
አዲስ አበባ፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት የከፋ ዞን አስተዳደር በሰውና በእንስሳት ጉልበት ላይ የቆየውን የእርሻ ሥራ ወደ ማሽን በመውሰድ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ 25 የእርሻ ትራክተሮችን ግዥ መፈፀሙን አስታወቀ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት የከፋ ዞን አስተዳደር የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጋዎ አባሜጫ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቱን በአግባቡ ያልተጠቀመ፤ ከእርሻ ሥራ ጋር ተያይዞ የምርትና ምርታማነት ዕድገቱ ካለው የተፈጥሮ ሀብት ጋር የማይሄድ በመሆኑ ግብርናውን ማዘመን አስፈልጓል።
በዞኑ በሰውና በእንስሳት ጉልበት ላይ የተንጠለጠለውን የግብርና ሥራ ወደ ማሽን ለመቀየር እየተሰራ ነው። ለዚህም በዞኑ አስተዳደር ሥር በሚገኙ አምስት የከተማ አስተዳደሮችና 12 የገጠር ወረዳዎች ላይ ያሉትን ከፍተኛ የእርሻ መሬት ሊያግዙ የሚችሉና በሰውና በእንስሳት ጉልበት ላይ የቆየውን የእርሻ ሥራ ለመቀየር 25 ትራክተሮች ተገዝተዋል።
ትራክተሮቹ ምርታማ ከሆነው የወጣት ክፍል ጋር የሚገናኙ ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ የፈረስ ጉልበታቸው 132 የሆኑ 25 ትራክተሮች መገዛታቸውን ገልጸዋል። የግዢ ሥርዓቱ በዱቤ መሆኑንና ሽያጩም በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በልዩ ሁኔታ ታይቶ 30 በመቶ ቅድመ ክፍያ 70 በመቶው ደግሞ በሦስት ዓመት የሚያልቅ ሆኖ እንደተፈጸመ ተናግረዋል።
ግዢው ወደ 58ሚሊዮን ብር ውል እንደተገባና 17 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ቅድመ ክፍያ እንደተፈጸመ ጠቅሰዋል። ይህም አካባቢው የመልማት አቅም እያለው ባለመታገዙ ወደ ኋላ ቀርቶ የነበረውን የግብርና ሥራ እንደሚያነቃቃ አመላክተዋል።
ኃለፊው በዞኑ ከአንድ ነጥብ 16 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እንዳለ አንስተዋል። ከደንና ከቋሚ ሰብሎች ከተሸፈነው ውጭ 236 ሺህ ሄክታሩ የእርሻ መሬት መሆኑን ጠቅሰዋል። ትራክተሮች አጠቃላይ የእርሻ ሥራ ላይ የሚውሉና ከሰብል ምርት ጋር የሚያያዙ እንደሆነም አስረድተዋል።
እንደ ዞን ከሦስቱ የአዝመራ ወቅቶች 36ሺህ 700 ሄክታር በተገዙት ትራክተሮች በዓመት ውስጥ እንደሚሰራ ነው የገለጹት። በሦስቱ የአዝመራ ወቅቶች እየታረሱ ካሉት ወደ 184ሺህ 250 ሄክታር ውስጥ በተገዙ ትራክተሮች የሚሸፈነው የእርሻ ሥራ 20 በመቶ እንደሆነ ጠቁመው፤ ይህ ዞኑን ትርፋማና ምርታማ ሊያደርግ የሚችል እንቅስቃሴ እንደሆነ አመላክተዋል።
እንደ አቶ ጋዎ ገለጻ፤ ግብርና በሰውም ሆነ በእንስሳት ጉልበት እያረጀ መጥቷል። ይህ በቴክኖሎጂ መደገፍ ይኖርበታል። የእርሻ ሥራዎችን በነባሩ ባህል ማስቀጠል ምርታማነትን ይቀንሳል። ትውልዱ ወደ ዘመናዊነት እየመጣ የእርሻን ሥራ እየናቀ ከሄደና ሥራው ከቆመ የሰው ልጅ በልቶ የማደር ጥያቄ ውስጥ ይገባል።
በአገር ደረጃ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነትን ሊፈታ የሚችል የእርሻ ሥራ ብቻ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ከነባሩ የእርሻ ሥራ እየሸሸ ያለውን የወጣት ጉልበት በተወሰነ መልኩ ከቴክኖሎጂ ጋር በማገናኘት ወደ ሜካናይዜሽን ውስጥ ማስገባት ምርታማውን የወጣት ጉልበት ለማቀናጀት ያግዛል። በምርትና ምርታማነት ላይም እድገት ያመጣል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 /2014