ከቀኝ አዝማች ወንድማገኝ አለሙና ከወይዘሮ አበራሽ ደስታ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ሰንጋ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው የዛሬ 66 ዓመት ገደማ የተወለደችው፡፡ ለአባትና ለእናቷ ሶስተኛ ልጅ ስትሆን አባቷ ሌላ ትዳር መስርተው ያፈሯቸው ስድስት እህትና ወንድሞች አንዳሏት ትናገራለች፡፡ የዛሬ የሕይወት ገጽታ እንግዳችን አንጋፋዋ ጋዜጠኛ ብዙ ወንድማገኝ። (በነገራችን ላይ፣ “ጋዜጠኛ አንቱ አይባልም” ያለችኝን በመቀበል” “አንቺ” እያልኩ የምቀጥል መሆኔን ከወዲሁ ማሳወቁ ተገቢ ነው።)
ብዙ ወንድማገኝ አዲስ አበባ ከተማ ተወልዳ ያደገች ብትሆንም ትምህቷን “ሀ” ብላ የጀመረችው ግን ጎላ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ በቄስ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ካዛ በፊት ደግሞ በአካባቢያቸው የሚኖሩት የኔታ ወልደጊዮርጊስ ልጆች እየሰበሰቡ ፊደል ያስቆጥሩ ስለነበር ብዙም በእሳቸው ፊደል የመቁጠር እድልን አግኝታለች፡፡
ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ለመግባት ስታስብ ግን ሁኔታዎች ቀላል አልሁኑላትም፡፡ ችግሩ ደግሞ አባትዋ “ሴት ልጅ የጸሎት መጽሐፍ ለማንበብ ፊደል መቁጠርና ዳዊት መድገም በቂዋ ነው” በማለታቸው ነበር፡፡
ብዙ “… አባቴ ሴት ልጅ ዳዊት ከደገመች በቂዋ ነው ስለሚሉ ዘመናዊ ትምህርትን አይደግፉም ነበር፡፡ በእርግጥ ይህ ሁኔታ የአባቴ ብቻ ሳይሆን በዘመኑ የነበሩ አባቶችና እናቶችም ሃሳብ ነበር” ትላለች፡፡
ነገር ግን ተምሮ ትልቅ ቦታ የመድረስ ህልም የሰነቀችው ብዙ በዚህ አባባል ልትሸነፍ ወይንም ደግሞ እንደ አባቷ ሃሳብ ትምህርቱን እርግፍ አድርጋ በመተው ወደ ቤት ስራው ልታመዝንላቸው አልቻለችም፡፡ እንደውም ለእሳቸው እልህ ብላ ሳይሆን አይቀርም ዳዊትን ብቻ ዘጠኝ ጊዜ ከልሳ ስለመማሯ ትናገራለች”
ብዙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመከታተልም ከፍተኛ የሆነ ችግር ገጥሟት ነበር። እንደውም ትምህርት መማሯን የሚደግፍ አንድ ሰው እንኳን ማግኘት ተስኗት እንደ ነበር ታስታውሳለች፡፡
“….ዳዊት መድገም በቂሽ ነው ያሉኝ አባቴ የቤት ስራው ላይ እንዳተኩር ከማድረጋቸውም በተጨማሪ ባል አመጥተው ሊድሩልኝ ማሰባቸውንም ሰማሁ፡፡ ይህ ደግሞ ለእኔ ትልቅ መርዶ ሆነብኝ። እንደውም የታጨልኝ ባልም ቤት ድረስ ይመጣም ነበር” ትላለች ሁኔታውን ስታስታውስ።
ነገር ግን የትምህርትን ጥቅም የሚያውቅ፣ ራሱም የተማረ፣ “ሴትን ልጅ አስተምሮ ክፍ ያለ ደረጃ ማድረስ ነው እንጂ በልጅነት መዳር ጎጂ ልማድ ነው” ብሎ የሚያምን ሰው ከመካከላቸው ተገኘ። እሱም የብዙ ታላቅ ወንድም አማረ ወንድማገኝ ነበር።
አቶ አማረ የብዙ በልጅነት ለትዳር መሰጠት በከፍተኛ ሁኔታ ከመቃወሙም በላይ ከአባቱ ጋር ከፍተኛ የሆነ ጸብ ውስጥ ገባ ፤ አባትም አንተ የልጅቷን ሕይወት ልታበላሽ ነው ትማር የምትለው ሴተኛ አዳሪ ልታደርጋት ነው ፤ በማለት ትልቅ ጸብ ፈጠሩ ትላለች ብዙ፤ በዚህ መካከልም የትምህር ሃሳብ እንዲቆም ቤት እንድውል ተወሰነብኝ በማለት ሁኔታውን ታስታውሳለች።
አቶ አማረ ግን ወትሮውንም ቢሆን የትምህርት ጥቅሙ የገባቸው ነበሩና ስለተማረች አትባልገም፤ በልጅነቷም ትዳርም ስለያዘች እናንተ እንደምታስቡት ስኬታማ አትሆንም ፤ ስለዚህ በእኔ ሃላፊነት ዘመናዊ ትምህርት ቤት ትገባለች ብለው በውሳኔያቸው ጸኑ፤ በዚህም ውሳኔያቸው መሰረት ብዙ ዘመናዊ ትምህርትን ልታገኝ ወደ በየነመርድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባች፡፡
ትምህርት ቤት መግባቱ አንድ እርምጃ ሆኖ ሳለ ለትምህርት ቤት ክፍያና ለደንብ ልብስ ገንዘብ እንዲሁም የክፍል ጥበት ስለነበር መቀመጫ ከቤት አምጡ መባሉ ሌላ እንቅፋት ሆነ፡፡ አባትም እነዚህን የተባሉትን ነገሮች ለመሟላት በፍጹም ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡
ነገር ግን አንዴ ተወስኗልና አቶ አማረ በወቅቱ ተግባረ እድ ትምህርት ቤት እየተማረ የኪስ ገንዘብ ያገኝ ስለነበር ከገንዘቡ ላይ የደንብ ልብሱን ስምንት ብር አውጥቶ ገዛ የተጠየቀውን መቀመጫ የሚተካ 10 ብር ደግሞ ጎረቤታቸው ኮረኔል ብርሃኑ ሰጧት፡፡ አሁን ሁሉም ነገር ስለተሟላ ጉዞ ወደ ትምህርት ቤት ሆነ፡፡
“… በዚህ ሁሉ ጉጉት ውስጥ የተገኘው ትምህርት በጣም ደስ ይል ነበር፤ በመሰረቱ እኔ መጀመሪያም ትምህርት ቤት ሳልገባ በተለይም ዳዊት ከደገምኩ በኋላ መሬት ላይ ወድቆ የማገኘውን ጋዜጣ ሁሉ እየለቀምኩ አነብ ነበር፤ ምናልባት ጋዜጠኛ የመሆን ህልሙም የመጣው ከዛ ሊሆን ይችላል፤ ” በማለት ስለሁኔታው ታስታውሳለች፡፡
ትምህርቱ ከተጀመረ በኋላም ቢሆን ግን አባቷ ሃሳባቸውን መቀየር አልቻሉም ፤ እሷም እንደ ተማሪ ሆና የሚጠበቅባትን ማሟላት አልቻለችም፤ ጽዳቷን ለመጠበቅ ጊዜ ስለማይኖራት ብሎም የሚከታተል የቤተሰብ አባልም ስለሌለ ሁል ጊዜ ጸጉሯ ቅጫምና ቅማል ይሆናል፤ በዚህ ደግሞ በየሳምንቱ ትምህርት ቤት በሚደረገው ፍተሻ እሷ ትባረራለች፡፡ ነገር ግን ይህም ቢሆን እሷ ለመማር ያላት ጉጉት ቤት እንዳትውል አድርጓታል፡፡
” … አባቴ እቤት ውዬ ሙያ እንድማር ከዛም ደግሞ ትዳር ይዤ እንድኖር ስለነበር ህልማቸው ቤት ውስጥ የቤት ሰራተኛ እያለ ጠዋት ትምህርት ቤት ከመሄዴ በፊት ተነስቼ ደጅ እንዳፀዳ ውሃ አሙቄ ፊታቸውን እንዳስታጥብ ቁርስ እንዳበላ ወሰኑብኝ፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከከወንኩ በኋላ ነበር ትምህርት ቤት የምሄደው” በማለት ለትምህርት የከፈለችውን መስዋዕትነት ታስታውሳለች፡፡
እነዚህን ተግባራት አከናውና ወጥታ ትምህርት ቤት ስትደር ከፍተኛ የሆነ ድካም ከመሰማቱም በላይ ሁል ጊዜ ልብሷ ሊጥ ነክቶት እጆቿ በጥላሸት ተለውሰው ነበር የምትደርሰው፤ በዚህም በትምህርት ቤት ጓደኞቿ ፊት ከመሸማቀቋም በላይ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ደጅ እየጠበቋት ክፍል ከመግባቷ እንድትታጠብ ይነግሯት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡
ብዙ ጊዜ ነገሮች አልጋ በአልጋ አይሆኑም ብዙ የገጠማት ነገርም እንደዛው ነው፤ በትግልና በመስዋዕትነት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በብዙ ችግሮች መካከል እያለፈች ብትማርም እድል ከእሷ ጋር አልነበረችምና የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ማለፍ ሳትችል ቀረች፡፡ ይህ ሁኔታ እሷ ከነበራት የትምህርት ተሳትፎ በቤተሰቦቿ ከማይደረግላት ድጋፍ አንጻር የምትጠብቀው ቢሆንም ነገሩ ግን እጅግ አሳዘናት፡፡ አባቷ ደግሞ ይኸው ያልኩት ይህንን ነው አርፈሽ ተቀመጪ ማለታቸውን ታስታውሳለች፡፡
“…. እኔ ትምህርት እማራለሁ ብዬ የገባሁበት አስቸጋሪ ሁኔታ የማልፈው ውጣ ውረድ እውነት ከቤተሰብ ጋር ነው እምኖረው ብዬ ሁሉ እራሴን እንድጠይቅ ያስገደደኝም ነበር፤ በነገራችን ላይ አንድ ጊዜ ትምህርቴ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ሲያሰሙ በቃ ካልተማርኩ ባልም አላገባም ራሴን ባጠፋ ይሻለኛል ብዬ ለመታነቅ ሞክሬ ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው እንደዚህ የለፋሁበት ትምህርት እድል ከእኔ ጋር ባለመሆኑ ስምንተኛ ክፍል ወደቅኩ” በማለት አሳዛኙን የትምህርት ጊዜዋን ትናገራለች፡፡
ነገር ግን ያ ታላቅ ወንድሟ አቶ አማረ በወቅቱ ከተግባረ እድ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ተመርቆ አሰብ መድሃኒት ማጣሪያ ላይ ስራ ጀምሮ ነበርና፤ ነገሩን ሲሰማ በጣም አዝኖ ብትወድቂም ትምህርትሽ አይቆምም ማለቱ የጠለቀች የምትመስለው የብዙ ፀሀይ በመጠኑም ቢሆን ፈካ አደረገችው፡፡ አቶ አማረ አዲስ አበባ በሚገኘው ጓደኛው አማካይነት ገንዝብ ልኮ የግል ትምህርት ቤት እንድትገባና ከስምንተኛ ክፍል ትምህርቷን እንድትቀጥል አደረገ፡፡ በጉርምስና እድሜ ክልል ላይ የምትገኘው ብዙም ከትምህርት ወጪዋ ባሻገር ሌሎች ወጪዎችም ይኖሩባት ይሆናል በማለትም ገንዘብ መላኩ ቀጠለ፡፡
በዚህ ገንዘብ ደግሞ ጫማ ልብስ እንዲሁም ቅባትና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮቿን እያሟላች ለትምህርት ቤት በወር 25 ብር እየተከፈለላት መማርን ቀጠለች፡፡
“…የስምንተኛ ክፍል ትምህርቴን በወቅቱ በአባሃና ጂማ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት የአሁኑ ጆን ኤፍ ኬኔዲ ትምህርት ቤት በሚባለው በወር 25 ብር እየተከፈለልኝ መማሬን ጀመርኩ፡፡ የመማር ፍላጎት የነበረኝ በመሆኑም ወድቄያለሁ ብዬ አንገቴን ሳልደፋ ትምህርቴን በአግባቡ መከታተል ቀጠልኩ፡፡ በዛው ስምንተኛን ክፍል አልፌ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴንም እዛው ቀጠልኩ” ትላለች፡፡
አሁን አባቷም ተሸነፉ እሷም ራሷን የምታውቅ ኮረዳ ሆነች ስለዚህ እነዛ የምትሰቃይበት ሁኔታ ቀነስ ማለት ጀመረ፤ ወንድሟ ደግሞ ለእሷ ትምህርት የሚከፍለውን መስዋዕትነት በመረዳት መጠንከርን ምርጫዋ አድርጋለች። ብዙ አንድ ጊዜ ነፍሷ ወደጋዜጠኝነቱ አዘንብላለችና ያገኘችውን እድል ሁሉ ትጠቀም ነበር፡፡ የሚሰማት ስታገኝም ስለ ጋዜጠኝነት እንደማውራት የሚያስደስታት ነገር አልነበረም፡፡ አሁን አባሃና ጅማ ትምህርት ቤት ደግሞ ይህንን የሕይወት ጥሪዋን ለማስተናገድ ምቹ ሁኔታ ተፈጠረላት፡፡ ጠዋት ጠዋት ከጸሎት በኋላ የትምህርት ቤቱን ሚኒ ሚዲያ በመጠቀም የተለያዩ ነገሮችን ማቅረብ ጀመረች፤ አድማጭ ማግኘቷ ደስ አሰኛት፡፡
“… በትምህርት ቤት አካባቢ ሰዎች ምን ይሉናል በማለት በሳምንት አንድ ጊዜ ከጸሎት በኋላ መድረክ ላይ እየወጣሁ የተለያዩ ነገሮችን ለተማሪዎች ማቅረብ ጀመርኩ፡፡ የአባ ሃና ጅማን ተማሪዎች በአካባቢው ያሉ ሰዎች የሚሉንን ነገር እየሰበሰብኩ ማስደመጥም ቀጠልኩ፡፡ በዚህም ትልቅ ተቀባይነት አገኘሁ ደስም አለኝ” በማለት ወደጋዜጠኝነቱ ለመቅረብ ያደረገችውን ጥረት ታስታውሳለች፡፡
በዚህ መካከልም የህይወት ጥሪዋ የሆነውን ጋዜጠኝነት ለመቀላቀል የተለያዩ መንገዶችን ማማተሯ አልቀረም፤ ያገኘቻቸውን ትልልቅ ሰዎችም ጋዜጠኛ መሆን እፈልጋለሁ ምን ማድረግ አለብኝ? ወይም ጋዜጠኛ ለመሆን ምን ያስፈልጋል? እያለች ማማከርም አላቆመችም፡፡ ምናልባትም ገንዘብ ያስፈልግ ይሆን በማለትም ለወንድሟ በመናገር ገንዘብ አስልካም ያዘች።
የት ብሔድ ከህልሜ ልገናኝ አችላለሁ ብላ ስታስብም ቀድሞ ወደጭንቅላቷ የመጣላት በአገር ፍቅር ማሕበር የምትታተመው “የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ” ሆነች። ጋዜጣው ወደሚታተምበት ቦታ በመሄድም ለደብዳቤዎች አምድ ጋዜጠኛ ለመሆን ምን ያስፈልጋል የሚል ደብዳቤና ገንዝብ ይዛ ወደዋና አዘጋጁ ፊት ቀረበች፡፡ የወቅቱ ዋና አዘጋጅ አቶ ከበደ አምቢሳ ጽሁፉን በመስጠት ስንት ብር መክፈል እንዳለባት ጠየቀቻቸው፤ እርሳቸውም “ምንድን ነው የምትከፍይው ምንም የሚከፈል ነገር የለም ይልቁንም ተሰጥኦው ካለሽ ጽሁፎችን እየጻፍሽ አምጪ” በማለት እንደሸኟትም ታስታውሳለች፡፡
የመጀመሪያ ሙከራዋ የሆነውና ጥያቄ አዘል የነበረው “ጋዜጠኛ ለመሆን ምን ያስፈልጋል?” የሚለው ጽሁፍ በዋና አዘጋጁ ተቀባይነት በማግኘቱ በማግስቱ ጋዜጣው ላይ ታተመ፡፡ ይህ ጅማሬ ደግሞ ለብዙ ትልቅ እርምጃዎች መነሻ ሆናት፡፡
“… የጻፍኩት ደብዳቤ ተቀባይነት አግኝቶ በማግስቱ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ሳየው በጣም ነው የተደሰትኩት። እሳቸውም እጅግ ስለተማመኑብኝ በእሳቸው ሃላፊነት በየቀኑ የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ ትምህርት ቤቴ ድረስ ትመጣልኝ ጀመር፡፡ በዚህም ከፍተኛ የሆነ መበረታታት በውስጤ ተፈጠረ” በማለት ወደ ጋዜጠኝነት የገባችበትን መንገድ ትናገራለች፡፡
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ባለበት አቁማ ወደሕይወት ጥሪዋ የገባችው ብዙ የአስረኛ ክፍል ተማሪ እንዳለች በጽሁፍ እየተከፈላት በጊዜያዊ ጸሀፊነት በኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ መጻፍ ጀመረች። ” … አይ አንዴ በሩ ከተከፈተ በኋላ እኮ ማን ይቻለኝ በቃ የማልጽፈው ነገር ምንድን ነው፡፡ በሙያው እየጎለመስኩ ስሄድ ደግሞ ታዋቂ ከሆኑት ጋዜጠኞች ጋር በጽሁፍ ፍልሚያን ጀመርኩ” ትላለች።
ከእነ ጋሽ ጸጋዬ ገብረመድህን፣ ተስፋዬ ዳባና ከሌሎች ጋር በመሆንም ከጋዜጠኝነቱ በተጓዳኝ በቲያትሩም ለመሳተፍ እድል አገኘች፡፡ ነገር ግን በእድሜዋ ማነስ ምክንያት በተለይም ጋሽ ጸጋዬ ገብረመድህን ስለተቃወሙ መሳተፍ ሳትችል ቀረች፡፡ ይህ ነገር እጅግ የቆጫት ብዙ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እነሱ በሚያዘጋጁት ጋዜጣ ላይ አንድ ጃፓናዊ ሕጻን የሂሳብ ሊቅ ሆነ የሚል ዜና አወጡ፤ ውስጧ በእልህ የተሞላው ብዙም ያንን ዜና በመያዝ ልጆች ከመድረኩ መገለል እንደሌለባቸው የሚገልጽና ሃሳባቸውን እርስ በእርሱ የሚያጣላ አርቲክል ጻፈች። በዚህ ጊዜ ትንሿ ጋዜጠኛ በትልልቆቹ ዘንድ ጥቁር ነጥብ ተያዘባት እንደውም እነሱን ማጥቃት የሚፈልግ ሰው እሷን እየተጠቀማት እንዳለ ሁሉ አሰቡ፤ ጋሽ ጸጋዬ ገብረመድህንም ቢሯቸው ድረስ አስጠርተው ጠየቋት እሷም ያላትን ብሶት ተናገረች እርሳቸውም “አሁን አንቺ ያለሽው በነስንዱ ገብሩ ደረጃ ነው፤ ከዚህ በላይ እንድትሆኚ ያስፈልጋል፤ በዚህ መልኩ ግን አትሂጂ” በማለት ምክር ሰጥተው እንደሸኟት ታስታውሳለች፡፡
ብዙ ለጋዜጠኝነት እንደ ስሟ ብዙ መከራን ከፍላለች ፤ የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ በቋሚ ሰራተኝነት ቢቀጥራትም ጋዜጣዋ ብዙ ርቀት ሳትጓዝ ታጠፈች፤ እሷም ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በዝውውር ገባች፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ “ከማጀት እስከ አደባባይ” በሚል የሴቶች ገጽ አምድን ማዘጋጀት ጀመረች፡፡ ወቅቱ የመንግሥት ለውጥ እየተካሄደበት ነበር የእሷ አለቃ ብርሃኑ ዘሪሁንም እንዲሁም ጳውሎስ ኞኞ ባሉበት የሴቶችን አምድ በቋሚነት እየሰራች ህልሟን መኖር ጀመረች፡፡
ዛሬ ላይ ያለን ጋዜጠኞች የመረጃ ምንጮቻችንን ብቻ ተጠቅመን ይሆናል ዜና የምንሰራው፣ የተለያዩ አርቲክሎችን የምንጽፈው ብዙ ግን እንደዛ አይደለም ስትሰራ የነበረው የኖረችውም አንድ ነገር ሆነ የሚል መረጃ ከደረሳት በቦታው ላይ ሄዳ በአይኗ አይታ ከማረጋገጥ በተጨማሪ እሷን ሊያሳትፍ በሚችል ነገር ላይ ተሳትፋ ሆናውና ኖራው ነበር ስትሰራ የቆየች፡፡ ይህ የስራ ሂደቷ ደግሞ የምትሰራቸው ስራዎች ሰውኛ ባሕርይ እንዲኖራቸው ብሎም የሕብረተሰቡን የልብ ትርታ በሚገባ እንዲመቱ አልፎም የተቸገረው ሰው መፍትሔ እንዲያገኝ መቃናት ያለባቸው ነገሮች በመንግሥትና በሚመለከታቸው አካላት የመታየት እድል እንዲያገኙ ያደረገም ስለመሆኑ የሚያውቋት ሁሉ የሚመሰክሩት ሃቅ ነው፡፡
“… የስራ ሂደቱ ጥሩ ነበር ፤ በምፈልገው መልኩም ሰርቻለሁ ማለት ይቻላል፡፡ ስራዎቼን በስማበለው የምሰራ ሳልሆን በቦታው ሄጄ የተቸገሩትን ሰዎች መስዬ ነው የምሰራው፤ በዚህም ውጤታማ የሆኑ ጊዜያትን አሳልፌያለሁ ብል ማጋነን አይሆንም” በማለት ትናገራለች፡፡
“… በአንድ ወቅት የወቅቱ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ አቶ ጳውሎስ ኞኞ ጠዋት ስራ ስንገባ አንድ ነገር ተናገሩ፤ ንፋስ ስልክ የሚባል ሰፈር ማታ ለመዝናናት በወጡበት ጊዜ በርካታ ሴቶችን በመጠጥ ቤት ማየታቸውን በጣም እያጋነኑ ያወራሉ፤ ይሄንን ስሰማም አይ አቶ ጳውሎስ እርሶ በሚገልጹት ልክ ሴቶች በምሽት ስራ ላይ ተሰማርተዋል ብዬ አላምንም ምናልባት የወቅቱ ፋሽን የነበረው “ቬል ሱሪ፣ ሻፍት ጫማና አፍሮ የጸጉር ቁርጥ ሁሉንም አንድ አይነት አድርጎቦት እንዳይሆን” አልኳቸው ግን በፍጹም ሴቶች ናቸው በማለት ተከራከሩኝ። እንግዲያውስ ይህንን ነገር ማጣራት አለብኝ በማለት ማታውኑ ወደጭፈራ ቤት አመራሁና እዛ ከሚሰሩት ሴቶች መካከል አንዷን ቦታው ላይ ስራ ለመጀመር አስቤ እንደመጣሁ በመንገር ቀረብኳት እሷም አዝናልኝ ባልገባበት እንደሚሻል ምክር ሰጠችኝ አይ ግዴለም ብዬ ሁሉንም ነገር እዛው ሆኜ አየሁ፤ አቶ ጳውሎስ ያሉት ነገር እውነት መሆኑን አረጋግጬ ተመለስኩ፤ ከዛም “አንድ ሌሊት በዳንስ ቤት” በማለት አርቲክል ጻፍኩ” በማለት ለስራዋ የምትሄድበትን ርቀት ትናገራለች፡፡
ነገር ግን አርቲክል አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ሳይወጣ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ ገብረእግዚ ስላዩት አገሪቱ የሴተኛ አዳሪዎች መናኸሪያ ሆናለች እያላችሁ ነው በማለት ስለተቆጡ እንዳይታተም ሆነ፤ ከዛም በላይ ጸሃፊዋን ማግኘት እፈልጋለሁ ብለው አናገሯት፤ ነገር ግን እርሷ መታረም ያለበት ነገር መታረም አለበት እንጂ እውነታውን መካድ ችግሩ ስር እንዲሰድ መንገድ መክፈት ነው የሚል እምነት ስለነበራት ጽሁፉ አዲስ ዘመን ላይ እንዳይወጣ ቢደረግም በፖሊስና እርምጃው ጋዜጣ ላይ እንዲወጣ አስደረገች፡፡
በዚህ ጽሁፍ ደግሞ ብዙዎች ደነገጡ ነገር ግን ብዙ ከስራዋ ወደኋላ አላላችም ቀጥላም ማታ ላይ መንገድ ዳር የሚቆሙት ሴቶች ላይ ትኩረት በማድረግ እነሱን ሆና ጎዳና ቆማ ያየችውን የገጠማትን በሙሉ በመጻፍ በወቅቱ መነን በመባል ለምትታተመው መጽሄት አስረከበች፡፡
ከዚህ በኋላ ነበር እስኪ ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በመሄድ ደግሞ ልስራ በማለት ዝውውር በመጠየቅ የሄደችው፡፡ በጣቢያውም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ስትሰራ የነበረውን ከማጀት እስከ አደባባይ ይዛ ቀጠለች፡፡ በዚህ ስራዋም መላ ኢትዮጵያን ዞራለች ብዙ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲታወቁ ከማድረግ ባሻገር እንዲታረሙም የበኩሏን ተወጥታለች፡፡
ኋላም ይህ የስራ ትጋቷ አልደከም ባይነቷና በሄደችበት ሁሉ ስኬታማ ብሎም የጣቢያውን ተደማጭነት ከፍ የሚያደርግ ስራዋ ተጓዥ ካሜራችን የሚለውን ፕሮግራም እንድታዘጋጅ በአለቆች ዘንድ አስመረጣት፡፡
“… በጋዜጠኝነት ስራ ከ18 ዓመት በላይ ሰርቻለሁ፡፡ ሰርቻለሁ ስልም ከልብ የሆነ ስራን ነው እንደ ዛሬው ቢሮ ቁጭ ብሎ ስራ የለም፡፡ እንደ ዛሬው መኪናው ካሜራው ተመቻችቶ ጉዞ የለም፡፡ መኪና እንደልብ የለም ካሜራም ማግኘት ችግር ነው ገንዘቡም ትንሽ ነው ነገር ግን የሙያው ፍቅር የመስራቱ ፍላጎት ስለነበረ አንዱን ስራ ጨርሼ ቆይ ቤቴ ሄጄ አርፌ ደግሞ ሌላውን እቀጥላለሁ አልልም በዛው ነበር ወደሌላ የምቀጥለው በጠቅላላው ስራው ደስ የሚል ውጤት የሚታይበት ነበር በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ” በማለት ያሳለፈችውን ጊዜ ትናገራለች፡፡
ከዚህ ከምትወደው ስራ ብሎም አገሯን ከማስተዋወቅ ባህልን ለቀሪው ሕዝብ ከማሳየት የነጠላት የኢህአዴግ መንግሥት ወደሥልጣን መምጣት ነው፡፡ በወቅቱ የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ ከተቋሙ ከተባረሩ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰራተኞች መካከል አንዷ ሆነች።
በወቅቱ ከአምስት ዓመቱ ብቸኛ ሕጻን ልጇ ጋር ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገባች፤ ስራ ማጣት ገንዘብ አጥቶ ለመኖር መቸገር ብቻ ብዙ ነገር ደረሰባት፤ ነገር ግን ፕሮፌሰር አስራት የሚመሩት የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት ብዙን በምትሰራው ስራ ያውቋት ስለነበርም ከነልጇ ስትራብ ማየት አንችልም በማለት በቢሯቸው ውስጥ ስራ እንድታገኝ እንዳደረጓት ትናገራለች፡፡
ነገር ግን እዛ መስራቷ ይበልጥ ለመንግሥት አላስደሰተም እንደውም ክትትል እንዲበዛባት ፕሮፌሰር አስራትንም እንድትሰልልላቸው እስከመጠየቅ የደረሰ ተልዕኮ ሁሉ ይሰጧት ጀመር። ምንም እንኳን ከነልጇ ረሃብ እንዳይገላት ያደረጓትን ሰው አሳልፋ ባትሰጥም። ይህ ሁኔታ ከተማው ላይ ለመኖር እንደማያስችላት ተረዳች፡፡ የተለያዩ መንገዶችን በመፈለግ በእስራኤል አገር እየሩሳሌምን ለመሳለም በሚል ከአገሯ ተሰደደች፡፡
ስደት በእስራኤል ከባድ እንደነበር የምትናገረው ብዙ ከምትወደው ስራ ያለአግባብ መሰናበቷ ልጇን እዚሁ አዲስ አበባ ትታ መሄዷ በጠቅላላው ብዙ የሚያስቸግር ነገር ገጠማት ነገር ግን መቋቋም ደግሞ እድሜ ያረዝማልና ለመቋቋም ወሰነች፤ ተቋቁማም አለፈችው፡፡
“… ወደ እስራኤል ስሄድ ከአየር መንገድ ጀምሮ የሚያውቁኝ ሁሉ በቃ እንቺም ልትሰደጂ ነው እያሉ ነበር፤ ይህ ደግሞ ለእኔ ብሶትን ነበር የሚያሰማኝ በጣምም አዝን ነበር፤ የደረሰብኝ በደል እራሱ ይሰማኛል ከዛ ደግሞ ሌላው ፍርሃቴ በአገር ውስጥ የደረሰብኝና ለስደት ያበቃኝ የመንግሥት እንግልት ተከትሎኝ ሄዶ እዛም መጥፎ ነገር እንዳይገጥመኝ ነበር ” ትላለች፡፡
ነገር ግን የእድል ነገር ሆኖ ችግሩ አብሯት አልተጓዘም እስራኤል አገር ሄዳ ለመኖር የነበረው አስቻይ ሁኔታ ከባድ ሆነባት ብዝ ዝቅተኛ የተባለውን ሁሉ ስራ እየሰራች ራሷን ለማቆየት ጣረች፡፡ ከዛም ሁኔታዎች በዛው አልቀጠሉም የተሻለ ነገር አግኝታ ወደካናዳ ለመጓዝ በቃች፡፡
ካናዳም ከሄደች በኋላ ኑሮን ለመኖር የሚያስችል የተለያዩ ስራዎችን ብትሰራም የአገሯ ሁኔታ ግን እጅግ ያሳስባት ነበር፤ ልክ እንደሷ በግፍ ከሚወዱት አገራቸውና ስራቸው ተባረው በባዕድ አገር የሚንከራተቱ ኢትዮጵያውያን ሁኔታም እንቅልፍ ይነሳት ነበር፤ ይህ ነገር ያበቃ ዘንድም ደግሞ ከግንቦት ሰባት ጀምሮ ከተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በገንዘቧም በጉልበቷም በእውቀቷም ደጋፊ በመሆን በአገሪቱ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ ትግልን ማድረጓንም ትናገራለች፡፡
ብዙ ዛሬ ላይ የናፈቀችው ለውጥ ቢመጣም እንደ ቀድሞ ለአገሯ ዘብ መቆም ለሙያዋ ደፋ ቀና ብላ መስራት የምትችልበት ሁኔታ ላይ አይደለችም፡፡ እድሜና ስደት ተደማምረው ዛሬ ላይ አቅመቢስ አድርገዋታል፡፡ በደጋግ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቿ ድጋፍ ወደምትወዳት እናት አገሯ መግባት ብትችልም ያለችበት ሁኔታ ግን ከባድ ነው፡፡
በጎ ጓደኞቿ ለጊዜው ታርፍበት ዘንድ በተከራዩላት የእንግዳ ማረፊያ ውስጥ ነው ውላ የምታድረው፡፡ አሁን ላይ አንድ ልጇም አብሯት የለም የራሱን ኑሮ መስርቶ እየኖረ ነው፡፡ ብዙ የአገሯን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ይላቀቁ ዘንድ ብዙ የለፋች በዱር በገደሉ በመንቀሳቀስ በኢትዮጵያን እንቃኛት ዝግጅቷ መላ አገራችንን ቤታችን ቁጭ ብለን እንድናውቅ ያደረገችን የጋዜጠኝነት ሙያ የተማረችው ሳይሆን የተሰጣት ነበረች፡፡ አሁን ከኛ የት ነው ያለሽው የሚል ጥየቃችንን ትፈልጋለች።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 12 ቀን 2014 ዓ.ም