በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ ቀና የሆነና ምናልባትም ሀገሪቱ ባለፉት በርካታ ዓመታት ውስጥ ያላየችው አይነት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ለውጡ በተግባር ደረጃም ሲፈተሽ የዴሞክራሲ ሥርዓትን መሰረት ለመጣል ጥረቶች የተደረጉበት መሆኑንም ያመለክታሉ – የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ገመቺስ ማሞ፡፡
አገራዊ ለውጡን በተመለከተ ሃሳባቸውን ካጋሩን የሲቪክ ማህበራት መካከል ዶክተር ገመቺስ እንዳሉን፤ የመንግስት ተቃዋሚ ሃይሎች በነፃነት የሚሰበሰቡበት መድረክ ተፈጥሯል፡፡ ዜጎች የሚሰማቸውን ስሜት በነፃነት መናገርም ሆነ መጠየቅ እንዲሁም በጋራ መደራጀትም ጀምረዋል፡፡ በለውጡ ሂደት የሲቪክ ማህበራትም በነፃነት መደራጀትና ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዲችሉ አዋጆች ተስተካክለዋል፡፡
ይህም የለውጡ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ አዋጆቹ ተግባራዊ መሆን ሲጀምሩም ማህበራቱ በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ መስራት እንዲችሉ በር የሚክፍት ይሆናል፡፡ ሆኖም የህክምና ጉዳይ ረጅም ሂደት የሚጠይቅ በመሆኑና በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው ለውጥ መሬት የነካ ባለመሆኑ በዘርፉ ለውጥ ሙሉ በሙሉ መጥቷል ብሎ ለመናገር እንደሚያስቸግር ገልፀዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት፣ በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የህዝብ መፈናቀል እየበዛ መምጣቱና የኢኮኖሚው ሁኔታ መቀዛቀዙ ለውጡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፎበታል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን እንዲህ አይነቱ ችግር ሲያጋጥም በጥበብ መወጣትን ይጠይቃል፡፡ ህብረተሰቡም ከለውጡ ጎን ሊቆም ይገባል፡፡ ሀገሪቷን እየመራት ያለው የፖለቲካ ፓርቲ ኢህአዴግ ከመሆኑ አኳያ መንግስት ሙሉ በሙሉ ስለመለወጡም ማጥናት ያስፈልጋል፡፡
‹‹በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ ሁሉን አቀፍ ለውጦች መልካም ቢሆኑም የሰላሙ ሁኔታ ግን አሁንም አጠያያቂ ነው፡፡›› የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያና የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ኢጋድ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚገልፁት፤ ለለውጡ መሰናክል በመሆን ላይ ያሉት በሀገሪቱ የተለዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ናቸው፡፡ ሰላምን ለማምጣት ደግሞ በጋራ መስራትና ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠልና መሬት እንዲይዝ ለማድረግ በተለይ ወጣቶች በሃሰተኛ ወሬ መወናበድ የለባቸውም፡፡ የተገኘውን የለውጥና የሰላም እድል በመጠቀም የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡
በተለይም ትላልቅ ከሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ከዳር ማድረስ የግድ ይላል፡ ፡ ወጣቶች ሊያሰናክሏቸው ከሚችሉ አመለካከቶች በመላቀቅ በአገር አንድነት ላይ የሚያጠነጥኑ አመለካከቶችን ቢያራምዱና እንዲሁም እናቶችም ልጆቻቸውን ቢመክሩ የታለመውን ሰላም ማምጣት ይቻላል፡፡ የሲቪክ ማህበራቱም ቢሆኑ በሰላም ዙሪያ መንቀሳቀስና የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርባቸዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለፃ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ማቋቋሚያ አዋጅ 341/95 እስካሁን ድረስ ባለመሻሻሉና ችግሮች ያሉበት በመሆኑ በዚህ የለውጥ ሂደት በንግዱ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሴቶችን መብት ያስጠበቀና ያካተተ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ሴቶች ተጠቃሚ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ምርቶቻቸውን፣ ማህበራቸውንና የተለያዩ ድጋፎችንም ሊያሳድጉ አልቻሉም፡፡
‹‹የፖሊሲ ክፍተቶችን ለማሻሻል ለሴቶችና ህፃናት ሚኒስቴርና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደጋጋሚ አቤቱታ ቀርቧል›› የሚሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ይሁንና እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱን ጠቅሰዋል፡፡ የለውጡ ሂደት በሌላው መልኩ ጥሩ ሆኖ ሳለ ማህበሩ ለመንግስት ግብር በአግባቡ እየከፈለ፣ የማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ፣ ከስደት ተመላሾችንም ተቀብሎ በማሰልጠን ወደ ስራ እንዲሰማሩ እያደረገ አዋጁ ባለመሻሻሉ ምክንያት ነጋዴ ሴቶች ኢኮኖሚያዊ
አቅማቸውን ማሳደግና ተወዳዳሪ መሆን አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ሌሎች ለውጦች እንዳሉ ሁሉ አዋጁም ሊሻሻልና ሴት ነጋዴዎች ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሰዎች ሃሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁበትና ፍላጎታቸውን የሚያንፀባርቁበት ምቹ የዴሞክራሲ ሥርዓት በመፈጠሩ ማህበሩ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን ሀገራዊ ለውጥ የሚደግፍ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዮሃንስ በንቲ ናቸው፡፡
ቀደም ሲል በማህበሩ በኩል የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተደረጉ ጥረቶች የነበሩ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እየተዘጋጀ ያለው ፍኖተ ካርታ የለውጥ ሂደቱ እንዱ ማሳያ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ‹‹በማህበሩ የተጠኑ ጥናቶችም የፍኖተ ካርታው ግብአት እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡›› ይላሉ፡፡ የትምህርት ጥራት ስልጠና፣ የመምህራን ማበረታቻዎችና ሌሎች ጉዳዮች በፍኖተ ካርታው የሚካተቱ እንደሚሆኑና ከዚህ አኳያም ለውጡ መልካም እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቱ አባባል፤ ቀደም ሲል በሀገሪቱ የመምህራን አገልግሎት ኮሚሽን አልነበረም፡፡ ይሁንና ኮሚሽኑ እንዲቋቋም ከመምህራን በኩል ጥያቄ በመቅረቡ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ በቀጣይም የመምህራኑን ሁኔታ በሚያንፀባርቅ መልኩ የሚቋቋም ይሆናል፡፡ ይህም እንደ አንድ ለውጥ የሚታይ ነው፡፡
‹‹እየታየ ያለው የለውጥ ሂደት በአመዛኙ መሬት አልነካም›› የሚሉት አቶ ዮሐንስ፤ ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረውና የታለመለትን ግብ እንዲመታ ከተፈለገ እስከ ወረዳ ድረስ መውረድ እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡ የሲቪክ ማህበራትም ለውጡን በማስቀጠል ሂደት የአባሎቻቸውን ጥቅምና ፍላጎት በማስጠበቅ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከታች ጀምሮ መምህራን ባሉበት ቦታ ሁሉ ለውጡን መነሻ በማድረግ በትምህርት ጥራትና የተማሪዎችን ባህሪ በመቅረፅ ዙሪያም ጠንክረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው አብራርተዋል፡፡
የሲቪክ ማህበራት ከማንኛውም የፖለቲካ አመለካከትና ወታደራዊ ጉዳዮች ነፃ የሆኑና በተለይም ለህብረተሰቡ የጋራ ተጠቃሚነት የሚሰሩ ለትርፍ ያልተቋቋሙ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ማህበራቱ በተለያዩ ዘርፎች የጋራ ፍላጎት ያላቸው ሰዎችን በማሰባሰብ የሚቋቋሙ ቢሆንም ዋነኛ አላማቸው ግን የአባላቱን መብትና ጥቅም ማስከበር አልያም የህብረተሰቡን የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሆነም ይታመናል፡፡
በተለያዩ የመንግስት ሥርዓት ውስጥ አልፈው አሁን እየታየ ባለው የለውጥ ሂደት ውስጥ የተገኙት እነዚህ ማበራት አገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ እንደሚደግፉና በጋራም አብረው መዝለቅ እንደሚፈልጉ አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት17/2011
በ አስናቀ ፀጋዬ