የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከዳር እስከ ዳር ያነቃቃና ሕዝቦቿንም ያስፈነጠዘው የድል ስሜት አሁንም አልበረደም። ብርቅዬዎቹ ዋልያዎች በአገራቸው ዓለም አቀፍ ጨዋታን ማድረግ የሚያስችል ስቴድየም በማጣታቸው ወደ ገለልተኛ አገር ማላዊ ተሰደው ጣፋጩን ድል ይዘው ተመልሰዋል። ዋልያዎቹ ከስልሳ ዓመት በኋላ የአፍሪካ እግር ኳስ ሃያሏን አገር ግብጽን ማሸነፋቸው ከስፖርት የበለጠ ብዙ ትርጉም እንዳለው ተደጋግሞ ተነግሯል። ሌላው ይቆየንና የዋልያዎቹ ድል በፖለቲካዊ ጉዳዮች ተከፋፍሎ በማሕበራዊ ገጾች ላይ ሲሻኮት ዘወትር የምናስተውለውን ማሕበረሰብ አንድ አድርጎ ማሳየቱ ለእግር ኳስ ስፖርታዊ ትርጉም ብቻ እንዳንሰጠው አድርጓል።
ዋልያዎቹ ለዘመናት ዝቅ ተደርገው ከሚታዩበት ደረጃ ወደ ከፍታው ተመልሰዋል። በዚህም ሕዝብ ተደስቷል፣ ኮርቷልም። ታዲያ ዋልያዎቹ በዚህ ደረጃ የሕዝብን ስሜት መግዛት ከቻሉና ልዩነቶቻችንን ወደ አንድነት የማምጣት ሃይል ካላቸው ከወጡበት ከፍታ እንዳይንሸራተቱ ምን ይደረግ? የሚለው ጉዳይ የሁሉም የቤት ስራ መሆን አለበት። ለዚህም ብዙ መስተካከል ካለባቸው አስተዳደራዊ ዝርዝር ነጥቦች ውስጥ አንኳሮቹን መጠቆም ወይም ማስታወስ ተገቢ ነው። ይህ የዋልያዎቹ ልብን የሚያሞቅና የሁሉም ኩራት የሆነ ድል ነገም እንዲቀጥል ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጀምሮ በፌዴሬሽን በኩል ከወዲሁ ዝርዝር እቅዶችን አውጥቶ መዘጋጀት ቀዳሚ ጉዳይ በመሆኑ ለስፖርቱ መሪዎችና ባለሙያዎች ትተነው መንግሥትንና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እናድርግ።
የዋልያዎቹና ፈርኦኖቹ ፍጥጫ አሁንም አላበቃም። በቀጣይ መስከረም ላይ የመልሱ ጨዋታ በካይሮ ይደረጋል። ዋልያዎቹ ታሪክ በቀየሩበት ጨዋታ አስደንጋጭ ሽንፈት የገጠማቸው ፈርኦኖቹ ከደረሰባቸው ትችት(ውግዘት ማለት ይቀላል) አገግመው ሕዝባቸውን በተሻለ ድል ለመካስና ዋልያዎቹን ለመበቀል ያንን ቀን እንደሚጠብቁ እርግጥ ነው። ለዚህ ዋልያዎቹም ከወዲሁ በሥነልቦናም በአካል ብቃትና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታሰብም። የአሁኑ ድል አንዴ ተመዝግቧል፣ታሪክም ያስታውሰዋል። የበለጠ ትርጉም ያለው ድል እንዲሆን ግን ስለመልሱ ጨዋታም ማሰብ ያስፈልጋል። ዋልያዎቹ ከየትኛውም የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ያነሰ አቅም እንደሌላቸው አሳይተዋል።
በእርግጥ ከዚህ ቀደም በተለይም ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ እንደ ኮትዲቯር ያሉ ግዙፍ ቡድኖችን በማሸነፍ ብልጭ ብሎ ሳናጣጥመው የሚጠፋ ተስፋ አሳይተውናል። ነገር ግን ቀጣይነት አልነበረውም።ለምን? ይህን በአግባቡ አጢኖ ዋልያዎቹ ፈርኦኖቹን በረቱበት ጨዋታ የነበራቸውን በውጤት የታጀበ አቅም እንዴት በቀጣይ ጨዋታዎች መድገም ይቻላል? የሚለውን ጉዳይ የአሰልጣኝ ቡድን አባላትና የቴክኒክ ኮሚቴው ጊዜ ወስዶ ሊመለከተው ቢችልም ከእግር ኳሳዊ ምክኒያቶች በበለጠ እገዛ የሚሹባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ የተሻሉ ከሚባሉ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ዋልያዎቹ በርካታ የወዳጅነት ጨዋታዎችን በማድረግ አቋማቸውን እየፈተሹ በጎደለው የሚሞሉበትን፣ የተጣመመውን የሚያቀኑበትን እድል መፍጠር ለነገ የሚለው የቤት ስራ አይደለም፡፡ ይህን ለማድረግ ግን በተለያዩ መንገዶች እገዛ እንደሚፈልግ ሚስጥር አይደለም፡፡
ፌዴሬሽኑ ዋልያዎቹ ከሜዳቸው ውጪ ጨዋታዎችን ለማድረግ በመገደዳቸው በአንድ ጨዋታ ለሜዳ ኪራይና ለመሳሰሉት ብቻ እስከ ሃምሳ ሺ ዶላር ወጪ እንደሚያደርግ ባለፈው መግለጫው ጠቁሞ ነበር። ይህም ካለው አቅም አንጻር ብዙ እንደማያራምደውና ጨዋታዎችን ከአገር ውጪ ሄዶ ማድረግ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደሚሳነው ስጋቱን ገልጾ ነበር። ይህ ዋልያዎቹና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በተነቃቃበት በዚህ ወቅት በሕዝብ ስሜት ላይ ውሃ ሊከልስ የሚችል አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ነገ ዋልያዎቹ በዚህ መነቃቃት ላይ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማምራት እድላቸው እየሰፋ ሲሄድ ይሄ አይነቱ እንቅፋት ሊያሳስብ አይገባም። መንግሥትም ይሁን የሚመለከተው አካልና ባለሀብቶች ድሎች ሲመዘገቡ ጮቤ ከመርገጥና ጊዜያዊ ሽልማቶችን ከማዥጎድጎድ በዘለለ ስለ ዋልያዎቹ ቀጣይ መንገድና እጣፋንታ በማሰብ እጃቸውን ወደ ኪሳቸው የሚሰዱበት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው፡፡
ይህን የፋይናንስ ጉዳይ እንቅፋት እንዲሆን ካደረጉ ምክንያቶች ዋነኛው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን በሜዳዋ የሚያስተናግድ ስቴድየም አለመኖሩ ነው። ከዚህ ቀደም ይህ የስቴድየም ችግር ሲነሳ ‹‹ለየትኛው እግር ኳስ ነው›› የሚሉ ምላሾች ከተለያዩ ወገኖች ሲሰጡ ማየት የተለመደ ነው። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ከወራት በፊት የፓርላማ ንግግራቸው ላይ በስቴድየሞች ዙሪያ በሰጡት ምላሽ ‹‹መጀመሪያ ሰርታችሁ የተሻለ ነገር አሳዩ፣ አፍሪካ ዋንጫና ኦሊምፒክ ላይ ደጋግማችሁ በመሳተፍ ውጤት አሳዩን›› በማለት መናገራቸው ይታወሳል። እርግጥ ነው መንግሥት ደረጃቸውን የጠበቁ ስቴድየሞች እንዲኖሩ ትኩረት ለመስጠት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉትን ማሳያዎች ይፈልግ ይሆናል። አዳዲስ የካፍና የፊፋን መስፈርት የሚያሟሉ ስቴድየሞችን ለመገንባት ብቻም ሳይሆን ተጀምረው ሳይጠናቀቁ ቆመው የቀሩትን ለማጠናቀቅም ቢሆን ገፊ ምክንያት ይፈልግ ይሆናል።
ዋልያዎቹ በፈርኦኖቹ ላይ የተቀዳጁት ይህ ታሪካዊ ድል ለዚህ በቂ ነው ማለት ባይቻልም የመንግሥትን አንጀት ለማራራት አያንስም። በዚህ ላይ እነዚህ ተጀምረው መጠናቀቅ የተሳናቸው ስቴድየሞች አገር በሌላት የውጭ ምንዛሬ ከመቀነቷ ፈታ፣ ሌሎች ሕዝብን ሊጠቅሙ የሚችሉ መሰረተ ልማቶች ከሚገነቡበት በጀት ቀንሳ የጀመረቻቸው በመሆኑ ዝምብሎ መመልከት እንደማይቻል ማስታወስ አስፈላጊ ነው። ይህን የተጀመረ መነቃቃት አስቀጥሎ ዋልያዎቹን በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ዳግም ለመመልከት ‹‹ብረትን እንደጋለ መቀጥቀጥ›› ነውና ነገሩ ሌላው ቢቀር አንድ ስቴድየም እንኳን ቢሆን ርብርብ ተደርጎበት ለመጨረሻዎቹ የማጣሪያ ጨዋታዎች ዋልያዎቹ ከስደት እንዲድኑ ግፊት ማድረግ ይገባል፡፡
እርግጥ ነው መንግሥት አሁን ያለበት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ይታወቃል። አብዛኞቹ የተጀመሩ ስቴድየሞችም አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቸው እንዲጠናቀቁ ቀላል የማይባል የውጭ ምንዛሬ ይፈልጋሉ። ለዚህ ግን ከታሰበበት መላ አይጠፋም። የመንግሥት ካዝና ቢነጥፍ በአገር ውስጥም ይሁን ባህርማዶ ለዋልያዎቹ የሚንሰፈሰፍ የእግር ኳስ ስሜት ያላቸው በርካታ ባለሀብት የስፖርት ቤተሰቦች ወደ ኪሳቸው እንዲገቡ ማስተባበር አንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል። በትናንሽ ድሎች ሳይቀር ጮቤ የሚረግጡ ተራ የእግር ኳስ አፍቃሪዎችም ቢሆኑ ለዋልያዎቹ ከገንዘብም ያለፈ መስዋእትነት ለመክፈል ችላ እንደማይሉ እዚህ ጋር ማስታወስ ተገቢ ነው። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህ የድል ስሜት ሳይበርድ የሚያስተባብረው ካገኘ ለዋልያዎቹ የሚሰስተው ነገር አይኖርምና ይታሰብበት።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 12 ቀን 2014 ዓ.ም