አዲስ አበባ፡- የለውጡ መሃንዲሶችና መሪዎች ስራቸውን በማከናወን ላይ እንደመሆናቸው ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል ከጎናቸው በመሆን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጠየቁ፡፡
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ ባለፈው አንድ ዓመት የለውጡ መሃንዲሶችና መሪዎች ስራቸውን በማከናወናቸው በአገር አቀፍ ደረጃ አስደናቂና ትልልቅ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ በመሆኑም ሌላውም አካል ለውጡ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ከጎናቸው በመሆን ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡
እንደ ወይዘሮ ፎዚያ ገለፃ፤ አስደናቂ ለውጦች ከሚባሉት መካከል የዴሞክራሲ ምህዳር መስፋት ሲሆን፣ የዚህ አንዱ ማሳያ ደግሞ በውጭ አገር የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው በተመቻቸላቸው ምህዳር መሰረት ሃሳባቸውን እየገለፁ አባላትም እየመለመሉ መሆናቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ጎረቤት አገር ብቻ ሳትሆን ከኢትዮጵያ ጋር የደም ትስስር ካላት ከኤርትራ ጋር በተደረገው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሰረት ‹‹ካሳ ክፈይኝ ክፈይኝ›› መባባል ሳይኖር መግባባት ላይ መደረሱ ትልቅ ውጤት ነው፡፡
ሰብሳቢዋ፣ ‹‹ሴቶችን ወደ አመራር ከማምጣት ጋር በተያያዘ ደግሞ የተደረገው እንቅስቃሴ በእኛ
ትውልድ እናየዋለን ብለን ያላሰብነው ጉዳይ ነው፡፡›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
እርሳቸው እንደተናገሩት፤ በአንፃሩ ደግሞ ችግሮችም አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ የህግ የበላይነትን ከማስከበር እና በነፃነት ወደተፈለገበት አካባቢ ከመንቀሳቀስ አኳያ ችግር በመኖሩ አሁንም መሰራት የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ አመላካቾች ናቸው፡፡ አንዳንድ ቦታ ደግሞ ህገ መንግስት ሲጣስም ይታያል፡፡ እነዚህን መሰል ችግሮች ከተስተካከሉ ለውጥ የተሟላ እንደሚሆን ይታመናል፡፡
‹‹እንዲያም ሆነ የለውጡ መሃንዲሶችና መሪዎች የራሳቸውን ስራ እየሰሩ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ደግሞ ከእኔ ምን ይጠበቃል የሚለውን ቆም ብሎ በማስተዋል መደገፍ ይጠበቅበታል፡፡ በትንንሽ ነገርና ምንጩ ባልታወቀ መረጃ ወዲያው ተስፋ ሲቆርጥ ይታያልና ይህ አይነቱ አካሄድ ለውጡን ውስጣዊ ካለማድረግ የመጣ መሆኑን የሚያመላክት ነውና ትልልቅ ፍሬዎቻችን እንዳይበላሹና እንዳይረግፉም ጭምር ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ በጎደለው እየሞላን ለውጡን ወደፊት ማስኬድ ከሁሉም የሚጠበቅ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃኑ ትልቁን ሚና ሊጫወቱ ይገባል›› ብለዋል፡፡
ለውጥ በራሱ ሂደት ነው፡፡ በመሆኑም ጊዜ ይፈልጋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ወደፊት መሄድ እንዳለ ሁሉ ወደ ኋላ መመለስም ሊኖር ስለሚችል ለውጡ ወደ ኋላ እንዳይመለስ እያንዳንዱ ሰው ቀዳዳዎች ሲያጋጥሙት ማስፋት ሳይሆን በመሙላት የለውጡ ባለቤት መሆንና ከለውጡም ተጠቃሚ መሆን እንደሚጠበቅበት ወይዘሮ ፎዚያ ገልፀዋል፡፡
ሰብሳቢዋ እንደገለፁት፤ በተለይ የመገናኛ ብዙሃን ህዝቡን ወደ አንድ ማምጣት፣ ሚዛናዊ የሆኑ ዘገባዎችን መዘገብ እና ምንጫቸው በማይታወቅ የማህበረሰብ ትስስር ደረ ገፅ ላይ የሚለቀቁ የሐሰት መረጃዎችን ሊያጋልጡ የሚችሉ ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝቡ በመስጠት የሐሰት ወሬዎች እንዲጨነግፉ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ከሆነ ህዝቡም፣ መገናኛ ብዙሃኑም ሆነ የለውጡ መሪ የሆነውም መንግስት ተጠናክረው ይሄዳሉ የሚል እምነት አላቸው፡፡ በተጨማሪም የዴሞክራሲ ተቋማትም ምንም አይነት እስራት ሳይኖራቸው በተልዕኳች ልክ እንዲሰሩ የሚደረግ ከሆነ እንዲሁም ፓርላማውም ከተጠናከረ ያለምንም ጥርጥር ለውጡ ወደ ኋላ የማይመለስ በመሆኑ ሰፊው ህዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት17/2011
በአስቴር ኤልያስ