የነፍሰ በላው ናዚ ጭፍጭፋ ካለፈ በኋላ በ1946 ማርቲን ኒሞለር የተሰኘ የሉተራን ቄስ የተናዘዘው ታዋቂ አባባል አለ:: ይህ አባባል ‹‹መጀመሪያ ወደ ሶሻሊስቶች መጡ፣ ሶሻሊስት ስላልሆንኩኝ ምንም አልተናገርኩም ነበር:: ቀጥሎ ወደ ንግድ ማኅበር መጡ፣ የነጋዴዎች ማኅበር ውስጥ ስላልሆንኩኝ ምንም አልናገርም ነበር::
ቀጥሎ ወደ አይሁዶች መጡ፣ አይሁድ ስላልሆንኩኝ ምንም አልተናገርኩም ነበር:: በመጨረሻም ወደ እኔ መጡ:: የሚጮህልኝ አንድም ሰው አልተረፈም ነበር›› ይላል። ማርቲን ኒሞለር ይህንን ያለው በናዚ ጭፍጭፋ ወቅት ምሁራን እና የቤተ ክርስቲያን ሰዎች የናዚን ጭፍጨፋ ላለማውገዝ ዝምታ በመምረጣቸው ምክንያት ነበር::
ዛሬ ላይ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በዚህ አይነት ድንዛዜ ውስጥ ያለን ይመስላል። ሁላችንም ቄስ ማርቲንን ሆነናል።ጥቃት እኛ ጋር የሚደርስ አልመስለን ብሏል።እንዲያውም ሲመቸን ለአጥቂ በግልጽም ስልታዊም ድጋፍ የምንሰጥ ነን።
ነፍሳቸውን ይማረውና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ስለዚህ የኢትዮጵያውያን ባህሪ በአንድ መጽሐፋቸው ላይ ሲገልጹ ‹‹ኢትዮጵያውያን አምባገነንን እንጂ አምባገነንነትን አይቃወሙም›› ይላሉ። እንደሳቸው አባባል ሕዝባችን የሚቃወመው አምባገነንትን ሳይሆን የሚቃወመው አምባገነኑ የሱ ወገን ካልሆነ ነው።ይህም ማለት አምባገነኑ ምንም ያህል አምባገነን ቢሆን የሱ ብሔር የሱ ሃይማኖት የሱ ሰፈር ከሆነ አይቃወምም። ድጋፍ እና ከለላ ይሰጠዋል። አምባገኑን ያጸድቅለታል።
ይሁን ብሎ ይቀበለዋል። በተቃራኒው አምባገነኑ ከሱ ወገን ካልሆነ ይነቅፈዋል፣ ከዓለም አምባገነኖች ሁሉ ክፉው እሱ እንደሆነ ተናግሮ አይጠግብም። መወገድ እንዳለበት ሲሰብክም ፋታ አይኖረውም። በዚህም የተነሳ የጋራ የምንለው ጀግና እንደሌለን ሁሉ የጋራ የሆነ አምባገነንም የለንም። በዚህም የተነሳ ተራ በተራ እንሞታለን።
ብዙዎች ዛሬ እነ እገሌን ያሸበረው ኃይል ነገ እነሱን የሚያሸብር አይመስላቸው ። ዛሬ እገሌን የገደለው ኃይል ነገ እነሱን ሊገድል እንደሚችል ይረሳሉ። ሀቁ ግን መግደል ሱስ ይሆናል ነው። ዛሬ በእነ እገሌ ላይ የተጀመረ ግድያ ነገ እነሱ ጋር እንደሚቀጥል ምንም ጥርጥር የለውም። ወይም ምንም ማስተማመኛ የለውም።
ዝነኛው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል በአንድ ወቅት የተናገረው ዝነኛ ንግግር አለ። ቸርችል እንዲህ አለ ‹‹አሽቃባጭ ማለት አዞው እኔን ቢበላኝ እንኳ የሚበላኝ ከሁሉም መጨረሻ ነው ብሎ አዞውን የሚመግብ ነው››። ቸርችል ይህን ያለበት ምክንያት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ናዚን ባለመቃወም ዝምታን በመምረጣቸው ነው።
ሀገራቱ ዝምታን የመረጡት ዝም ካልን እኛን አይነካንም ብለው በማሰብ ነበር።ነገር ግን ዝምታቸው አልጠቀማቸውም። ‹‹ዝምታ ለበግም አልበጃት›› እንዲሉ ሂትለር እንኳን ዝም ያሉትን በይፋ ወዳጆቹ የሆኑትንም አልማረም። ዛሬም በኛ ሀገር የሆነው ይህ ነው። የአንዱ ብሔር ለቅሶ ሌላውን አልቀሰቀሰውም። ሁሉም ድምጹን አጥፍቶ ተራውን ይጠብቃል።
እስኪ ሩቅ ሳንጓዝ የሰሞኑን ክስተቶች እንመልከት። መጀመሪያ ጎንደር ላይ ያ አሳፋሪ ክስተት ተከሰተ። ከዚያ አሁን በቅርቡ የጋምቤላው ቀጠለ። አሁን የወለጋው ሰለሰ። በነዚህ ሶስት ክስተቶች ላይ የተፈጸመው ድርጊት በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው። ያዘነው ሰው ግን የተለያየ ነው። ለምን? አንዱ ቦታ ሲጠቃ ዝምታን መርጦ የነበረው ወገን ሌላው ጋር የደረሰብኝ ጥቃት ይደርስብኛል ብሎ ስላላሰበ ነው። የጎንደሩን ጥቃት በጋራ ተቃውመነው ቢሆን ኖሮ የወለጋው አይከሰትም ነበር።አሁን የወለጋውን አንድ ወገን ሲቃወም ሌላው ዝም ብሏል።
ጠላታችን በተራ በተራ ያስለቅሰናል። የሁላችንም ብስጭት ግን ለምን አለቀስን ሳይሆን እኔ ሳለቅስ እነ እገሌ ለምን አላገዙኝም የሚል ነው። እነ እገሌ ደግሞ ዛሬ እኛ ስናለቅስ ዝም ያሉት አያገባንም ከእኛ ጋር አይገናኝም፣ እኛም ጋር አይደርስም ብለው በማሰብ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይቆይ ይሆናል እንጂ በዚህ አሰላለፋችን በተራ ከማለቅ የተለየ እጣ ፈንታ አይኖረንም።
የምንኖርበት ዓለም ግሎባላይዤሽን የሰፈነበት ዓለም ነው። የጋራ ጥቅም ብዙ ስለሆነ የጋራ ደህንነት ላይ ብዙ ይሠራል። እንኳን ሀገራት ዓለም ራሱ የምትመራው ብዙኃኑ በተስማሙበት የጋራ ሕግ ነው። ማንም ሀገር በነጠላ ራሴን ችዬ እቆማለሁ አይልም። ኃያላኑ ሁሉ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ጥገኛ ናቸው።ለዚህም ነው አንዱ ሀገር ላይ የተፈጠረ ችግርን እንደጋራ ችግር የሚያዩት። ለዚህ ነው ኔቶ የተፈጠረው።
ለዚህ ነው አሜሪካ ላይ አንድ የሽብር ጥቃት ሲፈጸም መላው የምዕራቡ ዓለም አብሮ ከማዘን እስከ አብሮ መዝመት የሚደርሰው። እኛ ጋር ነገሩ በተገላቢጦሽ ነው። አንዱ ጋር የሚፈጠር ክስተት የሌላው የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያ ግብዓት ነው። ከባህር ወዲህ እና ከባህር ወዲያ ያሉት አሜሪካ እና አውሮፓ በጋራ ህልውናቸው ላይ ተባብረው ሲሠሩ እኛ ጋር አብሮ የተዋለደው ሕዝብ አንዱ ሲሞት ሌላው ዳር ይዞ በዝምታ ያያል።
ይሄ ፈጽሞ አያዋጣም። ከተቃወምን በጋራ እንቃወም። አልያም ግን ዝም እንበል።በፈረቃ ማዘን እስካሁን መፍጠር የቻለው የማኅበራዊ ሚዲያ የብሽሽቅ መንፈስን እንጂ ሌላ ምንም ነገር አይደለም። ይህ ደግሞ ለዚህች ምስኪን ሀገር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንጂ የሚፈይዳት አንዳች ነገር የለውም።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2014