
ተማሪ ሳሚ ኑሪ የገላን የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው። ሳሚ የፈጠራ ሥራ ፍላጎቱ ገና በልጅነት እድሜው ላይ እያለ ነው የመነጨው።
ከህጻንነቴ ጀምሮ በገመድ የሚጎተት ተሽከርካሪ ሳይ ያናድደኝ ነበር የሚለው ተማሪ ሳሚ፤ ተሽከርካሪ መሄድ ብቻ ሳይሆን አዲስ ገፅታ እንደሚያስፈልገውም ያኔ በልጅነት እድሜው ይመኝ ነበር።
ይህ የልጅነት የፈጠራ ምኞቱን መሰረት አድርጎ አሁን በደረሰበት በትምህርት ቤት ባገኘው የታዳጊነት እድሜው እውን ማድረግ ችሏል።
የፈጠራ ሥራው ደግሞ ለስለላ አገልግሎት የሚውል ስምንት ሜጋ ፒክስል ተንቀሳቃሽ ምስል የሚቀርጽ እና በ3ጅ ኔትዎርክ የሚሰራ የተንቀሳቃሽ ምስል የስለላ ተሽከርካሪ ሰርቶ እውን አድርጓል።
ይህ የተማሪ ሳሚ የፈጠራ ሥራ ዋይፍይ ከተንቀሳቃሽ ስልክ ጋር በማገናኘት እና የራሱ ድረ ገጽ ኖሮት በተንቀሳቃሽ ስልክ ስክሪን እየታየ የሚነዳ የመካኒካል ተሽከርካሪ ነው።
ይህ የፈጠራ ሥራ የስነ ፈለክና የሂሳብ አልጎሪዝምን ጥቅም ላይ በማዋል የተሠራ ነው የሚለው ወጣት ሳሚ፤ ፈጠራው አንድ ቦታ ላይ በመሆን በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ መተግበሪያ በመጫን በስልክ ስክሪን አማካኝነት ካሜራውን መቆጣጠር እና ማንቀሳቀስ የሚቻል መሆኑ ፈጠራውን ልዩ ያደርገዋል ይላል።
በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ ያዋለው የፈጠራ ሥራው አንድ ካሜራ ብቻ የተገጠመለት እና 90 ዲግሪ በመንቀሳቀስ የሚያሳይ መሆኑን የጠቆመው ተማሪ ሳሚ፤ ይህን የፈጠራ ሥራ ሁለት ካሜራ በመግጠም እንደ ፈረስ ዓይን 180 ዲግሪ እንዲያሳይ ማድረግ የሚቻል መሆኑንም ጠቅሷል። ይህ የፈጠራ ሥራ ሙቀትን በማገናዘብ በአንድ አካባቢ የሚገኙ ሰዎችን መቁጠር እንደሚያስችልም ተማሪ ሳሚ ይናገራል።
ፈንጂ እና ተቀጣጣይ ነገሮች መኖራቸውን እና አለመኖራቸውን ለመለየት ሰው መላክ ሳያስፈልግ ይህን ተሽከርካሪ ቀድሞ በመላክ እንዲሁም ሴንሰር ወይም የመለያዎችን ጨረር በመልቀቅ ማክሸፍ እንደሚቻልም ያስረዳል።
ለስለላ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው ድሮን ድምፅ ያለው ነው። ይህ ደግሞ የድሮን ድክመት ነው የሚለው ተማሪ ሳሚ፤ ይህ አዲሱ የፈጠራ ሥራው ግን ይህንን ችግር ከመፍታት አልፎ ሙቀት መገንዘቢያ ያለው በመሆኑ በአካባቢው ምን ያህል ሰዎች እንዳሉ መረጃ ያቀብላል።
በተጨማሪም ድምፅ አልባ በመሆኑ ምሽግ ውስጥ በመግባት መረጃ የማቀበል አቅም አለው። የራሱ ዋይፋይ የሚያመነጭ እና ስምንት ሜጋ ፒክስል የፊት ለፊት ካሜራ እንዲሁም አንቴና አምፕሊፋይ ተገጥሞለታል።
ይህም ሰው መላክ ሳያስፈልግ በዋሻዎች፣ በቱቦዎች በመንቀሳቀስ በአካባቢው ያለውን መረጃ በተንቀሳቃሽ ምስል መቅረፅ ያስችላል፤ የራሱ ድረ ገፅ አድራሻ ያለው በመሆኑም ቅኝት ለማድረግ እንደሚያስችል ተማሪ ሳሚ ይናገራል።
ፈጠራው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እቃ ለማመላለስ፣ ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም ለህጻናት መዝናኛ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ተማሪ ሳሚ ይጠቅሳል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 /2014