በተለያዩ ጊዜያት በዘመቻ መልክም ሆነ የክረምቱ ወራት በመጣ ቁጥር ችግኝ ተከላ ኢትዮጵያ ውስጥ መከናወኑ የተለመደ ነው። ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የአረንጓዴ አሻራ የሚል መርሃ ግብር በመቅረጽ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች በመተከል ላይ ናቸው። የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አፈርን በንፋስም ሆነ በጎርፍ ከመከላት ለመከላከል ብሎም የአየር ጠባይ ሚዛንን በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ችግኝ መትከል አዲስ ባይሆንም ካለፉት ዓመታት ወዲህ ግን በህዝብም በመንግሥትም ያገኘው ትኩረት ላቅ ያለ ሆኗል። የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በደን የተሸፈነው መሬት 11ነጥብ 2 በመቶ ቢሆን ነው። የለም አፈርን በንፋስና በውኃ የመታጠብ ስጋት ለመከላከል የተጀመረው የችግኝ ተከላ እና ለተተከሉትም የሚደረገው ክትትል ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም የዘርፉ ባለሙያዎች ያሳስባሉ።
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች ተምሳሌት በሆነ ሁኔታ እያካሄደች ትገኛለች። ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለው አረንጓዴ ልማት በተለይም ከፊል ደረቃማ ለሆነው የምስራቅ አፍሪካ አየር ንብረት ወሳኝ መሆኑም ይነገራል ።ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው አረንጓዴ ልማት ከድህነት ለመውጣትና ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቷ ከፍተኛ ሚናም ያለው ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከ18ቢሊዮን በላይ ችግኞቸን መትከል ችላለች።በተለይም በአገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ቀን ብቻ ከ 353 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል አለምን አስደምማለች።
በተያዘው ዓመትም አራተኛውን የአረንጓዴ አሻራ ስራ ለማጠናከር ብዙ ስራ እየተሰራ ከመሆኑም በላይ ችግኝ ተከላው ከአገራችን አልፎ ጎረቤቶቻችንን አሳታፊ እንዲሆንም እየተሰራ ነው። እኛም በህይወት ገጽታ አምዳችን ላይ በአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በሜትሪዮሎጂ ዘርፍ ከፍተኛ ተመራማሪ በርካታ የጥናት ጽሁፎችን በዓለም አቀፍ መጽሄቶች ላይ ያሳተሙ በዘርፉ በርካታ ስራን እያከናወኑ ያሉትን ዶክተር አሳምነው ተሾመን ይዘን ቀርበናል። ዶክተር አሳምነው ተሾመ ብሔራዊ ሜትሪዮሎጂ ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪና የዋና ዳይሬክተሩ አማካሪም ናቸው።
ዶክተር አሳምነው ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሰላሌ በሚባለው አካባቢ ወረጃርሶ ወረዳ ኦሌሚኒሴ ቀበሌ ነው ። በተወለዱበት አካባቢ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን ኦሌሚኒሴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን እስከሚያጠናቅቁ ድረስም በጓሃ ጺዮን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል።
ለቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ዶክተር አሳምነው በቤት ውስጥ ልዩ ትኩረትና እንክብካቤ የሚደረግላቸው አይነትም ነበሩ። በዚህም ትምህርታቸውን ከማጥናት ባለፈ ምንም ዓይነት የቤት ውስጥ ስራ እንደማይታዘዙም ያስታውሳሉ።
“……ለቤተሰቤ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፤ በዚህም ልዩ ትኩረት ነበረኝ ማለት እችላለሁ። አባቴ ደግሞ ትምህርቴን በስነ ስርዓት ተምሬ ጥሩ ደረጃ ላይ እንድደርስለት ምኞቱ ነበርና እኔም በዚህ ልክ ነበር የምንቀሳቀሰው። ነገር ግን በትምህትርት አቀባበሌ በጣም ጎበዝም ሰነፍም ያልሆንኩ መካከለኛና በማስተዋል የምማር ተማሪ ነበርኩ” ይላሉ።
ነገር ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል ከጀመሩ በኋላ ለትምህርታቸው ልዩ ትኩረትን በመስጠትና ብዙ ነገሮችን በማሻሻል ጎበዝ ከሚባሉት ተርታ ለመመደብ የቻሉም ተማሪ ሆነዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የቀድሞ አርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ወይም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላም በርካታ የትምህርት አማራጮች እንደነበሩ የሚያስታውሱት ዶክተር አሳምነው፤ እሳቸው የገቡበት የውሃ ትምህርት ክፍል (ውሃ ፋኩሊቲ) ነበር። ብዙ ዓይነት የትምህርት አማራጮችን የያዘ ነበር በማለት ይገልጻሉ።
ከልጅነታቸው ጀምሮ ለሜትሮሎጂ ሳይንስ እንዲሁም ለአየር ንብረት ትምህርቶች ልዩ ቦታ የነበራቸው ዶክተር አሳምነው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም ካሉት የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ሜትሮዎሎጂን የመምረጣቸው ምክንያቱ ይኸው ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ መጀመሪያ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሲደርሱ የየትምህርት ክፍሉ ኃላፊዎች (ዲኖች) ተማሪዎችን ሰብስበው ስለ ትምህርት ክፍሎቻቸው ከፍ ያለ ገለጻን ያደርጉ ነበር ። በዚህም የየትምህርት ክፍሉ ጥቅም ለአገር የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ከአለም አቀፍ ሁኔታ ጋር ያላቸው መስተጋብር በደንብ ይገለጽ ነበር። ይህ በራሱ ከፍ ያለ ግንዛቤን የፈጠረላቸው ዶክተር አሳምነው በዚህ ገለጻ እንዲሁም በልጅነት ህልማቸው አማካይነት የመጀመሪያ ምርጫቸው የሜትሪዎሎጂ ሳይንስ ሊሆን መቻሉን ይናገራሉ።
“…..የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚተላለፍን የሜትሪዎሎጂ ዘገባ ስራዬ ብዬ እከታተል ነበር፤ ከዛም ከትምህርት መልስ በተለይም አክስቴ ጋር በመሄድ የሰማሁትን ዘገባ ደግሜ እልላት ነበር። ይህ አይነቱ መሳብና ፍቅር እንዴት ሊያድርበኝ እንደቻለ ግን አላውቅም” በማለት ይናገራሉ።
ምንም እንኳን ከልጅነታቸው ጀምሮ በሳይንሱ የተሳቡ ቢሆንም ዶክተር ግን ዩኒቨርሲቲ ገብተው በሚማሩበት ወቅት ሳይንሱ ከበድ ብሏቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፤ በተለይም የሂሳብና የፊዚክስ ችሎታቸውንም የጠየቀ ሆኖ ነበር ያገኙት። ይህም ቢሆን ግን ለትምህርቱ ክብደት እጅ ሳይሰጡ ጠንክረው እንደተማሩትም ይናገራሉ።
“…..የውሃ ትምህርት ክፍሉ በርካታ የትምህርት ዓይነቶችን የያዘ ነበር ። ለምሳሌ መስኖ (ኢሪጌሽን)፣ የአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም ሀይድሮሊክ ኢንጂነሪንግ ፤ ነገር ግን እኔ የመረጥኩት የሜትሪዎሎጂ ሳይንስ ትምህርት ክፍልን ነበር። በዚህ ትምህርት ክፍል ውስጥ ደግሞ ለሶስት ዓመታት ያህል በመቆየት የመጀመሪያ ዲግሪዬን ለማግኘት ችያለሁ ”ይላሉ።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ በቀጥታ ያመሩት ወይንም ደግሞ ስራን “ሀ” ብለው የጀመሩት የቀድሞው የብሔራዊ ሜትሪዎሎጂ ኤጀንሲ አሁኑ ደግሞ ሜትሪዎሎጂ ኢንስቲትዩት በጀማሪ ባለሙያነት ነበር።
የሜትሪዎሎጂ ስራ የአየር ሁኔታዎችን ከመቃኘትና ከመመዘገብ የሚጀምር ነውና በመጀመሪያም ይህንን ስራ ሰርተዋል፤ በዚህም የየዕለቱን የአየር ጸባይ ሁኔታ የመከታተል፣በ 24 ሰዓት ውስጥ ምን ዓይነት የዝናብ መጠን እንደነበር።የደመናው ሁኔታ የንፋሱ አቅጣጫና መጠን በምልከታ የመሰብሰብ ስራ በደንብ መስራታቸውንም ይናገራሉ።
ከዛም የሜትሪዎሎጂ መረጃዎችን የማደራጀት ጥራታቸውን የመጠበቅ ስራም ሰርተዋል ። በመቀጠል ግን ወደሚወዱት ወይንም ደግሞ ከልጅነታቸው ጀምሮ ወደሳባቸው የትንበያ ስራ ነበር እንዲገቡ የሆነው።
“……ሜትሪዎሎጂ ኤጀንሲ ስገባ በጣም ደስተኛ ነበርኩ ፤ምክንያቱም ከልጅነቴ ጀምሮ የትንበያ ባለሙያ መሆን ህልሜ ስለነበር ነው። በዚህም የአጭር ፤የመካከለኛ እንዲሁም የረጅም ጊዜ ትንበያዎችን ሁሉ ሰርቻለሁ። እንዲሁም የተለያዩ አለም አቀፋዊ የአየር ጸባይ ክስተቶችን እያየን የምናዘጋጃቸውን ትንበያዎች ሁሉ ተሳትፌ ወይም ሰርቼ ነው ያለፍኩባቸውና በጣም ደስተኛ ነኝ” ይላሉ።
ዶክተር የልጅነት ህልማቸው የነበረውን በቴሌቪዥን መስኮት ቀርቦ የእለቱን የአየር ሁኔታ መናገርንም አሳክተዋል። በዛም ለማህበረሰቡ የአየር ሁኔታውን በመናገርና የቅድመ ጥንቃቄ መልዕክቶች እንዲተላለፉ በማድረግም አገልግለዋል።
እንደው አልኳቸው ዶክተርን “ከእኛ አገር የሜትሪዎሎጂ ዘገባ የአንዳንድ እንስሳት ተፈጥሮአዊ ችሎታ ይሻላል የሚሉ ወገኖች አሉና ፤ የእኛ አገር የአየር ሁኔታ መግለጫዎች እንዲሁም ወቅታዊነትና ታዓማኒነት ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል? ስላቸው” ትንበያ መቶ በመቶ ስኬታማ አይሆንም፤ ያደጉ አገሮችም ቢሆኑ በዘርፉ የተጠናከረ ስራን እየሰሩ እንኳን ቅፅበታዊ የሆኑ የአየር ጸባይ ለውጦች ይከሰቱባቸዋል፤ በዚህም በርካታ የሰው ህይወት መሰረተ ልማትና ንብረቶች ይወድማሉ፤ ነገር ግን እነሱ ከእኛ የሚሻሉት የሚከሰተውን የአየር ጸባይ ለውጥ አስቀድመው ስለሚያውቁ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ የመቀነስ ሁኔታ ይሰራሉ። በአገራችንም ትንበያ ሳይንስ ከመሆኑ አንጻር ሙሉ በሙሉ ትንበያዎቻችን አስተማማኝ ናቸው ማለት ይከብዳል” ይላሉ።
ዶክተር አሳምነው ተሾመ ሁኔታውን ሲያብራሩም፤ እየተከሰቱ ላሉ የአየር ንብረት ለውጦች እንዲሁም የሜትሪዎሎጂ ትንበያ ውጤታማነት መቀነስ እንደ ምክንያት ሊነሳ የሚችለው በአካባቢያችን ላይ ያለው ጫናና ሁኔታ ነው። በመሆኑም የአካባቢ መራቆት የሚያስከትለው ችግር በተለይም ከአንድ ውቂያኖስ ላይ የሚነሳ ችግር የአንድን አካባቢ የአየር ጸባይ ከመለወጡም በላይ ተጽዕኖውም ቀላል ላይሆን ይችላል።
የአገራችን የትንበያ ስራም 1ሺ600 በሚደርሱ ማዕከላት የሚሰራ ሲሆን፤ በእነዚህ ውስጥም ከወጣት እስከ አንጋፋ ምሁራን በዘርፉ ትልቅ ልምድ ያላቸው ሰዎች የተካተቱበት ነው ። ከበርካታ ተቋማትና የትንበያ ተጠቃሚዎች ከመጣው ግብረ መልስ መሰረት የአውቶማቲክ መረጃ መሰብሰቢያዎች ተተክለዋል፤ እነዚህም ያለውን የአየር ሁኔታ በመሰብሰብ በየ15 ደቂቃው መረጃዎችን የሚልኩ ናቸው።
በመሆኑም ትንበያዎች የሚዘጋጁት ከእነዚህ ላይ በሚሰበሰቡ መረጃዎች እንዲሁም ከአለም አቀፍ ደረጃ ከምናገኛቸው የሳተላይት መረጃዎች አማካይነት ነው። እነዚህን በመደመርና ሳይንሳዊ ትንታኔዎችን በመጨመር መረጃዎች እየተሰጡም መሆኑን የስራ ልምዳቸውን በማከል ይናገራሉ። ተዓማኒነቱም በቴክኖሊጂ እንዲደገፍ ሰፊ ስራ እየተሰራም ስለመሆኑ ነው ዶክተር አሳምነው የሚናገሩት።
ዶክተር አሳምነው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአርባ መንጭ ዩኒቨርሲቲ ካገኙ በኋላ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ለመማር ከፍ ያለ ፍላጎት ነበራቸው። ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ አገር ድረስ ያሉ የተለያዩ ነጻ የትምህርት እድሎችን ሳይሰለቹ አፈላልገዋል። ኋላም መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ስለተሳካላቸው በአካባቢ ጥበቃ ሳይንስ (ክላይሜት ሳይንስ) ሁለተኛ ዲግሪያቸውን መማር ቀጠሉ።
“…..የመጀመሪያ ዲግሪዬን ይዤ የስራ አለምን ከተቀላቀልኩ በኋላ ስራዬን እየሰራሁ አስብ የነበረው ሁለተኛ ዲግሪዬን መቀጠል አለብኝ የሚለውን ነበር፤ በዚህም በርካታ ነጻ የትምህርት እድሎችን አፈላልጌያለሁ። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ እድሉን ሰጥቶኝ በአካባቢ ጥበቃ ሳይንስ ዘርፍ ትምህርቴን እንድማር ሆንኩ፤ የመመረቂያ ጽሁፌንም የአየር ትንበያ ሁኔታዎችን ለማሻሻል ምን ዓይነት ዘዴዎችን ብንጠቀም ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል? ወይንም ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወጡ የአየር ትንበያዎች የመተንበይ አቅማቸው ምን ያህል ነው? የሚለው ላይ ነበር” በማለት ይገልጻሉ።
ከዚህ በኋላም በርካታ የአየር ንብረትን የተመለከቱ ስልጠናዎችን በአገር ውስጥም በውጭ አገርም የተከታተሉት ዶክተር አሳምነው በተለይም የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት የአየር ጸባይ ትንበያ ማዕከል በአየር ሁኔታና ጸባይ ምርምር ባሳዩት ብቃት የምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ወጣት በሚል ሰርተፍኬት የወሰዱ ሲሆን፤ ከሌሎችም እንደዚሁ በርካታ ስልጠናዎችን በመውሰድ የምርመር ስራዎችን በመስራት እውቅናና ሽልማት አግኝተዋል።
ዶክተር አሳምነው ለትምህርት ያላቸው ጉጉት አሁንም ገና ነበርና የሶስተኛ ዲግሪያቸውን በቻይና አገር በሚገኘው የናንጆንግ ዩኒቨርሲቲ ኦቭ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ውስጥ በሜትሪዎሎጂ ሳይንስ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ለማግኘት ችለዋል። እዚህም ላይ የመመረቂያ ጽሁፋቸውን አሜሪካን አገር ከሚገኘው ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ አለም አቀፍ የምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር መስራታቸውን ይናገራሉ።
“……ትምህርት ላይ ትኩረት ለማድረጌ ትልቁ ምክንያት አባቴ ናቸው። እሳቸው ሁሌም ይመክሩኝ የነበረው በትምህርቴ እንድገፋ የተሻለ ነገር እንዲኖረኝ ነበር። ይህ ይሳካልኝ ዘንድ ደግሞ በቤት ውስጥ እንኳን ስራ አግዝ ተብዬ አላውቅም። ዋናው ትኩረቴም ትምህርቴ ላይ ነበር። ሌላው ደግሞ ሜትሪዎሎጂ ኤጀንሲን ከተቀላቀልኩ በኋላ በተቋሙ ይሰሩ የነበሩ አንጋፋም ወጣት ምሁራን መማር እንዳለብኝና አገሬን ተምሬ በሳይንሱ ዓለም የደረሰበት እንዳደርስ ይመክሩኝ ነበር እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ አግዘውኛል” ይላሉ።
ወጣቶች ይላሉ አገርን ወደፊት የሚያሻግሩት እነሱ መሆናቸውን በመገንዘብ በተለይም በትምሀርት መስኩ ላይ ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ነገር እንኳን ቢገጥማቸው እየተቋቋሙት ማለፍና መማር እንደሚያስፈልጋቸው አብራርተዋል።
ዶክተር አሳምነው ተሾመ እንደሚናገሩት፤ በአለም አቀፍ ደረጃ የአየር ጸባይ መቀየርና መዋዠቅ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ እያደረሰ ነው ያለው።በተለይም በግብርና በውሃ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ትንሽ አይደለም። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ የህዝብ ቁጥር መጨመር ይህንን ተከትሎም ለምድር እንክብካቤን መንፈግ መሆኑን ይጠቁማሉ።
“…….. የወቅቶች ዝናብ መቆራረጥ ወይንም ደግሞ በትክክለኛ ጊዜው ዝናብ ያለመዝነብ ሁኔታ በግብርናው ላይ ቀጥተኛ የሆነ ተጽዕኖ አለው። በቅርቡ እንኳን በአገራችን የተከሰተውን ብናነሳ በደቡብ አጋማሽ የአገራችን ክፍል ላይ የበልግና የበጋው የዝናብ መጠን በጣም አነስተኛ የነበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ችግር እየተስተዋለ ነው። በዚህም በግብርናው በእንስሳት እንዲሁም በሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም ። በመሆኑም የአካባቢ ጥበቃ ስራን መስራት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው” በማለት የአረንጓዴ ልማት ስራውን አስፈላጊነት ይገልጹታል።
ያደጉ አገሮች የሚለቋቸው አማቂ ጋዞች የዓለምን የሙቀት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር እያደረጉት ነው። በወቅቶች ላይ ያለው የዝናብ መጠንም እየተዛባ ደረቅ ሰሞናት እየበዙ መጥተዋል።እነዚህ ደግሞ በተለያዩ ሴክተሮች ላይ ጫናንም እያሳደሩ ነው። ይህንን ለመቆጣጣር ብሎም የአየር ንብረት ለውጥ ሊያደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ መቋቋም የሚቻለው አሁን እኛ እያደረገን እንዳለው በርካታ ችግኞችን በመትከል ነው።
በሌላ በኩልም ሌሎች የአየር ጸባይ ለውጡን ሊያርሙ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን መልመድና የግብርናና የውሃ ስራን ዘላቂ አድርጎ ማስኬድ ያስፈልጋል። በመሆኑም እነዚህን አሉታዊ ችግሮች ለመቀነስ የአካባቢ ጥበቃ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ስለመሆኑም ዶክተር አሳምነው ይናገራሉ።
ዶክተር አሳምነው በተለይ አካባቢ መራቆት በከፍተኛ ሁኔታ ለችግር የሚዳርገው ሴቶችን ነው።ይህንንም ለመከላከል ደግሞ ከበርካታ አለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ጋር በጋራ ይሰራሉ፤ ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝም በርካታ የጥናት ጽሁፎችንም በማዘጋጀት ዓለም አቀፍ መጽሄቶች ላይ ያሳትማሉ።
“…….ሴቶች በአካባቢያዊ እንቅስቃሴ በቤተሰብ ህይወት ብሎም በአገር ግንባታ ላይ ትልቅ ሚና ያላቸው ናቸው ብዬ አምናለሁ። በዓለም አቀፍ ደረጃ በአገራችንም ብሎም በምስራቅ አፍሪካ የተጠኑ ጥናቶችም የሚያሳዩት ለአየር ጸባይ መዋዠቅና መናወጥ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንደሚያርፍባቸው ነው የሚገልጹት፤ ለዚህ አስረጂ ሲጠቅሱም ሴቷ የቤተሰቧን ህይወት ለማስቀጠል ምግብ መስራት አለባት። ለዛ የሚሆን ማገዶ ትቸገራለች ።አካባቢው ድርቅ በሚሆንበት ጊዜም በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዛ ውሃ መቅዳት ሊጠበቅባት ይችላል” በማለት ይገልጻሉ።
ዶክተር አክለውም ሴቷ አካባቢ በመራቆቱ ምክንያት የሚደርስባትን የኑሮ ጫና ስለምትረዳው ደግሞ አካባቢን ለመንከባከበም ከወንዶች ይልቅ በጥሩ ሁኔታ ኃላፊነቷን ትወጣለች። በመሆኑም እስከ አሁንም እንደምናየው ሴቶች አካባቢያቸውን ለማልማት ዛፎችን ለመትከል ዝግጁ የሆኑና በስራም ተሞክረው ያረጋገጡ ስለመሆናቸው ይናገራሉ። በተለይም አገራችን በጀመረችው የአረንጓዴ ልማት ስራ ላይ ሴቶችን ግንባር ቀደም ተሳታፊ ማድረጉ እንደሚጠቅምም ነው የሚገልጹት።
“……አገራችን እየሄደችበት ያለው የአረንጓዴ አሻራ የማኖር ስራ በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ በተለይም የበልግ ዝናብ ከመላ አገራችን ከጊዜ ወደጊዜ እየተዳከመና እየቀነሰ ነው ፤ በተለይም በደቡብ አጋማሽ ߹ ሶማሌ ክልል፤ በደቡብ ኦሮሚያ ቆላማ ስፍራዎች ߹እንዲሁም በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ ߹የአገራችን አካባቢዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ ነው ያለው፤ ይህ ደግሞ በግብርናው ላይ ተጽዕኖው የጎላ ነው ፤ ለዚህ ምክንያቱ የአየር ጸባይ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማደሩ በመሆኑ ይህንን ሁኔታ መቀየር ከተፈለገ አሁን እንደተጀመረው በየዓመቱ ችግኞችን መትከል የተተከሉትን መንከባከብ ነው፤ ዓለም ዓቀፍ ተሞክሮውም ይኸው ነው” ይላሉ።
በሌላ በኩል ይላሉ ዶክተር አሳምነው አገራችንን አረንጓዴ ባደረግን ደኖችን ባበዛን ልክ የቱሪስት መስህብነታችንም ይጨምራል ። ይህ ደግሞ እንደ አገር ሌሎች ስራዎቻችንን የምንደግፍበት ትልቅ ገቢ ነው ። ስለዚህ አረንጓዴ አሻራን የማኖር ስራን ከዚህ አንጻር ማየትም እንደሚያስፈልግ ያብራራሉ።
ዶክተር አሳምነው ተሾመ ለአገር ለወገን የሚጠቅመውን ስራቸውን እየሰሩ ብሎም ትምህርታቸውን እየተማሩ የህይወት መንገድንም አልረሱምና ትዳር መስርተው ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ ልጅን አፍርተዋል። በትዳራቸው እጅግ ደስተኛ እንደሆኑ የሚናገሩት ዶክተር አሳምነው ባለቤታቸው በተለይም እርሳቸው ትምህርት ላይ በነበሩበት ወቅት ልጆቹን እናትም አባትም ሆነው በማሳደግ ለከፈሉላቸው ዋጋ ላቅ ያለ ምስጋናንም ያቀርባሉ።
የምርምር ስራዎች
የትምህርት ዋናው ግብ የንድፈ ሃሳብ እውቀትን ማግኛ ነው። ይህንን እውቀት ደግሞ ወደተግባር በመቀየር የተለያዩ ምርምሮችን መስራትን ያጠቃልላል። በመሆኑም እኔም ብዙ ጽሁፎቼና የምርምር ስራዎቼ የሚያተኩሩት የአየር ሁኔታንና ጸባይን ትንበያን ከማሻሻል አኳያ ነው። በዚህም መሰክ የጻፍኳቸው 17 ያህል የምርምር ስራዎች ያሉ ሲሆን ሁሉም በሚባል ደረጃ ዓለም አቀፍ በሆኑ ታዋቂ መጽሔቶች ላይ የመታተም እድልን ያገኙ ናቸው።
እነዚህን በምሰራበት ወቅት ከተለያዩ ትልልቅ ተቋማትና የዘርፉ አንጋፋ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ነው። ለምሳሌ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ፣ከምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት የአየር ጸባይ ምርምር ማዕከል፣ ከናሽናል ኦሽን አድምንስትሬሽን (ኖዓ)፣ከሌሎችም ጋር እንዲሁም በአገር ውስጥ ከአዲስ አበባና ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተለያዩ ምርምር ስራዎችን ሰርቻለሁ።
አሁን ላይም በአርባ ምንጭና በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የማስተማርና የምርምር ስራዎችን በማከናወን ላይ ነኝ። በጠቅላላው ከማህበረሰቡ የሚነሳውና በተለይም በትንበያ ላይ የሚነሳውን ቅሬታ ለመፍታትም እኔም አንደ አንድ ዜጋ ባለሙያ ብዙ ፕሮጀክቶች እንዲመጡ ከመጻጻፍ ጀምሮ የምርምር ስራዎችን እየሰራሁ እገኛለሁ።
መልዕክት
የአየር ጸባይ መለወጥና መዋዠቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። በተለይም ባደጉት አገሮች ላይ ከፍ ያለ አሉታዊ ተጽዕኖ አለ። በዚህ ውስጥም ምስራቅ አፍሪካ በየወቅቱ በድርቅ እየተጠቃች ለተለያዩ ነገሮች እየተጋለጠች ነው። የእኛም አገር ላይ ይህ መሰሉ በተለይም የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት አካባቢዎች ላይ እየተከሰተ የዝናብ መጠኑ እየቀነሰ ደረቅ ሰሞናት እየበዙ በግብርናው ለይ ከፍ ያለ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። ይህ ደግሞ የአካባቢ መራቆት ውጤት ነው።በመሆኑም ይህንን ነገር ለማስተካከል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አካባቢን የመንከባከብ ስራ ላይ በመስራት እና ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋናችን አሁን ካለበት በበርካታ እጥፎች እንዲጨምር ማድረግ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2014