በበጋው ወራት ሙቀት የሚቋቋም ቀለል ያለና ምቾት እንዳይነሳን መርጠን ያደረግናቸውን ጫማዎች ወልውለን ወደ መደርደሪያ የምንመልስበት ወቅት ላይ ነን። በምትኩ የክረምትን ቅዝቃዜ የሚቋቋሙ፣ እርጥበት ምቾት እንዳይነሳን የሚያደርጉ ጫማዎችን ከያሉበት አውጥተን የምንጫማበት፣ ከሌለንም ወደ ጫማ መሸጫ ሱቆች ጎራ የምንልበት ወቅት አሁን ነው። በበጋ ወራት በርካታ የጫማ የፋሽን አማራጮች እንዳሉ ሁሉ በክረምቱም ወራት ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ የፋሽን አማራጮች አይጠፉም። ፋሽን ተከታዮች ወቅቱን መሠረት ያደረጉ ጫማዎችን ለመሸመት ወደ ገበያ የሚያቀኑት ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮችን ከግምት አስገብተው ነው።
የመጀመሪያውና ዋነኛው ጉዳይ የሚጫሙት ጫማ የወቅቱን አየር ንብረት ተቋቁሞ የክረምቱ ቅዝቃዜ ምቾት ሳይነሳ ወደ በጋ ወራት ያሻግራል የሚለው ከጥንካሬ ጋር የተያያዘ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የጫማው ተጠቃሚ የሚሰጠውን ምቾት ከግምት ውስጥ የሚያስገባ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ እንደዘመነኛ ሰው ጫማው ከራስ ምቾት ባለፈ ለሚመለከተው ሰው የሚፈጥረው ውበትና የወቅቱ ፋሽን መሆኑ ከግምት ሊገባ ይችላል።
በክረምት ወራት ጥንካሬ፣ ምቾት፣ ውበትና ወቅቱን የዋጁ ጫማዎች በብዙዎች ይመረጣሉ። በክረምት ወራት ሸማቹ ብቻ አይደለም ከወቅቱ ጋር ለመራመድ ጥረት የሚያደርገው። የጫማ መሸጫ መደብሮችም ወቅቱን ታሳቢ ያደረጉ ለክረምት የሚሆኑ ጫማዎችን ከመደርደሪያቸው ፊት ላይ ማሰለፋቸው የተለመደ ነው። በዚህም ምክንያት የጫማ ብቻ ሳይሆን የአልባሳትም ዋጋ በተፈላጊነታቸው የተነሳ ከበጋ ወቅት ይልቅ ከፍ ሲል ይስተዋላል።
በዚህ ወቅት በተለይም በወጣቶች ተመራጭ የሆኑ ዘመናዊ ጫማዎች በሱቆቹ ውስጥ ተበራክተው ይታያሉ። እንደ አልባሳት ጫማም ወቅቱን ጠብቆ የሚለበስ እንደመሆኑ በበጋና ክረምት ታሳቢ ተደርጎ የሚዘጋጅ ነው። ወቅቱን መሠረት አድርገው ለተለያዩ ዝግጅቶች ከአልባሳት ጋር አብረው እንዲሄዱም የሚሰናዱ ናቸው። በዚህም ምክንያት ሰዎች መርጠው የሚጫሟቸው የጊዜው ፋሽን ልኬትን ያሟሉና ገበያው ላይ ተፈላጊ የሆኑ ጫማዎችን ለደንበኞቻቸው አዘጋጅተው የሚያቀርቡ ሱቆች በዚህ ወቅት ደንበኞቻቸውን በማስተናገድ ተጠምደው ይገኛሉ።
የክረምቱን ወቅት አስመልክተን በመዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ የተዘጋጁ አልባሳትና ጫማ መሸጫ መደብሮች ውስጥ ስንዘዋወር አይናችን አዳዲስ በገቡ የዘመኑ ዲዛይነሮች የተጠበቡባቸው የክረምት ወቅት ጫማዎች ላይ አረፈ። አይናለም ጥላሁን የሽያጭ ሠራተኛ ነች። ከ1 ዓመት በላይ በዚህ ሙያ ውስጥ ቆይታለች። ፒያሳ ከአምፒር ሲኒማ ጀርባ ካሉ የአልባሳትና ጫማ መሸጫ ሱቅ ውስጥ በሥራ ላይ ነች።
በምትሠራበት ሱቅ ውስጥ በአብዛኛው ከቱርክና ከዱባይ የመጡ ዘመናዊ የክረምት ጫማዎች በብዛት ይገኛሉ። በደንበኞቿ በአብዛኛው የሚፈለገው የውጪ ጫማዎች መሆኑን የምትናገረው አይናለም፣ ከክረምት ወቅት ጋር ተስማሚ የሆኑ የሀገር ውስጥ የጫማ ምርቶች ብዙም ባለመኖራቸው ሸማቹ ወደ ውጪ ምርቶች እንደሚሳብ ታስረዳለች።
የጫማ ገበያው እንደ ልብስ ገበያው ፈጣን የሆነ የመቀያየር ባህሪ ባይኖረውም ጫማዎችም በየወቅቱ በአዲስ መልክ ወደ ገበያው በዲዛይነሮች ተሠርተው እንደሚቀርቡ የምትናገረው አይናለም፣ ተጠቃሚዎችም አዳዲስና በሌሎች ያልተለበሱ ጫማዎች ገዝተው ማድረግን እንደሚመርጡ ትናገራለች። አብዛኞች ደንበኞቿ በወጣትነት እድሜ ላይ የሚገኙ ቢሆኑም የጫማ ፋሽን ተከትለው የሚገዙ አልፎ አልፎ ከፍ ባለ እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች መኖራቸውንም ታስረዳለች።
ከወጣቶች በስተቀር በአብዛኛው ወደ ሱቅ የሚመጡ ደንበኞቿ ፋሽንን ሳይሆን አብዛኛው ጊዜ ትኩረት የሚያደርጉት ክረምት ከሆነ ለክረምት የሚሆናቸውን ለመግዛት ነው።በጋ ላይ ደግሞ ሙቀት የሚከላከል ጫማ ብለው እንደሚጠይቁ ትናገራለች። በሱቋ ውስጥ ከብር 600 እስከ 3500 ብር ድረስ ዋጋ ወቶላቸው ለሽያጭ የተዘጋጁ የክረምትም የበጋም ወራት ጫማዎች በየረድፉ ተደርድረው እንደሚገኙም አስተውለናል።
ጫማዎቹ የተሠሩበት ወይም የተዘጋጁበት ጥሬ እቃ፣የዲዛይንና ውበት አይነት የተለያየ ነው። እንደየጥራት ሁኔታቸውም የዋጋቸው መጨመርና መቀነስ ሁኔታ የተለያየ ነው። በተለያየ ስሪት (ብራንድ) ተፈብርከው የቀረቡ የቆዳና የእስኒከር ጫማዎች በየምድባቸው ዋጋቸው የተለያየ ነው። የተለመዱ የጫማ ብራንዶች አዲዳስ፣ ፑማ፣ ስኬቸርስ፣ ጆርዳንና ናይኪ የተሰኙ ጫማዎች በቁጥር ከፍ ብለው የሚታዩና በሸማቹ ዘንድም የሚፈለጉ ናቸው።
አካባቢው ላይ ባሉ የጫማ መሸጫ ቤቶች የሀገር ውስጥ ስሪት የሆኑ ጫማዎችን እንደ ልብ ማግኘት ከባድ መሆኑን ተረድተናል። በእርግጥ እዚያ አካባቢ ባሉ ሱቁች የሀገር ውስት ስሪት ጫማዎች አይገኝ እንጂ በሌሎች አካባቢ ባደረግነው ቅኝት በተለይም ከቆዳ የተሠሩ የክረምት ወቅት ጫማዎች በብዛት ገበያው ላይ መመልከት ችለናል።
ነገር ግን በዚሁ አካባቢ የሚገኙ ባለሱቆችን ስለምን ለደንበኞች የሀገር ውስጥ ጫማዎች ማቅረብ እንዳልቻሉ ጠየቅን። የሀገር ውስጥ ጫማዎች በብዛት የማያቀርቡበትን ዋንኛ ምክንያት አይናለም ስታስረዳ፣ ደንበኞቿ በአብዛኛው የሚመርጡት የውጪ ጫማዎችን በመሆኑ እሷም የደንበኞቿን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ለገበያ እንደምታቀርብ ታስረዳለች።
የሀገር ውስጥ ጫማዎች በአብዛኛው በዲዛይን ምክንያት ደንበኞቿ እንደማይመረጡ የምትናገረው አይናለም፣ የዚህ ዋነኛ ምክንያትም ከዲዛይን ውበት ጋር በተያያዘ የሀገር ውስጥ ምርቶች ሳቢ አለመሆናቸው ወይም የውጪዎቹ ምርቶች የተሻለ ውበት ተላብሰው ስለሚገኙ መሆኑን ታስረዳለች።
መዓዛ ሙሉነህ ሱቋ ውስጥ በጫማና ልብስ ሽያጭ ተሰማርታ ትገኛለች። እሷም ሱቅ ውስጥ ሀገራዊ የሆኑ ጫማዎች የሌሉ መሆኑን አጫውታናለች። የሀገር ውስጥ ጫማዎች በብዙዎች እንደማይመረጡና የወቅቱን ፋሽን በተከተለ መልኩ በምርጫ ለገበያ አለመቅረባቸው ምክንያት መሆኑን ትናገራለች።
አገራዊ ኢኮኖሚን በማጠናከር ከውጪ የሚመጡ ምርቶችን መቀነስና የሀገር ውስጥ ምርት ገበያው ላይ በስፋት እንዲገኝ ማድረግና ማበረታታት ተገቢ መሆኑ አያከራክርም። የሀገር ውስጥ ጫማዎች በስፋት ገበያው ላይ አለመገኘት በጅምር ደረጃ ያሉት የዘርፉ አምራቾች የተሻለ ገቢ እንዳያገኙ እንቅፋት እንደሚሆን ይታመናል።
ገበያው ላይ ያሉ ምርቶች አብዛኞቹ ከውጪ የሚገቡ በመሆናቸው ይህን ሁኔታ ለመቀየር የሀገር ውስጥ ጫማ አምራች ኢንዱስትሪዎች ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። የሀገር ውስጥ ጫማ አምራቾች በተለይም የቆዳ ውጤት አምራች ኢንዱስትሪዎች ገበያው ላይ የተሻለ ምርት አምርተውና አቅርበው ከሌላው ጋር ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ በተለይም ከዲዛይንና ውበት ጋር በተያያዘ ሊያስቡበት እንደሚገባም የብዙዎች እምነት ነው። በገበያው ንቁ ተሳታፊ ያላደረጋቸው የሚያመርቱበት ማሽንና ቴክኖሎጂም ከዘመኑ ጋር አብሮ መጓዝ እንዳለበት ይታመናል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2014