በሀገራችን መልክዓ ሀሰተኛ መረጃ ፣ ሟርት ፣ ትርክትና የሴራ ፖለቲካ ገዥ ሆነው የወጡት ብዙኃን መገናኛዎች ከሁነት ፣ ከስብሰባና ከፕሮቶኮል ዘገባ አዙሪት ወጥተው የምርመራ ዘገባ ባለመስራታቸውና በሀገሪቱ ሳሎን ነጫጭ ዝሆን የሆኑ ጉዳዮችን ባልሰማና ባላየ ማለፍን በመምረጣቸው ነው ። ሰሞኑ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በፓርላማ ቀርበው ካነሷቸው ሶስቱን በአብነት እንመልከት ። “ሌብነት ፣ ተረኝነትንና ፋኖ”፤ በሀገሪቱ ስለተንሰራፋው ሙስናና አይን ያወጣ ሌብነት ሚዲያዎቻችን ቀድመው አጀንዳ አድርገው ንቅናቄ ሊፈጥሩበት በተገባ ነበር ። ሌላው በሀገሪቱ ተረኝነት ሰፍኗል የሚለው አደገኛ የተዘባ መረጃ ለውጡ ከባተ ጀምሮ የነበረ ነው። ይሄን የተዛባ መረጃ በተለይ የመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎች በምርመራ ጋዜጠኝነት መንገድ ሄደው በእርግጥ ተረኝነት አለ ወይስ የለም የሚለውን መርምረውና አጣርተው አበክረው ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ይገባቸው ነበር።
በአማራ ክልል እየተካሔደ ባለው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ እንቅስቃሴ ፋኖ እየተሳደደ እየታሰረ ነው፤ መንግሥት ትጥቅ ሊያስፈታው ነው የሚለውን በሴራ ፖለቲካ የተዳወረ ሀሰተኛና የተዛባ መረጃን ሚዲያው ደርሶ አጣርቶና መርምሮ ይፋ ሊያደርገው ሲገባ አለማድረጉ በተወሰነ ደረጃ ውዥንብርና ግርታ መፍጠሩ አልቀረም ። ስለ ተረኝነትም ሆነ ፋኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ እስኪሰጡ መጠበቅ አልነበረበትም። አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹትን መሬት ላይ ወርዶ በማመሳከርና በማረጋገጥ ወይም ተከታይ ዘገባ/follow up/በማጠናቀር ሀሜታውን መቋጨት ያሻል ። ሚዲያው ከአጀንዳ ተቀባይነት አባዜ ወጥቶ አጀንዳ ቀራጭና የሕዝብ አስተያየት መሪ ወደ መሆን ሊሸጋገር ይገባል።
በርካታ ምርመራና ማጣራት የሚሹ ጉዳዮች በራሱ ተነሳሽነት ከስር ከስርና ወዲያው ወዲያው እያጠናቀረ ሕዝብን ከበሬ ወለደና ከሀሰተኛ መረጃ መታደግ አለበት። ጉዳዩ ፓርላማ እስኪደርስና ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ እስኪሰጡበት መጠበቅ የለበትም። ይሂን ለማድረግ ደግሞ በተለይ ኢቲቪ ፣ ኢዜአና ፕሬስ ኤጀንሲ የምርመራ ጋዜጠኝነት ቡድን ካላቋቋሙ ሌላው ቢቀር በማሕበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፍ ሊያቋቋሙ ይገባል። እያንዳንዱ ዘርፍ ደግሞ ተመራማሪዎችና አማካሪዎች ሊኖሩት ይገባል ። ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ነውና ኢትበሀሉ የመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎች ከተለመደ አሰራር ወጥተው ፤ ከመንሸራተት ተጠንቅቀው ፤ አዲሱን ወይን በአዲሱ አቁማዳ ማጋባት ይጠበቅባቸዋል። ለመንደርደሪያነት ይሄን ካልሁ ወደ ተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ ልመለስ።
የምርመራ ጋዜጠኝነት ሲወሳ እሱ በዚያ አለ ። የምርመራ ጋዜጠኝነት አውራ ምሳሌ ነው። ወዲህ ዳናውም ጥላውም ነው። ወዲያ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ያለ እሱ ማሰብ አይቻልም። ዘውድና ጎፈር ነው። አንድም ሁለትም። እንደፈንጅ ጠራጊ አይለያዩም። የምርመራ ጋዜጠኝነት መደምደሚያና ጉልላላትም ነው ። “ዋሽንግተን ፖስት”ን ከምንም አንስቶ በጋዜጠኝነት ዙፋን በግርማ የኮፈሰ ባለውለታው ነው። የ “ዋሽንግተን ፖስት” የምርመራ ጋዜጠኞች ቦብ ውድዋርድና ካርል በርንስቴን ስም ያሰሩት ፤ እውቅና ያገኙት ፤ ዝናቸው ከአጽናፍ አጽናፍ የናኘው ፤ የጻፉት አይደለም አርትኦት የሰሩለት መጽሐፍ እንደ ከረሚላ በመላው ዓለም የሚቸበቸበው የማያረጀውን “የዋተርጌቴ” ቅሌት በሕይወታቸው ተወራርደው በማጋለጣቸውና በሥልጣን መባለግን አነውረው ፤ የሕግ የበላይነትን በማይናወጥ አለት ላይ በመመስረታቸው ነው ። እንደ ሰሞነኛው የአማራ ባንክ ማስታወቂያ በየደጁ ሲያንኳኳ “ከጎንህ ማነው!?” ተብሎ ሲጠየቅ መልስ ሳይሰጥ ከርሞ ሰሞኑን ይፋ እንደሆነው ፤ ከፍ ብዬ በተለያየ መንገድ ልገልጸው የሞከርሁት ያው “ዋተርጌት”ን መሆኑን ደርሳችሁበታል ። ትላንት አርብ ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም 50 ዓመት ሞልቶት እንኳ ሰርክ አዲስ ነው። የያዝነውን ዓመት ጨምሮ ባለፉት ዓመታት ከ20 በላይ ፊልሞች ተሰርተውለታል ። በርካታ መጽሐፍትና ዶክመንተሪዎችም ተሰናድተውለታል ።
ታሪኩ እንዲህ ነው ፤ የፕሬዝዳንት ኒክሰን አስተዳደር የላካቸው አምስት ሰርሳሪዎች በወርሀ ሰኔ 17 ቀን 1972 ዓ፣ም በዋሽንግተን ዲሲ ዋተርጌት ሕንጻ ላይ የሚገኘውን የዴሞክራቶችን ዋና መስሪያ ቤት ጨለማን ተገን አድርገው ሰብረው በመግባት ከምርጫ ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ከመስረቅ ባሻገር ሚስጥራዊ የድምጽ መቅረጫና ካሜራ አስቀምጠው ይወጣሉ። ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ሲውሉ የተገኘባቸው ረብጣ ዶላር ምንጭ በአቃቤ ሕግና በመርማሪ ጋዜጦች ሲጣራ በቀጥታ ፕሬዝዳንት ኒክሰንን ለ2ኛ ጊዜ ለማስመረጥ ከተሰየመው የምርጫ ኮሚቴ ጋር ይገናኛል። የኒክሰን አስተዳደር ራሱን ከዚህ ወንጀል ነጻ ለማውጣት ያደረገው መላላጥ ነው እንግዲህ የዋተርጌት ቅሌት የተባለው ።
የሰርሳሪዎች ጉዳይ ከሪፐብሊካኖች የምርጫ ኮሚቴ ጋር መያያዙና የአዳዲስ መረጃዎች ይፋ መሆንን ተከትሎ የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተጨማሪ ምርመራ ለሕግ አውጭ ኮሚቴ መራው። የሕግ መወሰኛ ምክር ቤትም(ሰኔቱ)በፊናው የዋትርጌት ኮሚቴ በማዋቀር ማጣራቱን ተያያዘው ። ሒደቱ በጋዜጦች ፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ሰፊ ሽፋን ያገኝ ስለነበር ያለልዩነት የአሜሪካውያንን ቀልብና ትኩረት ሳበ ። በተለይ በሴኔቱ ጉዳዩ መታየትና መሰማት (hearing) እንደጀመረ በPBS ሽፋን ማግኘቱ አሜሪካውያን ምርመራውን በጉጉት በጥፍራቸው ቆመው ይከታተሉት ጀመር ። ፕሬዝዳንት ኒክሰን ወንጀሉን ለማለባበስና ለመሸፋፈን አማካሪዎቻቸው ያቀረቡላቸውን ዕቅድ ያለምንም ማቅማማት አጽድቀው አፈጻጸሙን በቅርብ ይከታተሉ እንደነበር ምስክሮች ለሴኔቱ ካጋለጡ በኋላ ጉዳዩ ከፓርቲ ፖለቲካነት አልፎ የሕዝብና የሀገር ጉዳይ ሆነ ። የኒክሰን አስተዳደር ምርመራውን ለማስተጓጎል የተለያዩ ጋሬጣዎችን በመጋረጥና ለምርመራው ለመተባበር እግሩን ይጎትት ስለነበር ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ ለመፍጠሩ ተቃርቦ ነበር።
ትላልቅና አስደንጋጭ መረጃዎች መውጣት ሲጀምሩ የኒክሰን አስተዳደርም በዛው ልክ ምርመራውን ለማደናቀፍ በስፋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ሲደረስበት በፕሬዝዳንቱ ላይ ክስ ወይም impeachment ተመሰረተ። ይሄን ተከትሎ የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በነጩ ቤተ መንግሥት የሚገኙ ሚስጥራዊ የድምጽ ቅጂዎችን የያዙ ካሴቶች ለመንግሥት መርማሪዎች ተላልፈው እንዲሰጡ ወሰነ ። ቅጂዎቹ ሲደመጡ ፕሬዝዳንቱ ምርመራውን ለማደናቀፍ ማሻጠራቸውንና የምርመራ ሒደቱን አቅጣጫ ለማስቀየርም የሚመለከታቸውን የፌዴራል ባለሥልጣናትን ለመጠቀም መሞከራቸውን አጋለጡ ። የሕግ አውጭ ኮሚቴው ፕሬዝዳንት ኒክሰን ሶስት አንቀጾችን በመተላለፍ እንዲከሰሱ ወሰነ ። የፍርድ ሒደትን በማደናቀፍ ፤ ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀምና ለምክር ቤቱ ባለመታዘዝ በሚል ። ይሄን ተከትሎ ወንጀሉን ለመደበቅ ተባባሪ መሆናቸው ተረጋገጠ ።
ወዲያው ደጋፊዎቻቸውና ፓርቲያቸው አይንህን ለአፈር አሏቸው ። ፕሬዝዳንቱ በነሐሴ 7 ቀን 1974 ዓ.ም ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ ። ይህን ባያደርጉ ኑሮ ክሱ ቀጥሎ በሰኔቱ ውሳኔ ከሥልጣናቸው ይባረሩ ነበር ። ሥልጣኑን በገዛ ፈቃዱ የለቀቀ የመጀመሪያና ብቸኛ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኑ ። በእግራቸው የተኳቸው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄራልድ ፎርድ ወዲያው ምህረት አደረጉላቸው ። በዚህ ቅሌት 69 የፕሬዝዳንት ኒክሰን ተባባሪዎች የተከሰሱ ሲሆን በ48 ዋና ዋና የአስተዳደሩ አመራሮች ላይ የተለያየ ቅጣት ተላለፈ ። የፍርድ ሒደቱ የኒክሰን አስተዳደር በሚስጥር የተቀናቃኝ ፓርቲንና የተፎካካሪ ፖለቲከኞችን ቢሮዎች መሰርሰሩን ፤ ሲአይኤን ፣ ኤፍቢአይንና የሀገር ውስጥ ገቢ መስሪያቤትን ፖለቲካዊ መጠቀሚያ ማድረጉ ተደረሰበት ። ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ከእያንዳንዱ ቅሌት በኋላ gateን በባዕድ መዳረሻነት ወይም ቅጣያነት (suffix_gate) መጠቀም እየተለመደ የመጣው ። ፕሬዝዳንት ኒክሰንን ለ2ኛ ጊዜ ለማስመረጥ የተቋቋመው ኮሚቴ የፋይናንስ አማካሪ ጎርደን ሊዲ ይሄንን ጦሰኛና በዴሞክራት ፓርቲ ላይ ያነጣጠረ አይነት ብዙ ወንጀል የምረጡኝ ዘመቻ የደህንነት ዕቅዱን ለኮሚቴው ምክትል ሊቀመንበር ስቱዋርት ማግሩደር ፤ ለፕሬዝዳንቱ አማካሪ ጆን ዲን ፣ ለጠቅላይ አቃቢ ሕጉ ጆን ሚቼል ያቀርባል ።
የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቁ ፖለቲካዊ ቀውስና ፕሬዝዳንት ኒክሰን ሥልጣን እንዲለቁ ያስገደደው ቅሌት የሚጀምረው ከዚህ ዕቅድ ነው ይላል ጆን ዲን በቁጭት። የሕግ ቃፊርና መከታ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጆን ሚቼል ዕቅዱን ከጅምሩ ከመቃወም ይልቅ ለአፈጻጸም እንዲያመች ሆኖ እንዲከለስ አስተያየት ሰጠ ። ከሁለት ወራት በኋላ የዴሞክራት ዋና መስሪያቤትን ሰብሮ ሚስጥራዊ ሰነዶችን የመስረቅ እና ከኋይታወስ ጋር የሚያገናኝ የድምጽ መቅረጫና ሰነዶችን ፎቶ እያነሳ የሚልክ መሳሪያ በድብቅ የማስቀመጡን ሴራ አጸደቀ ። የሴራው ሸራቢ ጎርደን ሊዲ ዕቅዱን በበላይነት ማስተባበሩን በህቡዕ ተያያዘው ።
የፕሬዝዳንቱ የምርጫ ኃላፊ ዋልተር ማኮርድ ቀድሞውን የኤፍቢአይ ወኪል አልፍሬድ ባልድዊንን የድምጽ መቅጃውንና የሰነድ ፎቶማንሻ መሳሪያውን በዴሞክራቶች ዋና መስሪያ ቤት በሚስጥር እንዲያጠምድ በመመደብ ዕቅዱን ማስፈጸም ጀመረ ። የምርመራ ጋዜጠኛው ጂም ሆጋን ማኮርድ ባልዳዊንን የመረጠው እንደሱ የደህንነት ሰው ስለነበረ ነው ይላል። ከዴሞክራቶች ዋና ጽህፈት ፊት ለፊት አስፋልት ተሻግሮ በሚገኘው ሀዋርድ ጆንሰን ሞቴል በማኮርድ ኩባንያ ስም ባልድዊን ክፍል ይያዛል ። በዚህ ክፍል ሆነው ትዕዛዝ ይጠባበቁ የነበሩ ግብረ አበሮች ፤ ከሊዲና ከሀንት ትዕዛዝ ሲደርሳቸው ጨለማን ተገን አድርገው የመጀመሪያውን ስርሰራ አካሂደው መሳሪያዎችን ገጥመው ይመለሳሉ ይለናል ጂም።
ይሁንና ይላል አነፍናፊው ጋዜጠኛ ጂም ፤ በዴሞክራቶች የምርጫ ኃላፊ ስፔንሰር ኦሊቨር የግል ስልክ ላይ የተገጠመውን ድምጽ መቅጃ ለማስተካከል ሰርሳሪዎች በበነጋው በውድቅት ሌሊት ወደ ዋተርጌት ይመለሳሉ ። የህንጻው የዕለቱ የጸጥታ ሰራተኛ ፍራንክ ዊሊስ የተለመደ የጥበቃ ስራው ለማካሄድ ቅኝት በማድረግ ላይ ሳለ በየበሮቹ ቁልፍ ማስገቢያዎች ላይ ቀጫጭን ገመዶችን ይመለከታል ። ባጋጣሚ የተገኙ እንጂ ሌላ የተለየ ነገር ያላቸው ስላልመሰለው ያነሳቸውና ወደ ጥበቃ ክፍሉ ይመለሳል ። ዊሊስ እንዳሰበው ገመዶቹ በአጋጣሚ የተገኙ ሳይሆኑ በሮች እንደተዘጉ ግን ደግሞ እንዳይቆለፉ የሚያደርጉ ነበሩ። ከሰዓታት በኋላ ጥበቃው ለተመሳሳይ ቅኝት ሲመለስ ያነሳቸው እነዛው ገመዶች ተመልሰው በየበሮቹ የቁልፍ ማስገቢያ ተንጠልጥለው ይመለከታል። በሁኔታው ይደናገጥና ለፖሊስ ይደውላል።
ባጋጣሚ ስልኩን ያነሱ ፖሊሶች የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎችንና የመንገድ ላይ ወንጀለኞችን ለመያዝ የወጡ ስለነበር ማንነታቸው እንዳይታወቅ እንደዘመኑ ወጣቶች ለብሰው ተመሳስለውና መኪናቸውም እንዳትለይ እንዲሁ የሲቪል ነበረች። ከዋተርጌት ሕንጻ ፊት ለፊት በሚገኘው ሀዋርድ ጆንሰን ሆቴል ክፍሉ በረንዳ ሆኖ በዋተርጌት አካባቢ አጠራጣሪ ነገርና ጸጉረ ልውጥ ሰው ከተመለከተ የዴሞክራቶችን ቢሮ ሰብረው ለገቡት ሰርሳሪዎች ማንቂያ መልዕክት እንዲያስተላልፍ የቀድሞው የኤፍቢአይ ወኪል አልፍሬድ ባልድዊይን ተመድቧል ።
ሆኖም የተጣለበትን ኃላፊነት ችላ ብሎ ፊልም እያየ ስለነበር ፖሊሶችንም ሆነ መኪናቸው በዋተርጌት ሕንጻ ፊት ለፊት እየሆነ የነበረውን አላየም ። አልሰማም። ፖሊሶቹ 6ኛ ፎቅ ቢሮ ቁጥር 29 ላይ እስኪደርሱ አልፍሬድ አይኑን ከዋተርጌት ሕንጻ ይልቅ ፊልሙ ላይ እንደተከለ ነው ። ድንገት ወደ ሕንጻው ሲመለከት 6ኛ ፎቅ ላይ ያልተለመደ እንቅስቃሴ ያስተውላል። ወዲያው ይደናገጥና እየተጣደፈ ሬዲዮውን አንስቶ ለሰርሳሪዎች የማስጠንቀቂያ መልዕክት ለማስተላለፍ ሲሞክር ነገሮች ሁሉ አክትሞላቸዋል ። ፖሊሶች አምስቱንም ሰርሳሪዎች እጅ ከፈንጅ ያዟቸው ። በወርሀ መስከረም አጋማሽ 1972 ዓ.ም አምስቱን ሰርሳሪዎችን ጨምሮ ሀንትና ሊዲ ሴራ በማሴር ፣ ቢሮ ሰርስሮ በመግባትና የፌዴራሉን ስልክ የመጥለፍ ሕግ በመተላለፍ ክስ ተመሠረተባቸው። ለነገሩ ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይለቅም እንዲሉ ፤ ሀንትና ሊዲ የደህንነት መረጃዎች ማሾለክን ለማስቆምና ጥብቅ ሚስጥራዊ መረጃዎች ለማጣራት በሚል በህቡዕ የተደራጀና “White House Plumbers”በመባል የሚታወቀው ህቡዕ ቡድንም አባል ናቸው ።
ተማምለው የሸረቡት ሴራ ሲጋለጥ መከዳዳት ያለነውና የፕሬዝዳንት ኒክሰን አማካሪ የነበረው ዲን በኋላ ላይ በሰጠው ቃል ፤ የኒክሰን 2ኛ ምርጫ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ጆን ኤህሪሊችማን ከዋተርጌት ጋር የተያያዙ በተለይ የሀዋርድንና የኋይታወስን ግንኙነት የሚመለከቱ ማስረጃዎችን እንዲያስወግድ አዝዞት እንደነበር ሲል ቢያጋልጥም ጆን ግን ውንጀላውን አስተባብሏል ። መቼም ምን ያለበት ዝላይ አይችልም እንዲሉ በወቅቱ ፕሬዝዳንት ኒክሰን በየቀኑ ይሰጡት የነበረ የተምታታ አስተያየት ጥርጣሬ ማጫሩ አለቀረም ። ሆኖም የዋተርጌቱ አቃቤ ሕግ ጀምስ ኒል ፕሬዝዳንት ኒክሰን ስለዴሞክራቶች ቢሮ መሰርሰር የሰሙት ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላ ነው ብሎ ያምን ነበር ። ይሁንና በኋላ ላይ የወጡ መረጃዎች ይፋ እንዳደረጉት ፕሬዝዳንቱ የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ወይም ቺፍ ኦፍ ስታፋቸው የነበረውን ሀልድማን ኤፍቢአይ ስለዋተርጌት የፋይናንስ ምንጭ የሚያካሂደውን ምርመራ ለሲአይኤ ነገሮ እንዲያስቆመው አዝዘውት ነበር። በወቅቱ ስለጉዳዩ የተጠየቀው የፕሬዝዳንቱ የፕሬስ ኃላፊ ሀልድማን እንደታዘዘው ቢያደርግ ኖሮ ሌላ ቅሌት ይወጣው ነበር ሲል ተሳልቋል ። ሴኔቱም እንዲከሰሱ መወሰኑ እንደማይቀር ፤ ሕዝቡም ጀርባውን እንደሰጣቸው ሲረዱ የነጩ ቤተመንግሥት ቆይታቸው እህል ውሃ እንዳለቀ ተረዱ ።
ፕሬዝዳንት ኒክሰን አስተዳደራቸውንም ሆነ ራሳቸውን ለማዳን ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም ። በገዛ ፈቃዳቸው የማይለቁ ከሆነ በሴኔቱ የተከሳሽ ሳጥን ቆመው፤ ጥፋተኝነታቸው ተረጋግጦና ቅጣት ተላልፎባቸው ፤ ውርደትን ተከናንበው ከሚባረሩ በገዛ ፈቃዳቸው ለቀው ጥቅማ ጥቅማቸውንና የተረፈች ስም ለዛውም እንጥፍጣፊ ካለች ለማዳን ሲሉ ከፍ ብሎ እንደተገለጸው በወርሀ ነሐሴ 1974 ዓ.ም መራር ውሳኔን ተጎነጩ ። በገዛ ፈቃዱ ሥልጣኑን የለቀቀ የመጀመሪያ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኑ ። አራተኛው መንግሥት ሚዲያ ለሕግ የበላይነት ሽንጡን ገትሮ ተሟግቶ ግዳይ ጣለ። ታሪክ ሰራ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 12 ቀን 2014 ዓ.ም