አዲስ አበባ፡- ከአሜሪካው አውሮፕላን አምራች ቦይንግ ጋር የነበረውንና ለዓመታት የዘለቀውን አጋርነት በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።
የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት መግለጫ፤ በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት በሆነው ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 በተከሰተው አደጋ በደረሰው ሕይወት መጥፋት አየር መንገዱ የተሰማው ሐዘን መሪርና ጥልቅ መሆኑን አስታውሰዋል። አደጋው ከደረሰ በኋላም አየር መንገዱ ለመንገደኞች ደህንነትና ጥንቃቄ ሲባል አውሮፕላኖቹን ሙሉ በሙሉ ከበረራ አገልግሎት ማገዱንና ሌሎች አገራትም ተመሳሳይ ተግባር መፈፀማቸውን አመላክተዋል።
የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የተከሰተው አደጋ የአየር መንገዱን አቋም እንደማይገልፀውና ስምና ዝናውን የማጉደፍ አቅም እንደሌለው ያመላከቱት ስራ አስፈፃሚውም፤ እንደቀደመው ሁሉ አየር
መንገዱ በቀጣይም ከአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግና ከሌሎቹም አጋሮቹ ጋር የአየር ትራንስፖርቱን ደህንነት ይበልጥ ለማስጠበቅ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።
አቶ ተወልደ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አምራች ቦይንግ እምነት እንዳለው እንዲሁም ለዓመታትም ከተቋሙ ጋር በአጋርነት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት አውሮፕላኖቹም የቦይንግ ምርቶች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ አክለውም 767፣ 757፣ 777-200LR777 አውሮፕላኖች በመጠቀም ከአፍሪካ በቀዳሚነት እንደሚቀመጥና በተለይ 787 ድሪምላይነርን በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃም ከጃፓን ቀጥሎ ሁለተኛው መሆኑን አብራርተዋል።
በቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች አሁንም ቢሆን መልስ አለማግኘታቸውንና በአውሮፕላኑ ላይ ስለደረሰው አደጋም ምርምራው በመካሄድ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተሟላና ዝርዝር መረጃ እስኪገኝም አየር መንገዱ ምንም አይነት መላ ምቶችን ከመስጠት እንደሚቆጠብ አመልክተዋል፡፡ አየር መንገዱ በምርመራው ሂደት ተገቢውን ትብብር እንደሚያደርግም ገልፀዋል፡፡
የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገኛኛ ብዙኃን የኢትዮጵያው አየር መንገድ አብራሪ ይህን አውሮፕላን ለማብረር የሚያስፈልገውን ተጨማሪ ስልጠና እንዳልወሰደ በመጥቀስ ያቀረቡት ዘገባ የተሳሳተ መሆኑን አቶ ተወልደ አመልክተው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎችም አውሮፕላን አምራቹ ባወጣውና በአሜሪካ የአቪየሽን ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት ተቀባይነት ባለው መንገድ ተገቢውን ስልጠና መውሰዳቸውን አረጋግጠዋል።
‹‹አየር መንገዱ አውሮፕላኑን ለማብረር የሚያስችል የምስለ በረራ (ሲሙሌተር) መለማመጃ ባለቤት ነው» ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ይህን ዘመናዊ ምስለ በረራም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቂት አገራት እንዳላቸውና ከአፍሪካ ደግሞ የአትዮጵያ አየር መንገድ በብቸኝነት የመሳሪያው ባለቤት መሆኑን በመግለጫው አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአምስቱም አህጉሮች 119 መዳረሻዎች አሉት። በየዓመቱም ከ11 ሚሊዮን በላይ መንገዶኞችን አየር መንገዱን እንደሚጠቀሙ ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት17/2011
በ ታምራት ተስፋዬ