ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ በሚያዘዋውሩ አካላት ላይ 19 የክስ መዝገቦች ተከፍተው በመሰራት ላይ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ይገልፃል፡፡ የህግ ምሁራን ደግሞ የተያዙ ተጠርጣሪዎች አፋጣኝ እርምጃ ተወስዶባቸው ለሌሎች መቀጣጫ ሲሆኑ አለመታየታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ እንዳሉት፤በህግ ያልተፈቀደውን ንብረት ወደ አገር የማስገባት ሂደት በኮንትሮባንድ ወንጀልም የሚያስጠይቅ ስለሆነ በዚህ በኮንትሮባንድ ወይም በጉምሩክ ህጉ በአዋጅ 859/2000 አንቀፅ 168 መሰረት 19 መዝገቦች ላይ ክሰ መመስረት ተችሏል፡፡ ክስ መመስረት ብቻ ሳይሆን መሳሪያዎቹም ገቢ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
ባለፉት አራትና አምስት ወራት ውስጥ ወደ 60ሺ 94
የተለያዩ ሹጉጦች፣ወደ 136ሺ 95 የተለያዩ የሽጉጥ ጥይቶች፣ እንዲሁም ወደ 9 ከባድ መትረየስ፣ 5 ክላሾች፣ 2 ዝናር የጦር መሳሪያ እንዲሁም የተለያዩ የጦር መሳያዎች በዓቃቤ ህግ መዝገብ ክስ የተከፈተባቸው ናቸው፡፡ በምርመራ ላይ ያሉ እንዲሁም በቅርቡም የተያዙ አሉ፡፡ የክስ መዝገብ ከመክፈት ባሻገር የጦር መሳያዎችን ሲያዘዋውሩ የነበሩት ተሽከርካሪዎች ጭምር ውሳኔ አግኝተው ውርስ እንዲሆኑ መደረጉንም አቶ ዝናቡ ያስረዳሉ፡፡
እንደ አቶ ዝናቡ ገለጻ፣ የክስ መዝገብ ከተከፈተባቸው 19 ተከሳሾች መካከል አራቱ የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸው ጉዳዩን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ተደርጓል፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ የዋስትና መብታቸው ተከልክሎ በማረሚያ ቤት ቆይተው ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁር የሆኑት ዶክተር መሓሪ ረዳኢ እንደሚሉት፤ የህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን በተመለከተ የተያዙ ሰዎች የፍርድ ሂደታቸውና የተወሰደው እርምጃ ምን አይነት እንደሆነ ለማወቅ ሁለትና ሶስት ዓመታትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ጊዜ ስለማይሰጥ የተያዙትን ተጠርጣዎሪች በተጣደፈ ሁኔታ ቅድሚያ በመስጠት ውሳኔውን ማሳለፍ ተገቢ ነው፡፡
ጉዳዩ አንገብጋቢ በመሆኑ ፍርድ ቤቶች ለጉዳዩ ቅድሚያ ሰጥተው ቢሰሩ ለሌላውም መቀጣጫ ይሆን ዘንድ ይረዳል፡፡ ችግሩ እየሰፋ ለመሄዱ አንዱ ምክንያት ሊሆን የሚችለው በማዘዋወር ተግባር መያዛቸው እንጂ ምንም እንዳልተቀጡ ተደርገው በመታሰባቸው ነው፡፡ ምክንያቱም መቀጣታቸውን የሚገልጽ መረጃ እየተደመጠ ስላልሆነ ሌሎቹ እንዲበረታቱ አድርጓቸዋል፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ በፍርድ ቤት ቅድሚያ ተሰጥቶት ለተከታታይ ቀናት ችሎት እየተደመጠ ቢበዛ አንድ ወር ባልፈጀ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ የሚሰጥበት ሁኔታ ቢመቻች የተሻለ ነው ሲሉም ዶክተር መሓሪ ይመክራሉ፡፡
የህግ ምሁሩ፣ተጠርጣሪው ከተያዘ በኋላ ህጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ መሳሪያው የተወረሰ መሆኑንና አጥፊው ደግሞ ቅጣት የተወሰነበት መሆኑ ህብረተሰቡ ቢያውቅ ‹‹ነግ በእኔ›› የሚለውን ነገር ለማገናዘብ የሚጠቅም መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
ተጠርጣሪዎች ቅጣት ያገኙ መሆናቸውን ተከታትሎ መግለፅና ጉዳዩ የፀጥታና ያለመረጋጋት ምንጭ ስለሆነ እንደ መደበኛ የወንጀል ፋይሎች ወረፋ ከሚይዝ በተፋጠነ ሥነ ሥርዓት ታይቶ በአጭር ጊዜ ውሳኔ ተሰጥቶበት ሊገለፅ እንደሚገባ ዶክተሩ አብራርተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁር አቶ ሰለሞን ጎሹ በበኩላቸው፤ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ማሸጋገር ከባድ ቅጣት ከሚያስከትሉ ወንጀሎች ውስጥ አንዱ እንደሆነ አስታውሰው፤ ልክ እንደ ዶክተር መሓሪ ሁሉ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩ በሚመለከተው አካል መያዙ በሚዲያ እየተነገረ መሆኑን ይጠቅሱና እስከዛሬም እርምጃ ሲወሰድ እምብዛም አለመስተዋሉን ያመለክታሉ፡፡
እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤በአሁኑ ወቅት በርካታ ሪፎርሞች እየተደረጉ ነው፡፡ አንዱ ሪፎርም የፍርድ ቤቶችን አሰራር ማፋጠን፣የፍትህ ሥርዓቱንም ማዘመን ነው፡፡ ሪፎርሙ በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ እየተሰራ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች አካባቢ ባለው ክፍተትና የአቅም ችግርም ምክንያት ብዙ ጉዳዮች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ግን ትርጉም የሚኖራቸው የፖለቲካ ሁኔታውና የፀጥታው ጉዳይ ሲስተካከል ነው፡፡
‹‹በአሁኑ ሰዓት ሰው ሲቀጣ ቢያይም የዚያን ያህል ተስፋ ይቆርጥና ይተዋል የሚል አተያይ የለኝም፡፡ በእርግጥ ፍርድ ቤት እሱንም የማስተካከል ነገር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ መንግስት ስለመኖሩ ማሰማት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም አንዳንዴ ግምታዊ የሆኑ ነገሮች ከእውነታ የበለጠ አደጋ ያስከትላሉና ነው›› በማለት አብራርተዋል፡፡
አቶ ዝናቡ ቱኑ በበኩላቸው፤ በየቦታው ግጭት በመፈጠሩ ምክንያት ሰዎች የጦር መሳሪያን የመታጠቅ ዝንባሌ ይታይባቸዋል፡፡ይህን የሰው ፍላጎት ያስተዋሉ አዘዋዋሪዎች ደግሞ የረቀቀ ስልትን በመጠቀም ወደ አገር የማስገባቱን ሂደት ተያይዘውታል፡፡ ይሁንና በሚደርሰው ጥቆማ መሰረት ክትትል በማድረግ ለህግ የማቅረብ ስራ እየተሰራ ነው፡፡
የጦር መሳሪያ የመዘዋወሩ ዋነኛ ምክንያት የመጀመሪያው ይህን ሊያስቀጣ የሚችል የህግ ማዕቀፉ ደካማ መሆን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አዋጅ የማሻሻል ስራ ተጀምሯል፡፡ በፍጥነትም ፀድቆ ወደ ስራ እንዲገባም ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ ነው፡፡
‹‹የቀድሞ አዋጅ አንዳንዶቹ የዋስትና መብታቸውን የሚከለክልበት ሁኔታ የለም፡፡ ስለዚህ ግለሰቦቹ በዋስትና ይወጣሉ፡፡ እንዲሁም ደግሞ የቅጣት መጠኑም በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ አዲሱ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ነው የሚባለው የመጀመሪያ ዓላማ ተብሎ የሚወሰደው በተለይም መንግስት የአገሪቷን ህዝብ ሰላምና ፀጥታ የማስጠበቅ ኃላፊነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አሁን የታመነበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የጦር መሳያዎቹ በግለሰብ ደረጃ እንዴት ነው የሚታጠቁት? የሰዎችን ሰላም ለማስጠበቅ ሲባል ማነው መታጠቅ ያለበት? ዝውውርስ ሲዘዋወር መደረግ ያለበት ሁኔታ ምንድን ነው? ህገ ወጥ ሲሆንስ ምን አይነት የቅጣት እርምጃዎች ናቸው መወሰድ ያለባቸው? የጦር መሳሪያውስ እንዴት ነው የሚተዳደረው? የሚለውን ጭምር ዝርዝር ጉዳይ የሚይዝ ነው፡፡ ይህ ረቂቅ አዋጅ ሲፀድቅ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች ላይ በጣም ከባድ የሆነ ቅጣት ይጥላል ተብሎ ይታመናል፤ በቀጣዮቹ ወራት በአፋጣኝ ቅድሚያ ተሰጥቶ እንደሚፀድቅ የሚጠበቅ ሲሆን፣ እስከዚያው ግን ነባሩ ህግ ነው የሚሰራው›› ብለዋል፡፡
የህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩ ቀጣይነት የሚኖረው ከሆነ ሰላም ጠፍቶ አንዱ በአንዱ ላይ ለመነሳሳት የሚጋብዝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የህዝቡ አንድነትና አብሮነት የሚጠበቅ ከሆነ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ተቀባይ ያጣሉ፡፡ ህገ ወጥ መሳሪያን በሰራዊት ብዛት መጠበቅ አይቻልምና ህዝቡ ከመንግስት ጋር ሆኖ ሰላሙን ሊነሳ የሚሻውን እንዳያስተናግድ ግንዛቤ ሊፈጠርለት ይገባል፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤በዝውውሩ ሂደት ዋና የተባሉትን ለይቶ በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ የተጀመረ ሲሆን፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራም ነው፡፡ የጦር መሳሪያዎቹ የሚመጡባቸው አገራት ጋርም በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል የጋራ ስምምነቶች በማድረግ ላይ ነው፡
አዲስ ዘመን መጋቢት17/2011
በአስቴር ኤልያስ ��<�fW!h��%�+@