ኢሕአዴግ በትረ መንግሥቱን ከጨበጠ ቆየት ብሎ የፌዴራል ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ተቋቋመ፡፡ ስሙም እንደሚናገረው ኮሚሽኑ የተቋቋመበት ዓላማ ሙስና ለማጥፋት(ማጥፋት እንኳን አይቻልም) ሙስናን ለመከላከል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ውጤቱ በተቃራኒው ሆኖ አረፈው፡፡
ሙስና ለማስፋፋት የተቋቋመ እስኪመስል ድረስ ከኮሚሽኑ መቋቋም በኋላ ችግሩ በመቀነስ ፋንታ በመላ ሀገሪቱ ይባሱኑ ተንሠራፍቶ ተስተዋለ፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቅዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ካነሱት ጉዳይ አንዱ የሌብነት/የሙስና ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ በመሆኑ ብዙ ለመከራከርና ለመሟገት የሚመች አይደለም፡፡
ፀረ ሙስና ሲጀመር እንደተቋም ከፍ ያለ ስልጣንና ኃላፊነት ተሠጥቶት ሥራ ቢጀምርም በኋላ ግን ስልጣንና ኃላፊነቱን በሕግ ተነጥቆ ጥርስ የሌለው አንበሳ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ተቋሙ ስሙን ታቅፎ ሙስና ሲፈጸም እያየ እንዳላየ፣ እየሰማ እንዳልሰማ ሆኖ ቆይቷል፡፡ እርግጥ ነው የተወሰኑ በሙስና ተዘፍቀው ተገኙ የተባሉ እንዲከሰሱ ተደርገው ነበር፡፡ ግን በትልልቅ የሙስና ወንጀሎች እስከአፍንጫቸው ተዘፍቀው ሀገርንና ሕዝብን እስከጥግ ሲዘርፉ የነበሩ ዋነኞቹ ሙሰኞችና ሌቦችን መክሰስና ማሰር አልተቻለም ነበር፡፡
ምክንያቱም ዋነኞቹ ሙሰኞችና ሌቦች የገዥው መደብ አካል በመሆናቸው “ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ” በሚለው ብሂል የሚመራው “ዘመነ አብዮታዊ ዴሞክራሲ(አውቶክራሲ)” ንጉሦችን መክሰስ አይፈልግም ነበረና፡፡ ንጉሦችን ቢነካ ኖሮ ደግሞ ፀረ ሙስና ራሱ ውሃ ውስጥ እንደገባ ሳሙና ሟምቶ ይቀር ነበረና ነው ነገሩ፡፡
ሙስና ቃሉ የግዕዝ ነው፤ “አማሰነ” የሚለው የቃሉ መገኛ የግዕዝ ግስ “አባከነ” “አጠፋ” ከሚሉት የአማርኛ ቃላት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አማሰነ የሚለው የግዕዝ ግሳዊ ቃል ስም ሲሆን “ሙስና” የሚለውን ይወልዳል፡፡ ሙስና በአማርኛ ጉቦ ከሚለው ቃል ይቀራረባል፡፡
ማን እንደዘረፈኝ … ልቤ እያስተዋለ
የለመደው አፌ ”የመንግሥት ያለህ አለ!
የሚለው ስነ ቃላዊ ግጥምም ዘራፊዎቹ መንግሥት ነኝ ባይ አሸባሪዎቹ እንደነበሩ ያሳየናል፡፡
የቀድሞው ፌዴራል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች በአንድ ወቅት እንደነገሩኝ፤ ለሚሠሩት የስኳር ፕሮጀክት መረጃ የሚሰጥ ቢጥሌ መጽሔት (ቡክሌት) እንዲያዘጋጁ በመመሪያ ትዕዛዝ ይወርድላቸዋል፡፡ ሠራተኞቹም ትዕዛዙን ተቀብለው መጽሔቱን ለማዘጋጀት ሥራቸውን ጀመሩ።
ታዲያ በዚህ መሐል የተወሰኑ የፋብሪካዎቹ ፕሮጀክት ግንባታዎች ለማየት ጓጉ፤ ግንባታው በሚካሄድባቸው ቦታዎች አንድ ሁለቱን ቢጎበኙ ለሥራው እንደሚረዳቸው ስላመኑ፤ ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ “መጀመሪያ በተሰጣችሁ ትዕዛዝ መሠረት ጽሑፉን ጨርሱና ትሄዳላችሁ” የሚል ምላሽ ተሰጣቸው፡፡ ጽሑፉን እንደጨረሱ ተጨማሪ የመስክ ሥራ ሲጠይቁ “የጻፋችሁት በቂ ስለሆነ መስኩ አያስፈልግም” ተባሉና ጽሑፋቸው እንጎቻ በሚባለው መጽሔታቸው ታትሞ ተሠራጨ፡፡
መናገር የፈለኩት ስለመስክ መሄድና መቅረት፣ ስለመጽሔት መታተምና መሠራጨት አለመሆኑ ይሰመርበት፤ መዘዘኞቹ የስኳር ፋብሪካ ግንባታዎች ለሚዲያ ፍጆታና ዕይታ ብቻ ተብሎ መጽሔት ይታተምላቸው እንደነበር ለማሳየት ነው ጉዳዩን ያነሳሁት፡፡ እንጎቻ መጽሔቷን ታትማ ወጥታ በወቅቱ ሳነባት የሚያጓጉ ነገሮች ነበሩዋት፡፡ ኢትዮጵያ በስኳር ፋብሪካዎቹ ግንባታ ምርታማና ውጤታማ እንደምትሆን የሚያትቱ ጽሑፎችን ይዛ ነበር የወጣችው፡፡
ከጽሑፎቹ መካከል ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ በቡና ላኪነት ትልቁን የውጪ ምንዛሪ የምታገኘው ሀገራችን በስኳር የውጪ ንግድ ገቢ፤ የቡናን ቀዳሚ የውጪ ገቢ ቦታ ትረከባለች የሚል ሀሳብም ነበረበት፡፡ እነኩባን በስኳር ኤክስፖርት ትፎካከራለች ትቀድማች፤ በፋብሪካዎቹም ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል ያስገኛሉ፤ ብዙ ከተሞች ይስፋፋሉ፤ ይመሠረታሉ የሚሉ ሕልሞችን (ዕቅዳችን ለማለት ስለከበደኝም እንደሆነ እወቁልኝ) ይዛ ነበር፡፡
ሕልሞቹ ሕልም ሆነው እልም ብለው ቀሩ፡፡ የስኳር ፕሮጀክቱ እንደስኳር ሟሟ፤ የወቅቱ ባለሥልጣኖች በስኳር ሙስና ተዘፈቁ፡፡ በዚያን ጊዜ እየዳኸ የነበረው ሙስና፤ ቀና ብሎ በኩራት መራመድ፤ አልፎ ተርፎም በፈጣን ሪከርድ በአደባባይ መሮጥ ጀመረ፡፡
አሥር ስኳር ፋብሪካዎች ይከፈታሉ ተብሎ፤ ለግንባታዎቹም ከውጪ ገንዘብ በብድር መጣ፤ በተመረጡት ቦታዎች ገበሬዎች እንዲለቁ እንዲፈናቀሉ ተደረገ፤ ሕዝቡ ቅር እያለው ማለት ነው፡፡ ሕልሙ ሕልም ሆኖ ገንዘቡም ባክኖ፣ የሙሰኞች ኪስ ማድለቢያ ሆኖ ቀረ፡፡
ሌሎቹን ሙስና ጉዳዮች ብናነሳ ቦታ አይበቃንም። ሜቴክ ብቻ የዘረፈው በራሱ ምትክ የለሽ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሲነገረን የነበረው ነገር ግን፤ “ባለሁለት አኅዝ ዕድገት አስመዘገብን ተብሎ ነበር”፡፡ የተመዘገበው ዕድገት ግን አልታይ ያለን ጥቁር ሰሌዳ ላይ ተመዝግቦ ምቀኞች አጥፍተውት ይሆን እንዴ? አንዳንዳንዶች ለሙስና እንደ ኢሕአዴግ ሥርወ መንግሥት ምቹ ዘመን አልነበረም ይላሉ፤
ከደርግ ዘመን ጋር ሲያነፃፅሩት ማለት ነው፡፡ በደርግ ጊዜ የሠርቶ አደሩ የቁጥጥር ኮሚቴ የሚል ነገር ነበር፡፡ ዓላማው ጉቦን መከላከል ነበር፤ ሆኖም ጉቦን መከላከል ብቻ ሳይሆን አልፎ አልፎ ጉቦ የመቀበል ነገር ቢኖርም ሙስና ተስፋፍቶና ተንሠራፍቶ ሀገራዊ በሽታ መሆን የጀመረው ግን በኢሕአዴግ ዘመን መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በርግጥ ያለንበት ወቅት ስለሙስና ሳይሆን ስለሕልውና የምናስብበት ጊዜ ነው፡፡ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚሉ አህዮች እኛ ሀገር ካልመራን አቧራ እናቦናለን፣ እናሸብራለን፣ እንበታትናለን ብለው ተነስተዋል፡፡ ለሀገር የማያስቡ የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳድዱ መሆናቸውን ማሳያ ይሆናል፡፡ የተነገደበት ሀገር ወዳዱ የትግራይ ሕዝብ እያየው ነው፡፡ ከድህነት ማጥ እናወጣሀለን ብለው፤ ልጁን ለጦርነት እየማገዱት አባትና እናትን ኅዘን ጭንቀትና ድህነት አዘቅት ውስጥ እየከተቱት መሆኑ እርግጥ ነው፡፡
ግን ያለፉት ሦስት የለውጥ ዓመታት በርካታ አመርቂ ሥራዎችን ተሠርተውበታል፡፡ በሙስና እየታመሰ የነበረው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሥራ እንኳ የተነቃቃውና ውጤታማ የሆነው በለውጡ ነው፡፡ የመጀመሪያው እና የሁለተኛው ዙር ግድብ ሙሌት ቀደም ሲል የተካሄደ ሲሆን ሶስተኛ ዙር ደግሞ በቀጣይ እንደሚካሄድ ይጠበቃል ፡፡
በቀጣይ አዲሱ ዓመት ደግሞ ከግድቡ የሚለቀቀውን የኤሌክትሪክ ብርሃን ዜጎች በጉጉትና በናፍቆት እየጠበቁት ነው። ክረምቱን ጠብቆ ሲከናወን የነበረው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የሀገራችንን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስጠራ ነው፡፡ ሌሎች ብዙ አመርቂ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
ይህም ሆኖ ግን ሀገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ብዙ ቅድሚያ የሚፈልጉ አንገብጋቢ ጉዳዮች በመኖራቸው አጠቃላይ የፀረ ሙስና ሥራው ተቀዛቅዞ ቆይቷል ማለት ይቻላል። ለውጡን ሊያናውጡ የሚፈልጉ አሸባሪዎች በየቦታው ሁከት ሲፈጥሩ ቆይተዋል፡፡ አሁን ያለው የአሸባሪዎቹ ግርግር ተጨምሮበት አሁንም ሁከቱ አላባራም፡፡
አብዛኛው ሀገር ወዳድ ዜጋ የሀገርን ሕልውና ለማስከበር ሲታገል፤ በጎን ተሸሽገው ሙስናቸውን የሚያሳድዱ የውስጥ አርበኞችና ጥቅም አሳዳጅ ሌቦች ምቹ ሁኔታን አግኝተዋል፡፡ አጋጣሚው ሀገር የሚመዘብሩ ሙሰኞች እንዲበዙ አድርጓል። እነዚህም የሀገር ጠላቶችና ባንዳዎች ናቸው፡፡
ከዚህ አኳያ የሃገር ሕልውናን የማረጋገጥ ሥራው እንዳለ ሆኖ ለሃገርና ለሕዝብ ዕድገት ጠንቅ ሆነውን ሙስናን መከላከል ሥራም ጎን ለጎን አብሮ ሊሠራ ይገባል፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ብቻ እየዞሩ ገቢህ ስንት ነው? መመዝገብ ብቻ አይበቃም፡፡ ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ አድርጎ ከማደራጀት፣ ብቁ አመራሮችንና ባለሙያዎችን ከመመደብ፣ ሕግና ሥርዓት በማስፈን ግልጽነትና ተጠያቂነትን ከማስፈን አኳያ ትልልቅ ሥራዎችን ማቀድ መተግበር ያስፈልጋል፡፡ዛሬ ዛሬ በሜጋ ፕሮጀክቶች አካባቢ የታየውን የፀረ ሙስና ትግል ማስቀጠልም ወሳኝ ነው ፡፡
ይቤ ከደጃች ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም