ሁሉም ነገር ድሮ ቀረ የሚለውን አባባል ከሚጠሉ ሰዎች አንዷ ነኝ።ምክንያቴ ደግሞ ሁሉም ነገር በጊዜው መታየት አልያም መዳኘት አለበት ብዬ ስለማምን ነው።ሆኖም አሁን አሁን ይህንን እውነታ አምኜ ከመቀበል ባለፈ ከነጭራሹ ሁሉም ነገር እየጠፋ መሆኑ ስጋት ውስጥ ጥሎኛል።
በተለይ ለዘመናት የኖርንበት ፤ የተቀረፅንበት እረ እንዳውም የማንነታችን መገለጫ ከሚባሉት ነገሮች መካከል ቁንጮ የሆነው የመከባበር፣ የመቻቻልና የመደጋገፍ ባህላችን እየጠፋ መምጣቱ ነው።ወደፊት እንዳውም ልክ እንደሉሲ (ድንቅነሽ) ሙዚየም አስቀምጥነው ‹‹እንዲህ ነበርን እኮ›› ባንል እንኳን የማይዳሰስ የጠፋ ቅርሳችን አድርገን ከምንጎበኛቸውና ከምናስጎበኛቸው ነገሮች አንዱ ይሆናል የሚል ፍርሃትም አለኝ፡፡
ለመሆኑ ምን አጋጥሞሽ ነው በዚህ ደረጃ የተማረርሽው? ብላችሁ እንደምትጠይቁኝ አልጠራጠርም።እውነት ነው፤ እዚህ ድምዳሜ ላይ እንድደርስ ያደረገኝ በእኔም ሆነ በሌሎች ሰዎች ከሰሞኑ ካጋጠመው ነገር ተነስቼ ፍርሃቴን ላጋባባችሁ የወደድኩት። ከሰሞኑ በአንዱ ቀን እንደተለመደው ልጆቼን ትምህርት ቤት አድርሼ የመስሪያ ቤት የፊርማ ሰዓት እንዳይረፍድብኝ ከአንዱ ባጃጅ ተሳፈርኩኝ።
የባጃጇ ዘዋሪ ወጣትና ገና ዘሎ ያልጠገበ አንድፍሬ ልጅ ነው፤ እረ እንዳውም 18 ዓመት ስለመሙላቱ ጥርጣሬ አለኝ።ግን ያው እንደነገርኳቹ ስለረፈደብኝና ተረኛውም እሱ ስለነበር ሌላ አማራጭ ለማየት አልቻልኩም፤ ይልቁኑ በቶሎ እንዲያደርሰኝ ነበር ጉጉቴ።ይህ ልጅእግር የባጃጅ ሹፌርም ታዲያ አምስቱን ተሳፋሪዎቹን የተቀበለው የጆሮ ታምቡራችንን በሚበጥሰው የባህርማዶ ሙዚቃ ነው፡፡
አብዛኞቻችን ትንሽ ድምፁን እንዲቀንስ ማጉረምረም ብንጀምርም ወጣቱ ግን ቅሬታችንን ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም።በእድሜ ጠና ያሉት ግለሰብ ግን ሲፈሩ ሲቸሩ ‹‹ልጄ እባክህ ትንሽ ቀንሰው›› አሉት በተማፅኖ።እሱ ግን የባለሶስት እግሯ ተሽከርካሪ ፈላጭ ቆራጭ መሆኑን በሚያሳይ ገፅታ ከኋላ የተቀመጡትን አዛውንት ገልመጥ አድርጎ ተሽከርካሪዋን ያከንፋት ቀጠለ። ብዙ ሳንጓዝ ግን የሱ ቢጤ የባጃጅ ሹፌሮች መዳረሻው ላይ ትራፊክ መኖሩን በምልክት ቋንቋ ነገሩትና ድንገት ጨርሶ ትራንስፖርት በሌለበት አሳቻ መንገድ ላይ አቆመና ጥሎን ሄደ። እኛ ካለንበት ትንሽ ራቅ ብሎ ከኋላ ከመጡትና ቀድመው ቆመው ከነበሩ የባጃጅ ሹፌሮች ጋር ጨዋታውን ጀመረ።ካሰብንበት ለመደረስ በተስፋ ስንጠብቀው የነበርነውን ተሳፋሪዎች ጉዳይ ችላ በማለት ልፊያውንም ቀጠለ።
በሁኔታው የተበሳጩ ከፊት የነበሩት ተሳፋሪዎች ቢጠሩትም ያልሰማ መስሎ ምላሽ ስለነፈጋቸው እየተራገሙ ወርደው በእግራቸው መጓዛቸውን ቀጠሉ።ሌሎቻችንም ወርደን ‹‹ኧረ እባክህ ረፍዶብናል፤ ሌሎቹ ወርደውልሃል እኛን አድርሰን›› የሚል ጥያቄ አቀረብንለት።ይህንን ያልነው ትርፍ ስለጫነ እቀጣለሁ ብሎ ስለሰጋ ስለመሰለን ነበር። ሆኖም ጉዳዩ ሌላ ነበር፤ ያ ፊቱ ራሱ የሚያሳብቅበት ልጅ እግሩ ወጣት ከነጭራሹ መንጃ ፍቃድ ስላልነበረው ቅጣቱ ድርብ ስለሚሆንበት ነበር እኛን ገትሮን የጠፋው።ከሁሉ በላይ የሚያበሳጨው ደግሞ የጫናቸውን ሰዎች ሁለቱ አዛውንቶች ወደኋላም ወደፊትም ለመጓዝ የሚቸገሩ መሆናቸውን እያወቀ በንቀትና በምንቸገረኝነት የሰጣቸው ምላሽ ነበር።
እኔም ሁኔታው እጅግ ስላናደደኝ ጥፋቱን ገና ልነግረው ከመንደርደሬ የስድብ ናዳ አወረደብኝ፤ ከእኔ አልፎ ለፍታ ደክማ ያሳደገችኝን እናቴን ሳይቀር አርፋ ቤቷ በተቀመጠችበት መስደቡ አጥንቴ ድረስ የሚዘልቅ ሰሜት ነበር የወረረኝ።ይሁንና በአንድ በኩል ስራ ረፍዶብኛል በሌላ በኩል ደግሞ ከእሱ ጋር እሰጣ ገባው አዋጭ አለመሆኑን ተገንዝቤ ትቼው ሩጫዬን ቀጠልኩ።
የሚገርመው ግን ብዙ ርቀት ሳልጓዝ ሞተረኛ ትራፊክ አገኘሁና የደረሰብንን አጫወትኩት፤ ሄዶም ከተደበቁበት አሳቻ ስፍራ እንዲይዛቸው ጠቆምኩትና ወደመስሪያ ቤቴ በእግሬ ጉዞዬን ቀጠልኩ።ከትራፊኩ ቆሜ ሳወራ ለካ አንዳንድ የባጃጅ ሹፌሮች አይተውኝ ኖሮ እንደከሰስኩኳቸው አልተጠራጠሩም።ስለሆነም መነሻ ስፍራቸው ላይ አጥር ሰርተው ተሰብስበው ጠበቁኝ፤ አንዳንዶቹም በእግራቸው ጠልፈው ሊጥሉኝ ዝግጁ ይመስሉ ነበር።
ሁኔታውን በቅርብ ርቀት ላይ ሆኜ ስለተመለከትኩና ሊያጠቁኝ እንደሆነ ስለገባኝ ቀድሜ አስፋልቱን ተሻገርኩኝ።ከፊት ለፊታቸው ደግሞ ፖሊሶች ስለነበሩ፤ እኔም ስላመለጥኳቸው በእጅጉ ተበሳጭተው እየተቀባበሉ ፀያፍ ስድባቸውን አዘነቡብኝ፤ ዛቱብኝም።እኔም በጊዜው ከእነሱ ጋር መሰዳደቡንም ሆነ መካሰሱ ትርፉ ድካም እንዲያውም ከስራዬም በማስተጓጎል ተጨማሪ ኪሰራ ያደርስብኛል ብዬ ስላመንኩ ስድቤን ውጬ ፤ ያ ያጠፋ ይቅርታ የሚጠይቅበት፤ ሴት የምትከበርበት ባህላችን ድምጥማጡ መጥፋቱ እያንገበገበኝ ጉዞዬን ቀጠልኩኝ።
ለመነሻ ርዕሰ ጉዳዬ ድምዳሜ ላይ እንድደርስ ያደረገኝ የዚሁ ሰሞን ሌላው ገጠመኜ ነው።በዚያው ሳምንት አንዱ ማለዳ ላይ የባጃጅ ሹፌሮች ዛቻ ፍራቻ በአንዱ የከተማ አውቶቡስ ተሳፈርኩኝ።የተሳፈርኩት ደግሞ መነሻ ላይ ስለነበር አውቶቡሱ እስኪሞላ መጠበቅ ግድ ሆነብኝ።ይሁንና ደቂቃዎች አልፈው ግማሽ ሰዓት ቢያልፍም ሹፌሩ ጉዞ መጀመር ባለመፈለጉ እንደተለመደው የመስሪያ ቤታችን ፊርማ እንዳይነሳብኝ እየሰጋሁ መቁነጥነጥ ጀመርኩኝ።ሁኔታዬን የተረዳች አንዲት የእኔቢጤ ስራ የረፈደባት ሴት ጮክ ብላ በምሬት መናገር ጀመረች።ሌሎቹም ‹‹ኧረ እንሂድ›› እያሉ ሹፌሩን ይወተውቱት ያዙ።እሱም ሆነ ትኬት ቆራጭዋ በተሳፋሪው ላይ ማሾፍና መሳለቅ ጀመሩ።በተለይ ሹፌሩ ከጎኔ የተቀመጠችው ሴት ድምፅዋ ዘለግ ብሎ ስለተሰማ ዞር ብሎ ‹‹ነይና አንቺ ንጂው›› ሲል መለሰላትና በእልህ የተወሰኑ ደቂቃዎችን አቃጠለብን።
የሚገርመው ግን ሶስት ፌርማታዎችን ዘግቶ ከሄደ በኋላ አራተኛው ፌርማታ ላይ አንዲት ነፍሰጡር ሴት የተማሪ ልጇን እጅና ቦርሳ ይዛ እንዲያቆምላት ስትማፀነው አቆመላት፤ ግን ነፍሰጡር ስለሆነችና ልጅ ስለያዘች ከፊት ካለው ባዶ ወንበር ለመቀመጥ ብላ የፊተኛውን በር እንዲከፍትላት ስትጠይቀው በብስጭት ሞተሩን አስነሳ ትንሽ አለፍ ብሎ ከሄደ በኋላ ቆመ፤ እሷም ራርቶልኝ ነው ብላ ሮጣ ከቆመበት ስትደርስ ተመልሶ ተነስቶ እያበረረ ጉዞውን ቀጠለ።
ይህንን ያየ ተሳታሪም ሆነ መንገደኛ በእርግማንና በስድብ ጮሁበት።እሱ ግን ስለማንም ጩኸት ግድ የሚሰጠው ሰው አልነበረም፤ እንዳውም ከትኬት ቆራጯ ጋር እየተጋገዙ ተሳፋሪውን ከፍ ዝቅ እያደረጉ መናገራቸውን ያዙ።ከዚህ ድሃ ህዝብ ማህፀን የወጡ በማይመስል ሁኔታ ‹‹ይሄ ድሃ ሲያዝኑለት አይወድም›› እያለም ዘለፋውን አዥጎደጎደ። በሳምንቱ ክፉ ገጠመኞቼ አዝኜ ውስጥ ውስጤን ተብከነከንኩኝ፡፡
ዳሩ እኔ ብቻ የዚህ አይነቱ ገጠመኝ ባይተዋር የዚህ ዳተኛ ሹፌርና ትኬት ቆራጭ ባህሪ የባሷ ደንበኞች ሁሉ ያውቁ ኖሮ ሁሉም ያገጠመውን እያነሳ ጥሩ መወያያ ርዕስ አደረጋቸው።እኔ ግን ከመማረር ባለፈ አንድም እንደማህበረሰብ እየጠፋ ያለውን የመከባበር፤ የመደጋገፍና የመተራረም ወርቅ ባህል ጉዳይ አደጋ ላይ መሆኑ እጅጉን ዘልቆ ተሰማኝ፡፡
በተለይ ነገ ሀገር ለሚረከበው ትውልድ የምናወርሰው ጥላቻና ራስ ወዳድነት ላይ የተመሰረተ ስነልቦና ጉዳቱ ዘመናት የሚሻገር መሆኑን ሳስበው አሳመመኝ።ዛሬ በምን ቸገረኝነት ያለፍናቸው እነዚህ ማህበረሰባዊ ህፀፆች ወደፊት መከራ የሚያሳጭዱን ስለመሆኑም አልጠራጠርም።ስለሆነም ያንን ዕንቁና መለያችን የሆነውን እሴታችን እንደቀድሞ ለመመለስ ለነገ ሳንል ሁላችንም ስለመብታችን ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ዘብ በመቆም ኃላፊነታችንን እንድንወጣ አሳስባለሁ፡፡
ሜሎዲ ከኳስ ሜዳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 16 /2014