የሚያዚያ 2010 ዓ.ም ትውስታ
መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣናቸውን የተረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ቀጣዩን አንድ ወር ያሳለፉት በየክልሉ በመንቀሳቀስ ህብረተሰቡን በማረጋጋት ነበር። የመጀመሪያ ጉዟቸውን ያደረጉትም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለማረጋጋት ወደ ጅግጅጋ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጅግጅጋ በተገኙበት ወቅት ያስተላለፉት መልእክት ‹‹ግለሰቦች ለግል ጥቅማቸው ሲሉ በሁለት ህዝቦች መካከል ግጭት ፈጥረዋል። በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ወሰን አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅና መጥፎ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ነው። ላጋጠመን ጊዜያዊ ችግር ሳንበገር አብሮነታችንን ማጠናከር አለብን። ከወንድሞቻችን ጋር ተገናኝተን በባህላችን መሰረት ችግሩን በሽምግልና ለመፍታት ዝግጁ ነን።›› የሚል ነበር፡፡
አክለውም፤ ‹‹የደረሰው መፈናቀል፣ ሞትና ጉዳት የሁላችንም ህመም፣ ሃዘንና ኪሳራ ነው፡፡ በመሆኑም ጠባሳው ፈጥኖ እንዲሽር ችግሩ የማያዳግም መፍትሄ እስከሚያገኘበት ዳርቻ ድረስ ባለን አቅም ሁሉ በጋራ በርትተን መስራት ይጠበቅብናል›› ነበር ያሉት፡፡
በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአምቦ ከተማ በመገኝት ከተናገሩት መካከል የአገሪቱን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማጎልበት በአንድነት ጠንክሮ መስራት የሚገባ መሆኑን ሲሆን፣ ሁሉም ዜጋ ጊዜ የለንም በሚል ስሜት ተነሳስቶ ለአገር ዕድገት መቆም እንዳለበትም ነው ያመለከቱት፡፡ የአምቦ ከተማ ህዝብ ለለውጥ የሚጥርና የሚታገል መሆኑንም አስታውቀው፤ ያለፈውን ቁርሾ በመተው አዲስ ታሪክ መስራት እንደሚገባ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጅግጅጋ የጀመሩትን ይፋዊ ጉብኝት በመቀጠል ከአምቦ መልስ ወደ መቀሌ በማቅናት ከህዝብ ጋር በተወያዩበት ወጣቶች እንደ አባቶቻቸው ጽናትን በመውረስ ድህነትና ኋላቀርነትን ታሪክ ለማድረግ መስራት እንደሚኖርባቸው ተናግረው፤ «ትግራይ በሀገራችን ለውጥ ለማምጣትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በደርግ ወቅት ለበርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከለላና ማገር በመሆን አታግለዋል፡፡ ይህንን ከፍ ያለ ታሪክ ወጣቱ ትውልድ በመውረስ አንድነቱን ማጠናከር አለበት።›› ማለታቸው ይታወቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በጎንደር በመገኘትም ለነዋሪዎች ባደረጉት ንግግር እንዲህ ብለው ነበር፤ ‹‹በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጎንደር ጉልህ ሚና ያላት ከተማ ነች። በከተማዋ የሚገኙ የፋሲል ቤተ-መንግሥትን አንጸው የቆዩ አኩሪ ልጆች የነበሯትና ዛሬም ድረስ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ ወጣቶችን የያዘች የአንድነት ተምሳሌት ናት። የጎንደርና አካባቢዋ ወጣቶች ተፈጥሮ የቸረቻቸውን ሀብት በመጠቀም ራሳቸውንና አካባቢያቸውን መቀየር ይኖርባቸዋል፡፡ ሲሉ የተናገሩት ዶክተር አብይ፤ ‹‹ዛሬ የትልቅ አደራ ተረካቢ በመሆናችን አገሪቱን በዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ በፍትህና በነጻነት መደላድል ላይ መስርተን ለማስቀመጥ በጋራ መረባረብ ይገባናል›› ሲሉም ነው ያከሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎንደር ከነበራቸው ቆይታ በኋላ በባህር ዳር ከተማ በመገኘት ለነዋሪው ባደረጉት ንግግር፤ ‹‹ህዝቡ እስካሁን የነበረውን ለፍትህ የመቆምና ለህግ የመገዛት የቆየ ባህል በዘመናዊው የፍትህ ሥርዓት ውስጥም እንዲረጋገጥ ለማድረግ ቀን ከሌት መስራት ይገባዋል›› ብለዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃሃይለማርያም ደሳለኝ በተዘጋጀው ይፋዊ የሽኝት መርሐ ግብር ላይ እንዲህ ብለው ነበር። «የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ህልፈት ምክንያት ዓለም ‹ምን ይሆኑ ይሆን?› ሲል የአገሪቷን ለውጥ ያስቀጠለ ብልህ መሪ ነው፤ በንፅህና በተምሳሌትነት ከሚታዩ መሪዎች አንዱ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ እጁ ንፁህ የሆነና ሌብነትን የሚፀየፍ ለሁላችንም አርአያ መሆን የሚችልም ነው›› ብለዋል። በእለቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአቶ ኃይለማርያም በስልጣን ዘመናቸው በአገሪቱ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ የሚባለውን ሜዳሊያና ዲፕሎማ አበርክተውላቸዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በደቡብ ክልል በነበራቸውም ቆይታ በሃዋሳ ስታዲየም ለክልሉ ህዝብ ባደረጉት ንግግር «የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች በህብረ ብሄራዊ ቀለም ያጌጡ የአንድነትና የአብሮነት ረቂቅ ሸማ ድርና ማግ ሆኖ የተወዳጀበት የታላቋ ኢትዮጵያ ነፀብራቅ ነው» ሲሉ ጠቅሰው፤ በተጨማሪም ‹‹የደቡብ ክልል ህዝብ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ጠብቃ እንድትቀጥል በከፍተኛ አርበኝነትና የሀገር ፍቅር ስሜት የድርሻውን በመወጣት የሀገር ህልውናና አለኝታ ነው። በቀጣይም ከሀገሪቱ ህዝብ ጋር በአብሮነት በመሰለፍ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ እንድትቀጥል የድርሻውን በመወጣት ለሀገር ህልውና አለኝታ እንደሚሆን ፅኑ እምነት አለኝ›› በማለት ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በብሔራዊ ቤተመንግሥት ለሃይማኖት አባቶች፣ ለታዋቂና ነባር የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ኃላፊዎች፣ የሲቪክ ማህበራት መሪዎች፣ ታዋቂ ደራሲያን እና ለተለያዩ አርቲስቶች የእራት ግብዣ ባደረጉበት ወቅት ባስተላለፉት መልእክት አገሪቷ በቀጣይ የምታካሂደው አገራዊ ምርጫ ሕገመንግሥቱን በተከተለ መልኩ ከልብ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነፃ እንዲሆን ፓርቲያቸው አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ አባላት ሹመት ተከትሎ ባደረጉት ንግግር፤ አዲሶቹም ሆኑ በሽግሽግ የተሾሙት ሙስናን በመዋጋት፣ አላስፈላጊ የሆነ የሀብት ብክነትን በማስቀረት፣ የሥራ ባህልን በመጨመር፣ የአገልጋይነት መንፈስን በመላበስ ሰርቶ ማሰራት ኃላፊነት እንዳላበቸው አመላክተዋል፡፡ ጊዜና ገንዘብን የሚያባክን አሰራር ማስቀረት፣ ስብሰባና የውጭ አገር ጉዞም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ መከናወን እንዳለበትም አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት17/2011