የሰነድ ቁጥር 101675 የሆነው መዝገብ ባለጉዳዮች ጥቅምት 24 ቀን 2008 ዓ.ም ከችሎቱ ፊት ቆመዋል፤ ዳኞችም በችሎቱ ተሰይመዋል። የአመልካች ወይዘሮ መስከረም ሞጋ ጠበቃ መስፍን ጌታቸው በአካል ተገኝተዋል። ተጠሪዋ ወይዘሮ ትዕግስት አረጋ በኩል የቀረበ ባይኖርም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ፍርድ ከመስጠት አላገደውም።
የክሱ ይዘት
የሥራ ውል መነሻ ያደረገ የደመወዝ ክፍያ ጥያቄ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኗ ተጠሪ በአሁኗ አመልካች በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመሠረቱትን ክስ መሠረት በማድረግ ነው። አመልካች በየደረጃው ጉዳዩን የተመለከቱት ፍርድ ቤቶች መሠረታዊ የሕግ ስህተት የፈፀሙ በመሆኑ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ የሚል አቤቱታ በማቅረባቸው አጣርቶ ለመወሰን የቀረበ ጉዳይ ነው።
በተጠሪ የቀረበው ክስ ይዘት በአጭሩ በፈረንሳይ ሀገር በአመልካች መኖሪያ ቤት ውስጥ በየወሩ 1200 /አንድ ሺህ ሁለት መቶ ዩሮ/ ደመወዝ እየተከፈላቸው በሞግዚትነት እንዲሠሩ በ19/02/2001 ዓ.ም በተፃፈ ውል በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 09 በሚገኘው በአመልካች ወላጆች ቤት ውስጥ ተፈራርመው ከመጋቢት 02 ቀን 2001 ዓ.ም እስከ መጋቢት 08 ቀን 2002 ዓ.ም ድረስ ለአንድ ዓመት ሲሠሩ እንደቆዩ ያስረዳሉ።
የሥራ ውሉም አመልካች ፈረንሳይ አገርን ሲለቁ የሚቋረጥ ስለመሆኑ፣ አመልካች የተጠሪ ደመወዝ ሳይከፈሉ እንዳሰናበቷቸው የዓመት እረፍት ጊዜም አምስት ሳምንት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በውሉ የተመለከተ ቢሆንም እንዳልተሰጣቸው፣አመልካች ደመወዛቸውን እንዲከፍሉዋቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል፣ በሽምግልና ጥረት ቢያደርጉም ሊከፈላቸው እንዳልቻለ፣ 1200 ዩሮ በመሆኑ፣ ደመወዝ 299ሺ520.00 የአምስት ሳምንት የእረፍት ጊዜ 29ሺ120 በድምሩ 328ሺ640 ብር (ሦስት መቶ ሃያ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ አርባ ብር) እና ክስ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ገንዘብ ተከፍሎ እስከሚያልቅ ድረስ ዘጠኝ በመቶ ወለድ ጋር እንዲከፈላቸው፣ የወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።
ለአመልካች በስር ፍርድ ቤት
አመልካች የበኩላቸውን መልስ ያቀረቡ ሲሆን ዋና ፍሬ ነገሩም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያና በፍሬ ነገሩ በሰጡት መልስ ክሱ በፌደራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት ቀርቦ የተዘጋ ስለመሆኑ፤ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የማየት ስልጣን እንደሌለው፣ የተጠሪ የደመወዝ ጥያቄ በይርጋ የሚታገድ መሆኑ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ በፍሬ ጉዳዩም ተጠሪ ያልተከፈላቸው ደመወዝ አለመኖሩን፤ ደመወዝ ካልተከፈላቸው ውሉ ለመዘገበው የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያቀርቡ እንደነበር በመግለፅ መከራከራቸውን የሚያመለክት ነው።
የሥር ፍርድ ቤትም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በተመለከተ በ18/06/2006 ዓ.ም ብይን የሰጠ ሲሆን ጉዳዩን ተመልክቶ የመወሰን የሥረ-ነገር ስልጣን እንዳለው በመጥቀስ የአመልካች መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል። የሥር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር እና የቀረቡ ምስክሮች የሰጡት ቃል ከመረመረ በኋላ በግራ ቀኙ የተፈረመው የሥራ ቅጥር ውል መኖሩን ተቀብሎ የተጠሪ የወር ደመወዝ 1200 ዩሮ እንደነበር በአመልካች ከቀረበው ማስረጃ ፍርድ ቤት የተቀበለው የክፍያ መጠን በድምሩ 6ሺ408 ብር ብቻ እንደሆነ፤ ተጠሪ የሚገባቸው ቀሪ ክፍያ ብር 293ሺ112 መሆኑን፤ የአምስት ሳምንት የእረፍት ክፍያ በድምር ብር 29ሺ120 እንደሆነ በአጠቃላይ አመልካች ለተጠሪ ብር 322ሺ232 (ሦስት መቶ ሃያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሠላሳ ሁለት ብር) እንዲከፈሉ በማለት ወስኗል።
አመልካች በሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ቅሬታ ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኘም። ይህ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንን በመቃወም ለማስለወጥ ነው። ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ቀርቦ እንዲመረመር በመደረጉ ተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ግራ ቀኙ የጽሑፍ ክርክር አድርጓዋል።
የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሠረታዊ ይዘትም የተጠሪ የክፍያ ጥያቄ በፍትሐብሔር ቁጥር 2601 እና 2023/ሀ/ መሠረት በይርጋ የሚታገድ ነው፤ ጉዳዩ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች የሚዳኝ አይደለም፤ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች መቅረብ ከነበረበትም በሥራ ክርክር ችሎት መቅረብ ነበረበት የሚል ይዘት ያለው ነው።
ተጠሪ በበኩላቸው ክሱን በወቅቱ ማቅረባቸው እና በይርጋ የሚታገድበት ሕጋዊ ምክንያት የሌለ ስለመሆኑ ዝርዝር ክርክር አቅርበዋል። አመልካች ያቀረቡት የመልስ መልስም የሰበር አቤቱታውን የሚደግፍ ነው። የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙ የጽሑፍ ክርክር፤ ለሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነው ውሳኔ አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። በዚሁ መሠረት የችሎት ምላሽ የሚያስፈልጋቸው መሠረታዊ ነጥቦች ብሎ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ዘርዝሯል።
ግራ ቀኙ በሚከራከሩበት ጉዳይ አግባብነት ያለው የሕግ ማዕቀፍ የትኛው ነው?፣ የደመወዝ ክፍያ ግምት በተመለከተ የተነሳው የይርጋ ክርክር ተፈፃሚነት ያለው የይርጋ ድንጋጌ በአጣሪ ችሎቱ የተጠቀሰው የፍ/ሕ/ ቁ.2023/ሀ/ ነው ወይስ አይደለም ፤ አመልካች ለተጠሪ ሊከፍሏቸው የሚገባው በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠው የገንዘብ መጠን ምን ያህል ነው? የሚሉት ናቸው።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው፤ አመልካች እና ተጠሪ የሥራ ውል ግንኙነት እንደነበራቸው፤ ውሉም ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈርሞ በፈረንሳይ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደተመዘገበ የተካደ ጉዳይ አይደለም። አመልካች ከተጠሪ ጋር የሥራ ውል ግንኙነት እንደነበራቸው ሳይክዱ ሁሉም ክፍያዎች በወቅቱ እንደተከፈሉ፣ አልተከፈለም የሚባል ገንዘብ ካለም በይርጋ እንደሚታገድ ተከራክሯል።
ተጠሪ በበኩላቸው በአመልካች ቤት በሞግዚትነት ለአንድ ዓመት ማገልገላቸው እና የጠየቁት ክፍያ እንዳልተፈፀመላቸው እንዲሁም ክሱን በወቅቱ ስለማቅረባቸው በስር ፍርድ ቤት ካቀረቡት ክርክር መረዳት ይቻላል። ይህ ችሎትም ግራ ቀኙ እያከራከረ ያለው መሠረታዊ ጭብጥ እንደሚከተለው መርመሮታል።
የመጀመሪያው ጭብጥ በተመለከተም አመልካች የተጠሪ የሥራ ቅጥር ውል ከፍ/ሕ/ቁ. 2601 አንፃር እንዲታይ በሰበር አቤቱታቸው አመልክቷል። የዚህ ድንጋጌ መሠረታዊ ይዘት በቤተሰብ አስተዳደር ውስጥ ስለሚኖር አሽከር የሥራ ውል፤ ሠራተኛውን የሚኖሩት መብትና ግዴታዎች የሚመለከት ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል። ይህ ድንጋጌ ያለው የተፈፃሚነት ወሰን ሲታይ በአገር ውስጥ በሚቀጠሩ ሠራተኞች ስለመሆኑ የሚያከራክር ጉዳይ ነው።
በተያዘው ጉዳይ የአመልካች እና ተጠሪ የሥራ ውል በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈፅሞ በፈረንሳይ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፀድቆ አመልካች እና ተጠሪም በፈረንሳይ አገር ሲኖሩ እንደነበር ባልተካደበት ሁኔታ ከላይ የተመለከተው ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ለተያዘው ጉዳይ ተፈፃሚነት ያለው ሁኖ አልተገኘም። በሌላ በኩል ስለአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ የወጣው አዋጅ ቁጥር 377/96 እና የዚህ አዋጅ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 494/1998 ዓላማና ግብ በሀገር ውስጥ ስለሚኖረው የሥራ ስምሪት የተዋዋይ ወገኖች መብትና ግዴታ፤ ሊሟሉ የሚገባቸው አነስተኛ መመዘኛዎች ማለትም የሥራ ሰዓት፤ የእረፍት ጊዜ፣ የሕመም ፈቃድ ወዘተ ያካተቱ ሕግ እንጂ በውጭ አገር ተቀጠረው ሥራ ሲሠሩ የነበሩ ሰዎች የሚያነሱት የመብት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ሆኖ አልተገኘም። በመሆኑም አመልካች እና ተጠሪ በሚከራከሩበት ጉዳይ ተፈፃሚነት ያለው ሕግ /Governing Law/ በሀገር ውስጥ ባለው የሥራ ስምሪት የግራ ቀኙ አንፃራዊ መብትና ግዴታ የሚደነግጉ የፍ/ሕ/ቁ.2601 እና የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ የሚመለከት አዋጅ 377/96 አለመሆኑን ተረድተናል ይላል።
ለተያዘው ጉዳይ ተፈፃሚነት ያለው የሕግ ማዕቀፍ ስለሥራና ሠራተኛ ማገናኘት አገልግሎት የወጣ አዋጅ ቁጥር 632/2001 ነው። የዚህ አዋጅ መግቢያ፤ የተፈፃሚነት ወሰን የሚመለከት አንቀፅ 3/2/ “የግል አገልግሎት ሥራ ላይ ለመቀጠር ወደ ውጭ አገር በሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ላይ ተፈፃሚነት ይኖረዋል” በማለት ደንግጓል። በተያዘው ጉዳይ የአመልካች እና ተጠሪ የሥራ ውል የግል አገልግሎት ሥራ ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑ በስር ፍርድ ቤት ከተደረገው ክርክር መረዳት ይቻላል። በመሆኑም ለጉዳዩ አግባብነት ያለው የሕግ ማዕቀፍ አዋጅ ቁጥር 632/2001 ነው ብለናል ይላል።
ሁለተኛ ይርጋን የተመለከተ ክርክር ነው። አመልካች የተጠሪ የደመወዝ ክፍያ ጥያቄ በስድስት ወር የሚታገድ ነው በማለት ተከራክረዋል። በዚህ ችሎት እንዲመረመር የተያዘው ጭብጥም የይርጋ ጥያቄው ከፍ/ሕ/ቁ.2023/ሀ/ አንፃር እንዲታይ ነው። ይህ ድንጋጌ ከፍ/ሕ/ቁ.2601 በማጣመር ስንመለከተው በሀገር ውስጥ በቤት አገልጋይነት የተቀጠሩ አሽከሮች በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ክፍያ ካልተጠየቁ እንደተከፈለ የሕግ ግምት ይወሰዳል የሚል ይዘት ያለው ስለመሆኑ ተመልክተናል። በተያዘው ጉዳይ የፍ/ሕ/ቁ. 2601 ይሁን የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 በሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት ላይ በሚነሱ ክርክሮች እንደነገሩ ሁኔታ ተፈፃሚ ከሚሆኑ በስተቀር በውጭ አገር ለተሰጠው አገልግሎትና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የክፍያ ክርክር አግባብነት ያላቸው የሕግ ማዕቀፎች ባለመሆናቸው አመልካች የተጠሪ የመብት ጥያቄ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የሚታገድ ነው በማለት ያቀረቡት ክርክር የሕግ መሠረት የለውም።
አዋጅ ቁጥር 632/2001 አንቀፅ 3/1/ የአዋጁን የተፈፃሚነት ወሰን አንቀፅ 20 ስለ ሠራተኛው መብት፣ አንቀፅ 24 ስለ አነስተኛ ደመወዝ መጠን የሚመለከቱ መሠረታዊ ድንጋጌዎች ያካተተ ቢሆንም፤ በአሠሪና ሠራተኛው የሚነሳው የክፍያ ጥያቄ በተለይም የመብት ጥያቄ ለማቅረብ ተፈፃሚነት ያለው የይርጋ ድንጋጌ በግልፅ የተቀመጠ ነገር የለም። እንዲህ ከሆነ ደግሞ አመልካች እና ተጠሪ እያከራከረ ያለው የይርጋ ጉዳይ መታየት ያለበት ከአጠቃላይ የውል ድንጋጌዎች አንፃር ስለመሆኑ ተቀባይነት ያለው የሕግ አተረጓጎም ሥርዓት ነው። የፍ/ ሕ/ቁ. 1677/1/ ‹‹ግዴታዎቹ ከውል የተገኙ ባይሆኑም የዚህ አንቀፅ ደንቦች ይፈፀሙባቸዋል” በማለት የደነገገ ሲሆን የዚህ ድንጋጌ ተዛማጅ የሆነው የእንግሊዘኛው ትርጉም›› 1677/1/ the relevant provisions of this title shall apply to obligations not withstanding that they do not arise out of a contract” በማለት የተደነገገ መሆኑን ተረድተናል ይላል የምርመራ ውጤቱ።
በተያዘው ጉዳይ አመልካችና ተጠሪ እያከራከረ ያለው የክፍያ ጥያቄ ክርክር ተፈፃሚነት ያለው የሕግ ማዕቀፍ ከፍ/ሕ/ቁ.1677/1/ እና 1845 አንፃር መታየት ያለበት ነው። የአመልካችና ተጠሪ የሥራ ውል ግንኙት መሠረት በማድረግ የሚነሳው ክርክር በ10 ዓመት ይርጋ ቀሪ የሚሆን ነው። በመሆኑም በአመልካችና ተጠሪ መካከል የነበረው የውል ግንኙነት የተቋረጠው መጋቢት 2002 ዓ.ም በመሆኑ ክሱ እስከቀረበበት መጋቢት 13 ቀን 2003 ዓ.ም ያለው ጊዜ ሲታይ በፍ/ሕ/ቁ.1845 የተቀመጠው የይርጋ ጊዜ ሳይጠናቀቅ ክስ መቅረቡን የሚያሳይ ነው። በመሆኑም አመልካች የማያነሱት የይርጋ ጥያቄ ተፈፃሚነት ካለው የይርጋ ድንጋጌ አንፃር ሲታይ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም። ስለሆነም የተጠሪ የደመወዝ ክፍያ ጥያቄ በይርጋ የሚታገድ አይደለም።
መጨረሻው ጭብጥ በተመለከተ፤ የሥር ፍርድ ቤት ተጠሪ በወር 1200 ዩሮ እየተከፈላቸው ይሠሩ እንደነበር አረጋግጧል። አመልካች ክፍያ መፈፀማቸው ቢከራከሩም የሥር ፍ/ቤት በማስረጃ የተደገፈ ነው በማለት የተቀበለው ክፍያ 6ሺ408 ብር ብቻ መሆኑ ከውሳኔው ግልባጭ መረዳት ተችሏል። ተጠሪ ያልተከፈላቸው አጠቃላይ ደመወዝና የአምስት ሳምንት የእረፍት ጊዜ ክፍያ ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ ሲመነዘር (6ሺ408 ተቀንሶ) 322ሺ232ብርመሆኑን በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተመልክቷል።
የሥር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ መዝኖ አመልካች ለተጠሪ ብር 322ሺ232 ይክፈሉ በማለት የሰጠው የውሳኔ ክፍልም የሚነቀፍ ሆኖ አልተገኘም።በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የስር ከፍተኛና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔዎች በውጤት ፈርጆ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመባቸው መሆኑ የሚያሳይ ነገር ያልተገኘ በመሆኑ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
ው ሳ ኔ
1. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮድ መለያ ቁጥር 99933 በ12/07/2006 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ፤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ቁ 99977 ግንቦት 6/2006 የሰጠው ትዕዛዝ ፀንቷል፡፡
2. አመልካች እና ተጠሪ የሚከራከሩበት የይርጋ ጊዜ የሚገዛው በፍ/ሕ/ቁ 1677/1/ እና 1845 ነው፡፡ በዚህ መሠረት የተጠሪ የመብት ጥያቄ በይርጋ ቀሪ አልሆነም በማለት ወስነናል፡፡
3. አመልካች ለተጠሪ ብር 322ሺ232 ሦስት መቶ ሃያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰላሳ ሁለት/ ከ13/07/2003 ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሰብ 9% ወለድ እንዲከፍሉ መወሰኑ በአግባቡ ነው ብለናል፡፡
4. በዚህ ፍርድ ቤት ክርክር ያወጡት ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ በማለት የዘጋ ሲሆን፤ በፍርድ ቤት ሐምሌ 30 ቀን 2006 ዓ.ም የተሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል ሲል መዝገቡ ዘግቷል፡፡