ከሰሞኑ የምንሰማው የሰላም ወሬ መሰረት የያዘ ሆኖ ደም የመቀባቱ ምዕራፍ መቆም ይችል ዘንድ በማሰብ ከዚህ በፊት ይቅርታ፤ አይቅር ብለን ያስነበብነው ጽሁፍ “ለመደራደር መንደርደር” ብለን አቅርበነዋል። የሀገሬ ልጆች ቆም ብለን የሰላምን መንገድ በጋራ ፈልገን ወደ ውጤት የምንደርስበት ወቅት ነው። ሁላችንም የሰላምን ዜና በማስተጋባት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ውጤት እንዲደርስ መሻቴን እገልጻለሁ። በምናብ ታሪካችን እንጀምር።
የምናብ ታሪካችን ወደ ችሎት ይወስደናል። ለመጀመሪያ ጊዜ በፍርድ ቤት ችሎት ለመገኘት የተገኙ እናትን በችሎት የተነገረ አስተያየትን። እኒህ እናት አስቀድመው በተለያዩ ቦታዎች ላይ ስለ ብዙ ጉዳይ የሆነን ሰፊ ሰልፍ ተመልክተዋል። ቀበሌ ሄደው ከሸማቾች ለመግዛት ተሰልፈዋል። ዳቦ ለመግዛት ተሰልፈዋል። አውቶብስ ወረፋ ለመያዝ ተሰልፈዋል። ዛሬ ደግሞ ፍርድ ቤት መጥተው በሰው ጋጋታ ውስጥ ናቸው። ፍርድቤትም የሰው ጋጋታ ይኖራል ብለው ፈፅሞ አልጠበቁም።
የፍርድ ቤቱ መዝገብ ክፍል እጅግ ብዙ በሆነ መዝገብ ተሞልቶ ሲመለከቱ ግርምትን ፈጥሮባቸዋል። በየችሎቱ ስማቸው እየተጠራ ለመግባት ጥሪ የሚጠብቁትን የሰዎችን ትርምስምስ ተመልክተው እርሳቸውን ለፍርድቤት በር የዳረጋቸውን ጎረቤታቸውን “ምን አደረኩህ ልጄ?” አሉት። እርሳቸው የሚያውቁት እንደ ባህላችን በሽማግሌ ችግርን እየፈቱ በይቅርታም ሁሉም አሸናፊ እንደሚሆኑ ነው።
እማማ ከችሎት ያስገኛቸው ሁለት ተከራዮቻቸው እርስበእርስ ተጣልተው ምስክር ሆነው መጠራታቸው ነው። እማማ በትርምሱ ውስጥ ሆነው ንግግራቸውን በመቀጠል “ልጆቼ እዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ ከመግባት ምናለ በጓዳችን መክረን ችግራችንን ብንፈታ? እዚህ እንግልት ውስጥ በመግባት ጊዜያችሁን ገንዘባችሁን ለምን ታጠፋላችሁ? በመነጋገር ችግራችንን ፈተን በይቅርታ ብናልፈው አይሻልም?”አሉ። ከሳሽ ተከራይም ለምስክርነት የጠራቸውን አከራዩን “እማማ በይቅርታ ችግሩን መፍታት ያሉት እንኳን ይቅር፤ ይቅርታ እያልን አንተም ተው አንተም ተው በሚል ነገሮች እየተባባሰባቸው ሄዱ እንጂ መፍትሔ አላመጣም። ያለኝ አማራጭ በህግ ፊት መፋረድ ነው” አላቸው።
እማማም “ይቅርታው እንኳን ይቅር” የሚለውን አገላለፅ መላልሰው እያሰቡ ብዙ በሃሳብ ሄዱ። በይቅርታ በህይወት ዘመናቸው ያለፉትን ትልልቅ ጥፋት እያሰቡ ከራሳቸው ጋር አወሩ። ደም የተቃቡ ሰዎች እንኳን ነገራቸውን በሽማግሌ እግር ስር አስቀምጠው ችግርን እየፈቱ በኖሩበት ዘመን ውስጥ እንዲህ ቀላል ጉዳዮች ወደ አደባባይ ደርሰው ወረፋ ሲይዙምአስገረማቸው። ይቅርታ ሲቀር አብሮ መኖር የማይቻልበት እርስ በእርስ በጎሪጥ እየተያዩ መመላለስን የሚያመጣ አንዱ አሸናፊ ለመሆን ሌላውም ላለመሸነፍ ሁሉም ተሸናፊ ሆኖ እንደሚኖር በመረዳት ከራሳቸው ጋር መከሩ።
ችሎቱ ድረሱ ባላቸው ሰዓት ቢደርሱም ችሎቱ በሰዓቱ ሊጠራቸው ባለመቻሉ የመድኃኒት ሰዓት ደረሰባቸው። አዛውንቷ አከራይ ለጡረታቸው ብለው የሰሯቸውን የሰርቪስ ክፍል ቤትን በማከራየት ገቢ ያገኛሉ። የተከራዮቻቸው ፀብ ወደ ችሎት አምጥቷቸው የመድኃኒት ሰዓታቸውን አዛባባቸው። ይህም ችሎቱ የማይመዘግበው ወጪያቸው ነበር። የችሎቱ ሰዓት ደርሶም ተጠሩ። የምስክር ቃልም መሰማት ጀመረ እማማም ወደ ዳኛው እየተመለከቱ “ልጄ እኔ ምስክር ሆኜ የመጣሁት ያየሁትን ለመመስከር ነው።
እርሱንም አደርጋለሁ። ነገርግን የእናንተንም ሰዓት ላለመሻማት ሁሉንም ነገር ሰዎች እዚህ ይዘው ሲመጡ ለምን ትቀበላላችሁ? አንዳንዱን በአካባቢ ሽማግሌዎች በወጋችን ለምን አንፈታውም? አሁን እኔም የመድኃኒት ሰዓቴ ደርሶ እዚህ መምጣቴ አግባብ ነው?እንዴት ሰው ተነጋግሮ ይቅርታ በመጠያየቅ ውስጥ ያለውን ግሩም መፍትሔ ትቶ ይጠላለፋል?” አሉ። የችሎቱ ዳኛም የችሎት ስርዓትን አላከበሩም ብሎ ከዚህ በላይ እንዳይናገሩ አስቆማቸው።
እማማም ‹‹ዳግመኛ እግሬን አላነሳም›› እያሉ ከራሳቸው ጋር እያወሩ ምስክርነታቸውን አሰምተው ተመለሱ። ሁለቱም ተከራዮች ወደ ሰፈር ሲመለሱ እማማን ማንገላታታቸው ያስቆጫቸው በመሆኑ እማማን ሽማግሌ አድርገው ነገራቸውን ለመፍታት ተስማሙ። እማማ በሽምግልናቸው ካሳ ቢበይኑ ለመካካስ፤ ይቅርታም በቦታው ሥራውን እንዲሰራም ተስማሙ። እንደ እማማ አይነት የሚገሰፅ ኖሮ ችግሮችን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መፍታት ቢቻል ምንኛ መልካም በሆነ ነበር።አለመግባባትን በመቀነስ፤ ሲፈጠርም በአነስተኛ ዋጋ ለመፍታት በመስራት።
አለመግባባት
የሰዎች ልጅ በረጅም ታሪኩ ውስጥ ግጭት በጉልህ የሚታይ ነው። የሰው ልጅ ከግጭት ተፋቶ መኖር የማይችል ነው ብለን መደምደም እስክንችል ድረስ የሚያደርስ የግጭት ታሪክ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በጉልህ ይገኛል። ሰው አጠገቡ ካለው ሰው ጋር የመወዳጀትም ሆነ የመጋጨትን ጊዜዎችን ሊያሳልፍ ይችላል፤ ደግሞም ነው። አለመግባባት አድጎ ወደ ግጭት ሲያመራም ኪሳራው ይከተላል። ኪሳራውም በቀላሉ የሚከፈል ወይንም ፈጽሞውኑ የማይከፈል ሆኖም ያልፋል። የሰው ልጅ ህይወት ፈጽሞውኑ የማይከፈል ኪሳራ ውስጥ ተመድቦ እናገኘዋለን።
ግጭት ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ እየቀጠፈ ባለበት በዚህ ጊዜ ስለግጭት ማስረዳት አንባቢውን ማሰልቸት ሊሆን ይችላል። የግጭት መነሻ የሚሆንን አለመግባባትን ወደ መግባባት ለመቀየር ሊሰራ የሚገባው ሥራ ካልተሰራ አለመግባባት ግጭትን እያበዛ የሚቀጥል መሆኑ አይቀሬ እንደሆነ መረዳት አስፈላጊ ነው።
አለመግባባት በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር የሚችል ሲሆን ዋናው ጉዳይ ግን አለመግባባት እንዳይፈጠር ለማድረግ መሞከር፤ ከተሞከረም ፍሬያማ በሆነ በአነስተኛ ዋጋ ሊፈታ የሚችልበትን መንገድ መፈለግ ነው። አለመግባባት ወደ ውጤት እንዳይመጣ የሚያደርገው ኢ-ፍትሃዊነት ዋናው ጉዳይ ነው። አንድ አካል እኔ ብቻ የፈለኩትን ላድርግ አንተ ግን ፍላጎትህን አምቀህ ኑር ቢል ይህ ኢ-ፍትሃዊነትን አለመግባባትን፤ አለመግባባትም ግጭትን ይፈጥራል።
ከትላንት ታሪካችን እንደ አገር መማር እንዳንችል በአብዛኛው አንዱ የሌላኛውን ጥፋት ለማሳየት የሚሄደውን ያህል ራሱ ምን ያህል ለችግር አስተዋጽኦ እንዳደረገ መመልከት አለመቻሉ ነው። እያንዳንዱ ሰው የሚፈጥረውን ኢ-ፍትሃዊነት ወደ ጎን አድርጎ ሌሎች የሚፈጥሩትን ችግር የምናጎላ ከሆነ ወደ መፍትሔ መድረስ ሳንችል ቀርተን በአለመግባባትና በግጭት አዙሪት እንከርማለን። የመፍትሔ መንገዱ ብዙ ቢሆንም በዚህ ጽሁፍ የፍላጎት ልዩነትን ማጥበብንና የይቅርታን በር እንደ መፍትሔ እናነሳቸዋለን።
የፍላጎቶች ልዩነት
በአካባቢያችን ያሉ ልጆችን ስንመለከት ከምንረዳቸው ነገሮች መካከል አንዱ እርስበእርስ የሚኖራቸው ግጭት የሚነሳበት ዋና ምክንያት ይገኛል። ልጆች አብረው ሲሆኑ ሲጫወቱ፣ ሲያጠኑ ወይም ሲመገቡ በአጠቃላይ በሰላም ቆይተው በቅፅበት ድብልቅልቅ ያለ ፀብ ውስጥ ገብተው ልናገኛቸው እንችላለን። ቅድም ደማቅ በሆነ ጨዋታ ውስጥ የነበሩት ልጆች እንዴት በቅጽበት ጩኸት ወደ በረከተበት ፀብ ሊያመሩ ቻሉ ብለን ብንጠይቅ ምላሹ ከመካከላቸው አንዱ ኢ-ፍትሃዊነት የገጠመው መሆኑን እንረዳለን። ልጆቹ በተስማሙበት ህግ መሰረት ጨዋታው ሳይሄድ ሲቀር፤ አንዱ ልጅ የእርሱን ድርሻ የተነጠቀ ሲመስለው ግጭት ይፈጠራል። የቅድሙ ፍቅር በቅፅበት ወደ ፀብ ይቀየራል።
የሰው ልጅ በተፈጥሮው ኢ-ፍትሃዊነትን መቀበል የማይችል በመሆኑ የፍላጎቶች ልዩነት መኖሩ የሚያመጣው አለመግባባት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። መፍትሄው ፍትሃዊነትን በማስፈን ፍላጎትን ማቀራረብ እንጂ አስቀድሞ የሆነውን በማድረግ የተለየ ውጤት መጠበቅ አይደለም። ህፃናት ለመቀበል የሚቸግራቸውን ኢ-ፍትሃዊነት አዋቂ ሰው በተለይም የእውቀት ነፃነት የመረጃ ፍሰት ከፍተኛ በሆነበት ዘመን ሊቀበል የሚችልበት እድሉ አነስተኛ ነው። በመሆኑም አለመግባባትን እየፈታን ሰላማዊ ሕይወትን በግላችን፣ በቤታችን፣ በሥራቦታ መኖርን ስናስብ ልንገነዘብ የሚገባው እውነት ፍላጎቶቹን የማቀራረብን ጥቅም ነው።
የዛሬ 28 ዓመት በሩዋንዳ ውስጥ በእያንዳንዱ ቀን ከ10 ሺ በላይ ሰዎች ይጨፈጨፉ ነበር። ብሔርን ማዕከል አድርጎ የተነሳው ግጭት ለሦስት ወራት ያህል ቀጥሎ ከአንድ ሚሊዮን የማያንሱ ሰዎችን ህይወት ቀጥፎ ምድሪቱ በደም ጎርፍ ተመታ ነበር። ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች እንደ አንዱ ከሞት ጋር ፊትለፊት እንደተገናኘ ሰው ሆነን ራሳችንን ስንመለከት ለሰላም የሚሰጥ ዋጋ ያለውን ቦታ እንረዳለን። በጭንቅ ሰዓት የሰላም ትርጉሙ ከፍተኛ መሆኑን እንገነዘባለን። ሰውን በግፍ ከመጨፍጨፍ መለስ በጥሞና ፍላጎቶችን ማቀራረብ ላይ መስራት ቅድሚያ ቢሰጠው ኖሮ በታሪክ ውስጥ አንካሳ ታሪክን ጥሎ ማለፍ ባልሆነ ነበር።
በመግቢያችን ላይ ያነሳነው የፍርድቤቶች መኖር ለሰላም ያላቸው አስተዋጽኦ ቀላል ባይሆንም ፍትህን ለማግኘት ውድ በሆነበት ሁኔታ፤ የፍትህ ስርዓቱም አሸናፊና ተሸናፊ ብሎ በሁለት ጎራ ከፍሎ መዝገቡ በሚዘጋበት ሁኔታ፤ ፍላጎትን አቀራርቦ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት መንገድ ላይ መገኘትን አዳጋች ሊያደርገው ይችላል። የፍላጎቶች ልዩነት በሰፋ ቁጥር ግጭት አይቀሬ መሆኑን ስንረዳ አንዳችን በሌላችን ጫማ ውስጥ የማሰብን የወርቃማውን ህግ መሰረታዊነት እንረዳለን።
አንዳችን በሌላችን ጫማ
“ጎረቤቴ የሚለቀው ፍሳሽ ለጤናዬ እክል ሆነብኝ”፤ “ጎረቤቴ የሚያሰማው ድምጽ ሰላም ነሳኝ”፣ “ከጎረቤቴ የሚመጣው ጭስ አላስተኛ አለኝ” ወዘተ ብለው ሰዎች ፍትህን ፍለጋ ወደሚመለከተው አካል ከመሄዳቸው በፊት በሌላኛው ጫማ ውስጥ ቢኬድ ጥሩ ይሆን ነበር። አንዳችን በሌላችን ጫማ ሆነን ማሰብ በተሳነን ጊዜ ተጎድቼያለሁ የሚለው ሰው አለኝ በሚለው መንገድ ፍትህን ይፈልጋል ወይንም የሚፈልገውን ለማድረግ ጥረት ያደርጋል። አንዳችን በሌላችን ጫማ ሆነን ስንገኝ የሰላም አየር አካባቢያችንን ይከበዋል። በተፈጥሮ እናት ለልጆች አንዳች ጥቅምን ፈልጋ ብዙ እርቀት ትሄዳለች። ሰው ሁሉ ይህን እርስበእርሱ ማድረግ ባይችል እንኳን በሞራል ህግ ለእኔ እንዲሆን የምፈልገውን ለሌላው፤ በእኔ ላይ እንዲሆን የማልፈልገውን በሌላው ላይ ወዘተ ብለን ማሰብ ይኖርብናል።
ዋልት ዴዝኒ “አንድን ነገር ለመጀመር ዋናው ነገር ማውራትን አቁሞ የተግባር እርምጃን ማድረግ ነው” እንደሚለው አንዳችን በሌላችን ጫማን ለመተግበር የሚፈልገው የተግባር እርምጃን ብቻ ነው። ግጭትን ለመፍታት በመሄድ ውስጥ አንዳችን በሌላችን ጫማ ውስጥ መሆናችን ጥቅሙ ለሁሉም ነው። ይህም ሁሉ ሆኖ በሰዎች መካከል በተለያየ ምክንያት ግጭት ሊፈጠር ይችላል። በተለይ ከእኛ የሚጠበቀውን ተወጥተን ነገርግን አይቀሬ የሆነ ግጭት ውስጥ ስንገባ መፍትሔው አንዳችን በሌላችን ላይ ቢላ መሳል ሳይሆን ተነጋግሮ በይቅርታ ፋይሉን መዝጋት ነው።
ይቅርታ አይቅር ብለን የምናነሳው ነጥብም የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ የሆነበት ምክንያት በይቅርታ ውስጥ ያለውን መንፈሳዊም ሆነ ሥነ-ልቦናዊ ጥቅምን በማሰብ ነው። ለእኛ እንዲሆን የምንፈልገው ስለሆነ። የሰው ልጅ የጋራ ኑሮ ያለይቅርታ ትርጉም ሊኖረው ስለማይችል፤ ይቅርታ አይቅር ብለን ንባባችንን እንቀጥል።
ይቅርታ አይቅር
ኔልሰን ማንዴላ የሕይወት ታላቁ ክብር “ፈጽሞ አለመውደቅ ሳይሆን በወደቅን ቁጥር መነሳት መቻል ነው” ማለቱ ከመውደቅ መነሳት ዋና በመሆኑ ነው። ይቅርታ ደግሞ ከውድቀት የመነሻ አንዱ ነገር ነው። ሩዋንዳን ያለፉት 28 ዓመታት የሚሊዮን ዜጎችን ህይወት የቀጠፈውን ታሪክ በየዓመቱ እያስታወሰች ምን ሆነን ነበር ትላለች። ምን ሆነን ነበር የሚለው ጥያቄ ያኔ የመጀመሪያው ቢላ ከሚሳልበት ቅጽበት በፊት ቢሆን ኖሮ ምንኛ ጥሩ በሆነ ነበር። የሆነው ከሆነ በኋላ ግን ችግሩን በይቅርታ ለመፍታት የሄደችበት መንገድ አስተማሪ ነው።
በደቡብ አፍሪካም ታሪክ ውስጥ ለይቅርታ የተሰጠው ቦታ አስተማሪነቱ ብዙ ነው። የከበደውን ቁስል ግን በይቅርታ በማለፍ አዲስን ምእራፍ በስምምነት የመክፈት ምእራፍ። ይቅርታ ያለውን ትልቅ ቦታ የምንረዳው የግድ ጉዳዩ በአገር አቀፍ ደረጃ ባለ ጉዳይ ስለሆነ አይደለም።ዛሬ ብዙሪያችን ካሉ ሰዎች ጋር ያለንን ሰላም መሆን መርምረን የይቅርታ ጉዞችንን መፈተሽ ይኖርብናል። በመነጋገር እና ትላንትናን በእውነተኛ ይቅርታ በመዝጋት ወደ ውጤት ነገሮችን ማምጣት ይቻላል። ይቅርታ አይቅርም የምንለው ለዚህ ነው።
የይቅርታ በቦታው መገኘት እረፍቱ ለበዳይም ለተበዳይም መሆኑን ስንረዳ የሕይወታችን መገለጫ እናደርገዋለን። በዳይ ጥፋቱን እንዲረዳ የሚያደርገው፤ ተበዳይም በሞራል ልእልና ውስጥ ገብቶ ነገሮን ትቶ የሰላምን ኑሮ እንዲኖር የሚረዳው ነው። ግጭት የማይኖርበትን ጊዜ ምድር ላይ ከማለም ግጭት እንዳይፈጠርና ከተፈጠረም እንዴት ሊፈታ እንደሚገባ ማሰቡ የተሻለው ነው። የተሻለውን መንገድ በእርግጥም የተሻለ መሆኑን የሚያስረዳው የይቅርታ አቅም ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ለይቅርታ የሚሰጠውን ቦታ ከፍ አድርጎ ማስቀመጡን የምንረዳው ተበዳይ ወደ በደለው ሰው ሄዶ ይቅርታን እንዲያደርግ የሚጠይቅ በመሆኑ ነው። በዳይ ወደ ተበዳይ ወይንስ ተበዳይ ወደ በዳይ የሚለውን አንባቢ በጥንቃቄ እንዲያስተውል እጠይቃለሁ። ምላሹ ተበዳይ ወደ በዳይ የሚል ነው። በዳይ ወደ ተበዳይ መጥቶ የሚጠይቀውን ይቅርታ ሁላችንም የምናውቀው ቢሆንም በተቃራኒው ሲሆን ግን ግርታን የሚፈጥር ሊሆን ይችላል። ይህ የሚያሳየው ለይቅርታ ሊሰጥ የሚገባው ቦታ ከፍተኛ መሆኑን ነው።
እያንዳንዳችን ለይቅርታ ያለንን ቦታ እንፈትሽ? በትዳር ሕይወታችን ውስጥ ይቅርታ ምን ያህል እየተጠቀምንበት ነው?በሥራ ቦታስ? በምንሳተፍበት የትኛውም አይነት ማህበራዊ መስተጋብርስ? ምናልባትም ከራሳችንስ ጋርስ? አንዳንዴ ግጭቱ ከራሳችን ጋር ይሆንና ለራሳችን ይቅርታን ማድረግ ተስኖን ራሳችንን ለመቅጣት የምንሄድበት መንገድ አለ። ራሳችንን በመጣል የምንሄድበት መንገድ ራስን የመቅጫ መንገድ ሆኖ ሊታይ ይችላል።
ይህ በሆነ ጊዜ ጎልማሶቹ ሥራቸው ላይ የሚያተኩሩ፤ አዛውንቷን ለሽምግልና እንጂ ለማንገላታት ምክንያት የማይሆን፤ ታማሚዎች በአግባቡ አስታማሚ የሚያገኙ መድኃኒታቸውን በጊዜ የሚወስዱበት፤ ልጆች በሰላም ተጫውተው በሰላም ተጋጭተውና ታርቀው ተፈጥሮ ሥራዋን በአግባቡ የምትሰራበት ይሆናል። ለይቅርታ ቦታን ሰጥተን የምናደርገው ውይይትም ሆነ ድርድር ወደ ውጤት የሚያደርሰን ይሆናል። እነሆ ለመደራደር፤ መንደርደር! መንደርደሪያውም ለይቅርታ ቦታ መስጠት!።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2014