ንጹሕ ልብ ባላቸው አርሶ አደሮቿ በምታመርታቸው ጣፋጭና ወዛማ ቡናዎቿ የአረንጓዴ ወርቅ ምድር ትሰኝ ነበር። ወርቅን አስቀደምኩት እንጂ ወለጋ ሰሊጥ በስፋት የሚመረትባትና ከአፍ የወደቀ ጥሬ ማንም አበ ከና ሳይለው በቅሎ ፍሬ የሚያፈራባት ለም መሬት የታቀፈች ጥቅጥቅ ደኖች የከበቧት ውብ ምድር ናት።
ወለጋ እጽዋት ብቻ ሳይሆን እልፍ የሀገር ባለውለታዎችንም ለማፍራት የበቃች ነች ። ከእነዚህ በሺ ከሚቆጠሩት የወለጋ ማህፀን ክፋዮች መካከል አውሮጳ ምድር ላይ የጀገኑት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ አብዲሳ አጋ ፤ እውቁ የኢኮኖሚክስ ባለሙያ ይልማ ደሬሳ፤ የሀገር ባለውለታው ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሳቅ፤ ኢትዮጵያን በፕሬዚዳንትነት የመሩ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳንና ዶክተር ሙላቱ ተሾመን፤ ከጥበብ ሰዎችም በአማርኛና ኦሮሚኛ ዘፈኖቹ የምናስታውሰውን ሰለሞን ደነቀን ያበረከተችልን ድንቅ ምድር ነበረች።
«ነበረች» ያልኩት ከላይ የጠቀስኳቸውን በርካታ የኢትዮጵያ መለያዎች ያበረከተችልን ወለጋ በገዛ ልጆቿ ፤ በአብሯኳ ክፋዮች ሌላ ማንነት እየያዘች ስለመጣች ነው። ምንም እንኳን ስሟን በክፉ የሚያስነሱት እርግማኖች ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም እኛ ኢትዮጵያውያንና ቀሪው ዓለም ግን ወለጋን የደም ምድር አድርጎ እየመዘገባት ይገኛል። ዛሬ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያን የሚያውቅ ሁሉ ወለጋ የሚለውን ስም ሲሰማ በአዕምሮው የሚከሰትለት ያጣፋጭ ቡና አልያም ለሀገር ውለታ የሠሩ ተወላጆቿ ሳይሆን የወለጋን አኬል ዳማ´ነት ነው። የዚችን ከተማ ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚዘግብ ዜና ከሰማንም ዓመታትን አስቆጥረናል። እድሉ ገጥሞን የሰማነው ነገር እንኳን ቢኖር ሳናጣጥመው መርዶ ይደርሰናል።
እኛ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍልና የዓለም ሀገራት የምንገኝ ኢትዮጵያውያን በወለጋ የሚደርሰው ጭፍጨፋ የዚህ ያህል ካስመረረን በጅምላ ቤተሰባቸውን የሚቀብሩ ወገኖቻችን በምን አይነት ስሜት ውስጥ እንደሚቆዩ ማሰቡ በራሱ ሕመም ነው። ለነገሩ እዛ እሳት ውስጥ ቁጭ ብለውስ እንዴት ኃዘናቸውን ሊወጡ ይችላሉ ? ምክንያቱም ነገ ሊፈጠር የሚችለው ነገር ምን አልባትም እነሱን ራሳቸውን የሚነጥቃቸው ይሆናልና ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ በቀደሙት ጊዜያት ከድርቅ እስከ ረሀብ ከወረራ እስከ እርስ በእርስ ግጭት በርካታ ችግሮች ተፈጥረው ሕዝቦቿንም ብዙ ዋጋ አስከፍለው አልፈዋል። ምን አልባትም ወደፊትም የሚፈጠሩ አሳዛኝና አሰቃቂ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። በወለጋ ምድር እየተፈጸመ እንዳለው የጭካኔ ተግባር ግን የሚሆን አይመስለኝም ። ወንድም በወንድሙ ላይ ከሚያደርገው በተጨማሪ ተግባሩ አሰቃቂና በታሪካችን ያየነው ስላልሆነ ነው ።
የጭካኔ ተግባሩ በተራ የመንደር ጥላቻና ትርክት የተሞላ ጭንቅላት የተሸከመ አካል የሚፈጽመው ፤ እያደገ ከሄደም እንደ ሀገር ሊያስከትለው የሚችለው አደጋ የከፋ ነው ፣ ጥፋቱን ተመጣጣኝ በሆነ የኃይል ስሌት ማስቆም ወቅቱ የሚጠይቀው ትልቁ ሥራ ነው ።
እስካሁን በቡድኑ ለደረሰው አሰቃቂ ጭፍጨፋም አንዳንድ አካላት ቢያንስ ቢያንስ የሞራል ተጠያቂነት ሊሰማቸው ይገባል። ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ በየመገናኛ ብዙኃኑ ቀርበው ከሚሰጡት መግለጫ ይልቅ ችግሩን በአቅሙ ልክ የመከላከል ቁርጠኝት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
በተለይም ተደጋጋሚ ጥቃት የሚፈጸምባቸው አካባቢ ያሉ የአስተዳደርና የጸጥታ መዋቅሮች ፤ችግሩን ለዘለቄታው መፍታት ከአቅማቸውም በላይ ከሆነ ለሚመለከተው አካል በአግባቡ ማስታወቅ ይጠበቅባቸዋል ። ይህን ባለማድረግ ለሚፈጠረው ችግር መቼም ቢሆን ከተጠያቂነት አይዳንም ።
ችግሩን ለዘለቄታው ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአካባቢውን ሕዝብ በማስተባበር እስከ መስዋዕትነት የሚደርስ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ፤ይህንንም በተጨባጭ በተግባር ማሳየትና ተዓማኒነት ማትረፍ ይኖርባቸዋል።
በርግጥ ማዕከላዊ መንግሥቱ ለዘመናት በተተበተቡ ወጥመዶች ውስጥ በውጥረት እንዳለ ፤ከዚህ ወጥመድ ራሱን ለመታደግ የሚያደርገውም ጥረት ይታወቃል ።ይህም ሆኖ ግን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየሄደበት ያለው ርቀት በሕዝቡ ዘንድ አመኔታ እንዲያገኝ የተጠናከረ እርምጃ መውሰድና ውጤቱን ለሕዝብ ማሳወቅ ይጠበቅበታል።
በተለይ የለውጥ ኃይሉ በሕዝቡ ዘንድ እየሸረሸረ የመጣውን የለውጥ መንፈስ ዳግም ሕይወት ዘርቶ ፤ሕዝቡን በስፋትና በቁርጠኝነት ከጎኑ አሰልፎ ለመጓዝ ከሪፖርት በዘለለ እውነታውን በተጨባጭ መገምገምና አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል።
ብዙዎቹ የመንጋ ወንጀሎች የሚፈጸሙት እንደ እርሻ ሥራ በየገጠሩ ቢሆንም መፈልፈያቸው ከተማና ፊደል የቆጠረ የሚባል ጽንፈኛ መሆኑ ይታወቃል ። መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት… ዲሞክራሲ ለመገንባት… ከሚለው ሰሚ ያጣ አካሄድ ወጥቶ ሕግን በማስከበር ሥራው ተጠናክሮ መውጣት ይጠበቅበታል። በወንጀለኞች ላይ ጠንካራ እርምጃ ሊያሳርፍባቸው ይገባል።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ መከላከያን መንካት ኢትዮጵያን ለማፍረስ መሞከር እንደሆነ በአጽንኦት ነግረውናል። የተናገሩትን ሙሉ ለሙሉ የማምንበትና የምቀበለው ነው ። ከዚህ ጎን ለጎንም ሀገር የሚያፈርስ ጉዳይ ከሕዝብም ብሶት ይመነጫል የሚል ጽኑ አቋም አለኝ።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ከመከላከያ ጋር ተፋጦ የሚገኘው አሸባሪው ሕወሓት ይህን አጋጣሚ ከፕሮፖጋንዳ መንዛት ጀምሮ እንዴት ሊጠቀምበት እንደሚችል እያየነው ነው። ለነዚህ ትንንሽ እባቦች እድል መስጠት ለትልቁ ዘንዶ በር መክፈት መሆኑን በመገንዘብ መንግሥት ወለጋን ከአኬልዳማነት የማውጣት ኃላፊነቱን በፍጥነት መወጣት ይኖርበታል።
አሸባሪው ሸኔም ቢሆን እስካሁን በመጣበት የጥፋትና የሽብር መንገድ ሊያሳካው የሚችለው አንዳች የፖለቲካ ግብ አለመኖሩን በአግባቡ ተረድቶ ፤ እጁን በንጹሓን ደም ከማጨማለቅ ታቅቦ በጁ ያለውን የሰላም እድል ቢጠቀም መልካም ነው ። ለዚህም ጊዜው አላለቀም።
ራስወርቅ ሙሉጌታ