“አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” ይላል ያገሬ ገበሬ። አንድ አርሶ አደር ማሳውን አደፋርሶና ሰርዶውን ከስሩ መንግሎ አጎልጉሎ ካላረሰ ማሳው ዳዋ ይወርሰዋል። በአረም ይወጣል። ይህም አርሶ አደሩ በሚያርስበት ወቅት በደንብ አርሶ አረሙን በእንጭጩ መቅጨት ካልቻለ በአረም ወቅት የአርሶ አደሩን ልፋት እጥፍ ድርብ ከማድረጉ ባሻገር አረሙ ከአቅሙ በላይ ሆኖበት የልፋቱን ፍሬ ሳያገኝ መና ያስቀረዋል። ልፋቱም ከንቱ ይሆናል።
በዚህ የመንደርደሪያ ሃሳብ ዛሬ ለማንሳት የወደድሁት ጉዳይ በተለይ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ለውጡ ከመጣ በኋላ “ለምን የበላይነቴ ተነካ? እንዴት ከፈላጭ ቆራጭነቴ ተነስቼ እኩል እዳኛለሁ?” በሚል አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ህዝብን ሲያሸብር፣ ሲያፈናቅልና በየሳምንቱ የሞት ድግስ እየደገሰ አገሪቱን አኬል ዳማ አድርጓል። እያደረገም ይገኛል። እንዲሁም ከውጭ የአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተናቦ አገር ለማፍረስ ሲሰራም ቆይቷል። እየሠራም ይገኛል።
ይህ የሽብር ቡድን ይባስ ብሎ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ከጀርባው በመውጋት የአገሪቱን ሉኣላዊነት አደጋ ላይ በመጣል የአገር ክደት ወንጀል መፈጸሙ ዓለም የሚያውቀው ፀሐይ የሞቀው ሃቅ ነው። ጁንታው ይህንን ጥቃት መፈጸሙን እራሱ በአንደበቱ “መብረቃዊ ጥቃት” ሲል ገልጿታል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን የሕወሓት ቡድንን መንግስት አደብ ለማስገዛት በትግራይ ክልል ሕግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ይታወቃል። ይህንንም ዘመቻ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ አቅም ያለው ጦርሜዳ ተሰልፎ በመዋጋት አቅም የሌለው የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ለወገን ጦር ደጀን ሆኗል። ደግፏል። በዚህ ዘመቻም ብዙዎች ለአገራቸው ተሰውተዋል።
መንግስት በተወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ “የሽብር ቡድኑ ለአገሪቱ እንዲሁም ለህዝብ ስጋት በማይሆን ደረጃ ተመትቶ ተንኮታኩቷል። ሕወሓት ታሪክ ሆኗል” የሚል ዜና ሲናገር ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋና ኢትዮጵያን እንዳይኑ ብሌን የሚሳሳላት ህዝብ ጮቤ እረግጦ ነበር። “ታሪክ ሆኗል” የተባለው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከተሰገሰገበት ዋሻና የቀበሮ ጉድጓድ ወጥቶ በአፋርና በአማራ ክልል በፈፀመው ወረራ ያደረሰውን ግፍና መከራ መናገር የጉዳቱ ሰለባ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በቁስላቸው ላይ ጋሬጣ እንደመስደድ ይሆንብኛል።
የሽብር ቡድኑ 700 ኪሎ ሜትር አቆራርጦ የአራት ኪሎ ቤተመንግስትን ለመቆጣጠር 200 ኪሎ ሜትር የማይሞላ መንገድ ቀርቶት ጣርማበር ደርሶ እልህ አስጨራሽ ትግል ተደርጎ ከባድ መሰዋዕትነት ተከፍሎ ነው የተመለሰው። በዚህም ህዝብ እንደ ህዝብ ጉዳት ደርሶበታል። በአንጻሩ አገረ መንግስቱም ቢሆን ከፍ ባለ የመፍረስ ስጋት ውስጥ ወድቆ እንደነበር የሚታወስ ነው።
አሁንም ይህ የሽብር ቡድን ዳግም በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ጦርነት ለመክፈትና ወረራ ለመፈጸም ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሽብር ቡድኑ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ግዳን ወረዳ ወትወት፣ ጥራሪ በሚባሉ የገጠር መንደር እንዲሁም በራያ ቆቦ ወረዳ በሚገኙ የክልሉ አዋሳኝ ቀበሌዎች ሰርጎ በመግባት የንጹሃንን ሃብትና ንብረት ከመዝረፉ ባለፈ ወጣቶችን አፍኖ በመውሰድ “መከላከያ የት፣ የት ይገኛል? ምን ያህል ቁጥር አለው? ፋኖ የት ይሰለጥናል?” በሚል መረጃ ለማጣራት ንጹሃንን እያሰቃየ ይገኛል።
ከዚህ ባሻገር በዋግ ህምራ ዞን በጁንታው ከቀያቸው ተፈናቅለው በሰቆጣ ከተማ ከከተማዋ ህዝብ ቁጥር በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ። በጠለምት፣ አደርቃይ በቁጥጥር ስር ያደረጋቸው የአማራ ክልል ቀበሌዎችም መኖራቸው ይታወቃል። ቡድኑ ከትናንት ጥፋቱ መማር የማይችል መሆኑ ከቀደመው ታሪኩ የሚቀዳ እውነት ከመሆኑ አንጻር ስለ ነገ በልበ ሙሉነት መናገር አይቻልም።
አሸባሪው በድኑ በትግራይ ሆነ ከትግራይ ውጪ አሁንም እያካሄዳቸው ባሉ የሽብር ተግባራት ንጹሃን ዜጎች ለብዙ ስቃይና መከራዎች ተጋላጭ ከመሆናቸው ባለፈ ህይወታቸውን እያጡ ነው። መንግስት ለዚህ አሸባሪ ቡድን ለሽብር ተግባሩ ተጨማሪ እድል ሊሰጠው አይገባም። ይህንን የሽብር ቡድን አደብ ሊያስገዛው ይገባል።
የቡድኑ ፍጥረታዊ ስብእናው ለሰላም ምንም አይነት እድል መስጠት የሚችል ባይሆንም ይሰጣል ቦሎ ከታመነም ድርድሩ ህዝብ ተሳተፊ የሚሆንበትና ዘላቂ መፍትሄ መምጣት የሚያስችል መሆን አለበት። ለቡድኑ ጊዜ መግዣ መሆን የለበትም።
መንግስት ዜጎችን ከየትኛውም አይነት ህገወጥ ተግባር ለመታደግ ካለበት ኃላፊነት አንጻርም የትግራይ ህዝብን ከሽብር ቡድኑ የግዞት ቀንበር የማላቀቅ ግዴታ አለበት። የትግራይ ህዝብም እንደ ህዝብ ይህንን ቀንበር ከጫንቃው ላይ መጣል የሚያስችል ቁርጠኝነት መፍጠር ይጠበቅበታል።
ሌላው በአገሪቱ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ለሚፈሰው ደም አጋፋሪ ተደርጎ የተወሰደው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ሸኔ ነው። ለውጡን ተከትሎ በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ ብሎ ወደ አገር ቤት የገባው ይህ የሽብር ቡድን በኦሮሚያ ክልል የንጹሃንን እያፈሰሰ ይገኛል።
በክልሉ በተለያዩ ቀናት ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ዜጎች በቡድኑ ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ለሞት ተዳርገዋል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተጠልፈው የገቡበት ደብዛ ጠፍቷል። በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ሃብት ንብረታቸው ተዘርፏል፤ ወድሟል።
መንግስትም በሽብር ቡድን ላይ የማያዳግም እርምጃ ወስጃለሁ ቢልም ቡድኑ በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚሰነዝረው የክፋት ሰይፍ አልቆመም። ጊዜና ቦታ ለይቶ በሚያደርሳቸው ጥቃቶች ዜጎች ከፍ ያለ ዋጋ እየከፈሉ ነው። ይባስ ብሎ ከሰሞኑ ከጋምቤላ ነጻነት ግንባር ጋር በመሆን የጋምቤላ ከተማን ለመቆጣጠር ጦርነት ከፍቶ ብዙ ንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱ እየተነገረ ነው።
አገሪቱን የሽብርና የአሸባሪዎች ደሴት ለማድረግ እየተናበቡ የሚንቀሳቀሱትን እነዚህን አሸባሪ ቡድኖች ሆነ፤ ከነሱ ጋር በነጻ አውጪ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሀይሎች ላይ መንግስት የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ህዝቡን ከሰቀቀን፣ አገሪቱን ከአደጋ የመታደግ ኃላፊነት አለበት፤ ይህንን ኃላፊነት በስኬት ለመወጣት የጀመረውን የሕግ የማስከበር እና አገርን የመታደግ ዘመቻ በተጠናከረ መንገድ ሊቀጥልበት ይገባል፤ መላው ህዝብም ከመንግስት ጎን በመቆም ለሀገር ያለውን ፍቅርና ታማኝነት በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል። ከአገር ሊያስበልጠው የሚችለው ነገር የለም!።
ይህንን ማድረግ ካልተቻለ መነሻዬ ላይ ለማሳየት እንደ ሞከርኩት አንድ አርሶ አደር ማሳውን አደፋርሶና ሰርዶውን ከስሩ መንግሎ አጎልጉሎ ካላረሰ ማሳው ዳዋ እንደሚወርሰው። በአረም እንደሚዋጥ መጪው የተስፋ ዘመናችን ከፍ ባለ የአረም ስጋት ውስጥ መውደቁ እንደማይቀር መገመት አይከብድም። ፍሬ አልባ ሊያደርገን እንደሚችል መሳብ አላዋቂነት አይሆንም። አበቃሁ። ቸር እንሰንብት!
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም