ስለ ቤት ሠራተኛና አሰሪ ብዙም መልካም ነገሮች አይደመጥም። ሁለቱም በየፊናቸው ቻል አድርገውት ቢቀመጡም አንዳንድ ጊዜ ግን ተግባቦታቸው ላይ ችግሮች ያጋጥማሉ። የብዙዎቹን የአሰሪና ሠራተኞች ግንኙነትን የእሳትና ጭድ ማለቱ እንደሚሻል የገለፁልንም አሉ።
የአሰሪና የቤት ሰራተኞችን ግንኙነት እንዲህ የሚያሻክረው ምንድነው? ስንል ላነሳነው ጥያቄ ወይዘሮ ዝማም ጅሮ የቤት ውስጥ ፍጆታ እንደሆነ አጫውተውናል። ወይዘሮዋ በተለይ አሁን ባለው የኑሮ ውድነት እሳትና ጭድ የሚያደርጋቸው እንደ ዘይት ያሉ በውድ ዋጋ እየተገዙ ያሉ የምግብ ግብዓቶች በክነት መሆኑን ይናገራሉ ። ይህንን መሰሉን የቤት ውስጥ ፍጆታ መቋቋም ያልቻሉት አሰሪዎች ግብዓቶቹን ከመቆለፍ ጀምሮ ሰፍረው እስከመስጠት ደርሰዋል።
የሥራ ጫና፤ የዕረፍት ጊዜ በአግባቡ አለመስጠት፣ የትምህርት ጥያቄ አለመመለስ፤ ዝቅተኛ ደመወዝና ሌሎችም አሰሪና ሰራተኞች ከማይግባቡባቸው ሌሎች ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
ዛሬ ልናነሳ የወደድነው ለብዙዎች አሰሪና የቤት ሠራተኞች አርአያ ስለሆኑ ግለሰብ ነው። አሰሪዋ ወይዘሮ አልማዝ ለማ በቅርቡ በቤት ውስጥ ለስምንት ዓመት ስታገለግላቸው የነበረችውን የቤት ሰራተኛቸውን አስተምረው አስመርቀውና ድረው ለወግ ማዕረግ ያበቁ ናቸው።
ሰራተኛዋ በለጡ ሞገስ ከወይዘሮ አልማዝ ጋር የኖረችባቸው ስምንት ዓመታት ምንም ዓይነት የባዕድነት ስሜት ያልተሰማት ራሷን እንደ ሰራተኛ ሳይሆን እንደቤተሰብ ቆጥራ በፍቅርና በጥሩ መግባባት አብራ መኖሯን ትናገራለች። እንደ ቤተሰብ እንዴውም ልክ እንደ ቤቱ ባለቤት ነው አይታ የኖረችው። ባለቤቶቹም ቢሆኑ ከዚህ በተለየ እንደቤት ሰራተኛ አይተዋት አያውቁም። አንቺ እንዳልሽ ነው የሚሏት። በመሆኑም በሁሉም ነገር ወሳኝ ነበረች። በተለይ ወይዘሮ አልማዝ አብዝተውም ይተማመኑባት ስለነበር ‹‹ሌላው ቀርቶ አልሚ መኖሪያ ቤቷን ስታስገነባ ለኮንትራክተሩ የግንባታ ቁሳቁስና የሰራተኛ ወጪ በቅርበትና በፍጥነት እንድሰጠው በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር እኔ ጋር ነበር የምታስቀምጠው›› ብላናለች። ሽሮና በርበሬ ወይም ዘይት አለ የለም፤ በመባባል ጭቅጭቅ የለም።
መቆለፍ የሚባል ነገር ፍፁም አያውቁም። የሚያስፈልጋት ሁሉ ፍጆታ በእጅዋ ነው። የሚያስፈልገውን በሙሉ አስባ ነው የምትሰራውና ይሄን ሥሪ ብለው አዘዋትም አያውቁም። አንዳንዴ እሷ ሥራ ላይ ሳለች ልጆቹ ድንገት ያልታሰበ ነገር ይሰራልን ብለው ቢሉም አሰሪዋ ይሄን ትተሸ እነሱ ያሉትን አድርጊ ብለው በትዕዛዝ አያጨናንቋትም። እሳቸው ራሳቸው የሚሰሩበት ጊዜም አለ። ‹‹ዘመድ አዝማድም ሆነ ጎረቤት ሲመጣ ቡና አፍይ ወይም እንዲህ አድርጊ የሚለኝ የለም›› ስትልም የሚገባውን ሁሉ አስባ እንደምታደርግም ነግራናለች። በለጡ እንደምትለው አሰሪዋ እንደ ታናሽ እህታቸው ነው የሚያይዋት። ጎረቤት ወይም እንግዳ መጥቶ ሠራተኛሽ ሲሏቸው ደስ አይላቸውም።
‹‹በእርግጥ አስተምሮ፣ ድሮ ኩሎ የሚሸኝ አሰሪ ለእኔ ከእህትም በላይ ነው›› የምትለው በለጡ ቅዳሜና እሁድ አስተምረው ከመደወላቦ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ በዲፕሎማ እንዳስመረቋትም ትናገራለች። 10ኛ ክፍል ፈተና ተፈትና ውጤት ሳይመጣላት በቀረበት ወቅት በዘመድ እነ ወይዘሮ አልማዝ ቤት መቀጠሯን የምታስታውሰው በለጡ ዘንድሮ ድረው ኩለው የሴትነት ክብሯን ለማየት ያበቋት መሆኑንም ትናገራለች።
‹‹እኔ ታማኝ የሆንኩት አሰሪዬ ታማኝና ፈራሂ እግዚአብሔር ያላት ስለሆነች ነው›› አንዳንድ አሰሪዎች ሁሉንም ፍጆታ ቆልፈው መሄዳቸው ሳያንስ ማታ ወደቤት ሲገቡም ለምን ይሄ አልተሰራም ለምን ያ አልሆነም እያሉ ቁም ሰቅል የሚያሳዩም እንዳሉም ትናገራለች። ነገር ግን ኃላፊነት መስጠት፤ ማመንና ማክበርም ከጭቅጭቅ አድኖ አብሮ እንደሚያከርምም ትናገራለች።
አሰሪዋ ወይዘሮ አልማዝ ለማ በበኩላቸው ለኔ መልካም የሆነችልኝ እኔ መልካም ስለሆንኩላት ይሆናል። ሰራተኞቻችንን እንመናቸው፤ ኃላፊነት እንስጣቸው፣ እናክብራቸው። ክፉ የሚሆኑት እኛ ክፉ ስለምንሆንባቸው ነው። እኔ የሚያስፈልጋትን ፍጆታ ደብቄባት ብወጣ ስላልሰጠኋትና ሰርታ ስለማትቆየኝ ከሥራ ስመለስ መነጫነጭ ነው የሚሆነው ይላሉ። ስለሚያምኗትና እንደ ታናሽ እህታቸው ስለሚያይዋት ቆልፈውባት የሚሄዱትም የለም። መኖሪያ ቤታቸውን በሚገነቡበት ወቅት ኮንትራክተሩ ይዛው ብትጠፋስ ብሎ እስከሚገረም ድረስ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ከባንክ አውጥተው ለሚያስፈልገው ግብዓት መግዣ ሁሉ እየቀነሰች እንድትሰጠው ማድረጋቸውን ይናገራሉ ።
በለጡ እኔ አዝዣት የምትሰረው ነገር የለም የሚሉት አሰሪዋ ከጠዋቱ 11 ሰዓት ከመኝታዋ ተነስታ ለልጆቹም ለቤተሰቡም የሚያስፈልገውን ሰርታ ምሳ ቋጥራ ትሸኛለች። እዚህ ላይ ግን እኔ እንደዚህ አድርጊው የምለው ነገር የለም ሁሉንም የምትሰራው ራሷ አስባ ነውም ይላሉ። ‹‹የራሷ ፕሮግራም አላት። ማታ ስመጣ ቁጭ ብላ ፊልም ስታይ ወይም የምትወደውን ፕሮግራም በቴሌቪዥን ስትከታተል ነው የማገኛት›› በዚህ ምንም ቅር አይለኝም ምክንያቱም ሁሉንም የሚጠበቅባትን አከናውና ስለሆነ የምትቀመጠው በማለትም የልጅቷን ትጉነት ይመሰክራሉ።
ልብስ በማሽን እያጠበች ከጎን ሌሎች ሥራዎችን ትሰራለች። እሷን እረፍት ሰደው እሳቸው ኃላፊነቱን በሚወስዱበት ሰዓት ግን እንኳን ሊያርፉና ፊልም ሊያዩ የጣዱትን ይረሱታል። ምሳቸውንም ዘንግተውት ይውላሉ። ‹‹እኔ ቤቴን ብዙም አላውቀውም የጎደለውን ሞልታ አስተካክላ የምትጠብቀኝ በለጡ ነች›› የሚሉት አሰሪዋ ወይዘሮ አልማዝ ሲሰሩም፣ ሲማሩም ሲወልዱም ብዙዎቹን ኃላፊነቶች የምትሸፍንላቸው አጋዣቸው እንደነበረች ያወሳሉ። ሁለት ልጆቻቸውን እንደራሷ ልጆች ተንከባክባ አሳድጋላቸዋለች። አስተምረው ድረው ኩለው የሸኟትም ለዚህ ነው። የሌሎቹም ግንኙነቶች እንዲህ ቢሆኑ ስንመኝ ከሴቶችና ማህበራዊ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት የተሻለ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ ነው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2014