አዲስ አበባ፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማፋጠን ሰባት ኮንትራክተሮች ወደ ስራ መግባታቸው ተገለጸ፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ከብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ብኢኮ) ጋር በንዑስ ኮንትራክተርነት ሲሰሩ የነበሩ ሰባት ኮንትራክተሮች ሙሉ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው እንዲሰሩ በተወሰነው መሰረት ወደ
ስራ ገብተዋል፡፡
እንደ ኢንጂነር ክፍሌ ገለጻ፤ የህዳሴ ግድቡ መዘግየት ዋናው ምክንያት ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በገባው ውል መሰረት ስራውን ስላልሰራ ነው፡፡ ከብኢኮ ጋር ንዑስ ኮንትራክተሮች ሆነው ሲሰሩ የነበሩት ሙሉ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው እንዲሰሩ ከሰባቱም ኮንትራክተሮች ጋር ውል ተፈርሟል፡፡ ወደ ስራም ገብተዋል፡፡
ከሰባቱ ሁለቱ የፈረንሳይና የቻይና ኩባንያዎች ከቅድመ ኃይል ማመንጫ ጋር በተያያዘ ጎን ለጎን ስራውን የሚሰሩ ሲሆን፣ በእቅዱ መሰረትም ሁለት ጀነሬተር ተርባይኖች ግድቡ ሳይጠናቀቅ ኃይል ለማመንጨት በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው፡፡ የፈረንሳዩ ኩባንያ በተባለው መሰረት ተርባይኑን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት ሰራተኞች አስገብቶ ስራውን በተጓዳኝ ጀምሯል፡፡ ሁለተኛ የቻይና ኩባንያ ደግሞ የብረታብረት ስራዎችን በተመለከተ ስራ ጀምሯል፡፡
እንደ ኢንጂነሩ ገለፃ፤ ከቀሩት አምስቱ ኮንትራክተሮች አንደኛው ሲኖ ሃይድሮ የሚባል የቻይና ኩባንያ ከብረታብረት ስራ ጋር የዲዛይን ስራዎችን እንደዚሁም የዎርክሾፕ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ ሌሎችም እንዲሁ የዲዛይን ስራ ላይ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ የዲዛይን፣ የአቅርቦት እንዲሁም የግዥ ሂደት ላይ ናቸው፡፡
ሁሉም ተከላ ጀምረዋል፡፡ ስራው ዲዛይን፣ የግዥ ሂደት እንዲሁም ተከላ ያለው ሲሆን፣ እንዲሁም ደግሞ የወርክሾፕና የአቅርቦት ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ በጥቅሉ ሁሉም ኮንትራክተሮች ስራ ላይ ሲሆኑ፣ ተከላው ላይ ያሉት ግን ሁለቱ የፈረንሳይና የቻይና ኩባንያዎች ናቸው፡፡
በቅርቡም ከኮንትራክተሮቹ ጋር ውይይት መደረጉን የተናገሩት ኢንጂነር ክፍሌ፣ በዚህም ስለ ስራ ዝግጅታቸው፣ በተገባው ኮንትራት መሰረት ስለመስራታቸውና ስለማጠናቀቃቸው እንዲሁም በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ከሁለት ዓመት በኋላ ሀለቱን ጀነሬተሮች በመጠቀም ኃይል ማመንጨትን ጨምሮ ስራዎቹን ለማቀላጠፍ ምን መደረግ አለበት በሚል ዝርዝር ውይይት ተካሂዶ ውሳኔ ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡ ኮንትራቱን የማስተዳደር ኃላፊነት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት ማኔጅመንት መሆኑንም ጠቅሰው፣
ኢንጂነሩ፣ ‹‹የህዝቡን አመኔታ ሙሉ ሉሙ መመለስ የምንችለው ስራውን ጀምረን ህዝቡም ስራው መሰራቱን በዓይኑ አይቶ ሲረዳ ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ መስክ ላይ ሙሉ እንቅስቃሴ ይኖራል ብለን መናገር እንችላለን›› ሲሉ ጠቅሰው፡፡
ስራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ያሉት ሁለት ግድብ ናቸው፤ አንደኛ ሳድል ዳም ሲሆን፣ እሱ ደግሞ 94 በመቶ ተጠናቋል፡፡ ትልቁ የኮንክሪት ሙሊቱ ግድብ ደግሞ 82 በመቶ ተጠናቋል፡፡ ያልተጠናቀቀበት ምክንያት ደግሞ ግድቡ ውስጥ መተከል ያለባቸው የብረታብረት ስራዎች ባመሰራታቸው ነው፡፡ ስለዚህ አሁን እየተደረገ ያለው የብረታብረት ስራዎች በቅርብ ጊዜ ተጠናቀው ስራ እንዲጀምር ማድረግ ነው፡፡
‹‹የትም አገር የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ይዘገያሉ፡፡ በተያዘው የጊዜ ገደብ የሚጠናቀቅ ፕሮጀክት የለም፡፡ ዋናው ነገር የመዘግየታቸውን መነሻ ምክንያት ማወቅ ሲሆን ይህም ምክንያት ተለይቶ እርምጃ ተወሰዷል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የፕሮጀክቱ ስራ በሙሉ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው በሙሉ አቅም መስራት ጀምሯል፡፡
ምክንያቱም ሁሉም ሰባቱም ኮንትራክተሮች ወደስራ ገብተዋል፡፡ ዋናው ግድብ ደግሞ የብረታብረት ስራው ግድቡ ውስጥ ከተተከለ በኋላ ስራው ይጀመራል፡፡ ስለዚህ ይህ ሄዶ ትክክለኛ መስመር ላይ ስላለ ህዝቡ ይህን እንዲገነዘብ እንፈልጋለን›› ሲሉ አብራርተው፤ ‹‹ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ሁሉም ነገሮች በሙሉ አቅም ተንቀሳቅስው በሁለት ዓመት ውስጥ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀመር ነው መግለፅ የምንወደውና ሕዝቡ ይህን ተረድቶ በትዕግስት እንዲከታተል እንፈልጋለን›› ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ግድቡ 66 ነጥብ 24 በመቶ ደርሷል፡፡ የዛሬ ሳምንት መጋቢት 24 ስምንተኛ ዓመቱን እንደሚያከብርም ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት17/2011
በአስቴር ኤልያስ