በወጣትነት እድሜ ላይ የምትገኝ ሴት ነች። በአካባቢዋ ለየት ባለው የለውጥ ሃሳብ አራማጅነቷ ትታወቃለች። ሕይወት የምትጣፍጠው በለውጥ ውስጥ ነው ብላ የምታምን ወጣች ነች። አንድ ሰው ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለውጥን መከተል እንዳለበት የምትገልጽ፤ በአለባበስ፣ በአበላል፣ በመዋያ ቦታ፣ በቤት ውስጥ ያለውን ቁሳቁስ በማስተካከል፣ ወዘተ ለውጥ መኖር እንዳለበት ታምናለች። የቤቷን ዕቃ አቀማመጥ በየጊዜው በማድረግ የለውጥ ስሜት እንዲሰማት ታደርጋለች።
ወጣቷ አንድ ሰሞን የሆነን ቲቪ የምትከታተል ከሆነ በሌላ ጊዜ ሌላውን ታደርጋለች። የእንቅልፍ ሰዓቷን ከረጅም ወደ አጭር፤ ከአጭር ወደ ረጅም በማድረግ ለውጥን እንቅልፍ በማጣትም ሆነ እንቅልፍ በማብዛት ውስጥ ለማየት የምትሞክር። ለውጥ ስሜት አለው፤ ለውጥ ድምጽ አለው፤ ለውጥ ቅርብም እርቁም ነው ብላ የምትፈላሰፍ። የሕይወትን ትርጉም በለውጥ ውስጥ የምትፈልግ ዓይነት ሰው ነች።
አንድ ቀን በሰፈሩ ውስጥ ባለ ሱቅ ውስጥ ሄዳ ዕቃ ትገዛለች። የገዛችው ዕቃ ደግሞ ክብሪት ነበር። ክብሪቱን ተጠቅማ የመጀመሪያውን ሻማ ለኩሳ ማንበብ ጀመረች። ይህን የምታደርገው ከመብራት አምፖል ለየት ያለ ነገር ለማድረግ፤ እንዲሁም ሻማው ትኩረትን ሰብስቦ ለማሰብ ይጠቅማል የንባብንም ፍላጎት ይጨምራል ብላም ስለምታምን ነው።
ሻማውን እያየች በሀሳብ ፈረስ ተሳፈረች። የሀሳቡ ፈረስ አንድ ቦታ አደረሳት፤ በፖለቲካ ለውጥ ምክንያት ሕይወታቸውን ስላጡት አባቷ። አባቷ የደርግ ባለሥልጣን ነበሩ፤ ትውልዱ እርስበእርሱ ሲገዳደል እርሳቸውም ሕይወታቸውን አጡ። አባቷ «ትንንሽ ለውጦች ትልልቅ ለውጥ ያመጣሉ ሁሌም ለለውጥ ጥሩ ስሜት ይኑርሽ» እያሉ ይመክሯት ነበር።
ትንንሽ ለውጦችን መኖር የጀመረችው ከእዚያ ጊዜ በኋላ ነው። በመሠረታዊነት ጥቅምና ጉዳቱን የመዘነ ባይሆንም ለውጥን በበጎ የምትወስድ ለለውጥ ትልቅ ቦታ የምትሰጥ ሴት ነች። ትንንሽ ለውጦችን በየቀኑ ለማድረግ የምትሠራ።
ከአገራችን እልፍ ብለን ሌላውን ዓለም በምናይበት ጊዜ ለለውጥ የሚሰጡትን ከፍተኛ ትኩረት እናያለን። እንዴት ቢሠሩ ነው እንዲህ የተለወጡት የሚልም ጥያቄ ያጭራል። ለለውጥ ዝግ በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ እድገት እንደሚታሰበው አለመሆኑንም እንረዳለን። ለውጥ ሁልጊዜ ተፈጥሮዊ ሆኖ የሚሳል ቢሆንም የሰዎች ፍቃድ ውጤት የመሆን ዕድሉ ግን ሰፊ ሆኖ እናገኘዋለን።
አንድ አካል ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ባያደርግ እንኳን የለውጥ ስሜት ውስጥ የሚገባ መሆኑ ግድ ነው። ለውጥ ትልቅ አቅም ነው፤ ወደፊት መስፈንጠሪያ ተስፋ። ለውጥን የሚለማመድ የሕይወት ሥርዓት ይኖረን ዘንድ የተወሰኑትን እናንሳ። ጥንካሬና ድክመታችን ውስጥ የለውጥ አምጪነት ወይንም የለውጥ አደናቃፊነት ትርጉም አለ።
ወደ ውስጥ ስንመለከት
ሁሉም ነገር ዛሬ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አመታትን ሊቆይ አይችልም። ለውጥ ተፈጥሯዊ ወይንስ ሰው ሰራሽ የሚለውን የተለመደ ክርክር ወደ ጎን አድርገን የለውጥ መኖርን ግን የማንክድ ከሆነ ስለ ለውጥ ስናስብ ስለ ውስጣችን እናስባለን። የውስጥ እድገትም ሆነ ውድቀት ከለውጥ ጋር ቀጥተኛ ትርጉም ያለው መሆኑን በመረዳት።
አዲስ ነገርን ህልም ስናደርግ፤ አዲሱን ነገር በለውጥ ውስጥ እየፈለግን በጥንካሬና ድክመታችን ውስጥ ከመዳረሻው እንደርሳለን። በለውጥ ጉዞ እየተሻሻሉ መሄድን እናስባለን። እየተሻሻልን መሄድን የምናስብ ከሆነ መለወጥን እና ነገሮችን እያሻሻሉ መሄድ ይገባል። አዳዲስ ነገሮች ከጥንካሬ ጋር የተገናኙ ሊሆኑም ይገባቸዋል። በጥንካሬያችን ላይ አዳዲስ ነገሮችን እየጨመሩ መሄድ። ጥንካሬያችን ይበልጥ ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ። ልዩነት መፍጠር የሚያስችል ጥንካሬ ላይ መድረስ።
በዘርፉ ላይ ጥናት የሚያደርጉ ባለሙያዎች 25% የሚሆነውን ጊዜህን፣ ኃይልህን፣ እና ሀብትን በጥንካሬህ ላይ አዳዲስ ነገሮችን በማድረግ ማዋል አዎንታዊ ለውጥን ለማምጣት እንደሚያስችል ይመክራሉ። ይህ ሲሆን የሚመጣው ለውጥ በእድገት ውስጥ ትርጉም ያለው ይሆናል።
የውጭ አቅማቸውን አውቀው በጥንካሬያቸው ላይ ትኩረት የማድረግ ችግር ያለባቸው ሰዎች ሁሉም ነገር ላይ ሲባትሉ ይገኛሉ። በባተሉበት ሁሉ ፍሬ ሊያገኙ አይችሉም። በጥንካሬያቸው ላይ የተመሠረተ መባተል ቢሆን በቀላሉ የፈለጉትን ነገር በቀላሉ ማሳካት ይችላሉ። የአንድ ነጋዴ ጥንካሬው ደንበኛ አያያዙ፤ ደንበኛ ተኮር ሆኖ አገልግሎትን ማቅረቡ ነው። አዲስ ነገር እዚያ ላይ እየጨመረ በሄደ ቁጥር እጅግ ጠንካራ መሆን ቻለ ማለት ነው። ምናልባትም በሳምንት ውስጥ አንድ እቁብ ሳይሆን ሁለት እቁብ መግባት የሚያስችል ጥንካሬ።
ወደ ውስጥም ወደ ውጭም ስንመለከት
ወደ ውስጥ ስንመለከት ጥንካሬንና ድክመትን ከለውጥ አንጻር መመልከቱ ዋና ነገር ሲሆን ወደ ውጭም መመልከት ደግሞ ሌላው ቁልፍ ነጥብ ነው። ራስን መቀበል ወደ ውስጥም ወደ ውጭም የመቀበል ውጤት ነው። ሰዎች ሌሎች ሰዎች እነርሱን የሚያዩበትን መንገድ ተመልክተው ጉዟቸውን ሊገቱ ይችላሉ። ሰዎች ራሳቸውን የሚያዩበትን መንገድም ካላስተካከሉም በተመሳሳይ ሁኔታ እክል ይገጥማቸዋል።
ራስን መቀበል መቻል የሚበረታታ እያንዳንዱ ሰው ሊያደርገው የሚገባ ነው። ለራስ ቦታ መስጠት ተገቢነቱ እንዲሁ አያጠያይቅም። ፈጣሪም ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን እንድንወድ ሲጋብዘን ለራሳችን ከምንሰጠው ቦታ ተነስተን መሆኑን መረዳት ይገባል። ለለውጥ የሚነሳ ሰው ለራሱ የሚሰጠው አመለካከት በራሱም ሆነ በሌሎች ሰዎች አመለካከት ያልተበላሸ ሰው ነው።
ሰዎች በመሠረታዊ ነገራቸው እኩል ናቸው። ነገርግን ባደጉበት ባህል፣ በሚናገሩት ቋንቋ፣ በእድሜያቸው፣ በጾታቸው፣ በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በሚሠሩት ሥራ፣ ባላቸው ተሰጥዖ ወዘተ ሊለያዩ ይችላሉ። ሰዎች ከቆዳ ቀለማቸው ባሻገር በሰውነታቸው የሚጋሩት የጋራ ማንነት ከፍ ያለነው። በምድር ላይ ባሉ የሰውልጆች መካከል ያለው ልዩነት ካለን አንድነት አንጻር ፈጽሞውኑ ለውድድር የሚቀርብም አይደለም።
ሆኖም በታሪክ ውስጥ ለራስ ከሚሰጥ የተሳሳተ ትርጉም የተነሳ ብዙ ጥፋት ሲሆን አይተናል። የለውጥ መንገድን የሚያዛባ ጥፋት። ለራስ የሚሰጠው የተሳሳተ ትርጉም ራስን ከሌሎች የተለየ አድርጎ ማሰብ፣ ሌሎችን ከራስ በታች አሳንሶ ማየት፣ ሌሎች ከእኛ ተለይተው በሚታዩበት ልዩነት ምክንያት ከሰውነት አውርዶ መመልከት ወዘተ ነው። ለራስ የሚሰጥ የተለየ ትርጉም ያለንበትን ትክክለኛ ነባራዊ ሁኔታ እንዳንረዳና የተሳሳተ መንገድ ውስጥ እንድንገባ ያደርገናል። የተሳሳተው መንገድም ወደ አዎንታዊ ለውጥ ሳይሆን ወደ አሉታዊ ለውጥ ሊሆን የሚችል።
ለውጥን አስቦ ነገርግን ለውጥን ሌሎችን በማጥፋት ውስጥ በማለም ከሆነ ጉዳቱ ከፍ ያለ ነው። ይህን መሰል የለውጥ አስተሳሰብም ታሪክንም ዓለማችን መዝግባለች። ለራስ የተለየ ትርጉም ከመስጠት ውስጥ የወጣ። አይሁድን ከምድረገጽ ለማጥፋት የተዘረጋው ፕሮጀክት መነሻና መድረሻው ለራስ የተለየ ትርጉም መስጠት ነበር። ጣሊያን ኢትዮጵያን ዳግም ለመውረርና ለከፍተኛ ጥፋት ድግስ ውስጥ እንድትገባ ያደረጋት ለራስ የተለየ ትርጉም በመስጠት ነበር። የባሪያአሳዳሪ ሥርዓትን ከአሜሪካ ለማስቀረት የተደረገው ትግል ሚሊዮኖችን እንዲጨርስ የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከንንም በበቀል ለመግደል የተደረገው ለራስ በሚሰጠው የተለየ ትርጉም ነበር።
በቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ የፍሎይድ አሟሟት የቀሰቀሰው «የጥቁርም ሕይወት ይገዳል» የተሰኘው እንቅስቃሴ መነሻው ለራስ ከሚሰጥ የተለየ ትርጉም የተነሳ የተፈጠረን ኀዘን ለመግለጽ ነው። በአገር እንዲሁም በዓለምአቀፍ ደረጃ ካሉት ማሳያዎች ወደ አካባቢያችን እንዲሁም ቤተሰባችን ጉዳዩን ይዘን ብንመጣ የበረከቱ ማሳያዎችን ልናነሳ እንችላለን።
ራስን በመቀበልና ለራስ የተለየ ትርጉም በመስጠት መካከል ያለውን ልዩነት በመረዳት አዎንታዊ ለውጥን በመኖር ጤናማ ሕይወትን እርሱም ከሌሎች ጋር በሰላም የመኖርን ጥበብ ማግኘትን ይገባል። ብቻችንን ልንኖረው የምንችለው ሕይወት ምድር ላይ እንደሌለ በመረዳት በዙሪያችን ላሉት ሰዎች ከየትኛውም ልዩነት ባሻገር ትርጉም በመስጠት መኖርን መልመድ አለብን።
ሁላችንንም ያለብንን ውስንነት በመረዳት በውስንነት ውስጥ የምንኖር በመሆናችን መደጋገፋችን የግድ መሆኑን በመገንዘብ መኖር ብልህነት ነው። ራስን ውስንነት የሌለበት፤ ሌላውን ግን በውስንነት የሚኖር አድርጎ የመሳል ውስንነትን በማስወገድ ትርጉም ያለው ሕይወት ልንኖር ይገባል። የለውጥ ሕይወት ሌሎችን በምናይበት መንገድ ራሳችንንም መመልከት ነውና። ወደ ውስጥም ወደ ውጭም በመመልከት ለራስ ትክክለኛውን ትርጉም መያዝ ይገባናል።
ለውጥን በማምጣት ሂደት ውስጥ ሌላው ነጥብ ከልካዩን መረዳት ነው። በውስጣችን ለለውጥ ጥሩ ቦታ ሰጥተን ነገርግን ለውጥ ሆኖልን አናይ ይሆናል። ይህ የሚሆነው አንዳች ከልካይ በሕይወታችን ውስጥ ሲኖር ነው።
ከልካዩን መከልከል
ለውጥን ስናስብ የምንኖርበትን ነባራዊ ሁኔታን ተረድተን ሕይወትን በአግባቡ መምራትን ይጠይቃል። ነባራዊ ሁኔታን ማወቅን ተከትሎ ሁኔታውን መቀበል ወይንም መቀየር ያለበትን ለመቀየር መነሳሳትን ያመጣል። ከነባራዊ ሁኔታ ግምገማ ውስጥ ከምናወጣቸው ነጥቦች መካከል አንዱ ለለውጥ በምናደርገው ጉዞ ውስጥ የሚገጥመንን ውስንነትን መረዳት ነው።
ውስንነት በምድር ላይ ባለ በየትኛውም አካል ላይ በተፈጥሮ ውስጥ የሚሰጥ የጋራ መገለጫ ነው። የሰው ልጅ ያለፈው ታሪኩ የሚያሳየን ውስንነቱን ለማሸነፍ የሚያደርገው ጥረት መኖሩን ነው። በሂደቱም ለውጥ እየተወለደ ይሄዳል።
ውስንነትን ሳይረዱ ለውጥን ማሰብ አንዳንዴ ውስን ሀብትን እንዲሁ ለማባከን የሚዳርግ ሊሆን ይችላል። አንዳንዱ ውስንነት ቀን በቀን የምናውቀው ሲሆን ሌላው ግን ድንገተኛ ክስተትም ሊሆን ይችላል። ሞክሮ ሞክሮ አልሳካ ሲል የምንቀበለው ውስንነት እርሱ የትህትናን መንገድ የሚያሳይ፤ በውስንነት ውስጥ የመኖርን ጥበብ መረዳትን የሚያመጣምነው።
አካላዊ ውስንነት፣ ከቤተሰብ የሚመጣ ውስንነት፣ በትዳር ሕይወት ውስጥ የሚገኝ፣ የጊዜ፣ የገንዘብ ወዘተ ብለን ለለውጥ መምጣት ውስን የሚሆንብንን ለይተን እንዴት መፍትሔ እንደምናገኝለት ማሰብ ያስፈልጋል። ከልካዩን ውስንነትን መከልከል ከቻልን የለውጥ እርምጃ ለመተለም አቅጣጫን መንደፍ ያስፈልጋል። ምን ዓይነት አቅጣጫን ተከትለን እንደምንራመድ የሚያሳይ።
መስመሩን ማግኘት
ጉዞ ለማድረግ ተነስተን ከእዚህ በፊት ወደማናውቀው አካባቢ ለመሄድ ስንነሳ አቅጣጫውን ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን። ለለውጥ አቅጣጫን ማግኘት ወሳኝ የሆነውን ያህል፤ አቅጣጫን መሳት ልብን ያደክማል። አቅጣጫ መሳት የሚያስከፍለውም ዋጋም ብዙ ነው።
በሕይወት ጉዟችን ውስጥ አቅጣጫ ከፍተኛ ቦታ የምንሰጠው ነገር ነው። አቅጣጫን ማስተካከል ጤናማ የለውጥ እቅድን ለመምራት ያግዛል። አቅጣጫን ማስተካከል ግን ለሁሉም ቀላል አይደለም። ስህተት እንደሆነ ከምናስበው ነገር ለመውጣት ከራሳችን ጋር መማማሉ የተለመደ ነው። ሆኖም ያሰብነውን ማድረግ ሳንችል ቀርተን ራሳችንን እናገኘውና እንገረማለን። አመት መጥቶ በሄደ ቁጥር በተሳሳተ መንገድ ውስጥ ያለው አቅጣጫችን እንዲስተካከል ተስፋ እናደርግም ይሆናል።
አቅጣጫ ፍለጋ በብዙ የሕይወት ክፍል ውስጥ ሊገጥመን ይችላል። በትዳር ሕይወት ጉዳይ፣ በሥራ ጉዳይ፣ በማህበራዊ ሕይወት፣ ከሱስ በመውጣት፣ ገንዘብ በመያዝ ወዘተ አቅጣጫ ፍለጋ ውስጥ እንሆን ይሆናል። ከትናንት ትምህርት ውስጥ የሚቀዳ ነገን ስናስብ መሆን ወደ ምንፈልገው እንድንደርስ የሚያደርግን እይታም የያዘ ነው። የአዲስ አመት ዋዜማ ውስጥ ያሉት ሳምንታትን በስፋት አእምሮችን በአቅጣጫ ፍለጋ ተሞልቶ እናየውም ይሆናል። አቅጣጫ ፍለጋ አስፈላጊ ነገር ነው፤ የለውጥ ጉዞ መስመር ነውና ።
ዛሬ ወደ ውስጣችን ስናዳምጥ በተሳሳተ መንገድ እንደሆንን የሚሰማን ምን ጉዳይ አለ? ውስጣችንን ባዳመጥን ቁጥር የሚያስቃስተንም ይሆን? እንዲህ ዓይነት ስሜትን ተሸክመን ወደ አዲስ አመት ከመግባት ስሜቱን አዳምጦ መስተካከል የሚገባው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ማሳለፍ ተገቢነት ይኖረዋል። በተደጋጋሚ ሞክረን ባልተሳካልን ነገር ተስፋ ወደመቁረጥ ከመሄድ የቀደመው ግምገማችን ውስጥ የነበረውን ጉድለት በመገምገም አሁንም ለሌላ ሙከራ በእችላለሁ መንፈስ በመነሳት የለውጥ አቅጣጫ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።
አዲስ አመትን አዲስ የሚያደርገው፤ አዲስን ወር አዲስ የሚያደርገው፤ አዲስን ሳምንት አዲስ የሚያደርገው እንዲሁም አዲስን ቀን አዲስ የሚያደርገው በራሱ በቀኑ ሳይሆን በውስጣችን በሚፈጠረው አዲስ መነሳሳት ነው። አዲሱ መነሳሳት በጥንካሬ ሲሆን አቅጣጫ ፍለጋውን ያቀለዋል። አቅጣጫ ፍለጋው ወደ ውጤት ከመምጣት ባሻገር ነገ ላይ ለሚገጥመን ፈተና የሚረዳ ትምህርትን ከትናንት ማግኘት የምንችለው በአዲስ ልብ በመነሳሳት ነው።
አቅጣጫ ፍለጋ ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚሠራ ስህተት ትናንትን ሙሉ ለሙሉ አፍርሶ እንደ አዲስ ነገሮችን ለመሥራት መሞከር ነው። በሕይወታችን እጅግ ውስን ጉዳዮች ብቻ ሙሉ ለሙሉ አፍርሶ መስራትን የሚጠይቁ ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨባጭ ግን ሁሉንም ነገር አፍርሶ ለመሥራት መዘጋጀት አደጋ አለው። ትናንት ውስጥ ያገኘነው በጎነገር ላይ ተጨማሪውን እየጨምርን ወደፊት መራመድ ውስጥ የተሻለው ውጤት አለ። የተሻለው የሕይወት አቅጣጫ።
የተለምነው አቅጣጫ፣ ለራሳችን የምንሰጠው ቦታ፣ በጥንካሬና ድክመታችን ውስጥ ያለው ቁምነገር ወዘተ በልባችን ውስጥ ይብላላል፤ ለተግባር እርምጃም የሚያነሳሳን ይሆናል። ልባችን የለውጥ ማቀነባበሪያ ስፍራ ስለሆነ።
የለውጥ ማቀነባበሪያ ስፍራ
ልብ የሕይወት መውጫ ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትርጉም ተሰጥቶት እናገኛለን። በልብ በኩል የሚወጣውና የሚገባው ረጅሙን አቅጣጫ የመወሰን ጉልበቱን በሚገባ የሚያሳይ ስለሆነ። ልባችን ውስጥ የሚሆነውን ስሜት ቃላት ሊገልጹ የማይችሉበት የሕይወት ጉዞ ውስጥ አልፈን ይሆናል፤ ምናልባትም በእዚህ ወቅት እያለፍን ያለን።
አንባቢው አሁን ባለበት ቦታ ሆኖ በዙሪያው ያሉትን ሰዎች ይቃኝ። በልባቸው ውስጥ ምን ይዘው እየኖሩ እንደሆነ ለማወቅ ይመርምር። ለውጥን ወይንስ ባሉበት ነገር ተመቻችቶ እዚያው አመታትን እየረገጡ መኖርን። በእርግጥ ከባድ ጥያቄ ነው። ልብ የሕይወት መውጫናት ሲባል የሕይወት መላ አቅጣጫ የሚብላላባት መባሉ ነው። የለውጥ ጉዞም የውስጥ መነካትን፤ ስለ ለውጥ ሊከፈል የሚገባውን የትኛውንም ዋጋ ለመክፈል መቁረጥን ወዘተ ይጠይቃል። በልባችን ውስጥ ተራራ የመውጣት ውሳኔ ሲኖር ለውጥ ዳር ይደርሳል። ስለሆነም ዛሬ ራሳችንን በመመልከት ስለ ለውጥ እናስብ፤ መሰናክሉን በሙሉ በመውጣት ወደ ሚደረስበት ከፍታ። ለውጥ በመውጣት!!!!
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ