነው።ሰላም !!
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም