ችግር ባለበት አገር ሁሉ መፍትሄ ማፈላለግ ምርጫ ሳይሆን ግዴታና የህልውና ጉዳይ ነው። ችግር ካለ መፍትሄ መምጣት አለበት። ችግር ካለና ለችግሩ መፍትሄን ማምጣት ካልተቻለ ያለው እድል በዛው በችግር ውስጥ መከራን ሲዝቁ፤ አበሳን ሲገፉ መኖር ነው።
ከሕይወትም ይሁን ከዘመናዊው ትምህርት እንደ ተማርነው መፍትሄ ደግሞ ከየትም ሳይሆን ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ተቋማት ድረስ ከዘለቀ አስተሳሰብና ድርጊት ወይም እንቅስቃሴ የሚመጣ የተመረጠ ሃሳብ ነው። ለዚህ ደግሞ ማስረጃችን ዛሬ እዚህ የምናወራለትን አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።
ችግሮች ከሚስተዋሉባቸው በርካታ አገሮች አገራችን አንዷና ምናልባትም ቀዳሚዋ ትሁን እንጂ በችግሯ ልክ መፍትሄዎች ሲመነጩ ማየትም ሆነ መስማት የተለመደ አይደለም። በመሆኑም በችግር ላይ ችግር፤ በግጭት ላይ ግጭት፤ ከጦርነት ወደ ጦርነት፤ ከአለመግባባት ወደ ባሰ አለመግባባት … ስንሸጋገር እንኖር ዘንድ የተገደድን እስኪመስል ድረስ ከአዙሪቱ መውጣት ተስኖን እነሆ ዘመናት እየጣሉን እየገሰገሱ፤ እኛም ዝም ብለን እድሜ ብቻ እየቆጠርን እንገኛለን።
ብዙ ጊዜ የተለመደና በተደጋጋሚም ሲገለፅ የሚሰማ የቆየ አትዮጵያዊ አባባል አለ፤ “ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ” የሚል። እርግጥ ነው በጣም ከመለመዱና አገር በቀል ከመሆኑ አኳያ የሰለቸና፤ ምናልባትም ትርጓሜው በዛው በ “ሰርዶ” ና በ”በሬ” ተወስኖ ቀርቶ ሊሆን ይችላል፤ ብዙም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ … መልእክት ያለው አልመሰለን ሊሆንም ይችላል። በማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሆኑ ጉዳዮች በቀጥታ ተፅእኖ ያለውና ተፅእኖ ፈጣሪም አባባል ነው።
ጉዳዩ ከእኛም አልፎ አፍሪካን የሚያካትት፤ “እኛ ነን የምናውቅላችሁ” የሚሉትና አደጉ የሚባሉትንም አገራት እጅጉን የሚያስፈራ ሲሆን፤ ለዚህም “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለው ከበቂ በላይ ማሳያ ነው። ይህ ማለት ደግሞ፣ በሌላ አባባል “ሀገርኛ” ወይም “አገር በቀል” የሚለው ነውና ወደ’ዛው፣ “የብርሃን ልጆች የሕፃናትና የአረጋውያን መንደር” በሚል ወደ’ሚታወቀው ግብረ ሰናይ ድርጅት እንሂድ።
“የብርሃን ልጆች የሕጻናት እና የአረጋውያን መንደር” በጎዳና እና በቤተ ክርስቲያን አጸድ የሚኖሩ ሕጻናት እና አረጋውያንን ለመርዳት ከሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በሰርተፍኬት ቁጥር 4972 ተመዝግቦ ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ሀገር በቀል፤ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲሆን፤ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጁም (ከሌሎች ሁለት ግለሰቦች ጋር) መምህር ያሬድ ብርሃኑ ናቸው።
ይህ ግብረ ሰናይ ድርጅት የተመሰረተው ሀምሌ ወር 2013 ዓ.ም ሲሆን በዚህ ወቅት ሕጋዊነትን አግኝቶ በተፈቀደና በተሰጠ ሰርተፊኬት ይቋቋም እንጂ ከዛ በፊትም ወደ ስራ ገብቶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።
መምህር ያሬድ እንደሚሉት የድርጅቱ አቢይ ዓላማ የተቸገሩና ረዳት የሌላቸውን ወገኖች መድረስ ሲሆን፤ እስካሁን ድረስ በተመላላሽነት በተለለያዩ ጊዜያት ከድርጅቱ ድጋፍን ሲያገኙ የነበሩ አሉ ፤ እነዚህ ወገኖች በተለያዩ ጊዜያትም ቁጥራቸው ይለያያል። ያም ሆኖ ለምሳሌ በአንድ ዙር ብቻ ከ400 በላይ ሰዎች ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። አሁንም እየተደገፉ ያሉ በርካቶች ናቸው።
የ “የብርሃን ልጆች የሕፃናትና የአረጋውያን መንደር” ዋና ስራ አስኪያጅ እኔ ልሁን እንጂ መንደሩ የሚመራው ራሱን በቻለ ቦርድ ነው የሚሉት መምህር
ያሬድ ግብረ ሰናይ ድርጅቱ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችንም ያዘጋጃል ፤ “ለበጎ ማዕድ የድጋፍ መርሐ ግብር ያዘጋጀናቸውን ኩፖኖች በመግዛትም ሆነ በመሸጥ እንድታግዙ አቅሙ ያላችሁ አንድ ሕጻን ወይም አረጋዊ ድጋፍ በማድረግም እንድትሳተፉ እንጋብዛለን!!!” በሚል መርሀ ግብር ሁሉም የቻለውን እንዲያደርግልን የቻልነውን ጥረት ሁሉ ስናደርግ ቆይተናል፤ እያደረግንም ነው ብለዋል።
ድርጅቱ ከአገር ውስጥም ከውጭም ከፍተኛ ድጋፍ እያገኘ ስለመሆኑ የሚናገሩት መምህር ያሬድ በጎ ፈቃደኛ አምባሳደሮችን በመመልመል እንደሚሰራ ይናገራሉ። ለምሳሌ በዘንድሮው ዓመት የለዛ አዋርድ ላይ አሸናፊ የሆኑት አርቲስት ሚሊዮን ብርሃኔ እና አርቲስት ድርበወርቅ ሰይፉ የብርሃን ልጆች በጎ ፈቃደኛ አምባሳደሮች መሆናቸውንም ይናገራሉ።
“የብርሃን ልጆች የሕፃናትና የአረጋውያን መንደር” ሲቋቋም ከኪሳቸው 10ሺህ ብር ወጪ በማድረግ ስራውን ማስጀመራቸውን የሚናገሩት መምህር ያሬድ ረድኤት ያለውና ቤተልሔም ፀጋዬ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ይገልጻሉ።
አሁን መንደሩ የሚንቀሳቀስበት በጀት ምንጭ የአባላት መዋጮ በተለያዩ አገራት ሆነው የገንዘብና ፤ የአይነት ድጋፎችን በሚያደርጉ ዳጋግ ኢትዮጵያውያን መልካም ፍቃድ መሆኑን ይናገራሉ። ድርጅቱ የራሱ የሆነ ምንም አይነት ንብረት የሌለውና ሕንፃ ተከራይቶ ስራውን እንደሚሰራ የሚናገሩት መስራቹ በአብዛኛው አገልግሎቱም መንፋሳዊ በመሆኑ ግንኙነቱ ከቤተክርስቲያን ጋር ነው። አንዳንድ እንዲሟሉ የሚፈለጉ ነገሮችንም የሚጠየቀው ከቤተክርስቲያኗ መሆኑን ያብራራሉ።
ወደ ፊት መንግሥት ቦታ ሰጥቶን የራሳችን የሆነ ህንፃ እንገነባለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን የሚሉት ስራ እስኪያጁ በእርግጥ ጽሕፈት ቤትን በተመለከተ ወረዳው/ክፍለ ከተማውም ተስፋ ሰጥቶናል፤ ይሳካል ብለንም እንጠብቃለን ብለዋል።
የወደፊት ዓላማችን አንድ ግዙፍ “የብርሃን ልጆች የህፃናትና የአረጋውያን መንደር” ገንብተን አገልግሎታችንን ማስፋትና ድጋፍ ለሚፈልጉ ሕፃናትና አረጋውያን ሁሉ መድረስ ነው። ለዚህ ደግሞ ከቅን አሳቢ ግለሰቦች ጀምሮ የመንግሥትና ሌሎች ተቋማት ድጋፍና ትብብር ያስፈልጋልም ይላሉ ።
የብርሃን ልጆች መስራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ያሬድ ብርሃኑ ባለፈው ቅዳሜ ሰኔ 4 ቀን 2014 ዓ.ም የተጀመረውን ድርጅቱን የማጠናከርና የመደገፍ ስራ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በቀና መንፈስ ተመለክተውት እገዛቸውን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
”የብርሃን ልጆች የሕፃናትና የአረጋውያን መንደር” በርካታ አሳዛኝ ታሪክ ያላቸው ጧሪ ጠያቂ የሌላቸው አረጋውያን መማር እየፈለጉ ፊደል የናፈቃቸው ሕጻናትን ሁሉ ታሳቢ አድርጎ እነሱም ጋር ለመድረስ በርትቶ እየሰራ ያለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው። ይህንን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው ደግሞ በበጎ ተግባር የሚያምኑ ቅን ልቦችና የበጎ ተግባር ደጋፊዎች ሁሉ ከጎናችን ሲሆኑ ነው። የተቋማት፣ ባለ ሀብቶች፣ ግለሰቦች፤ እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት ድጋፍ ሁሌም ያስፈልገናል የሚሉት መምህር ያሬድ ይህ እውን ከሆነ፣ ለበርካታ ድጋፍና እርዳታ ፈላጊዎች መድረስ ይችላል ።
“የብርሃን ልጆች የሕፃናትና የአረጋውያን መንደር” በሰዎች ተቀባይነት ከማግኘቱም በላይ አስፈላጊውን እውቅና፣ ድጋፍና ትብብር እያገኘ ነው፤ ለዚህ ማሳያው ደግሞ አርቲስት ሚሊዮን ብርሃኔ፣ ለሁለት ጧሪ እና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋውያን በጎ ማዕድ ድጋፍ የሚውል የ25ሺ ብር ስጦታ፤ እንዲሁም፣ “የድርጅት 1ኛ ደረጃ ቸር አባል በመሆን በዓመት 50ሺ ብር ለድርጅታችን ለመርዳት የአባይ ባንክ አራዳ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ተገኝተው ቃል ገብተዋል” ም ከዚሁ ጋር አብሮ የሚታይ ነው ይላሉ።
“የብርሃን ልጆች የህጻናት እና የአረጋውያን መንደር አባል ይስሀቅ ልሳነ ክርስቶስ በበጎ ማዕድ የድጋፍ መርሐ ግብር አማካይነት ለአንድ ህጻን ልጅ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቶ መሄዱን የተናገሩት ስራ አስኪያጁ ይህ መሰሉ ጥረት ወደሌሎችም ተጋብቶ እንዲጠናከር የተለመደ ጥሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡
ከላይ በአጭሩ ያወራንለት አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት በርካታ ስራዎችን እየሰራ ከመሆኑ አንጻር የራሳችንን ችግር በራሳችን መንገድ ለመወጣት የምናደርገው ጥረትና ተስፋ ሰጪ እንደሆነ የሚያመላክት ነው።
አገራችን ከማንኛውም አይነት ጥገኝነት እንድትላቀቅ ካስፈለገ የአገር በቀል ተቋሟት በአይነትም፣ በጥራትም፣ በብዛትም ሊፈልቁ ይገባል ፤ ከዚህ አኳያ፣ “የብርሃን ልጆች የህጻናት እና የአረጋውያን መንደር” አስፈላጊው ድጋፍና ማበረታቻ ከተደረገለት፤ ቅን ልቦች ከጎኑ ከሆኑ … የነገው ትልቁ የአገርን ችግር ፈቺ ተቋም የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም ። በመሆኑም ማንኛቸውም ዓላማውን የሚደግፉ ግለሰብ፣ ቡድን፣ ተቋማት፣ ባለ ሀብት … ሁሉ፤ ከጎኑ ሊቆሙና በጽኑ መሰረት ላይ ሊያቆሙት፤ ተጠቃሚዎችምንም አለሁ ሊሏቸው ይገባል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 /2014