ሀዋሳ፦ በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ በይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስድስት ኩባንያዎች ሥራ እንደሚጀምሩ የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ። ኩባንያዎቹ ከአርሶ አደሩ ወተት፣ አቮካዶ፣ ማርና ቡናን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ የሚያቀርቡ መሆናቸውን አመለከተ።
የፓርኩ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ኢያሱ ነጆ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በቀጣይ ሁለት ወራት ስድስት የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ሥራ ይጀምራሉ። ይህም በፓርኩ ወደ ሥራ የገቡ ኩባንያዎች ቁጥር ወደ ዘጠኝ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ይህም ለአርሶ አደሩና ለወጣቱ ተጨማሪ ገበያና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል ።
በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከዚህ ቀደም ሦስት የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ባለፉት አራት ዓመታት ከፓርኮቹ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 16 ሚሊዮን 720 ሺህ ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን፤ ይህም እንደሀገር የሚስተዋለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ እንደሚረዳ አስታውቀዋል።
በአካባቢው የሚመረቱ የግብርና ምርቶችን እሴት ተጨምሮባቸው ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁንም በኢንዱስትሪ ፓርኩ 120 ሺህ የኅብረተሰብ ክፍል የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል። በቀጣይም ለወጣቱ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በፓርኩ የተሰማሩ ኩባንያዎች ከአርሶ አደሩ ወተት፣ የአቮካዶ፣ ማርና ቡናን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ተረክበው በማቀነባበር ለሀገር ውስጥና ውጭ ገበያ የሚያቀርቡ መሆናቸውን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።
ኩባንያዎቹ በሚያመርቱበት ወቅት የሚመነጨው ተረፈ ምርት አካባቢውን እንዳይበክል ማከሚያ በፓርኩ ውስጥ መኖሩን ጠቁመው፤ ፓርኩ ውስጥ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ እና የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።
በ294 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በኢትዮጵያ ለምርት ማቀነባበሪያነት ታልመው ከተገነቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አንዱ ሲሆን በውስጡ 151 ፋብሪካዎችን መገንባት የሚያስችል አቅም እንዳለው ታውቋል።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም