ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከትናንት በስቲያ በተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት የምክር ቤት አባላቱ በወቅታዊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በዛሬም እትማችን “ለውጡና አገራዊ ሪፎርሙ በሀዲዱ እየሄደ ነው ወይስ ሀዲዱን ስቶ ከመስመር ወጥቷል? ወይም አንዳንዶች እንደሚገልፁት ከሽፏል ወይ?” የሚለውን ጨምሮ በመንገድ ግንባታዎች ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄ የሰጡትን ሰፊና ዝርዝር ምላሽ ይዘን ቀርበናል፦
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ምላሽ፦
በመጀመሪያ የተከበረው ምክር ቤት ከግምት ሊያስገባና የእይታ መነጽሩን ሊያስተካክል የሚገባው ባለፉት አራት ዓመታት ቀደም ሲል ከነበረው ጊዜ በተለየ ሁኔታ የገጠሙንን ከበድ ከበድ ያሉ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ፈተናዎች መልሶ ማስታወስ ያስፈልጋል:: እነዚህን ፈተናዎች በደንብ ካልተረዳን አውዱ ይበላሻል:: እንዲህ ብለው ነበር፤ እንዲህ አልሆነም፤ ለማለት እነዚያን ሁኔታዎች በትክክል መገንዘብ ጠቃሚ ይመስለኛል:: ለምሳሌ ከሪፎርም በፊት ኮሮና አልነበረም:: ኮሮና እንደሚመጣ አጋጣሚ ሆኖ ጠንቋይ ስለማንቀልብና እኛም ስለማናውቅ ምን ሊመጣ እንደሚችል መገመት እኛም ዓለምም ልናውቅ አንችልም::
ኮሮና የሚያስከትላቸው ኢኮኖሚክ እና ሌሎች አስጊ ሁኔታዎችን እንዴት እንደምንወጣ ተለምዷዊ በሆነ መንገድ እቅዳችንን እንከልሳለን እንጂ ቀድመን የምናውቀው ጉዳይ አልነበረም:: አንበጣ፣ ጎርፍና ድርቅ ነበር:: እነዚህ የተፈጥሮ ተግዳሮቶች እቅዶቻችንን ለመከለስ፤ የአሰራር ስርዓታችንን ለመፈተሽ እንዲሁም ያቀድናቸውን ነገሮች ለማሳካት የራሳቸው የሆነ እንቅፋት ይሆናሉ:: ከእነዚህ በተጨማሪም ቀደም ሲል ያልነበሩ ሰው ሰራሽ ችግሮች አጋጥመዋል:: አንደኛ ውጊያ ነው:: በአገር ውስጥ የገጠመን ውጊያ እጅግ ከፍተኛ የሰብዓዊ እና የኢኮኖሚ ቀውስ ያስከተለ ነው:: አገር ለማፍረስ ታቅዶ የተሰራ፤ የተጀመረ ውጊያ ነው:: ለማክሸፍ የነበረው ሂደት ቀላል አይደለም::
የአገራችን ውጊያ ረገብ ብሎ አሁን ደግሞ ልማታችንን እንሰራለን ስንል የዩክሬን ውጊያ ደግሞ አጋጠመን። እንደማንኛውም ዓለም የዩክሬንና የራሽያ ግጭትም በእኛ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ጫና አለ፤ የአገር ውስጡን ጨርሰን እፎይ ሳንል የውጭው መምጣቱንም በአግባቡ ማየት ጠቃሚ ይሆናል:: መፈናቀል፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ያልተገባ የውጭ ጫና በዚህ ውስጥ ሊታይ የሚገባው ነው:: የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የገጠሙንን በደንብ ማስተዋል እና ማስታወስ ስንችል ከእቅዶቻችን ምን ያህል አሳካን፤ ምን ያህል አላሳካንም፤ የገጠሙን ፈተናዎች እንዴት አለፍናቸው የሚለውን ለማየት ያግዛል::
እንግዲህ ውጊያ ገጠመን ሲባል ዝም ብሎ ተራ ግጭት አይደለም:: ህዝብ ሊያናክሱ፣ አገር ሊያፈርሱ በይፋ ተናግረው አውጀው የተነሱ ኃይሎች ናቸው የገጠሙን:: ህዝብ አታናክሱ፤ አገር አታፍረሱ የሚለው የመከላከል ውጊያ እንዲሁ አንዳንዶች በቀላሉ እንደሚያነሱት የሚታይ ሳይሆን አገርን ከማፍረስ የታደገ ዘመቻ ነበር:: ኢትዮጵያ አበቃላት የሚለውን በርካቶች በተናገሩት አፋቸው ነገር ተቀልብሷል እንዲሉ ማድረግ ያስቻለ ሁኔታ ነው::
የእነዚህ ሰዎች ዓላማ ኢትዮጵያ የሚባለው የከበረ ስም ታሪክ ማድረግ ነው:: ይህ ስም ከነክብሩ እንዳይዘልቅ የማድረግ ፍላጎት ነበራቸው:: ይህንን ስም ለማጥፋት አስፈላጊውን መስዋዕትነት እንከፍላለን ብለው በግልጽ ያወጁ ኃይሎች ናቸው:: ከእነዚህ ጋር የገጠምነው ጦርነት ኢትዮጵያ አትፈርስም ነው አልፈረሰችም? ኢትዮጵያ አልፈረሰችም ብቻ ሳይሆን የብልጽግና መሰረቷን እየጣለች ነው ያለችው:: ይህን ደግሞ የተከበረው ምክር ቤት በቅርቡ በነበረው ጉብኝት በርካታዎቹን ነገሮች ስላየ እኔም ደጋግሜ አነሳቸዋለሁ::
እነዚህ ሁሉ ፈተናዎችና ችግሮች ያጋጠሙን ደግሞ በወጉ ሳንደራጅ ነው:: ተቋም ሳንፈጥር፣ ከላይ እስከታች እንደመንግስት ሳንቆም የገጠመን ችግር ነው:: ተመሳሳይ ችግር ነገ ቢገጥመን የምንወጣበት መንገድ ከትናትናው ይለያል:: ዛሬ የተሻለ ቁመና ስላለን በተሻለ መንገድ እንወጣዋለን:: ከዚህ ቀደም ግን ችግሩ ሲገጥመን እንደመንግስት ሳንደረጅ፤ እንደፓርቲ ሳንደረጅ የነበረበት ሁኔታ ተግዳሮቱን ለመጋፈጥ የሚጠይቀው ዋጋ በዛው ልክ ከበድ ያለ ያደርገዋል::
ነገር ግን ይህ ችግር የራሱ የሆነ ስጋት ብቻ ሳይሆን እድልም አለው:: እድሉንም ስጋቱንም፤ መከራውንም ልማቱንም፤ ጥፋቱንም በሚዛን ማየት ስንችል የተሟላ ግንዛቤ እንይዛለን:: ኮሮና ስለመጣ ሁሉን ያጠፋ ብቻ ሳይሆን መሬት ጦም አይደር ብለን እንድንዘምት ደግሞ በር ከፍቷል:: ኮሮኖ መጥቶ መሬት ጦም አይደር ባንል ኖሮ ዛሬ የዩክሬን ውጊያ ላይ አፍሪካ በስንዴ ምክንያት እየደረሰበት ያለው መከራ እኛ ስለኤክስፖርት ቀርቶ ከዚ በመለስ ባለው ጉዳይ ላይ ለመነጋገር እንቸገር ነበር:: እያንዳንዱ መከራ የራሱ የሆነ እድል ይዞ ይመጣል:: ያንን እድል በምን ያህል ልክ እንጠቀምበታለን የሚለው ጉዳይ ከብዙ አገራት ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል::
ተደራራቢ ፈተናዎች የገጠማቸው አገራት፤ የተደራረቡ ችግሮች የገጠሟቸው አገራት፤ እንደ አገር የፈረሱ አገራት በአጠረ ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን አደራጅተው እንዴት ቆሙ ነው:: ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ጀርመን ፈርሳ እንዴት ራሷን አደራጅታ በአውሮፓ ትልቁን ኢኮኖሚ መገንባት ቻለች? በኤዥያ ጃፓን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ፈርሳ በአጠረ ጊዜ ውስጥ ራሷን አደራጅታ እንዴት በኤዥያ ከዓለም ከፍተኛ ኢኮኖሚ ካላቸው አገራት ተርታ መመደብ ቻለች? በሲቪል ጦርነት ኮሪያ ከፈረሰች በኋላ በአጠረ ጊዜ ውስጥ ራሷን ለመቻል እና ለመርዳት የሚያችል የኢኮኖሚ አቅም እንዴት ገነባች? መከራ አገራን የሚያጠፋ ብቻ ከሆነ እነዚህ አገራት ከችግር ውስጥ ወጥተው ራሳቸውን የቻሉበት መንገድ ያንን እሳቤ ይቃረናል::
ሩሲያ እንኳ ብንወስድ የዛሬ 30 ዓመት ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ሩሲያ ተንኮታኮተች የሚባልበት ዘመን ደርሶ ባለፉት 30 ዓመታት ራሷን አደራጅታ አሁን ላለችበት ቁመና ደርሳለች:: የገጠመን ፈተና፤ የገጠመን ችግር /በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሰራሽ፤ በውስጡ ያመጣውን እድል መጠቀም ከቻልን፣ በትጋት መስራት ከቻልን ኢትዮጵያን አስተማማኝ መሰረት ላይ ማስቀመጥ የሚችል እድል ሊያመጣ እንደሚችል አይተናል፤ ተምረናል፤ ያለውም እውነታ እሱን ነው የሚያሳየው:: ስለዚህ መከራውንም ችግሩንም በአውዱ ማየትና በዛ መነጽር መገንዘብና መረዳት በእጅጉ ያግዛል::
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሪፎርሙን በሚመለከት ሪፎርሙ ተቀልብሷል ወይ? አለ ወይ? የለም ወይ? የሚል ጥያቄ ተነስቷል፤ ሪፎርሙ፣ መነሻ ያደረጋቸው እሳቤዎች እና ሐሳቦች በደንብ ካልተገነዘብንና በዚያው መመዘኛ መሰረት መገምገም ካልቻልን የተዛባ ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል:: በኢትዮጵያ ብዙዎች አንድ የሚያግባባቸው ሞቶ አለ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ቦታ “It’s My Dam” እየተባለ ይነገራል:: It’s My Dam> የተባለው ከህዳሴ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ቢሆንም ለእኛ ሪፎርም ግን አጋዥ በሆነ መንገድ እና ሰዎች በቀላሉ እንዲያስታውሱት እኛ ደግሞ ‹My>ን አጥፍተን ‹Its Dam> በሚል ምህጻረ ቃል ያሰርነውን ሪፎርም ነው የምናካሂደው::
It’s Dam> የሚለውን ነገር በቀለለ መንገድ ስንገነዘብ ከዚያ ተነስተን ሪፎርሙ ምን ላይ እንዳለና እንዴት እየተሳካ እንደሆነ ምን ችግሮች እንዳሉበት፤ ምን ሊታረም እንደሚገባው ከውስጡ በቀላሉ ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል::
‹It’s Dam> የሚለው የመጀመሪያው ‹I› የሚለው ‹Idea› ሐሳብ ነው:: የሐሳብ ድህነት በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው:: ሰዎችን ይንጣል፤ ባለተስተካከለ ጎዳና እንዲጓዙ ያደርጋል:: ምክንያቱም ሐሳብ የመገንባት የማፍረስ አቅም አለው:: አገር የሚገነባውም የሚፈርሰውም ጭንቅላት ውስጥ ነው:: የፈረሰ ጭንቅላት አገር ሊገነባ አይችልም:: የተገነባ ጭንቅላት አገር ሊያፈርስ አይችልም:: ሐሳብ ይገነባል፤ ሐሳብ ያፈርሳል፡ ግልጽነት ያለው እሳቤ ካልያዝን በስተቀር በዚያ ላይ የሚመሰረተው የልማት እንቅስቃሴ ዘላቂ ሊሆን አይችልም::
ሐሳብ ሰው ይገነባል:: ሰው ተቋም ይገነባል:: ተቋም አገር ይገነባል:: ያልተገነባ ሰው ተቋም አይገነባም:: ያልተገነባ ተቋም አገር አይገነባም:: የነገር ሁሉ መሰረት ሐሳብ ነው:: ምክንያቱም ሐሳብ ዘር ነው:: ሐሳብ ዘር ስለሆነ፤ ሰው ዛፍ ነው:: ተቋም ጫካ ነው:: አገር የጫካዎች ድምር ናት:: አገር የሚባለውን ትልቅ የጫካዎች ድምር ስናወራ ዘር የሆነውን ሐሳብ፤ ዛፍ የሆነውን ሰው፤ ጫካ የሆነውን ተቋም በየቦታው በትክክል ማየት ካቻልን አገር ፈርሳ፣ አገር ተገንብታ፣ አገር ወድቃ፣ አገር ተነስታ የሚለው ቋንቋ፣ ቋንቋ ብቻ ነው የሚሆነው::
የነገር ሁሉ ዘርና መሰረት ሐሳብ ነው:: ሐሳብን በዚህ ደረጃ የምናከብርና ዋጋውን የምንገነዘብ ደግሞ ከሆንን እኛ ዘር የማናመክን መሆን አለብን:: ዘር የማያመክነው አርሶ አደር ያንን ዘር ዘርቶ ፍሬያማ ይሆናል:: ዘር የማናመክን፣ ዛፍ የማንቆርጥ፣ ጫካ የማንመነጥር ከሆን፤ ሐሳብ አይመክንም፤ ሰው አይመክንም:: ተቋም እንደ ተቋም ደግሞ የፈረሰና ከፖለቲካ ጋር የሚሄድ የሚመጣ አይሆንም:: ዘር፣ ዛፍና ጫካ በመሰረቱ እየገነባን የምሄድበትን መንገድ ከፈጠርን ግን ፓርቲ ቢሄድ ፓርቲ ቢመጣ እንደ አገር ስጋት አይገባንም::
ከሰሞኑን የጎበኛችሁት ተቋም የሚያሳዩት የሐሳብ ዘር በየተቋማቱ እንደተዘራ፣ ሰው የሚባለው ዛፍ በየተቋሙ እየተፈጠረ መሆኑን፣ ይህ ዛፍ ተደምሮ ደግሞ ጫካ የተሰኘው ተቋም እየገነባን መሆኑን ጅማሮ ነው:: ይህንን አሰናስለን አገር ልናቆም፤ አገር ልናስቀጥል የሚያስችል መሰረታዊ ስራ እየሰራን መሆኑን ያመላክታል::
ይህ ባይሆንስ? ሐሳብ ዋጋ እንዳለው ባንገነዘብስ? ሐሳብ ዘር መሆኑን፤ መሰረት መሆኑን ባንገነዘብስ ያ ደግሞ ወፍ ዘራሽ አረም ይሆናል:: ጫካው ተቋሙ አገሩ ወፍ ዘራሽ ይሆናል፤ ወይም በረሃ ይሆናል፤ የተመነጠረ ይሆናል:: በሐሳብ ላይ ስንግባባና ሐሳብ ስናደራጅ ቅድም እንደጠቀስኳቸው ሳንቸገር ወደሚቀጥለው ደረጃ ለመጓዝ እድል እናገኛለን:: እስካሁን የተናገርኩት ሐሳብ የሚለውን ነው::
ቀጥሎ ደግሞ <Time> የሚለውን ‹ጊዜ› ነው:: ጊዜ የሚሰጥ ውድ ሀብት ነው:: ጊዜ ይስጥሃል እንጂ አትገዛውም:: የተሰጠህን ጊዜ ተገንዝበህ መጠቀም ካልቻልክ ጸጸት ታተርፋለህ፤ ጸጸት ትወልዳለህ:: በተሰጠው ጊዜ የማይጠቀም ሰው ትርፉ ጸጸት ነው:: ጊዜ ሲባል ወደመንግስት፣ ወደ ፓርላማ እንዲሁም ወደሚዲያ እጅ የሚቀሰርበት ሳይሆን እያንዳንዱ ሰው የጊዜን ዋጋንና ምንነት እንዲሁም አጠቃቀም በቀለለ መንገድ መገንዘብ አለበት::
ለምሳሌ እዚህ ያላችሁ የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት በቸርነትና በደግነት ሰጪው ዘጠና ዓመት የተባ ጊዜ ለእያንዳንዳችሁ ቢሰጣችሁ፤ ከዚህ ውስጥ 30 ዓመት በእንቅልፍ ነው የሚያልቀው:: በቀን ውስጥ ስምንት ሰዓት ትተኛላችሁ፤ ስለዚህ 30 ዓመቱ በእንቅልፍ ያልቃል ማለት ነው:: ስለዚህ 60 ዓመት ቀረ:: 30ው ዓመት በእንቅልፍ ስለሄደ ቢሰጥም ባይሰጥም የእንቅልፍ አካል ተደርጎ የሚታይ ነው:: የምንነጋገረው በ60ው ብቻ ይሆናል:: ከ60 ዓመቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታ አሁን እንደእናንተ ተምሮ ተመርቆ ፓርላማ የመጣ ሰው ቢያንስ ቢያንስ ኮሌጅ እስኪገባ 20 ዓመት በእናት በአባቱ ጫንቃ ላይ የሚቀመጥ ነው:: 20 ዓመት ስራ አይሰራም:: ሃይስኩል ጨርሶ ኮሌጅ እስኪገባ ድረስ ማለት ነው::
ግን ምናልባት ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከደረሱ በኋላ ቤተሰቦቻቸውን ያግዛሉ፤ ውሃ ይቀዳሉ፤ በእርሻ ይተባበራሉ:: 20 ከምናደርገው 15 ዓመት እናድርገው:: 15ቱን ዓመት በእናት በአባቱ ጫንቃ ላይ ይቀመጣሉ:: ከዚያ በኋላ ነው ስራ የሚጀምረው ብንል ከ60ው 15ቱን ቀንሱ:: 45 ቀረ:: በኢትዮጵያ ህግ መሰረት ሰው ከ55 እስከ 60 ዓመት ጡረታ ይወጣል:: ነገር ግን በ60 ብንወጣም አንድ አምስት ዓመት ሰው ካለበት የስራ መስክ ከወጣ በኋላ ይፍጨረጨራል፤ ይሠራል ብለን እስከ 65 እንግፋው:: ከታች አምስት ገፍቻለሁ:: ከላይም አምስት ጨምሪያለሁ/ ደግ ለመሆን እንጂ ያን ያህል የሚሠራ አለ ማለት አይደለም/ ::
በ65 ዓመቱ ጡረታ ይወጣል ብለን ብናስብ ከ65 እስከ 90 ለ25 ዓመታት የጡረታ ጊዜ ነው:: 25 ጡረታ፤ 30 እንቅልፍ፤ 15 አልሰራህም ቢባል ያለህ የሥራ ጊዜ 20 ዓመት ነው:: ከ90 ነው:: ከ20 ዓመት ደግሞ ቅዳሜ እና እሁድ፣ የሻይ እረፍት፣ የምሳ ዕረፍት ጨምሩበት፤ ሰው ከተወለደ ጀምሮ እስከሚያርፍበት ቀን ድረስ ለመብላት ሳይታክት፤ ከተወለደ ጀምሮ እስከሚያርፍበት ቀን ድረስ ለመተኛት ሳይታክት 10 እና 15 ዓመት በወጉ ሳይሠራ የተዝናና ሕይወት ሊኖረው አይችልም::
ማንም ሰው የተዝናና ሕይወትን የሚፈልግ ከሆነ መትጋት ግዴታው እንደሆነ ማወቅ አለበት:: ለምን? ውስን ጊዜ ነው:: ለምሳሌ እኔ እና እናንተ ያለን የሥራ ጊዜ ከአሁን በኋላ ቢበዛ 15 ወይም 10 ዓመት ገደማ ነው:: ባንጠቀመው ሰጪው ይወስደዋል:: ብዙ ሰው 20 ዓመት ቤተሰቡ ላይ ተቀምጦ፤ ከዛ ደግሞ በሻይ እረፍት ብዙ ጊዜን አሳልፎ ጡረታው ሲደርስ መብላቱን መቀጠል ይፈልጋል:: ነገር ግን አይቻልም:: መብላት መቀጠል የሚያስብ ሰው ያቺን ጊዜ በአግባቡ መጠቀም አለበት:: ለምን ክረምት በጋ አይሆንም ጨለማም ብርሃን አይሆንም:: ይህ የተፈጥሮ ሕግ ነው::
የተሰጠንን ጊዜ አውቀን ጠዋትና ማታ ክረምት እና በጋ እንደማይቀላቀሉ ሁሉም ነገር በወቅት በጊዜው እንደሚሆን ተረድተን ካልተጠቀምን በስተቀር ጊዜ ባለቤት አለው:: ነገ ይደርሳል ብለህ ብትተወው አታገኘውም:: ጊዜ እንደኪራይ ቤቶች ነው:: የፓርላማ አባል ስትሆኑ ኪራይ ቤቶች ቤት ሠጥቷችኋል:: ልክ አምስት ዓመት አገልግላችሁ የማትቀጥሉ ከሆነ ኪራይ ቤቶች በል ቤቱን ልቀቅ ይላል:: ጊዜ እንደእርሱ ነው:: ይሰጥሃል፤ ትኖርበታለህ:: ሲያልቅ ይወሰድብሃል:: ሌብነቱን፣ ውጤቱን ፣ ፕሮጀክቱን ሁሉንም ከጊዜ አንፃር ማየት ነው:: እያንዳንዱ ሰው የተሰጠችውን ውስን ጊዜ ምን ያህል እየተጠቀምኩበት ነው ብሎ ማየት እና ማሰብ መቻል አለበት::
ከጊዜ ባልተናነሰ ሶስተኛው ሃሳብ ቦታ ነው:: ብዙ ጊዜ ሰዎች ለጊዜ ከበድ ያለ ቦታ ሰጥተው ለቦታ ዝቅ ያለ ቦታ ይሰጣሉ:: ሰው ግን የጊዜ ብቻ ሳይሆን የቦታ እስረኛ ነው:: ሰውን ከቦታ ውጭ ነጥሎ ማየት አይቻልም:: ሁሉ ነገር የሰው እንቅስቃሴ በቦታ ውስጥ ያለ ነው:: ለምሳሌ አልጋ ሰው የሚተኛበት ቦታ ነው:: ቤት ሰው የሚኖርበት ቦታ ነው:: ትምህርት ቤት ሰው የሚማርበት ቦታ ነው:: ቤተክርስቲያን መስጂድ ሰው የሚያመልክበት ቦታ ነው:: መንገድ ሰው የሚጓዝበት ቦታ ነው:: የእርሻ ማሳ ሰው የሚጓዝበት ቦታ ነው:: ሁሉ ቀርቶ ሰው ሲያልፍ ሲቀበር የሚያርፍበትም ቦታ ነው:: ሁሉም ነገር ቦታ ነው::
ቦታን በወጉ የሚረዳ፣ የሚያይ እና የሚጠቀም ሰው ይለማል፤ ይበለጽጋል አይለምንም:: ቦታን በወጉ መጠቀም የማይችል ሰው ግን ይደኸያል:: ለምሳሌ የበጋ ስንዴ ሲባል እያንዳንዱ ዜጋ መገንዘብ ያለበት በበጋ ወቅት የረሳነውን መሬት መጠቀም ማለት ነው:: ክረምት አርሰን በጋ የጣልነው ቦታ፤ አይ በጋም ጥቅም ላይ መዋል አለበት ብሎ መጠቀም መቻል ማለት ነው:: ጊዜውም ቦታውም ያለውን ጉድኝት ማየት ይጠቅማል::
እኛ ስለቦታ <Space> (ስፔስ) ያለን ግንዛቤ እጅግ ያነሰ በመሆኑ በርካታ ነገር መቀየር ስንችል በማይቸግረን ቦታ ራሳችን ተይዘን ታስረን መርዳት የሚችል አገርን ለማኝ አድርገናል:: ይህ ደግሞ የሆነው ሰው ከራሱ ነው የሚጀምረው:: የጊዜ እና የቦታ እይታውን መገንዘብ የሚችለው ከራሱ ነው:: አንድ ሰው ብብቱን የማያፀዳ ፣ ጥርሱን የማያፀዳ ፣ ጫማውን የማያፀዳ ከሆነ ስለቤቱ አታውራ፤ ቤቱን ያፀዳል ብለህ አታስብ:: እላዩ ላይ ያለውን ቦታ ያልጠበቀ፤ የከበረ ማንነት በትክክል ያልጠበቀ ሰው ቤቱን አይጠብቅም፡ መጀመሪያ ጥርስ ማፅዳት፣ ጫማ ማፅዳት፤ ያ ግንዛቤ ያለው ሰው ቤቱን እንደሚያፀዳ መገመት ይቻላል:: ይሔ በግለሰብ ደረጃ ነው:: ቤተሰብስ የምግብ ማብሰያ ክፍሉን (ኩሽናውን) ካላፀዳ፣ መጸዳጃ ቤት ካላፀዳ፣ ጓሮውን ካላፀዳ እና ካልተጠቀመ አንድ ቤተሰብ ከተማውን ያፀዳል የሚባለው በየት በኩል ነው ?
አንድ ሰው ላዩ ላይ ያለውን ሳያፀዳ ቤቱን አያፀዳም:: አምስት አስር ሰው የሚኖርበት አንድ ቤተሰብ በጋራ የሚጠቀምበትን ኩሽና ካላፀዳ፤ ከተማውን አያፀዳም:: አንድ መንደርተኛ፣ አንድ ጎረቤት ደግሞ ሰፈሩን በትክክል ካላፀዳ እና ካልተጠቀመ አገሩን ሊያለማ አይችልም:: አገሩንም አያውቅም:: ከእናንተ መካከል ኢትዮጵያን ከጫፍ ጫፍ የሚያውቅ ስንት ሰው አለ? አምስት ሰው የለም:: አገራችንን በወጉ አናውቅም:: ሰው ሰፈሩን ሳያፀዳ፤ ሰፈሩን ሳያስተካክል አገሩን ያፀዳል ማለት ዘበት ነው:: ቤተሰብ በቤቱ በጋራ የሚጠቀምበትን ሳያፀዳ፤ ከባቢ ሳይጠቀም ከተማውን ያፀዳል ማለት ዘበት ነው::
ቦታ ላይ ያለን ግንዛቤ ልክ እንደጊዜው ግልጥ ያለና ያልታወቀ ከሆነ ልማት ችግር ነው:: ለዚህ ነው፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ የጠበበን:: ሶፍ-ዑመር የተረሳው፤ ላልይበላ ያረጀው፤ ኮያሻ የተዘነጋው፤ ስለቦታ ያለን ግምት እጅግ አነስተኛ ስለሆነ ነው:: አይገባንም ስፔስ፤ በቅርቡ እዚሁ አዲስ አበባ አካባቢ ለአንዳንድ ጉዳይ ቦታ ስናፈላልግ፤ የሆነ የሚገርም ቦታ አየን፤ ቦታው መኪና አይገባበትም:: የምንሔደው በእግር ነበር:: እኔም አብረውኝ የነበሩት ሰዎችም ደነገጥን::
እንደዚያ ያለ ከፍታ፤ እንደዛ ያለ የሚያምር ቦታ፤ አዲሰ አበባን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ፤ ልክ እኔ እንደማያችሁ ከተማዋን የሚያሳይ ቦታ በዚህ ከባቢ አለ ብለን አስበን አናውቅም:: ስለእንጦጦ እያወራሁ አይደለም:: ለማንኛውም ይህ ቦታ ብዙዎች ሊዝናኑበት የሚችሉበት በጣም በጣም ምርጥ እይታ (ቪው) ያለው በመሆኑ ኮብልስቶን ሰርተን እያዘጋጀነው ነው:: አረንጓዴ ልማት የምንጀምረው እዛ ስለሆነ በሚቀጥለው ሳምንት ታዩታላችሁ:: ለምን ይህንን ቦታ አላየንም:: ምናልባት እኛ ትንሽ ራቅ ያልን እንሆናለን ብለን ለከተማው ቀረብ ያሉ ሰዎችን ይዘናቸው ሔድን፤ ያውቁት እንደሆን ብለን ነበር፤ አያውቁትም::
ለቦታ፣ ለጊዜ እና ለሐሳብ ያለን ግምት እጅግ ውስን ስለሆነ እንደተባለው ነው:: ችግር ስንተነትን እንኖራለን:: መፍትሔ የሚባል ነገር የለም:: ኢትስ ‹It’s› ያልነው አይዲያ፤ ታይም እና ስፔስ ነው:: ዳም <Dam> ያልነው ዲውቲ እና ሞራል ነው:: ሥራ ሲባል መድከም አይደለም:: ስምንት ሰዓት ቢሮ ቆይቼ መጣሁ ደከመኝ አይደለም:: ከሥራህ ፍሬ ማፍራት አለብህ:: ውጤት ማምጣት አለብህ:: ከጀመርክ መጨረስ አለብህ:: ህዳሴን ጀምሪያለሁ፤ ስኳርን ጀምሪያለሁ ሳይሆን ማለቅ አለበት:: መጀመርና መጨረስ መድከም እና ፍሬ ማፍራት ማለት ነው::
ለምን የሚሠራ ሰው አይለምንም:: ያካፍላል:: በሥራ እንደሚጠቀም እንደሚያገኝ የሚያውቅ ሰው አርሶ አደርም ቢሆን ከማሳው ያካፍላል፤ እንጂ አይለምንም:: የሚሠራ ሰው አያባክንም፤ ዝም ብሎ አይረጭም፤ እንዴት ደክሞ እንዳመጣው ስለሚያውቅ ይቆጥባል:: አያባክንም:: የሚሠራ ሰው የዕጦት ጭንቅላት የለውም:: በሥራ ውስጥ ፈጣሪ ስለሆነ፤ የተትረፈረፈ ሃሳብ ነው ያለው:: የማካፈል ሐሳብ ነው ያለው:: የመስጠት የማጋራት ሐሳብ ነው ያለው:: በዚህ ሐሳብ የተነሳ በሰላም መኖር ይችላል::
ሥራ እንደኛ በድህነት ላሉ እና ልመናን ለተለማመዱ አገራት እጅግ ወሳኝ ነገር ነው:: ከሥራ አንፃር ሁላችንም መገንዘብ ያለብን ምድር ለሚሠራ ሰው ክብርን፣ ለሚያወራ ሰው ችግርን፤ ለሚበላ ሰው መቃብርን አትነፍግም:: ከበላህ የሆነ ጊዜ ስትሞት ትሰጥሃለች፤ ቦታ አትከለክልህም፤ አትነፍግህም:: ምድር ደግ ናት:: ካወራህም ችግርን ታስታቅፍሃለች:: በወሬ ችግር እንጂ ውጤት ስለማይመጣ::
ዓለም ከሠራህ ታከብርሃለች:: የሚሠሩ ሰዎች ጠዋት ቢወቀሱ፤ ጠዋት ቢነቀፉ፤ ማታ ሞገስ እና ክብር ይጠብቃቸዋል:: ስትሠራ አሁን ያለውን ጫጫታ ሳይሆን፤ ነገ የሚመጣውን ክብር እያሰብክ መሆን አለበት:: የጠዋት ወቀሳ የማታ ሞገስ እና ክብር ስለሚያመጣ:: እስኪ እኛ አገር ኢትዮጵያ ውስጥ የማይሠራ አይብላ ቢባል፤ ከ100 ሚሊዮን ስንት ሰው ይበላል ብላችሁ ታስባላችሁ?
የማይሠራ ሰው አይብላ ብላችሁ አዋጅ ብታወጡ፤ ህግ ብታወጡ፤ ይህ ትንሽ ይከብዳል:: እናንተንም ምናልባት ላይምር ስለሚችል፤ የማይሠራ አይብላ የሚለው ይቅርና ተግቶ የማይሠራ ሰው አርባ ጅራፍ ይገረፍ፤ ቢባል ከዚህ ውስጥ ስንት ሰው ሳይገረፍ ይወጣል የሚለው ነው ጥያቄው:: ሕግ አውጥታችሁ በቃ ካልሰራህ አትብላ፤ እርሱም ከባድ ስለሆነ ግዴለም ትንሽ ትንሽ ቅመስ፤ ግን አርባ ጅራፍ ትገረፋለህ ብትሉ፤ ከ100 ሚሊዮን ስንት ሰው እንደሚተርፍ እናንተው አስቡበት::
ወገኖቼ መስራት አለብን:: በሥራ ብቻ ነው ለውጥ የሚመጣው:: እኛ የምንሰራው ሰባት ቀን ነው:: እኛ የምንሰራው ሶስት እና አራት ሰዓት እየተኛን ነው የምንሰራው:: ለምን? ውጤት ፍሬ ስለምንፈልግ ነው:: ቅድም አንድ ወንድሜ በመግቢያ ንግግሩ ያነሱትን ጉዳይ በኋላ እመጣበታለሁ:: በጣም የረሳኋቸውን ቁም ነገሮች ስላስታወሱኝ፤ ለምሳሌ ‹‹የወሰን ጉዳይ ይመለሳል ብለው ነበር::›› አሉ:: እንዴት እንደረሱ አላውቅም:: ሲዳማ እንዴት በሰላማዊ መንገድ የራሱን ክልል እንዳወጀ፤ እንዴት ምዕራብ በሰላማዊ መንገድ የራሱን ክልል እንዳወጀ እንዴት ማስታወስ እንዳልቻሉ አልገባኝም:: እሱ ማለት እኮ ነው:: የወሰን ጉዳይ ሲባል የሕዝቦች ጥያቄ ህጋዊ በሆነና በሰላማዊ መንገድ በሕዝቦች ድምፅ ምላሽ መስጠት መቻል ማለት ነው::
የመጨረሻው ሞራል ነው:: አይዲያ፣ ታይም እና ስፔስ (ኢትስ) ያልኳችሁ ይህንን ነው:: በመጨረሻ ሞራል ነው:: በተለይ ሌብነት፤ የተከበሩ የምክር ቤት አባል ከንብረት ጋር ተያይዞ ጥያቄ አንስተዋል:: ሌብነት ቅድም ያነሳኋቸውን ነገሮች ሁሉ የሚያፈርስ ካንሰር ነው:: ነቀርሳ ነው:: የሚሰርቅ ሰው ስለጊዜ፣ ስለስፔስ እና ስለአይዲያ ቢገባውም ባይገባውም ዋጋ የለውም:: ሰራቂ ማለት አጉዳይ ማለት ነው:: ግን የኛ ሌብነት መንግስት፤ መንግስት፤ እንደሚባለው ነው ወይ? የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት የኛ ልጆች እኮ ናቸው ፈተና እየኮረጁ ያስቸገሩን:: ተማሪ ይኮርጃል፤ ሌብነት እርሱ ነው:: ተማሪን አትኮርጅ ሳንል መንግስት ከሆነ በኋላ አትስረቅ ብንል ዋጋ የለውም:: የሌላ ሰው እኮ አይደለም:: ከኬኒያ መጥቶ አይደለም የሚኮርጀው፤ የኛ ልጆች ናቸው የሚኮርጁት::
ሰራተኛ ብሎ መንግስት ቀጥሮ በሌለው ሃብት፤ የተቀጠረው ሰራተኛ አብዛኛውን ጊዜውን ቅድም ካልኳችሁ ውስን ጊዜ ውስጥ የሚያጠፋው ዩቲዩብ ላይ ነው:: ዩቲዩብ ማለት የአገር እና የሕዝብን ጊዜ ሰርቀህ አልባሌ ወሬ ስትሰማ መዋል ማለት ነው:: ዩቲዩብ ውስጥ አስተማሪ ጉዳዮች አሉ፤ ጠቃሚ ጉዳዮች አሉ:: እነርሱን በፕሮግራም ማድመጥ ጠቃሚ ነገር ነው:: ነገር ግን አብዛኛው ሰው ያለው እዛ አይደለም:: ይህ ሌብነት ነው:: ካሽ መቀባበል ብቻ አይደለም:: ምክንያቱም ጊዜን ስለሚበላ፤ ታናሽ ታላቅን አያከብርም፤ መከባበር የሚባል ነገር የለም::
ወንድ ሴትን አያከብርም፤ ዜጎች ሕግ አያከብሩም:: ሌብነት አደገኛ ካንሰር ነው:: የሞራል ዝቅጠት ነው:: ልማታችንን ይጥላል ስንል በእነዚህ አይቆምም:: የሃይማኖት አባቶች፤ ቅድም እንደተባለው የምዕመኖቻቸውን የተከታዮቻቸውን ሕይወት አስይዘው ቁማር ይጫወታሉ:: በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ተቋማት መሬት ሊዝ የማይከፍሉት፤ ኦዲት የማይደረጉት፤ ታክስ የማይከፍሉት የሃይማኖት ተቋማት እንዳሻቸው ይሁኑ የሚል ህግ ስላለ አይደለም:: እንደዛ ዓይነት ህግ የለም::
አሜሪካ ውስጥ የሃይማት ተቋማት ቤቱን ይገዛል:: ቤተክርስቲያኑንም ሆነ መስጂዱን ይገዛል:: ዝም ብሎ የሃይማኖት ተቋም ነው የሚባል ነገር የለም:: ኢትዮጵያ ውስጥ ያ የሚሆነው ለምንድን ነው? የሃይማኖት ተቋማት እንደአጋጣሚ ሆኖ የውስጥ ማንነት ይሰራሉ፤ ሞራል ላይ ይሰራሉ፤ ሰላም ወዳድነት ላይ ይሰራሉ፤ ግድየለም፤ አንዳንዱ ቢቀርም መንግስት የማይሸፍነውን ነገር ይሸፍናሉ፤ መሬት ቢቀር ፤ ኦዲት ባይደረጉ ችግር የለውም ፤ እኛ የማንሰራቸውና ወሳኝ ስራዎችን ስለሚሰሩ ይካካሳል ነው እሳቤው:: አሁን ያለው የተገላበጠ ነው:: ከፍተኛ ምዝበራ ያለው እዚያ ነው፤ የሞራል ዝቅጠት ያለው እዚያ ነው፤ እንኳን የውስጥ ማንነት ሊሰሩ የውስጥ ማንነት በይፋ እያፈረሱ ይውላሉ:: በዚህ ምክንያት ሌብነት በእያንዳንዱ ሰው ጓዳ ውስጥ በምርጫው የታቀፈው ካንሰር ሆኖ ይታያል:: ይህንን ካላስተካከለ ሪፎርሙ የተከበሩ ወንድሜ እንዳነሱት የትም አይደርስም::
ሃሳብ ላይ የጠራ ሃሳብ አለን፤ የጠራ ግንዛቤ አለን ሁላችሁም እንደምታውቁት:: ጊዜን በሚመለከት እንዳልኩት ነው ፤ ሰባት ቀን ነው የምንሮጠው፤ ውጤት ለማምጣት፤ ስፔስን በሚመለከት የምንዞረው የምናየው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ሃብቶች ለማውጣት ነው:: በስራ መቼም አንታማም:: በስራ የሚያሙን ሰዎች ካሉ መቼም ስራ የማያውቁ ናቸው:: ከሞራል ጋር ተያይዞ ያለው ውስንነትና ድካም በጣም ስራ ይፈልጋል:: በካሽ ብቻ ካየነው ሁሉም ነገር አያመጣም:: ተቋሞቻችን በዚህ ውስጥ ነው ያሉት፤ የዚህን ሪፎርም ፈተና በአንዲት ቀላል ምሳሌ ማንሳት ይቻላል::
አራት ሸምገል ያሉ ታላላቅ ሰዎች ላልተወሰነ ጊዜ በአርምሞ በፀጥታ ሪፍሌክት እናድርግ፤ በጥሞና እንቆይ፤ እንፀልይ ብለው ይወስናሉ:: ንግግር አይፈቀድም፤ ከፈጣሪያችን ጋር ብቻ ነው የምናወራው ያም ንግግር የሚፈቀደው በአርምሞ በዝምታ ውስጥ ነው ብለው ተስማምተው ፀሎት ይጀምራሉ:: ከትንሽ ደቂቃ በኋላ ጧፍ ለኩሰው እየፀለዩ እያሉ ንፋስ እየመጣ ጧፉን ለማጥፋት ይረብሻል:: ከአራቱ አንዱ ሰው ንፋሱ እኮ ጧፋችንን ሊያጠፋብን ነው ብሎ ይናገራል:: ሁለተኛው ሰው ዝም እንበል በል ተብሎ አልነበረም ወይ ይላል:: ሶስተኛው ሰው እናንተ ሁለት ሰዎች በጠበጣችሁን፤ ለምን ትናገራላችሁ ይላል:: አራተኛው ሰው ደግሞ ዋው እኔ ብቻ ቃሌን ጠበኩኝ ይላል::
የመጀመሪያው ንፋሱ በአፉ ሊያጠፋብን ነው ያለው ሰው የተፈጥሮን ፈተና መቋቋምና ቃል ለገባለት አላማ መቆም የማይችል ነው:: ምክንያት የሚፈልግ ማለት ነው:: ሁለተኛው ዝም እንበል ብለን አልነበረም ወይ የሚለው ሰው ከዋናው አላማው ከፀሎቱ ፤ ከስምምነቱ በላይ ህግ ያስጨንቀዋል:: ዝም እንበል የተባለበት ዋናው ምክንያት ለፀሎት ነው:: ዝም እንበል የተባለበትን ምክንያት ረስቶት ስምምነት ተጣሰ ይላል:: የሚስጨንቀው ህግ ነው:: ሶስተኛው ዝም አትሉም ወይ ያለው ሰው ትዕግስት የለውም:: መታገስ አይችልም:: መታገስ አይችልም ብቻ ሳይሆን በሰዎች ይሰናከላል::
ለምሳሌ ሪፎርሙ ችግር ያገጠመው የሚመስላቸው ሰዎች የምናቆም ይመስላቸዋል:: እኛ ግን አንቆምም፤ የጀመርንበትንም፤ የምንደርስበትንም እናውቃለን:: በሰዎች ንግግር የሚሰናከል ሰው ነው ሶስተኛው:: አራተኛው በሰራው ስራ ሳይሆን፤ በራሱ ውጤት ሳይሆን፤ በሰዎች ስህተት አንደኛ መሆን የሚፈልግ ማለት ነው:: በአንድ ደቂቃ ውስጥ ጧፉ ሊጠፋ ነው አለ፤ ዝም እንበል ተብሏል አለ፤ ዝም አትሉም ወይ አለ፤ እኔ ጠበኩኝ አለ:: ሁሉም የአምስት ደቂቃ ጉዳይ ነው::
በሰዎች ድካምና ስንፍና እሱ አንደኛ መሆን ይፈልጋል:: እንደዚህ አይነት ተግዳሮቶች ሪፎርሙ አሉበት:: የተፈጥሮ ህግ የማይቋቋሙ አሉ፤ ነገሮች በስምምነትና በህግ ያሉ ብቻ እንጂ ውጤት የማያዩ ሰዎች አሉ:: በሰዎች ድካምና ስህተት በቃኝ የሚሉ ሰዎች አሉ:: ምን አቃጠለኝ የሚሉ ሰዎች አሉ:: በቃን ምን አቃጠለን የሚሉ ሰዎች አሉ ፤ አንዳንዶች ደግሞ ሳይሰሩ በሌላው ድካም የተሻለ መስለው የሚቀርቡ ሰዎች አሉ:: ይህ ስራ ይፈልጋል::
ሪፎርማችን ከዚህ አንፃር ለማመን የሚከብዱ ውጤቶች እያመጣ ነው:: ለእናንተ አይደለም፤ ለእኔ ለራሴ ፤ የፈጣሪን ቸርነት፤ ደግነት የመከናወን የመጨረሻ ውጤት የሚታይባቸው አስደማሚ ነገሮች በሪፎርም እየመጡ ነው:: ዩቲብና ፌስቡክ የሚያወራውን አይደለም የምላችሁ፤ መሬት ላይ ያለውን ነው የምነግራችሁ፤ ለምሳሌ አንደኛው ከመንገድ ጋር ተያይዞ ያነሳችኋቸውን ጥያቄዎች በሚመለከት በጥቅሉ ላንሳ::
በኢትዮጵያ ውስጥ ከሪፎርሙ በፊት የመንገድ አውታር 127 ሺ ኪሎ ሜትር ነበር:: ይህ የገጠር መንገድ፣ ክልሎች የሚሰሩትን፤ የከተማ መስተዳደር የሚሰራውን፤ ፌዴራል መንግስት የሚሰራው ተደምሮ ነው:: ከሪፎርሙ በኋላ 165 ሺ ደርሷል:: ነገር ግን 165 ሺ ደርሷል ሲባል ቀድሞ የሚቆጠር መሬት አስፓልት የሚደገምም አለ:: 30 እና 40 ዓመት የሞላው አስፓልት ፤ አስፓልት የሚባል የነበረ፤ ግን የፈራረሰ አሁን ደግሞ እንደአዲስ የሚሰራ ሊኖር ይችላል:: ለምሳሌ ከጅማ አጋሮ እንደሚሰራው አይነት ማለት ነው:: ድሮም አስፋልት ነው፤ አሁንም የሚጠገን አስፋልት ነው:: በዚያም ይቆጠራል፤ በዚህም ይቆጠራል::
ነገር ግን የሚያስደነግጠው ነገር አጠቃላይ ኔትወርኩ ሳይሆን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የሰራቸው ኮንክሪት አስፓልቶች ከሪፎርም በፊት 13 ሺ ኪሎ ሜትር ነበሩ:: ባለፉት ሶስት ዓመት ተኩልና አራት ዓመት ገደማ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ብቻ በአገር ደረጃ 4ሺ 700 ኪሎ ሜትር መንገድ አጠናቆ አስገብቷል አንድ፤ 8 ሺ113 ኪሎ ሜትር አሁን እየተገነባ ነው ያለው፤ ግማሹ በሚቀጥለው ዓመት አንዳንዱም ከሁለት ዓመት በኋላ የሚያልቅ ማለት ነው:: ተጨማሪ 9ሺ102 ኪሎ ሜትር እናንተ በጀት አፅድቃችሁ ፤ ኮንትራት ወጥቶለት ግማሹ ጨረታ ከወጣለት በኋላ በፀጥታ ምክንያት በጀት እያለው ያልተጀመረ፤ አንዳንዱ ኮንትራቱ ችግር ኖሮበት ተሰርዞ ድጋሚ የጨረታ ሂደት ላይ ያለ፤ ቢያንስ ግን በጀት የፀደቀለት፤ ያለቀና የተጀመረ ስትደምሩ 22ሺ ኪሎ ሜትር ነው::
ይሄ የተረተረት ቁጥር አይደለም፤ መንገዶች ባለስልጣን ሄዳችሁ መቼ እንደተጀመረ? ከየት እስከየት ከተማ ተሰራ? በምን ያህል ገንዘብ ብላችሁ ማጣራት ትችላላችሁ:: ከ22ሺ ውስጥ 9ሺው በፀጥታና በአንዳንድ ምክንያት ያልተጀመረ ቢሆንም ድሮ የነበረን ያህል ቁጥር የሚያክል ግን ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን እየተገነባ ይገኛል:: ሪፎርሙ ያመጣው ውጤት ይሄ ነው:: ይህንን በአዲስ አበባ ብቻ እንመልከት፤ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመት አዲስ አበባ ውስጥ 151 ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ ተጠናቆ ስራ ጀምሯል:: አንዳንዱ እስከ 60 ሜትር ስፋት አለው:: 151 ኪሎ ሜትር ሲባል እንደገጠሮቹ ሰባት አስር ሳይሆን እስከ 60 ሜትር ስፋት አለው:: ከአስፓልት ውጪ 470 ኪሎ ሜትር ኮብልስቶን ተሰርቷል::
በጣም የሚገርመው እዚህ ምክር ቤት ላይ አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ ሰዎች መኪና የላቸውም፤ ታስታውሶ እንደሆነ አስፋልት ብቻ ሳይሆን ሰፋ ያለ የእግረኛ መንገድ ያስፈልጋል ብዬ ነበር:: 116ኪሎ ሜትር ሰፋፊ የእግረኛ መንገድ ተገንብቷል:: ልክ በአራት ኪሎና ቸርቸር ጎዳና እንደምታዩት ወደሜክሲኮ እንደምታዩት ሰፋፊ የእግር መንገድ ከዚህ ቀደም በዚህ መጠን ያልነበረ፤ በዚያ ጥራትም ያልነበረ 116 ኪሎ ሜትር ተገንብቷል:: ይሄ ብቻ አይደለም ከተማ ውስጥ ትራፊክ መጨናነቅ ስላለ ማቋረጫዎች ተሰርተዋል:: ለምሳሌ ቦሌ ሚካኤል፤ ኢምፔሪያል፤ መብራት ኃይል አካባቢ እየተፈጠኑ ይገኛል:: ከሳርቤት ጎተራ ያለውና ሁለት ዓመት ተኩል የፈጀው መንገድ አሁን እያለቀ ነው:: ይህ መንገድ እንደምታውቁት በአዲስ አበባ ውስጥ ረጅም ታናል የያዘ ነው:: የመጀመሪያው ታናል የተገነባው አሁን ነው፤ ከፑሽኪን ጎተራ ያለው ማለት ነው::
(ይቀጥላል)
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2014