ምዕራብ ጎጃም፣ ደምበጫ ከተማ ተወልዳ ያደገችበት አካባቢ ነው።ከትውልድ አካባቢዋ አክስቷ ወዳሉበት አዲስ አበባ ያቀናቸው ገና በጠዋቱ ነበር።ትምህርቷንም በደምበጫ እና አዲስ አበባ ተከታትላ የ10ኛ ክፍል ትምህርቷን አጠናቅቃለች።በትምህርቷ ከ10ኛ ክፍል በላይ ባትዘልቅም በግብርና ሥራ እና በንግዱ ዘርፍ ግን ሰፊ አበርክቶ አላት።ውሎዋን ከእርሻ አዳሯን ደግሞ ምርቶቿን ወደ ገበያ ሸክፎ ከሚንቀሳቀሰው አይሱዙ መኪና ላይ አድርጋለች።
ብዙ ጊዜዋን በእርሻ ቦታ በማድረግ መሬት የሰጠቻትን ምርት ወደ ገበያ አውጥታ ትነግዳለች። ሩጫዋ ከልባችን ምት እኩል ከሚነጉደው ከጊዜ ጋር ነው። ‹‹በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ›› እንዲል ቃሉ፤ ሮጣ በማይደክማት በጉብዝናዋ ወራት ለነብስ ስጋዋ ከላይ ታች በማለት ትታትራለች። ወጣትነቷ ከጨመረላት ትጋትና ሞራል በበለጠ ለሥራ ያላት ተነሳሽነትና ፍላጎት ‹‹አልሠራሁም›› ከሚለው ቁጭቷ ጋር ተዳምሮ የምርት እጥረትና የዋጋ ንረት በተለይም በሽንኩርት ዋጋ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት ሌት ተቀን ተፍ ተፍ ትላለች።
ሽንኩርት በማምረት ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነት የወደቀበት የወንድሟን ዱካ ተከትላ ወደ ግብርና የገባችው የዕለቱ እንግዳችን ለግብርናው ዘርፍ በተለይም ለመሬት ልዩ ፍቅር አላት።ወንድሟ እያመረተ የሚያቀርበውን ሽንኩርት በመሸጥ ታግዘው የነበረችው የያኔዋ ነጋዴ ያሁኗ አርሶ አደር ነጋዴ፤ ሽንኩርትን ጨምሮ የተለያዩ አትክልቶችን በማምረት ትታወቃለች።የተመረተውን ምርት በአይሱዙ መኪኖቿ በመጫን ሌሊቱን ስትጓዝ አድራ ንግዱን የምታቀላጥፈው የዕለቱ የስኬት እንግዳችን አርሶ አደርና ነጋዴ ቃልኪዳን ጠብቀው ናት።
ቃልኪዳን፤ ከ10 አመት አስቀድማ ወደ ግብርናው ዘርፍ በመሰማራት በተለያዩ አካባቢዎች አትክልትና ፍራፍሬን እያመረተች ለገበያ ታቀርባለች።ያመረተችውን ምርት ከማሳዋ ላይ ማንም ነጋዴ አያነሳውም።በገዛ መኪኖቿ ጭና ወደ አዲስ አበባ ከተማም ይሁን በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ፍላጎት ወዳለበት ታቀርባለች።አምራችና ነጋዴ እንደመሆኗም ‹‹ውሎዬ ከማሳ አዳሬም ከአይሱዙ ላይ ነው›› ትላለች።
ቃልኪዳን ወንድሟ አምርቶ የሚያቀርበውን አትክልት በምትሸጥበት ጊዜ የምርት እጥረትና የዋጋ ንረት የሚከሰተው ብዙ አምራች ባለመኖሩ እንደሆነና ወደ ምርት መግባት እንዳለባት ታስብ ነበር።በዚህ እሳቤ ውስጥ እያለች ታድያ ወንድሟ ከግብርና ሥራው ለቆ መውጣቱ ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነላትና በቀጥታ ወደ ማምረት መግባቷን ትናገራለች።
በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በተለይም በሽንኩርት ምርት ላይ በስፋት የተሰማራችው ታታሪዋ አርሶ አደር ነጋዴ፤ ምንም እንኳን አርሶ አደር ከሆነ ቤተሰብ የመጣች ባትሆንም ለግብርና ሥራ ጥልቅ ፍቅር ያላትና ‹‹መሬትን የሚያህል ትልቅ ሀብት ይዘን፤ ወቅት ጠብቆ የሚፈራረቅን ምቹ የአየር ጸባይን ታድለን ለምን ተራብን? ለምንስ ድሆች ሆንን?›› የሚል ቁጭት የወለደውን ጥያቄ ታነሳለች።ለዚህም ‹‹ከዚህ በበለጠ መሥራት ማምረት ባለመቻሌ ነው›› በማለት ራሷን ተወቃሽ ታደርጋለች።
ያደገችበት አካባቢን ጨምሮ አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ሴት ልጅ በዚህ ደረጃ ወጥታ ወርዳ መሥራት የሌለባትና የቤት እመቤት መሆን እንዳለባት ያምናል።የቃልኪዳን ቤተሰቦችም የዚሁ ማህበረሰብ አካል እንደመሆናቸው ሥራዋን አይወዱላትም።የእነርሱ ፍላጎት አግብታና ወልዳ ኑሮ ስትመራ ማየት፤ ይህ ካልሆነ ደግሞ የቢሮ ሠራተኛ መሆን ትልቁ ግባቸው ነውና ሥራዋን አልተቀበሉትም።ካለመቀበላቸውም ባለፈ ከዛሬ ነገ ትታ ትወጣለች የሚል ሀሳብ አላቸው።እርሷ ግን ሁሉንም ተቋቁማ ስኬታማ ገበሬና ነጋዴ ሆናለች፡፡
ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ‹‹አፈር ቆፍሬ፣ ጭቃ አቡክቼ መሬት በምትሰጠኝ ምርት እራሴም ተጠቅሜ ለሌሎች እተርፋለሁ›› በማለት ወደ ግብርናው የገባችው ቃልኪዳን፤ ቀዳሚ ምርጫዋ የሆነው ወንድሟ ሲያመርትበት በነበረው ኦሮሚያ ክልል ቦሌኑራሄራ አካባቢ 32 ሄክታር የአርሶ አደር መሬት ተከራይታ መስራት ነበር።ሰፊ የገበሬ መሬት አንድ ቦታ ላይ የማይገኝ በመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውራ በኪራይ በምታገኘው መሬት የተለያዩ አትክልቶችን የምታመርተው ቃልኪዳን፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመረተችው ቀይ ሽንኩርት እንደነበር ታስታውሳለች።ከቀይ ሽንኩርት ቀጥላም መሬት የማይቀበለው ነገር የለምና ካሮት፣ ቃሪያ፣ ድንች፣ ስኳር ድንች፣ የአበባ ጎመን፣ ሀባብና ሌሎችንም በማምረት ወደ ውጤት አምርታለች።
ቀይና ነጭ ሽንኩርት ለምግብነት ለመድረስ አራት ወራትን የሚፈልጉ ሲሆን፤ በሁለት ወራትና ከዚያም ባነሰ ጊዜ የሚደርሱ ሌሎች አትክልቶች መኖራቸውን የምትናገረው ቃልኪዳን፤ ሽንኩርትን በዓመት አራት ጊዜ እንዲሁም ሌሎች ምርቶችን በዓመት ስድስት ጊዜ አምርታ ለገበያ ታቀርባለች።ያመረተቻቸውን ምርቶችንም የመሸጫ ሱቅ ተከራይታ፣ በዋናነት ኃይሌ ጋርመንትና ሰባራ ባቡር በሚገኘው የአትክልት መሸጫ ቦታ፣ ታቀርባለች፡፡
በኦሮሚያ ክልል ቡሌሄራ አካባቢ የጀመረችው የግብርና ሥራ ተስፋፍቶ በሰመራ ዱፍቲ፣ ገዋኔ፣ መተሃራና ሆረር በሚባሉ አካባቢዎች እና በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ አቃቂ አካባቢ ከአርሶ አደሮች በኪራይ በምታገኘው መሬት የተለያዩ አትክልቶችን በስፋት ታመርታለች።ስፋት ያለው ምርት ደግሞ ሰፊ የገበያ መዳረሻዎችን ይፈልጋልና የአትክልት ምርቶቿን በስፋት ከሚፈለግበት አዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ ሀረር፣ ድሬዳዋ፣ ወለጋ እና ደብረ ማርቆስ ተደራሽ ታደርጋለች፡፡
ከእርሻ ቦታዋ የማትጠፋው ቃልኪዳን፤ ቱታዋን ለብሳ ቦቲ ጫማዋን ተጫምታ በማሳ ውስጥ ካሰማራቻቸው ሠራተኞቿ ጋር እኩል ስትቆፍር፣ ስትዘራ፣ ስትጎለጉልና የደረሰውን ሽንኩርት ስትለቅም ውላ ለሊቱን ደግሞ በአይሱዙ መኪኖቿ ጭና ወደ ገበያ ለማድረስ በውድቅት ለሊት መጓዟ የግድ ነው።ያኔ እህል ውሃ ማለትና ጎን ማሳረፍ ብሎ ነገር አይታሰብም። እዚያው ሽንኩርት ከጫነው መኪናዋ ውስጥ ሆና መንጋቱን ትጠባበቃለች።ጨለማው ለብርሃን ቦታውን ሲለቅ ደግሞ አትክልቶቹን ለገበያ ታቀርባለች።
ብዙ ልፋትና ድካም በሚጠይቀው የግብርና ሥራ አርሶ አደርነትን ከንግድ ጋር በማዋደዷ ምክንያት ውሎዋ ከእርሻ አዳሯም በአይሱዙ የለሊት ጉዞ እንዲሆን የግድ ቢሆንም በሴትነቷ የገጠማት ችግር እንደሌለ ስትገልጽ ‹‹ሴት በመሆኔ የቸገረኝና ወደኋላ የቀረሁበትን ጊዜ አላስታውስም፤ ከዚያ ይልቅ ያልሠራኋቸው በርካታ ሥራዎች እንዳሉና ከዚህ የበለጠ መሥራት ብችል አገሪቷ ላይ የማንኛውም ነገር እጥረት አይገጥማትም›› በሚል ቁጭት ነው።
‹‹የግብርና ሥራ በጭቃ ከመቡካቱ ጀምሮ ሁሉም ነገር የሚያስደስት ነው፤ በተለይም መሬትን አምነን የምንጥላት አንዲት ፍሬ ብዙ ሺ አፍርታ በእጥፍ ስትመልስልን ማየት ከምንም በላይ አስደሳችና ድካምን የሚያስረሳ ነው›› የምትለው ቃልኪዳን፤ ‹‹አንድ ፍሬ ብንሰጠው ታምኖ በብዙ እጥፍ የሚመልስልን ለም መሬት፣ ውሃና ምቹ የአየር ጸባይ እያለን መቸገራችን ባለመሥራታችን ነው።በአገር ውስጥ ያለው ለም መሬት ገና ብዙ የሚያሠራንና ምንም ያልተሠራበት ነው እኔም ሠርቻለሁ ብዬ አላምንም›› ትላለች።
ቃልኪዳን፤ አትክልት ለማልማት በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ተንቀሳቅሳለች።ታዲያ በሁሉም አካባቢዎች የታዘበችው ነገር ቢኖር የተሰጠንን ጸጋ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እንዳልተጠቀምንበት ነው።‹‹ምንም ያልተነኩና ጾም እያደሩ ያሉ ክፍት ቦታዎች በምርት ቢሸፈኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር አይወራም።ልቡ ወደ ውጭ አገር የሚሸፍት ወጣትም አይፈጠርም ነበር። አሁንም ቢሆን ጊዜው አልረፈደምና መሬቱም እኛም ጾም ከምናድር ለም የሆነውን መሬታችንን በመጠቀም ምርትና ምርታማነት ላይ ብቻ አተኩረን በመሥራት ድህነትን እናሸንፍ›› በማለት ትናገራለች።
ሹፌሮችንና የሽያጭ ሠራተኞችን ሳይጨምር በቋሚነት ለ959 ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረችው ቃልኪዳን፣ በቀጣይም ይህን ቁጥር በእጥፍ በማሳደግ በተለይም በጎዳና ላይ ያሉትን ወጣቶች አሰልጥና ወደ ሥራ ለማስገባት ሰፊ ዕቅድ አላት።ይህን ዕቅድ ለማሳካት በየአካባቢው ጾም እያደሩ ያሉ ቦታዎችን መጠቀምን ታስባለች። ለዚህም በኦሮሚያና በአማራ ክልል መሬት እንዲሰጣት ጠይቃለች።ይሁንና ለአማራ ክልል ያቀረበችው የመሬት ጥያቄ መስመር የያዘና ወደ ተግባር ለመግባት ጫፍ የደረሰች እንደሆነም አጫውታናለች።
የሽንኩርት ምርቷን ወደ አዲስ አበባ ከተማ ገበያ ለማቅረብ በምታደርገው የሌሊት ጉዞ የተመለከተችው ትእይንት ከአማራ ክልል በምታገኘው መሬት ላይ ስንዴን በስፋት ለማምረት አስገድዷታል።ነገሩ እንዲህ ነው በአንዱ የሌሊት ጉዞዋ በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ከሌሊቱ ስምንት እና ዘጠኝ ሰዓት ላይ ሸገር ዳቦ ለመግዛት የተሰለፉ ዜጎቿን ትመለከታለች።ታዲያ በዚህ ጊዜ የተትረፈረፈ የስንዴ ምርት ማምረትና ይህን ታሪክ መቀየር እንዳለባት ለራሷ ቃል ገባች።ቃሏን ተግባራዊ ለማድረግም እንቅስቃሴ የጀመረችው ቃልኪዳን፤ ስንዴ ለማምረት በጠየቀችው መሬት ላይ ሠርተው፣ በልተውና ጠግበው ማደር የሚችሉ 58650 ዜጎችን እንደምትፈልግና እነዚህ የሥራ ዕድል የሚፈጠርላቸው ዜጎችም በዋናነት ከጎዳና ተነስተው በሚያገኙት ስልጠና ወደ ሥራ የሚገቡ እንደሚሆኑ አጫውታናለች።
‹‹አሁን ምን ያህል ካፒታል ላይ ደርሰሻል?›› ስንል ላነሳንላት ጥያቄ አርሶ አደርና ነጋዴዋ ቃልኪዳን፤ ስትመልስ ‹‹የገበሬ ሀብቱ መሬት ነው፤ መሬትን ደግሞ በዋጋ ልንተምናት አንችልም።ስለዚህ ስለካፒታል መጠየቅ ካለባትም መሬት እራሷ ናት መጠየቅ ያለባት።እኔ ያገኘሁትን ሁሉ መሬትን አምኜያት እሰጣታለሁ እሷም እጥፍ ድርብ አድርጋ ትመልስልኛለች›› በማለት ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥባለች፡፡
ያፈራችውን ሀብት በቁጥር ከመግለጽ የተቆጠበችው ቃልኪዳን፤ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ስላበረከተችው አስተዋጽኦም እንዲሁ ‹‹ቀኝ እጅህ ሲሰጥ ግራ እጅህ አይመልከት›› በሚለው አስተምህሮ መነሻነት በይፋ ከመናገር ተቆጥባለች።ለዚህም ‹‹ምክንያቱም ማንም ሰው ሰው በጠፋበት ቦታ ሁሉ ሰው ሆኖ መገኘት ከቻለ እሱ በቂ ነው።እኔም መክፈል ያለብኝን መስዋዕትነት ከፍዬ ሰው በሌለበት ቦታ ላይ ሰው ሆኜ እገኛለሁ›› ትላለች።
ከሁለትና ሶስት ዓመት በፊት ከፍተኛው የሽንኩርት ዋጋ በኪሎ ስምንት ብር የነበረ መሆኑን ያስታወሰችው ቃልኪዳን፤ በአሁን ወቅት አንድ ኪሎ ሽንኩርት 40 ብር መሸጡ አግባብ እንዳልሆነና ይህም የሆነው መሬት ጦሙን እያደረ ማምረት ባለመቻሉ እንደሆነ ትገልፃለች።በተለይ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ሰው ከሚሠራው ይልቅ በሰበብ አስባቡ ከሥራ ውጭ እንደሚሆንና ከሙያው ውጭ በመሆኑ ምርት ላይ ትኩረት አድርጎ እንዳይሠራ ስለማድረጉም ታስረዳለች።ስለዚህ ‹‹ለዋጋ ንረቱም ሆነ ለምርት እጥረቱ ተጠያቂዎቹ እኛው ነንና ሁላችንም በሙያችን እንሥራ›› በማለት የምትመክረው ቃልኪዳን፤ አምራች እንደመሆኗ ምርቶቿን በቀጥታ ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያን የማረጋጋት ሥራ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት አላት፡፡
ይሁን እንጂ ይህን ፍላጎቷን ዕውን ለማድረግ የመሸጫ ቦታ ያስፈልጋታል።የመሸጫ ቦታ እንዲሰጣት በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች 150 መኪኖች የጫኑትን የተለያዩ አትክልቶች ማራገፍ የሚያስችላትን ቦታ ለማግኘት ጥያቄ ብታቀርብም አንዳቸውም ፈቃደኞች ሳይሆኑ ከአንድ ቢሮ ወደ ሌላኛው ቢሮ ትመላለሳለች።‹‹ሸማቹን በቀጥታ ላግኝ›› የሚለው ጥያቄዋ ዋጋን በመቀነስ ገበያን ማረጋጋት የሚችል ከመሆኑም በላይ የማህበረሰቡን ችግር በከፊል የሚያቀል እንደሆነ ይታመናልና ምነው ጥያቄው አልተመለሰም ? በማለት እየጠየቅን፤ መሰል ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ፣ አምራቾችን በማበራከት ወቅታዊና አገራዊ የሆነውን የኑሮ ውድነት ከማቃለል ባለፈ ድህነትን በተባበረ ክንድ እናጥፋ በማለት አበቃን።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2014