የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ከጎረቤቶቻችን ጋር አብረን እንድንሠራ እና እንድናድግ እንደሚያስችል ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- የዓባይ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ጥቅም ከማስገኘት ባለፈ ጎረቤት ሀገሮች እንዲጠቀሙ፣ አብረን እንድንሠራ እና አብረን እንድናድግ እንደሚያደርግ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ገለጹ:: የግድቡ ግንባታ 97 ነጥብ 6 ከመቶ መጠናቀቁንም ጠቁመዋል::

አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን አንዱ እና ትልቁ ስኬት ነው:: ለኢትዮጵያ ጥቅም ከማስገኘት በተጨማሪ ጎረቤት አገሮችም እንዲጠቀሙ፣ አብረን እንድንሠራ እና አብረን እንድናድግ ያደርጋል ብለዋል::

የግድቡ ግንባታ 97 ነጥብ 6 ከመቶ ተጠናቋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይ የግድቡ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ወይም የግድቡ ግንባታ ተጠናቋል ማለት እንደሚቻል አመልክተዋል:: አሁን ላይ የቀረው የኤሌክትሮኒክ እና መካኒካል ሥራዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል::

በግድቡ ኃይል ለማመንጨት ወደ ሥራ እንደሚገቡ ከሚጠበቁ 13ቱ ተርባይኖች 4ቱ ሥራ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ 9ኙ ተርባይኖች መገጠም አለባቸው:: ዕቃዎቹ ከባድ እና ውድ ናቸው:: ሥራዎቹን ለመጨረስ ሕዝባዊ ንቅናቄው ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል ::

ግብፆችም ሆኑ የግብፅ ተባባሪዎች የውጭ ጠላቶች የግድቡን ግንባታ የማደናቀፍ ሙከራ አድርገው እንደነበር አስታውሰው፤ መንግሥት ከሕዝቡ ጋር ተባብሮ ሙከራዎቹ እንዲከሽፉ አድርጓል:: በቀጣይነትም የግድቡ ግንባታ በታቀደለት መንገድ እንዲሔድ እና የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ ሕዝቡ በሙሉ አቅሙ በመተባበር ሥራውን ወደ ፍፃሜ ማድረስ እንደሚገባው አሳስበዋል::

እንደ አረጋዊ (ዶ/ር) ገለጻ፤ የግድቡ መጠናቀቅን ተከትሎ 5ሺህ 500 ሜጋ ዋት ማመንጨት ይቻላል:: ይህ ኃይል አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት የኢኮኖሚ ደረጃ ከበቂ በላይ ይሆናል:: የሚመነጨው ኃይል የኢትዮጵያን ፍላጎት ሸፍኖ ለጎረቤት ሀገሮችም ይተርፋል:: ከእነዚህ ሀገራት ጋር መገናኘታችን የውጭ ምንዛሪ ከማግኘት ባለፈ ተባብሮ እና ተደጋግፎ ለመሥራት በር ይከፍታል::

ኢትዮጵያ ወደ አስራ አንድ የሚደርሱ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እንዳሏት ጠቅሰው፤ በእነዚህ ወንዞች ላይ ብዙ የልማት ሥራዎችን መሥራት ይቻላል:: ሀገርን የሚመግቡ ሰፋፊ እርሻዎችን ማከናወን እንደሚገባም አመልክተዋል::

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You