ኢትዮጵያን እናልብሳት መርሀ ግብር ባለፉት ሶስት አመታት ውስጥ ያላማቋረጥ ሲተገበር የነበረ የአረንጓዴ ልማት አሻራ ፕሮግራም ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሪነት ኢትዮጵያ አገራችን ካከናወነቻቸው በጎ ተግባራት ውስጥ ቀዳሚ ሆኖ የሚጠቀስም ነው። ዘንድሮም የክረምቱን መግባት ተከትሎ ለአራተኛ ጊዜ አገራችንን አረንጓዴ ልናለብሳት ዝግጅታችንን አጠናቀናል።
የዛሬ አመት ኢትዮጵያን እናልብሳት በሚል መርሀ ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ በተያዘ እቅድ ስድስት ቢሊዮን የሚደርሱ ችግኞችን መትከላችን ይታወሳል። እነዚያ ችግኞች አድገው ለመጪው ትውልድ የህልውና ዋስትና እንደሚሆኑ በእጅጉ ይታመናል። እምነታችን በጎ አሻራችንን በአገር ላይ ማሳረፍ ነውና ዘንድሮም እንደ አምናው ሁሉ ለነገ ህይወታችን ጥላ ከለላ የሚሆኑ ችግኞችን ለመትከል የክረምቱን መምጣት እየጠበቅን ነው።
በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም የተደቀነብንን የአየር መዛባትም ሆነ የተፈጥሮ አደጋ ለመከላከል በአዲስ አበባ ጨምሮ በሁሉም የክልል ከተሞች እስከ ወረዳ ድረስ በሚደርስ የተቀናጀ ስራ በመተግበር ላይ ይገኛል። በጠቅላይ ሚኒስትራችን ፊታውራሪነት፣ በእኛ በዜጎቿ መልካም ፍቃድ ኢትዮጵያን በአረንጓዴ ሸማ ለመኳል ዶማና አካፋችንን ይዘን እንሆ ክረምት ሆይ ቶሎ ና እያልን ነው።
ባሳለፍነው 2013 ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት የተናገሩት ንግግር የመርሀ ግብሩን አላማ በግልጽ ያሳየ እንደነበረ ይታወሳል። እንዲህ ነበር ያሉት ‹የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩ የአካባቢ ብክለትንና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን አገራዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመቅረፍና ለመመከት የወጣ የአራት አመት እቅድ አካል በመሆኑ ሁሉም ማህበረሰብ ለጋራ ጥቅም ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል›። ይህ ማለት መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ የሰጠው ቦታ ምን ያክል እንደሆነ የሚያሳይ ነው። መንግስት ለጉዳዩ ከሰጠው ትኩረት አንጻር በችግኝ ተከላው ገና ረጅም ርቀትን እንደሚጓዝ የታመነ ነው። ከአገር አልፎ ሌሎች የውጪ አገራትንም በእቅዱ ውስጥ አስገብቶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ሀቅ ነው።
የጎረቤት አገራት ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንደሆነ በመቀበል የችግኝ ተከላው መርሀ ግብር ከአገር አልፎ እስከ ጎረቤት አገራት ድረስ የዘለቀ እንደነበር አይዘነጋም። የዛሬ አመት እንደ አገር ከተያዘው ስድስት ቢሊዮን ችግኝ በተጨማሪም አንድ ቢሊዮን የሚሆን ችግኝ ለጎረቤት አገራት የሰጠን መሆኑ ሁላችንም የምናውቀው ነው። በመርሀ ግብሩ መሰረትም ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ኬንያን ተጠቃሚ ያደረገ ሰፊ ፕሮጀክት ነበር።
ዘንድሮ ካምናው ስህተቶቻችን ተምረን የተሻለ አገራዊ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም እንደሚኖረን የታመነ ነው። መጪውን ጊዜ እስኪ አስቡት..አገራችን በአረንጓዴ አጊጣ፣ የአየር ንብረት ለውጥንና የሚያስከትላቸውን ችግሮች ተቋቁማ አዲስ የህይወት ምዕራፍ ስትገልጥ። መጪውን ጊዜ አገራችን ከበረሀማነት ስጋት ተላቃ፣ ከተፈጥሮ አደጋ ርቃ፣ ለትውልዱ ምቹ መኖሪያ ስትሆን።
ችግኝ ተከላን በተመለከተ አብዛኛውን ጊዜ የምንታማበት አንድ ነገር አለ እርሱም ለመትከል የተነሳሳነውን ያክል ለእንክብካቤ አለመነሳታችን ነው። ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ተክለን ከእንክብካቤና ከክትትል ማነስ ብዙ ችግኞች እንደደረቁብን እንሰማለን። ይህ የአሁኑ ህዝባዊ መነሳሳት ግን ከዚህ በፊት እንደነበረው አይሆንም። ከትላንት ተምረን፣ ከአምና አስተውለን ለአላማችን ስኬታማነት እንክብካቤውም ላይ ዋጋ መክፈል አለብን።
ሁሉም ተካይ የተከለውን ችግኝ እንዲንከባከብና እስኪጸድቅ ድረስ ኃላፊነቱን ወስዶ እንዲከታተል በሚያስችል መልኩ የተገነባ ህዝባዊ እንቅስቃሴ በመሆኑ ብዙም ስጋት አለው ብዬ አላስብም። እርግጥ ነው የተከልነውን ያክል ጸድቆልን አያውቅም። የአሁኑ መነሳሳት ግን ከነበረው ሁሉ ይለያል። መንግስት ከእቅዶቹ አንዱ በማድረግ ከፍ ያለ ገንዘብ መድቦ የሚያንቀሳቀሰውም ለዚሁ ነው።
ያለፉትን ሶስት አመታት ብናይ እንኳን በአገር አቀፍ ደረጃ ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ አብዛኞቹ የጸደቁ ሲሆን ይሄም ማለት በመቶኛ ሲሰላ 87 ከመቶ የሚሆኑት ችግኞች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳሉ በመንግስት ደረጃ የተገለጸበት ሁኔታ ነው ያለው። የምንለፋው የምንደክመው ለለውጥ ነውና ወደ ፊት መቀጠሉ አዋጭነት አለው ማለት ነው።
ከፍ ብዬ ለመግለጥ እንደሞከርኩት የአየር መዛባት የአለም ወቅታዊ ችግር ነው። ትላንትም ሆነ ዛሬ አለም ከተቸገረችባቸውና መፍትሄ ካጣችባቸው ጉዳዮቿ ውስጥ ዋነኛው ይሄው የአየር ንብረት ለውጥ ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ደግሞ በአብዛኛው የዚህ ገፈት ቀማሽ ከሆኑ አገራት መካከል ድሀ አገራት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። ይህ ማለት አገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ መሰል ታዳጊ አገራት የገፈቱ ግንባር ቀደም ተጠቂዎች ናቸው ማለት ነው።
ከአየር ንብረቱ ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ በርካታ አገራዊ ችግሮችም አሉ። የዝናብ እጥረትን በማስከተል ድርቅና መሰል ኢኮኖሚያዊ እንቅፋቶችን በመፍጠር በአገርና ህዝብ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም። ተለምዶአዊ የአካባቢ ምህዳርን በመዛባት በሰው ልጅ ላይ እና ህይወት ባላቸው ማናቸውም ፍጡራን ላይ መጥፎ አሻራውን በማሳረፍ ህልውናን አደጋ ላይ ይከታል።
እንደዚህ አይነት ተጨማሪ እንከኖች ታክለውብን ይቅርና ወትሮም ኑሯችን በብዙ ተግዳሮቶች የተሞላ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ተሰምቶት ከመንግስት ጎን በመቆም በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ላይ የበኩላችንን በመወጣት የአራት አመቱን እቅድ ማሳካት ይኖርብናል። እኛ በህብረት ከተነሳን ጥሩ ነገር እናውቅበታለን። አሁንም በህብረት መነሳት ነው ያለብን። ክረምቱ ሳያልፈን ወቅቱም ሳይሄድብን የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ነጋችንን ብሩህ ማድረግ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል ።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ መልበስ የእኔና የእናንተ የነገ ዋስትና ነው። ዛሬ ላይ የምንተክላትና የምንከባከባት አንድ ችግኝ ነገ ላይ ለኛና ለልጆቻችን የህይወት ዋስትና ሆና መምጣቷ የማይቀር ነው። ስለዚህም በተባበረ ክንድ ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናልብስ።
ከዚህ ጋር አያይዤ አንድ ያስገረመኝን ነገር ላውጋችሁ። ከሰሞኑ አምስት ኪሎ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም ጎራ ብዬ ነበር። ግድግዳው ላይ ሌላ አለም፣ ሌላ ሰማይና ምድር የሚመስል ፍጹም የሚደንቅ አረንጓዴ የለበሰ አንድ ፎቶ ግራፍ ግድግዳው ላይ ተሰቅሎ ተመለከትኩ። ቀርቤ አየሁት..ከስሩ ያለውን ጽሁፍ ሳነበው ለካ ከሚሊዮን አመት በፊት የነበረችው የኛ ምድር ፎቶ ግራፍ ነበር።
ከጎኑ ደግሞ በበርሀ የተዋጠችው አሁናዊ የምድራችን ገጽታ አለ። የሁለቱን ልዩነት በአግራሞት ነበር ያየሁት። በነገራችን ላይ አለም ትጠፋለች ተብሎ በሳይንሱ ከሚተነበይባቸው እውነታዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የአየር ንብረት ለውጥ ነው። ይህ ማለት የአለም ፍጻሜ የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚመጣ ነው ማለት ነው። ለመጪው ትውልድ የተራቆተችን አገር ማስረከብ የለብንም። ተባብረን ኢትዮጵያን ማልበስ አለብን። አረንጓዴ መሬት፣ አረንጓዴ ምድር ታስፈልገናለች።
የአየር ንብረት ለውጥ ሁሉንም ማህበረሰብ የሚያጠቃ የአለም በሽታ ነው። ዋናውና ብቸኛው መከላከያ መንገድ ዛፍ መትከል፣ ችግኞችን መንከባከብ ብቻ ነው። መንግስት በያዘው የአረንጓዴ ልማት መርሀ ግብር ላይ በመሳተፍ ኢትዮጵያንና ምድሯን ከበርሀማነት መታደግ እንችላለን። በአየር ንብረት ለውጥ አማካኝነት የሚመጡ ጉዳቶችን ለመከላከል ከድሀ አገራት ይልቅ የበለጸጉ አገራት የተሻለ አቅም ቢኖራቸውም ሙሉ በሙሉ ከችግሮች መላቀቅ ግን አይችሉም።
በኢኮኖሚያቸው ልክ እንደዚህ አይነት ችግሮችን ለመመከት የሚያስችል አቅም ያዳበሩ ቢሆንም የጉዳቱ ሰለባ ከመሆን የሚያድናቸው አንዳች ሀይል የለም። ምክንያቱም የአየር ንብረት ለውጥ በጋራ የምንከላከለው የአለም ሁሉ የጋራ ችግር ስለሆነ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ችግሩ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ታኮ የሚመጣ ነው። ለዚህም ነው ባለጸጋ አገራት በለኮሱት ድሀ አገራት የሚጨሱት።
በሀብታም አገራት የስልጣኔ ገፈት ድሀ አገራት አሳራቸውን የሚያዩት። የአየር ንብረት ለውጥ የሁሉም አገራት የጋራ ችግር ቢሆንም በድሀ አገራት ላይ በይበልጥ ያይላል። የአየር ንብረት ለውጥ ከትላንት እስከዛሬ የአለም የቤት ስራ ሆኖ ያለ ትልቅ ጉዳይ ነው። እልባትና መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ግን አብዛኛው አገር ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው።
በተለይ በኢኮኖሚያቸው አደጉ የሚባሉ አገራት ለችግሩ መፈጠር የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ከፊት የሚሰለፉ ናቸው። ከትላንት እስከዛሬ ለአለም ሰላም ማጣት ተጠያቂዎቹ እነርሱ ናቸው። አፍሪካና ህዝቦቿ ምንም በማያውቁት ባለጸጎቹ በፈጠሩት ችግር ስቃይ ላይ ይገኛሉ። በአለም ዙሪያ በተለያየ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ የበለጸጉ አገራት ለድሀ አገራት ድጎማ ማድረግ አለባቸው የሚሉ በርካታ መከራከሪያ ሀሳቦች ሲነሱ ቆይተዋል። አሁንም ድረስ እኚህ ሀሳቦች መቋጫ አላገኙም።
” ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ መንግስታችንም ይሄን ተገንዝቦ እያደረገ ያለው የቅድመ መከላከል ተግባር እጅጉን የሚደነቅ እንደሆነ ሳልጠቅስ አላልፍም። ልክ እንደ አገራችን ኢትዮጵያ ሁሉም የአለም አገራት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የበኩሉን ማድረግ ቢችል ምድራችን በዚህ ልክ ሲኦል አትሆንብንም ነበር እላለው። የሆነው ሆኖ ግን መንግስታችንን ሳላደንቅ አላልፍም። በእያንዳንዱ ኩነት ላይ ህዝብ ችግኝ እንዲተክል በማድረግ አገራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል። አለም በሁለት እጁ ምርጫ ሲመርጥ እኛ ግን በአንድ እጃችን ችግኝ እየተከልን በአንድ እጃችን ስንመርጥ ነበር።
ችግኝ በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ጎን ለጎን መንግስት ማህበረሰቡ ለምግብ የሚሆኑ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችንም እንዲተክልና ራሱን በምግብ እንዲችል እያደረገ ያለውም ጥረት የሚደነቅ ነው። አሁን ላይ ከችግኝ ተከላው እኩል ሁሉም በየደጁና በየጓሮው በከተማ ግብርና ራሱን ከወጪ ተከላክሎ ከጓሮው ቀጥፎ የሚበላበት ሁኔታ እየተፈጠረ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።
አዲስ አበባን ጨምሮ በርካቶች በዚህ የመንግስት መርሀ ግብር ውስጥ በመሳተፍ በጓሮአቸውና በግቢያቸው ውስጥ ለምግብ የሚሆኑ አትክልቶችን በመትከል ራሳቸውን በመደጎም ላይ እንደሆኑ በተለያየ ሚዲያ ላይ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ አድምጫለው። በቀላል መንገድ፣ በትንሽ ቦታ ላይ ራስን ከወጪ መታደግ ዘመናዊነት ነው። ይሄ ተግባር በስፋት ተሰርቶበት ማህበረሰቡ ከጓሮው ቀጥፎ መብላትን ልምድ እንዲያደርግና ድህነትን አሸንፎ እንዲወጣ መንግስት በያዘው በጎ መንገድ መቀጠል አለበት። ” በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” ማለት ይላሉ ይሄ ነው። የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ችግኝ እየተከሉ በዛውም ለህይወት አስፈላጊ የሆኑ ፍራፍሬና አትክልቶችን በመትከል ራስን በምግብ መቻል።
ይህ ተግባር መንግስትን እንደ መንግስት ሲያስ መሰግነው ማህበረሰቡን ደግሞ ከመጠበቅና ከልመና ወጥቶ በህይወት ለመኖር የተለያዩ አማራጮችን እንዲፈልግ መንገድ ይጠቁማል። በዚህ ኑሮ በተወደደበት ወቅት፣ በዚህ በንክኪ ብዙ በሽታዎች በሚተላለፉበት ሰሞን የራስን ምግብ ከጓሮ ቀጥፎ እንደመብላት ስልጣኔ አለ ብዬ አላምንም።
ህይወት በብዙ አማራጮች የተከበበች ናት። ከመጠበቅ ወጥተን ለመኖር የሚያስችለንን ቀላልና አዋጪ ዘዴ ማየት ይኖርብናል። ገንዘብ አውጥተን መርካቶና አትክልት ተራ ድረስ ሄደን ጊዜና ጉልበታችንን ከምናባክን በአንድ እጃችን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ችግኝ እየተከልን በአንዱ ደግሞ ርሀባችንን የምናስታግስበትን አትክልትና ፍራፍሬ መትከልን ባህል ማድረግ ይኖርብናል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 /2014