ቢሮ የሚውሉ ሴቶች ከወንድ ሠራተኞች የሚለዩባቸው ብዙ ኃላፊነቶች አሉባቸው። በቤት ውስጥ ያለባቸውን ድርብ ኃላፊነት እንደ አንድ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። ጎልቶም ባይወጣ በእነዚህ ድርብ ኃላፊነቶች ምክንያት አንዳንድ ሴቶች ሲቸገሩ ይስተዋላል ። ሁለቱንም ሃላፊነቶች አስታርቆ መሄድ የሚሳናቸው ጊዜም ብዙ ነው። አንዳንዴ ከኃላፊነቱ መብዛትና ከጫናው መበርታት የተነሳ ከባድ የሆነ የህይወት ውጣ ውረድ ወስጥ የሚገቡበትም ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ።
በዚህ ምክንያት ብዙ ጊዜያቸው ወደቤታቸው ይሆንና የመማር ራሳቸውን በእውቀት የማሳደግና ከሰዎች የመወዳደር ሁኔታው አጣብቅኝ ውሰጥ ይገባል። በሌላ በኩልም በተሰማሩበት የስራ መስክ ላይ ከሌሎች በተለይም ከወንዶች እኩል ተወዳድረው በቅተው የመውጣት ሁኔታቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥላን ያጠላልም፡፡ በተለይ ሥራ ገበታ ላይ ከተሰማሩ በኋላ በዚሁ ድርብ ኃላፊነት ምክንያት ሥራቸውን በሰዓቱና በአግባቡ ላይሰሩም ይችላሉ።
ለዛሬ የቢሮና የቤት ውስጥ ኃላፊነቶችን አስታርቆ በመሄድ ረገድ ሰዓት አጠቃቀምን ማወቅና እንደ ልምድ እያዳበሩ መምጣት ወሳኝ የመሆኑን ተሞክሩ ከወይዘሮ አልማዝ ለማ እናያለን ፤ ወይዘሮ አልማዝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የእንስሳት የተፈጥሮ ቅርስ መዘክር (ሙዚየም) ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
ወይዘሮዋ የሥራ ቦታቸው አራት ኪሎ ሲሆን የመኖርያ አድራሻቸው ደግሞ ከአዲስ አበባ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሰበታ ከተማ ነው ። ‹‹ትልቁ የጊዜ አጠቃቀምን ማወቅ መቻል ነው›› የሚሉት ወይዘሮ አልማዝ የስራ ቦታቸው የሚገኝበት አካባቢ ከማለዳው 12 ሰዓት እንደሚደርሱም ይናገራሉ። ከንጋቱ 11 ሰዓት ከመኝታቸው ተነስተው አስፈላጊውን ነገር ካከናወኑ በኋላ ከቤታቸው ከጠዋቱ 12 ሰዓት በመውጣትና ትራንስፖርት በመያዝ በቶሎ የስራ ገበታቸው ላይ አንደሚገኙም ይናገራሉ፡፡
“ከሰፈሬ ተነስቶ አራት ኪሎ የሚዘልቅ ፐብሊክ ሰርቪስ አለ፤ ነገር ግን የመነሻው ሰዓት ትንሽ ዘግየት ስለሚልና ያስረፍደኝ ይሆናል ብዬ ስለማስብ አልጠቀምበትም ፤ ከዛ ይልቅ በትራንስፖርት እመጣለሁ ምናልባት በሰርቪሱ ብመጣ የማተርፈው ገንዘብ ይኖር ይሆናል ነገር ግን እኔ ከገንዘብ ይልቅ ጊዜያን ማትረፍ ስለምፈልግ በታክሲ እጠቀማለሁ” ይላሉ፡፡
ቢሯቸው ከደረሱ በኋላም ቦርሳቸውን በማስቀመጥ ባተረፉት ሰዓት የዕለት ተግባራቶ ቻቸውን ማከናወናቸውን ይቀጥላሉ። መሄድ ካለባቸው ወደ ቤተእምነት በመሄድ ቀጣይ ተግባራቸው ደግሞ ስፖርት ቤት (ጅም ) መግባት ነው ። እዚህ ቢያንስ እስከ 40 ደቂቃ ያሳልፋሉ። ከጅም መልስ ለ20 ደቂቃ ሻወር ከወሰዱ በኋላ ይወስዳሉ።
ከአንድ ሰዓት ከ20 በኋላ ቢሯቸው ይገባሉ። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጊዚያቸውን ማጥፋት ስለማይፈልጉ ቀጥታ ከሥራ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚጠቀሙበትን ኢሜል ላፍታ መልከት ያደርጋሉ። ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል ጀምሮ እስከ 11 ሰዓት ከ 30 ወይዘሮ አልማዝ መደበኛ ሥራቸውን ትኩረት አድርገው የሚሰሩበት ወቅት ነው። ምሳ ይዘው ስለሚመጡ ሻይም እዛው ቢሯቸው አፍልተው ስለሚጠጡ ለሻይ ቡና ብለው የሚያባክኑት ጊዜም የለም ይህ ደግሞ በስራቸው ውጤታማ እንዲሁኑ አስችሏቸዋል።
እሳቸውም ሆኑ የሥራ ባልደረቦቻቸው እንደሚሉት ሥራው የሚሰራው ከእሁድ እስከ እሁድ በመሆኑ ምንም እረፍት የለም። ሠራተኞቹ ቅዳሜና እሁድ ብቻ ሳይሆን በበዓላት ወቅቶች በሙሉ ቢሮ መግባት ይጠበቅባቸዋል። ከሁለት ወንዶች በስተቀር ቀሪዎቹ በሥራቸው ያሉት የሙዚየሙ ሰራተኞች ሴቶች ናቸው።
ከእሁድ እስከ እሁድ ሥራ ገበታቸው ላይ ከመገኘት ባሻገር በየቤታቸው ውስጥም የሚጠብቃቸው ድርብ ሃላፊነት አለ። ወይዘሮ አልማዝ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይሉ እነዚህን ክፍተቶች በመሸፈን ቀዳሚ ናቸው። በአብዛኛው ቅዳሜ የሚገቡ ባይሆንም የአስጎብኝንና ጨምሮ እስከ ጥበቃ ድረስ ያለውን ሥራ ኃላፊ ነኝ እኔን አይመለከትም ብለው ሳይገፉ ገብተው በመሥራት ይሸፍናሉ።
እንደ አለቃ ቢያስተባብሩም የሥራ ቅርበታቸው የአለቃና ምንዝር ሳይሆን የጓደኛ ዓይነት መሆኑ ለመሸፋፈኑ ጠቅሟቸዋል። ሥራው በባህርይው በአንድ ሰው ብቻ የሚሸፈን አለመሆኑ ተባብሮ ለመስራትም አግዟቸዋል። ምክራቸውን ትንሽና ታናሽ ናት ብለው ሳይተው ይቀበላሉ። ደረጃቸውንና ማንነታቸውን ያከብሩላቸዋል። ህፃናትም ሆነ አዋቂና የውጪ ዜጋ ጎብኚ የእንስሳት የተፈጥሮ ቅርስ መዘክርን አስመልክቶ ግንዛቤ መጨበጥ ይፈልጋል። ሙዚየሙም የተቋቋመው ለዚህ ነውና አስጎብኚዎች በማይኖሩበት ጊዜ እየተዟዟሩ ገለፃ ሲያደርጉና ሲያስተምሩ ብዙ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ።
በሙዚየሙ ያሉት ሦስት ዓይነት የወፍ ዝርያዎች በራሳቸው ብዙውን የትምህርት ጊዜ ይወስዳሉ። ለምሳሌ ከነዚህ አንዷና መሬት ወርዳ ጥራጥሬ በመልቀም ምትመገበዋን ወፍ እንዳነሷት እነዚህ የወፍ ዝርያዎች ማስቲካዋ ጥሬ ትመስላቸውና ያነሷታል። ማስቲካ ደግሞ በተፈጥሮው የራሱ የማጣበቅ ባህርይ ስላለው መንቁራቸው ላይ ይጣበቃል። በዚህ ምክንያት በረሃብና በውሃ ጥም ይሞታሉ። በመሆኑም ያኘክነውን ማስቲካ በወረቀት ወይ በሶፍት ጠቅልለን ማስወገድ እንደሚገባ ለጎብኝዎች ለማስተማር ከገለፃ ጋር ብዙ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ።
ማታ ከሥራ መልስ እቤታቸው ሲገቡ ብዙ ኃላፊነቶች ይጠብቋቸዋል ። በአሁኑ ወቅት ልጆቻቸውን በማሳደግ የቤትና የሥራ ጫናቸውን ስታቀልላቸው የነበረችው ሰራተኛቸው አብራቸው አለመሆኗ የቤቱን ኃላፊነት አክብዶባቸዋል።ከሥራ መልስ እሷ ታከናውናቸው የነበረውን የቤት ሥራዎች በሙሉ ይሰራሉ። አጋጣሚ ሆኖ ባለቤታቸው አብዝተው መስክ የሚወጡ በመሆናቸውና በቤት ውስጥ ባለመገኘታቸው ሁለቱን ልጆቻቸውን ማስጠናትና የቤት ሥራ ማሰራቱ ሰርክ የእሳቸው ኃላፊነት ነው።
ማታ ላይ የጠዋት ልብሳቸውን ያዘጋጁና ማልደውም ትምህርት ቤት ይዘው የሚሄዱትን ምግባቸውን ይቋጥራሉ። ወይዘሮ አልማዝ በሚኖሩበት አካባቢም ያለውን ማህበራዊ ኑሮ ዕድር፣ ለቅሶ፣ የዓውድ ዓመትና ሌሎች ጉዳዮችን የሚያስተናግዱት ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ባለው በዚህ ሰዓታቸው መካከል ነው። በተለይ ቅዳሜ ላይ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለመሸኘት የሚያደርጉት ሥራ ስለሚቀንስላቸው ሰዓቱን ለማህበራዊ ሕይወት ያውሉታል።
ወይዘሮ አልማዝ ጋር ቤተሰብ፣ ወዳጅ፣ ዘመድም በዚህ ሰዓትና በዓመት ዕረፍት ወቅት ነው የሚጠየቀው።ይሄን መሰሉን ሰዓት አጠቃቀማቸውን ከልጅነታቸው ጀምሮ ከወላጆቻቸው በመውረስ እያዳበሩት እንደመጡ ይናገራሉ። ለወላጆቻቸው አራተኛ ልጅ ሲሆኑ እሳቸውን ጨምሮ ሦስት ወንድና ሦስት ሴት ልጆች ያላቸው ቢሆኑም በቤታቸው የወንድና የሴት የሚባል የሥራ ክፍፍል እንዳልነበረ ያስታውሳሉ።
በተጨማሪም ሴት ልጅ የመጀመርያ ልጅ በመሆኗና ሴት ልጅን በሥራ የመጥመድ የማህበረሰብ አስተሳሰብ ጫና ድነዋል። የወንድና ሴት የሚባል የሥራ ክፍፍል ባለመኖሩ የወላጆቻቸው የበኩር ልጅ የሆነው ወንድማቸው እንጀራ ከመጋገር ጀምሮ የቤት ውስጥ ሥራን በሙሉ እየሰራ እንዲያድግ ነው የተደረገው። ታላቅ ወንድማቸው እሳቸውን ጨምሮ ታናናሾቹን በማሳደጉ ረገድ ቤተሰቡን ይረዳ ነበር። በቤት ጽዳትና በልብስ አጠባም በኩል የሚተካላቸው አልነበረም። ሁለቱ ወንድሞቻቸው የቤቱ ታላቅ ስለነበሩ እነሱ ነበሩ የቤት ውስጥ ኃላፊነቱን በሙሉ የሚወስዱት ።
‹‹የትምህርት ዕድል አግኝቶ ያደገ ባለመሆኑ የአባቴ ገቢ ምንጭ ትንሽ ነበር›› የሚሉት ወይዘሮ አልማዝ አባታቸው ጡረታ ከወጡ በኃላ በአነስተኛ እርሻ ሥራና ከብቶች በማርባት ተሰማርተው የነበሩ መሆናቸውንም ያነሳሉ። እንዳከሉት እናታቸው በፊናቸው ባለቤታቸውን የገቢ ምንጫቸውን በሚያጎለብቱበት አንፃር አብዝተው ሲያግዟቸው ነው የኖሩት። ለአብነት እናታቸው አንድ ሳይሆን ሁለት ሶስት የገቢ ማስገኛ ንግዶች ላይ ተሰማርተው መሥራታቸው ይጠቅሳሉ። የሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ፣ ሻይ ቤት፣ ወፍጮ ቤት እናታቸው ገቢያቸውን ከፍ በማድረግ ባለቤታቸውን ለማገዝና ቤተሰባቸውን በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር ሲሰሩባቸው የነበሩ ሥራዎች ናቸው።
ሴቶቹ ከተወለዱ በኋላ ሦስተኛዋ ልጅና ታላቅ እህታቸው የቤት ውስጥ ሥራን እሳቸው ደግሞ የውጪ የውጪውን ሥራ አብዝተው ይወዱ እንደነበር ያስታውሳሉ። እህታቸው ለሻይ ቤቱ ዳቦ ሲጋግሩ እሳቸው ወፍጮ ቤት የመሄድና ዱቄት የማስፈጨት ፣ ሻይ ቤት ሄደው ዳቦና ሻዩን ሲሸጡ የመዋል፣ ወፍጮ ቤት ገንዘብ የመሰብሰብ ሥራ ይሰራሉ።
እንዲህም ሆኖ ወላጆቻቸው ሁሉም ልጆቻቸው በሥራ ጫና ከትምህርት እንዲደነቃቀፉባቸው ወይም እንዲደክሙባቸው አይፈልጉምና ለትምህርታቸውም ጊዜ እንዲሰጡ በወላጆቻቸው ይገደዱና ይደገፉም ነበር። በተለይ አባታቸው ዝቅተኛ ገቢና የኑሮ ደረጃ ላይ ለመኖር የበቁት ባለመማራቸው በመሆኑ የእሳቸው ዕጣ እንዳይደርሳቸው ለትምህርታቸው ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡ ከጎናቸው ሆነው በእጅጉ ይደግፏቸው ነበር።
በቤት ውስጥ የሚሰጣቸው ሥራ ከትምህርት ገበታቸው እንዳያስተጓጉላቸው ከነበሯቸው ከብቶች ጋር የተያያዘውን የሌሊቱን ሥራ ከሌሊቱ ስድስትና ሰባት ሰዓት ተነስተው አባታቸው ይሰሩ እንደነበር ይናገራሉ ። እናታቸው በፊናቸው ከማለዳው 11 ሰዓት ይነሱና ከብቶች የበሉበትን ግርግም የማንሳትና የማፅዳቱን ሥራ ይሰራሉ። እንዲሁም ወተት ያልባሉ።
ከዚያም ቁርስ አዘጋጅተው በማብላት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ይሸኛሉ። ከትምህርት ቤት መልስ ደግሞ እነሱ ለከብቶች የሚያስፈልገውን ያቀርባሉ ። ወፍጮ ቤት መሄድና ሌሎች የመላላክና እንደ ልብስና የተበላበትን ዕቃ ማጠብ ያሉ የቤት ውስጥ ሥራዎች ካሉ እስከ ማታ ድረስ ሲሰሩ ያመሻሉ ። የማታው ጊዜ በሙሉ ለልጆች ይሰጥና ይሸፍናሉ።ይሄ ሰዓት አጠቃቀምን ማዕከል ያደረገ የሥራ ባህልና ልምድ የባከነ ጊዜ ሳይኖራቸው ከትምህርት ቤት ወደ ሥራ ያሸጋገራቸው መሆኑንም ወይዘሮ አልማዝ ያወሳሉ።
ከሀሁ ዳዊት እስከ መድገም በመዝለቅ ትምህርት ከቄስ መጀመራቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ አልማዝ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ክፍል ያለውን የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን ጌቴሴማኔ የሴቶች ገዳም ነው የተማሩት። ከስድስት እስከ ስምንት ሙሉጌታ ገድሉ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ9 እስከ 12 ያለውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ሰበታ ኮምፒሬሄንሲፕ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቅቀዋል። ከዛም በቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ ገብተው የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በኮምፒውተር ሳይንስ አግኝተዋል ። ሌላኛውን ዲግሪያቸውን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በባይሎጂ ተመርቀዋል ።
ያኔ ወንድና ሴት የሚለው በትምህርት ሚኒስትር ደረጃ ካልሆነ በየትምህርት ቤቶቹ፤ በየክፍሉና በሕብረተሰቡ ዘንድ ልዩነት አልነበረውም። እንደውም ሴቶች ይበረታታሉ። መምህራኖቻቸው ከወንዶች እንዳያንሱ የሴቶች ክበብ በማቋቋም ብዙ አስተዋጾ ያደርጉላቸው ነበር። በመሆኑም በአጠቃላይ ውጤትም ሆነ በክፍል ተሳትፎ ከወንዶቹ ጋር ልዩነት አልነበራቸውም።
ለመጀመርያ ጊዜ የሥራውን ዓለም የተቀላቀሉት በመምህርነት ሙያ ነው።በዚህ መካከል በኢትዮዸያ ቴሌቪዥን ለሦስት ወራት ሰርተዋል። ከ1997 ዓ.ም መጨረሻ ጀምረው ደግሞ አሁን እየሰሩበት ባለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብትዋል ። ከዚህ ውስጥ ከ1997 መጨረሻ እስከ 2005 ዓ.ም በዕፅዋት ማዕከል ውስጥ አገልግለዋል። ከዚህ በኋላ ደግሞ አሁን ላሉበት የኃላፊነት ቦታ ተወዳድረው አለፉ። ልምድ ባካበቱበት የወላጆቻቸው ሰዓት አጠቃቀምን ማዕከል ያደረገ የሥራ ባህል ከሚባክን ጊዜ ሰለባነት ድነው ጊዚያቸውን በአግባቡ መጠቀም ቻሉ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2014