በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ግንደበረት ወረዳ ነው ተወልደው ያደጉት። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ጊጥሬ በተባለ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ግንደበረት እና የቀድሞው አምቦ መስከረም ሁለት ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። አምቦ እርሻ ኮሌጅ ገብተውም በእርሻ መምህርነትና አጠቃላይ እርሻ ትምህርት መስክ ሰልጥነዋል። አምቦ ቢዝነስ ኮሌጅ በሕግ ዲፕሎማዎችን አግኝተዋል። ከዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ገብተው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዲሁም አምቦ ዩኒቨርስቲ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሕግ የትምህርት መስክ ተቀብለዋል። በመቀጠልም ሊድስታር በሚያስተባብረው በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ተጨማሪ የማስተርስ ዲግሪያቸውን እንዲሁም ገሊላ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በሊደርሺፕና ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ የዶክትሪት ዲግሪያቸውን ሠርተዋል።
ለረጅም ዓመታት በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ አገልግለዋል። ከእዚህም መካከል በኦሮሚያ ፖሊስ አምቦ ከተማ የፖሊዝ አዛዥ ሆነው ለአራት ዓመታት እንዲሁም በምዕራብ ሸዋ ዞን ማኅበራት ማደራጃ መምሪያና በትምህርት ቢሮ ለአራት ዓመታት የሕግ ባለሙያነትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው መሥራታቸው ይጠቀሳል ። ካለፉት 13 ዓመታት ወዲህ ደግሞ በፌደራልና በክልል ፈቃድ አግኝተው በሕግ አማካሪነትና ጥብቅና ሥራ ላይ እየሠሩ ይገኛሉ። በእነዚህ ዓመታትም በሕወሓት በግፍ ለታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችን ጥብቅና በመቆም በርካቶችን ነፃ ያወጡት እኚሁ ሰው በዚህም ሽብርተኞችን ትረዳለህ በሚል ዘብጥያ ወርደው ለሦስት ወራት በስቃይና በእንግልት ቆይተዋል። ዶክተር ዳባ ጩፋ የዛሬው የዘመን እንግዳችን ናቸው። በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- ለእስር የዳረገዎትን አጋጣሚ ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
ዶክተር ዳባ፡- እንደምታስታውሽው ለውጡ ከመምጣቱ በፊት በኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎች ሕዝባዊ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር። ኅብረተሰቡ ከ27 ዓመታት የሕወሓት የጭቆና ቀምበር ለመላቀቅ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲያደርግና ጥያቄዎችንም ሲያነሳ ነበር። በእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ እኔም ተሳትፌ ነበር። የነበረው ሥርዓትና አስተዳደር ዘይቤ ኅብረተሰቡን ያማከለ አልነበረም። እስራት አለ፤ ግርፋት አለ። ኅብረተሰቡ እምቢታውን ሲገልፅ እኔም ጩኸቱን ተጋርቻለሁ። በተጨማሪ ደግሞ በወቅቱ በኦሮሚያ ውስጥ በርካታ ወጣቶች ታስረው ነበር። በመሆኑም ለ264 የኦሮሚያ ወጣቶች ነፃ የጥብቅና አገልግሎት በ28 መዝገብ ላይ የሽብር መዝገብ ቆሜ 182 የሚሆኑትን ነፃ አውጥቻለሁ። ያንን ክርክር በማካሂድበት ሰዓት በወቅቱ የነበሩት የወያኔ ሰዎች ለአሸባሪ የቆመ ሽብርተኛ ነው በማለት ከችሎት ወስደው ለሶስት ወራት ጦላይ አስረውኛል። ለሶስት ወራት ጦላይ በስቃይ ካቆዩኝ በኋላ ያለምንም ክስና አንድም ቀን ፍርድ ቤት ሳያቀርቡኝ ነው በነፃ የለቀቁኝ። በወህኒ በቆየሁባቸው ጊዜ ድንጋይ መሬት ላይ ነበር እተኛ የነበረው፤ የሚጠጣ ውሃ አልነበረም። በዚህ ምክንያት ለከፋ የኩላሊት ሕመም ተዳርጌ ነበር። ለአንድ ወር ያህል ደም ነበር ስሸና የነበረው። በኋላ በግሌ ባደረኩት ሕክምና ማገገም ችያለሁ ።
አዲስ ዘመን፡- ለታሰሩበት የተሰጠዎት ምክንያት አልነበረም?
ዶክተር ዳባ፡- በግሌ ምንም አልተነገረኝም፤ ግን የታሰርነውን ሁሉ በጅምላ ሕዝብ ለአመፅ ቀስቅሳችኋል፤ ወጣቱ ለመንግሥት ተገዢ እንዳይሆን አነሳስታችኋል ይሉን ነበር። በተለይም በወቅቱ አነጋጋሪ የሆነው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጉዳይ ክልል ከተሞች ድረስ ዘልቆ ለነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ እኛ እንዳስተባበርን አድርገው ነበር ሲናገሩን የነበረው። እርግጥ ነው የሕዝብ ጥያቄ ነበር፤ ሆኖም ነውጥና ረብሻ ይደረግ የነበረው በእዛው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በነበሩ ሰዎች መሪነት ነው። ሕዝቡ እንዳደረገው ለማስመሰል የተለያዩ ጥረቶች ይደረግ ነበር። ለምሳሌ በወቅቱ ኦነግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ ተፈርጆ ነበር፤ የኦነግ ባንዲራ የግለሰቦች ቤት ውስጥ ያስቀምጡና የብርበራ ትዕዛዝ አውጥተው ‹‹የኦነግ ባንዲራ ተገኝቶብሃል›› ተብለው በርካቶች እንዲታሰሩ ተደርገዋል። እኛም ይህንን ድርጊታቸውን ነበር የተቃወምነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ተነስቶ የለወጡ መምጣት በሰብዓዊና ዲሞክራሲ መብቶች መከበር ላይ ምን ውጤት አስገኝቷል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ዳባ፡- እንግዲህ ያንንም ሆነ አሁን ያለውን መንግሥት በደንብ እንደሚያውቅ ሰው አንፃራዊ የሆነ ለውጥ እንዳለ አምናለሁ።ፍፁም የሆነ ለውጥ መጥቷል ባይባልም መሻሻል አለ፤ ይህንን መካድ አይቻልም። መሻሻሎቹ ቀጠሉ፤ አልቀጠሉ የሚለው ነገር ሌላ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ በፊት ሰው በአደባባይ ወጥቶ መናገርም ሆነ ሃሳብ መግለፅ አይችልም ነበር። በመንግሥት መዋቅሩ ውስጥ ያለው አካል እንኳን እንደልቡ ሃሳቡን እየገለፀ የሚሰራበት ምህዳር አልነበረም። እነዚያ ነገሮች ተሻሽለዋል። የተገኙ መሻሻሎች እንዳሉ ሆነው የሚቀሩ ብዙ ነገሮች አሉ። ችግሮቹ በአብዛኛው ካለፈው ሥርዓት የተሻገሩ ናቸው። በሌላ በኩልም ሰዎች ሃሳባቸውን እንዳይገልፁ አፍኖ ይዞ የነበረው ሥርዓት ነፃ ሲለቀቅ ሌላ ችግር ፈጠረ። ታፍኖ የነበረው ሁሉ አሁን ላይ መረን ሆነ። ከፋፋይ የሆኑ ሃሳቦች ተፈጠሩ፤ ቀድሞ የነበረው ችግር ራሱ ሌላ አዲስ ችግር ወለደ። አሁን እንደምናየው የሕዝብ አስተሳሰቦች ተከፋፍለዋል።
አዲስ ዘመን፡- የሕዝብ አስተሳሰቦች ተከፋፍለዋል ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ዶክተር ዳባ፡- ለምሳሌ አሁን ላይ ሕዝቡ በሶስት ሃሳቦች የተከፈለ ይመስለኛል። አንደኛው በአንድ ሀገር የሚያምንና ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች በእኩል የሚኖሩባት አንዲት ኢትዮጵያ መኖሯን የሚያምነው የኅብረተሰብ ክፍል ሲሆን፤ ሁለተኛው ኢትዮጵያ አንዲት ሀገር ብቻ የሚለውን ሃሳብ በመቀበል ብሔር ብሔረሰቦችን የማያከብር አቋም የሚያራምድ ነው። ሶስተኛው ደግሞ ብሔርን ወይም ክልልን እንደሀገር የሚቆጥር ሲሆን ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያዊነት ቦታ የማይሰጥና ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር በዓይናችን አንይ የሚሉ ናቸው። ለምሳሌ ወደ ኦሮሚያ ክልል ብንሄድ ኦሮሚያ ሀገር እንደሆነች፤ ኢትዮጵያ ራሱ ኦሮሚያ እንደሆነች የሚናገሩ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሁለት ሃሳቦች ጫፍ የረገጡ ናቸው። ሁለቱም ሃሳቦች የዘነጉት ነገር አለ። የራሳቸውን ብሔር ከፍ አድርገው ሲያወሩ የሌላውን ቢያንስ በልኩ ማሞገስ አለባቸው። እነዚህን ፅንፍ የረገጡ ሃሳቦችን በዋናነት የሚያራምዱት በአብዛኛው ሊሂቃን የምንላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። ማኅበረሰቡ ውስጥ ግን እንዲህ አይነቱን ነገር እምብዛም አናገኘውም። ከዚያ ይልቅም በመንግሥት መዋቅር ያሉ ሰዎችም ሊኖሩበት እንደሚችሉ እገምታለሁ።
በአጠቃላይ ከዚህ ቀደም ታጭቆና ታፍኖ የነበረው ስሜት መረን ሲለቅ እንዲህ አይነት መከፋፈሎችን ፈጠረ። ስለዚህ እነዚህ ፅንፍ የረገጡ አስተሳሰቦች ወደኋላ እንድንመለስ እያደረጉን ነው። ምክንያቱም ምንም እንኳን ከ80 በላይ ብሔረሰቦች ቢኖሩንም ዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ የሚያውቀን በኢትዮጵያ ነው። ኦሮሚያም ሆነ ትግራይ አልያም አማራ ክልል የሚታወቁት በኢትዮጵያ እንጂ ራሳቸውን ችለው እንደወጡ ሀገራት ተደርገው አይደለም። ይህም ቢሆን ግን አሁን ድረስ ትግራይን፤ ኦሮሚያንና አማራን ‹‹ሀገር›› የሚሉ ሰዎች አሉ። ይህንን አስተሳሰብ የሚያራምዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ኢትዮጵያን በዓይን ማየት የማይፈልጉ ናቸው። ይህም ለዘመናት የኖርንበት ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር እሴታችን ለፅንፈኝነት ቦታውን እንዲለቅ አደረገ። አሁን ላይ ኅብረተሰቡ እርስ በርስ መቀባበል፤ መከባበርና በጋራ ለመኖር የማይፈልግበት ሁኔታ ተፈጠረ። በነገራችን ላይ ይህ የልዩነት አስተሳሰብ ወደ
አንድ መሰብሰብ ባለመቻላችን ነው ሀገር እየታመሰች ያለችው። ምክንያቱም ሀገር ማለት ኦሮሚያ ወይም አማራ ክልል ማለት አይደለም፤ ሀገር ማለት ኢትዮጵያ ናት። ይህ ሆኖ ሳለ ሃሳቦች ሲሸነሸኑ ታሪኮቻችን ትርክት ሆኑ፤ የነበረ እንዳልነበረ ተተረከ፤ ያልነበረ እንደነበረ ተነገረ። ሰው እውነቱን መዋጥ አቃተው። ውሸቶች እየተነባበሩ ሲሄዱ የእኛን ታሪክ ዋጡት። ለምሳሌ የእኛ ታሪክ ተብሎ ከሚጠቀሱ ነገሮች አንዱ አብሮ ተቻችሎ መኖር ነው። እነዚህን አስተሳሰቦች መሰብሰብ ያለመቻላችን ነው እንደሀገርና እንደ አንድ ሕዝብ እንዳንረጋጋ ያደረገን።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያዊነት ለእርስዎ ምንድን ነው?
ዶክተር ዳባ፡- ለእኔ ኢትዮጵያ ሀገር ናት። እኔ ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ ሃገር የለኝም። ኢትዮጵያ ሃገሬ ብቻ ሳትሆን የትም ብሄድ የምታወቅባት መለያዬ ናት። እንደ አንድ ብሔረሰብ ደግሞ ብሔሬ ኦሮሞ ነው። ትውልዴም ኦሮሚያ ክልል ነው ፤ሃገሬ ግን ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ ለእኔ ብቻ ሳትሆን የ80 ብሔር ብሔረሰቦች እናት ናት። አቅፋ የያዘችን እሷው ናት። እኔ የሚሰማኝም ሆነ የማውቀው በዚያ ልክ ነው። በነገራችን ላይ በአሁኑ ወቅት በሃሳብ ፈርሰን በአካል ብቻ ነው ያለነው። እሱንም ጭምር ለማጥፋት ነው እያተራመሱን ያሉት። እኔ ተማሪ ሆኜ የነበሩት ዘፈኖች ስለሃገር ፍቅርና ስለተቃራኒ ፆታ ፍቅር ብቻ ነበር።የሕዝቡ ሃገራዊ ስሜት ተመሳሳይ ነበር። አሁን ላይ ያሉት ዘፋኞች ግን ብሔር ላይ መንጠልጠላቸው ሳይበቃቻው መንደርና ቀበሌ ድረስ ወርደው በመዝፈን ሃገራዊ ስሜት እንዲጠፋ አድርገዋል። እነዚህ ዘፈኖች ሕዝቡ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ኢትዮጵያ የምትባለውን ሃገር በሃሳብ ሸረሸሯት። አብሮ የመኖር መስተጋብራችን ጠንካራ እንዲሆን ኪነ-ጥበቡ የነበረው ሚና ቀላል አልነበረም። አሁን ደግሞ አብሮነቱ እንዲሸረሸርም ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን ሕዝቡ የተገነዘበው አይመስለኝም።
በመሠረቱ የ27 ዓመቱ ትውልድ ልዩነቱን ብቻ አስቦ እንዲኖር ተደርጎ ነው የተቀረፀው። ልዩነትን አንግበው መቀራረብን እንዲያመጡ ይደረግ የነበረው ጥረትም በእኔ እምነት ከንቱ ድካም ብቻ ነበር። አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተፈጠረውን ችግር በመቀራረብ እንጂ በመለያየት አይፈቱትም። ችግር የሚፈታው አንድ ላይ በመሆን ነው። ሁሉም በየራሱ ክልል አጥር ስር ተቀምጦ ችግር አይፈታም። ምክንያቱም ከችግሩ በላይ የአብሮነት ስሜቱ በጣም ረጅም ነው። ስለዚህ በጋራ ሆነን እንደቀድሞ ተባብረን ነው ፅንፈኝነት ያጣቡንን ሃገር የማፍረስ ሴራ መታገል የምንችለው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የነበረው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ ቀርቷል ማለት ይቻላል?
ዶክተር ዳባ፡- እንግዲህ በ27 ዓመታት ውስጥ ሦስቱ የመንግሥት መዋቅሮች የድርሻቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ በግልፅ ነበር የፖለቲካ ጣልቃገብነት ሲደረግባቸው የነበረው። ለዚያም ነው የሕዝብ ማዕበል ተነስቶ ሥርዓቱን ከመነቅነቅ እስከ ማፍረስ የደረሰው። አሁን ላይም ቢሆን ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ማለት አይቻልም። ምክንያቱም አሁንም ቢሆን ሕግ የሚያወጣው ፖለቲከኛው ነው፤ ይህም የሆነው ያሸነፈው የፖለቲካ ፓርቲ መንግሥት ስለሚያቋቁም ነው። የዚህ ዘመን ችግር ሕጉን የሚመራው ፖለቲካው በመሆኑ ነው። እንደድሮው በቀጥታ ጣልቃ ባይገባም ፖለቲካው ሕጉን ተቆጣጥሮታል። መሆን የነበረበት ግን ሕጉ ፖለቲካውን መምራት ይገባው ነበር። ፓርቲውም ቢሆን መንግሥት ሲመሠርት ይገዛኛል፤ እገዛበታለሁ ብሎ ያወጣውን ሕግ ማክበር አለበት። የፍትሕ ተቋማት ነፃነታቸው ተጠብቆ እንዲሠሩ ማድረግና ማክበር ይገባዋል። ፖለቲካው ለወጣው ሕግ የማይገዛ ከሆነ ፖለቲካው ራሱ የተረጋጋ አይሆንም።
አዲስ ዘመን፡- ከፖለቲካው ባሻገር ብሔርተኝነቱም በፍትሕ ተቋማት ዘልቆ መግባቱ ፍትሕ እንዳይሰፍን ያደረገው መሆኑን አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይናገራሉ። እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ዶክተር ዳባ፡- እኔ በበኩሌ በብሔረሰብ ዳኝነት ላይ የተፈጠረ ችግር አላየሁም። ግን እንደነገርኩሽ ፖለቲካው በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ዘልቆ በመግባቱ ከአንዳንድ ግለሰቦችና ኢንቨስተሮች ጋር ችግር ያለባቸው ፖለቲከኞች የፍትሕ ሥርዓቱ እንዲዛባ ሊያደርጉ ይችላሉ። ምክንያቱም አሁንም ፖለቲካው ነው ሕጉን እየመራው ያለው።ይህም ሲባል ለምሳሌ በፍትሕ ሥርዓት ያለፈ አንድ ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ነፃ ብሎት ካበቃ በኋላ በፖለቲካ ባለስልጣናት ትዕዛዝ እንዳይፈታ የሚደረግበት ሁኔታ አለ። እኔ እንደእውነቱ ከሆነ እገሌ የእገሌ ብሔር አባል ነው ተብሎ ነፃ የሚለቀቅበት ወይም የሚታሰርበት ሁኔታ በግሌ አልገጠመኝም። ይሁንና ካለፈው ሥርዓት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ኢንቨስተሮች አሉ፤ በተለይም በወቅቱ ከነበሩት የሕወሓት ሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት በማጭበርበር ያፈሩት ሃብት ሊኖር ይችላል። እነሱንም ቢሆን ሕግ እንጂ ሊዳኛቸው የሚገባው ፖለቲካው አይደለም። ይህም ሲባል እነዚህ ሰዎች የመደመጥ፤ መብታቸውን የማስከበር ፤ አቤቱታቸውን የማቅረብ ፤ ውሳኔ የማግኘት መብት አላቸው።
እንዳልኩሽ ግን ወደ ፍርድቤት የሚሄዱ ጉዳዮች የፖለቲካ ትርጉም ይሰጣቸዋል ወይም በፖለቲካው ይቃኛሉ። አልያም ከአመለካከት ችግር የመጣ ተደርጎ በማካተት ፍትሕ እንዳያገኝ ይደረጋል። ስለዚህ በእኔ እምነት በፍትሕ ተቋማት ያለው የብሔር ውግንና ሳይሆን የፖለቲካ ውግና ነው። እርግጥ ነው አንድ ቦታ ላይ በፖለቲካ አመለካከት እየተባለ ሳይጣራ ታስረው ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ዜጎች አሉ። ለምሳሌ ሶስት ወርና አራት ወር ምርመራቸውን ማጓተትና ፍትሕ ሳያገኙ እንዲቆዩ የሚደረግበት አጋጣሚ አለ። ይህም የሆነው አስቀድሜ እንዳልኩሽ ፖለቲካው ሕጉን ስለሚመራው ነው። ፍርድ ቤት የለቀቃቸው ሰዎች መልሰው ሲታሰሩ እናያለን። በመሆኑም ይህንን ውዝግብ ማርገብ የሚቻለው ፖለቲካው ራሱ ለሕጉ ሲገዛና በሕግ ሲመራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ማንኛውም ዜጋ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመሥራት፤ የመኖርና ሃብት የማፍራት መብት ሕገ-መንግሥቱ ያጎናፀፈው ቢሆንም የክልል ሕጎች ግን ከሌላ የሃገሪቱ አካባቢ የመጡ ዜጎችን የሚያገልበት ሁኔታ አለ። እርስዎ ይህ ዓይነቱ የሕግ መጣረስ ምን ችግር አምጥቷል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ዳባ፡- የእኛ ሃገር የብሔር ብሔረሰቦች ሰነድ ሕገ-መንግሥቱ ነው። ሕገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጡና የሕገ-መንግሥቱ ዋና ዋና ምሰሶዎች ተብለው የሚጠቀሱ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አሉ። ክልሎች የሚያወጧቸው ሕጎች ሕገ-መንግሥቱን ሳይጣረሱ መውጣት አለባቸው። ተጣርሰው ከወጡ ከሆነ ተቀባይነት የላቸውም። ይህንን በሚጣረስ መልኩ ሕግ ያወጣ ማንኛውም የመንግሥት አካል ተጠያቂ ነው። ይህንን ደግሞ ሕገ-መንግሥቱ በግልፅ አስቀምጦታል። በዚህ ረገድ ተጣርሰው የወጡ ብዙ ሕጎችን ማንሳት ይቻላል። ለዚህ ደግሞ የመሬት አዋጅ፤ የተለያዩ የሙያ ማኅበራት አዋጅ መጥቀስ እንችላለን። ለምሳሌ የእኛ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበርን የሚመለከተው አዋጅ ከሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ ያፈነገጠ ሃሳብ ይዞ ነው የወጣው። ሕገ-መንግሥታችን መደራጀት መብት ነው ብሎ ነው እንጂ ግዴታ ነው ብሎ አልደነገገም። የጠበቆች ማኅበር አዋጅ ግን ‹‹ማንኛውም ጠበቃ የጥብቅና ፍቃድ ሲያወጣ የመደራጀት ግዴታ አለበት›› ብሏል። ይህ ፈፅሞ ከዋናው ሕጋችን የተጣረሰ ነው።
በተመሳሳይ የመሬት አዋጁም የሕግ መጣረስ አለበት። አንድ ሰው መሬት 15 ዓመት ከተቀመጠበት፤ ሃብት ካፈራበት በኋላ ሕገወጥ ተብሎ በግሬደር የሚታረስበትና ግለሰቡም የሚፈናቀልበት ሁኔታ አለ። በዚህ መልኩ የብሔረሰብንና የብሔርን መብት የሚጣረሱ በርካታ ሕጎችና አዋጆችን መጥቀስ እንችላለን። በመሠረቱ በትክክል ሳይጣረሱ የወጡ ሕጎችም ቢሆኑ ወደታች በተሄደ ቁጥር አስፈፃሚ አካላት በሚፈጥሩት ችግር ምክንያት ተዛንፈው የሚቀርቡበት ሁኔታ አለ። ግለሰቦች በሚፈጥሩት ችግር፤ ትንኮሳ በማድረግና አንዱ ሌላውን እንዲጠራጠር በማድረግ የሚፈጠሩ ነገሮች አሁን ያለንበትን ችግር መንስኤ ሊሆን ይችላል ።
ሌላው አሁን ላለንበት ችግር ዋነኛ ምክንያት ነው ብዬ የማስበው በየትኛው የመንግሥት ኃላፊነት ላይ የተቀመጠ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ጨምሮ የሚፈፅመው ስህተት ወንበሩ ላይ በመቀመጡ ያጠፋው ጥፋት ተብሎ መወሰድ ነው እንጂ ያለበት ከእሱ በስተጀርባ ያለው ብሔረሰብ ተጠያቂ ሊሆንም፤ ሊወቀስም አይገባም። አማራ ወይም ኦሮሞ ስለሆነ ተብሎ ምንም የማያውቀውን ማኅበረሰብ ከአጥፊው ጋር በማላተም የሚፈጠረው ችግር ነው አስቸጋሪ እየሆነ ያለው፤ ትልቁ እሳት ይሄ ነው። አቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር ነው፤ መጠየቅ የሚችለው ራሱ በስልጣን ዘመኑ በሠራቸው ሥራዎች ነው እንጂ ወክሎ የመጣውን ብሔረሰብ ሊሆን አይገባም። መንግሥትም ቢሆን ትኩሳቱን ማብረድ ያልቻለው ሁሉንም ነገር በብሔር መነፅር የሚያይና የሚለካ በመሆኑ ነው። ይህም የብሔር ብሔረሰቦች አንድነት እንዲጠፋና እርስበርስ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል። በአጠቃላይ ዋናው ሕጋችን ሕገ-መንግሥቱ ነው ብለናል፤ ከዚያ በኋላ የሚወጡ ሕጎች የሚጣረሱ ከሆነ ዋጋ የላቸውም። ክልሎች የሚያወጡት ሕግ ሌላውን በሚጎዳ፣ በሚነቅፍና ዝቅ በሚያደርግ መልኩ የሚወጣ ከሆነ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው።
ለምሳሌ አንዳንድ ቦታ ላይ ተደራጅተው መሬት ለመውሰድ የሚጠየቁ ነገሮች አሉ፤ መታወቂያ ይጠየቃል፤ ነዋሪነት ይጠየቃል። መሬት ወስዶ ቤት ሠርቶ ለመኖር የዚያ አካባቢ ተወላጅ መሆን ብቻ መስፈርት ሊሆን አይችልም፤ ሰው መሆን በቂ ነው። አንተ ከዚያኛው ክልል ነህ እዚህ መኖር አትችልም የሚባለውን ነገር ሕገ-መንግሥቱን የሚጋጭ ነው። ይህ አይነቱ አካሄድ ኢ-ሕገመንግሥታዊ ከመሆኑም ባሻገር አብሮነትንም የሚሸረሽር ነው። እንዳነሳሁልሽ የእኛን የጠበቆች ማኅበር አዋጅ ጉዳይን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ ዝግጅት እያደረግን ነው። የሚገርመው ኦሮሚያ ላይ ብቻ 1ሺ700 ጠበቆች አሉ፤ እኔ የማኅበሩ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ነኝ። ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በፌደራል ደረጃ የሚሠራ ነው። ተደራጅቶ መሥራት መብት ነው፤ ሕገ-መንግሥቱ ግዴታ አላደረገም።ይሁንና በግዴታ ካልተደራጀን የጥብቅና ፈቃዳችን እንደሚሰረዝ ነው የተነገረን። እንግዲህ እኛ የሕግ ባለሙያዎች ሆነን ሳለ ሕግ ተጣርሶ ኢ-ፍትሐዊ ነገር ከተፈፀመብን፤ ሌላው ሕዝብ ላይ ምንአይነት ግፍ ሊሠራ እንደሚችል መገመት አይከብድም።
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤት ተገኝተው ካነሷቸው ዋና ዋና ችግሮች መካከል የፍትሕ ሥርዓቱ በተለይ ሕግ ተርጓሚዎቹ ላይ እየተስፋፋ የመጣው የሌብነት ወንጀል ነው። በእርስዎ እይታ ይህ ችግር በተጨባጭ አለ? ካለስ በምን መልኩ ነው ከዚህ ችግር መውጣት የሚቻለው?
ዶክተር ዳባ፡- በጣም ከባድ ጥያቄ ነው፤ ችግሩም ከባድ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጉዳይ ላይ አፅዕኖት የሰጡበት ምክንያት አላቸው። እኛም የምናውቀው እውነት ነው። በዚህ ዘርፍ ላይ በጣም ትልቅ የሚባል ችግር ነው ያለው። ችግሩ እንዳይፈታ ያደረገው ደግሞ በቦታው ላይ እነዚህን ሰዎች የሚያስቀምጠው ራሱ መንግሥት መሆኑ ነው። የሚያስቀምጣቸው በራሱ መስፈርትና መለኪያ ነው። እንደእኔ እይታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከገለፁትም በላይ በጣም ውስብስብ የሆነ ችግር ነው ያለው። በነገራችን ላይ ሌብነት ማለት በቀጥታ ገንዘብ ከመሰብሰብ ጋር ብቻ አይገናኝም። ለምሳሌ የሥራ መግቢያ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ30 ሆኖ ሳለ እንዲሁም ፍርድ ቤት ሥራን የሚሠራው በቀጠሮና በሰዓት እንደሆነ እየታወቀ አንድ ዳኛ ባለጉዳይን 4፡00 ሰዓት ቀጥሮ እሱ 5፡00 ሰዓት ይመጣል። ይሄ አንዱ ሌብነት ነው። እነዚህ ባለጉዳዮች ምንአልባትም ከጋምቤላ ወይም ከኢሉአባቦራ ሁለትና ከዚያ በላይ ቀናት መንገድ ላይ አድሮ መጥቶ ይሆናል ፍርድ ቤት የተገኘው። መዝገቡ ላይ የሚሰጡ የዳኝነት አሰጣጥ ሂደቶች ናቸው። መዝገቦችን ያለገደብ አራትና አምስት ጊዜ ለምርመራ መቅጠር ይህም ሌላው ሌብነት ነው። ሰዎችን በዘመድ ሲጠይቋቸው በጓሮ ተገናኝተው ፍትሕ ማዛባት በስፋት ይታያል። በቀጥታ በገንዘብም ተደራድሮ የሚደረግ ነገር ሊኖር ይችላል። እኔ ራሴ ሥራዬም ሆነ ውሎዬ ፍርድ ቤት ነው፤ ብዙ የሚደርስብኝ ግፍ አለ። በተለይ መዝገብ ጠፋ በሚልና ቀጠሮ በማብዛት እኔንም ሆነ ደንበኞችን የማንከራተት ሁኔታ በተደጋጋሚ ያጋጥመኛል።ይህ ሁኔታ ደግሞ ደንበኞቼ በእኔ፣ በፍትሕ ሥርዓቱና በመንግሥት ላይ ያላቸውን እምነት ጭምር እንዲያጡ አድርጓል።
በአጠቃላይ አሁንም ቢሆን የፍትሕ ተቋማት ካልተጠናከሩ ችግሩ የበለጠ እየከበደ ነው የሚመጣው። በነገራችን ላይ ኅብረተሰቡን በቅንነት ማገልገል የሚፈልጉ ጎበዝና ጠንካራ ዳኞች፣ አቃቤ ሕጎችና ጠበቆች አሉ። ይሁንና በሐቅና በቅንነት የሚሠሩ ሰዎችን ብዙ ጊዜ መንግሥት አይፈልጋቸውም። ምክንያቱም መንግሥት የሚሠሩ ሳይሆን የሚፈልጋቸውን ሰዎች መልምሎ ነው የሚያመጣው። የሚሠሩትን ሰዎች እኛ እናውቃቸዋለን። የአቅም ችግር ኖሮባቸው አይደለም። ይልቁንም በመንግሥት ተመልምለው የሚመጡ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ የስነ-ምግባር ችግር እንዳለባቸው በተግባር ታይቷል። ለምሳሌ ጠበቆች ከዳኛው በላይ በምንሠራው ሥራ ተከፋይ ሆነን ሳለ ጥቂት የማይባሉት ዳኞች በጣም ቅንጡ በሆነ ቤት ሲኖሩ ነው የሚታየው። ይህንን ያህል ገንዘብ በየወሩ መንግሥት ከሚከፍለው አግኝቶ ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው የሚመስለኝ። ምክንያቱም ዳኛ የመንግሥት ቅጥረኛ እንጂ ነጋዴ ባለመሆኑ ነው።
ስለዚህ መንግሥት የፖለቲካ ሥራውን የሚያበላሽበት ትልቁ ችግር የፍትሕ ተቋማት በሥርዓት እንዲመራ አለማድረጉ ነው። የሚሾሟቸው ሰዎች ለእሱ ፖለቲካ ስለተመቹ ሳይሆን ፍትሕን ማስፈን እስከቻሉ ድረስ የማይፈልጋቸውንም ቢሆን አምጥቶ ማሠራት ይገባዋል። ምክንያቱም ጉዳዩ የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ሳይሆን የሃገር ጉዳይ በመሆኑ ነው። እውነቱንም ለመናገር በፍትሕ ተቋማት ላይ ባለው ስር የሰደደ ብልሹ አሠራር ምክንያት ተስፋ እንድቆርጥ ተደርጌያለሁ። በተለይ ክልሎች ላይ ፍትሕ የሚባል ነገር የለም። ሕዝቡ ከገጠር ቀበሌ ለቀናት በእግርና በፈረስ ተጉዞ ዞን ላይ ፍትሕ ለማግኘት አምኖ ቢመጣም ፍትሕ እያገኘ አይደለም። መዝገብ ጠፋ እየተባለ ሕዝብ መከራ እንዲያይና እንዲያለቅስ እየተደረገ ነው። ስለዚህ መንግሥት የማይፈልጋቸውንም ሰዎች ቢሆን ለሃገር ሕልውና እና ለሕዝብ መብት ሲባል መልሶ ማሠራት ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡- በተለይም ቀበሌ፤ ወረዳና ክፍለ ከተሞች እንዲሁም የፍትሕ ተቋማት ላይ መዝገብ ጠፋ እየተባለ ተገልጋይ የማንከራተቱ ባህል አሁን ላይ በእጅጉ ተለምዷል። ለመሆኑ ይህንን ችግር የመዝገብ አያያዙ ነው ወይስ ሆን ተብሎ ለሌብነት ሲባል የሚደረግ ተግባር ነው?
ዶክተር ዳባ፡– እውነት ነው፤ ይህ ችግር በጣም ከባድ እየሆነ ነው የመጣው። ሆን ተብሎ መዝገብ ጠፋ ትባያለሽ፤ እኔም ገጥሞኝ ያውቃል። ጠፋ ይሉኝና አልበገር ስላቸውና ብዙ ሳስጨንቃቸው ከሰማይ ይውረድ፤ ከመሬት ይፍለቅ በማላውቀበት ሁኔታ አቆይተው ‹‹አግኝተነዋል›› ይሉኛል። ይሄ ግልፅ የሆነ ሌብነት ነው። ይህ አይነቱን ሌብነት ከወዲሁ በእንጭጩ ካልቀጨነው ወደ ነውጥ ይሄዳል። ሕዝባዊ አመፅ ያመጣል። ሰው መብቱን ከተነፈገ ዝም ብሎ ቁጭ አይልም፤ የትና ማን እንዳጠፋበት ያውቃል፤ ከዚያ በኋላ ሥርዓት አልበኝነት ይመጣል። አንዱ በሌላው ላይ ይነሳል፤ መገዳደል ይከሰታል። ይህም የሚሆነው ደግሞ ከአመራር ችግር ነው። ልክ እንደፍርድ ቤቱ በየክፍለከተማው፤ ወረዳውና ቀበሌ ያሉ አመራሮች በዚያው ልክ ሌቦች ናቸው። መዝገብ ይሰርቃሉ፤ የፍርድ ቤት ውሳኔን ያስገለብጣሉ፤ ምክንያቱም እጃቸው ረጅም ነው። በተለይ አዲስ አበባ ላይ የሚታየው የአመራር ብቃት ማነስ ሳይሆን የስነ-ምግባር ችግር ነው። ይህም ሥርዓቱ እንዳይረጋጋ ያደርጋል። ሥርዓቱ ካልተረጋጋ ደግሞ ብዙ የሚበላሹ ነገሮች አሉ።
አዲስ ዘመን፡- ከሁለት ዓመታት በላይ የዘለቀው የፀጥታ ችግር በመስፋቱ ላይ ምን አይነት ተግዳሮት ፈጥሯል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ዳባ፡- ይህ ችግር ከሁለት ዓመት በላይም የዘለቀ ይመስለኛል። እኔ የተወለድኩበት ገጠር አካባቢ በዚህ ሃገር መንግሥት ያለ እስከማይመስል ድረስ በፀጥታ ችግር ምክንያት ፍትሕ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል ማለት ይቻላል። እንደሚታወቀው የሁሉም ስልጣን ባለቤት መንግሥት ነው፤ ስልጣኑን ተጠቅሞ የሕዝብንና የሃገርን ደህንነት የማስጠበቅ፤ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት አለበት። ምክንያቱም ሕዝቡ ሃገርን እንዲያስተዳድር ቀጥተኛ ውክልና የሰጠው ለመንግሥት በመሆኑ ነው። በእኔ እምነት በአሸባሪ ቡድኖችና ሃገር አዋኪዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ የላላ ነው። ከዚህ የተነሳ ለምሳሌ በኦሮሚያ በበርካታ ወረዳዎች የፍትሕ ተቋማት አገልግሎት አይሰጡም። ስለዚህ ኅብረተሰቡ ፍትሕ የማግኘት፤ በሰላም የመኖር ህልውና ተጠብቆ የመኖር መብታቸው አደጋ ውስጥ ወድቋል። በርካታ ፍርድ ቤቶች፤ ፖሊስ ጣቢያዎች ተዘግተዋል። አገልግሎት እየሰጡም አይደለም። ይህም ማለት ደግሞ እዛ አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ ፍትሕ የማግኘት ሕገ-መንግሥታዊ መብቱ እየተከበረ አይደለም ማለት ነው። ይህ ደግሞ ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለው አመኔታ እንዲሸረሸር ያደርገዋል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ዳባ፡- እኔም ሃሳቤን እንድገልፅ እድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኔ 18 /2014