ጥበብን ፍለጋ
ወደ ሙዚቃ ሕይወት የገባው በአጋጣሚ አልነበረም:: አስቦበት በመሆኑ ያሳለፋቸው አስቸጋሪ ጊዜያትና የከፈላቸው ዋጋዎች ሁሉ አምኖበት ያደረጋቸው በመሆናቸው አይከፋባቸውም::እርሱ ከጥበብ ጋር ሲተዋወቅ ገና ነፍሱን ለሙያው አስገዝቶ ለመኖር ለራሱ ቃልኪዳኑን አስሯል:: ቃሉንም ጠብቆ በደስታና በመከራ ውስጥ እንዳከበራት ዛሬ ላይ ደርሷል:: ወደፊትም ፈጣሪ በሰጠው እድሜ ጥበብን በጥበብነቷ ተቀብሎ ነጻ ሊያወጣባት፤ ነጻነትንና እኩልነትን ሊሰብክባት፤ ታግሎ ሊያታገልባት፤ የተቸገሩ ሊያግዝባት፣ ሊደግፍባት ቃሉን አጽንቶላታል:: እድሜውን ለጥበብና ለህዝብ የሰጠው ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ::
ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ ከመሰንቆና ሙዚቃ ጋር የተዋወቀው በልጅነቱ ነው::ገና በለጋ እድሜው ከቦረቀባት የያኔው የጎንደር ክፍለ ሀገር ቃፍታ ሁመራ አካባቢ የለመዳትን ማሲንቆ ብቻ ይዞ ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣው:: የማያውቃትን አዲስ አበባን የናፈቀበትና “አዲስ አበባ የሚባል አገር ውሰዱኝ” ብሎ ያለቀሰውን ሲያስታውስ ዛሬም ድረስ ይገርመዋል::አልቅሶም አልቀረ ለመሳፈሪያ የሚሆን ቤሳ ቢስቲን ባይኖረውም አንዱን ተሳፋሪ ለምኖ ነበር ከጭኑ ላይ ተቀምጦ ጥበብን ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ የገባው::
አዲስ አበባ እንደመጣ ያለችው ብቸኛ ወዳጅ ማሲንቆው ብቻ ስለነበረች በየመጠጥ ቤቱ እየዞረ በማሲንቆው እየተጫወተ የዕለት ጉርሱን ይሸፍን ነበር::በአንድ የተባረከች እለት ግን ማሲንቆው የሕይወቱን መስመር የሚቃኝበትን አጋጣሚ ፈጠረችለት::በዛች የተባረከች ዕለት “ኧረ ገዳሙ ገዳሙ ገዳሙ” እያለ ሲዘፍን ነበር አቶ ታደለ ይደንቃቸውና ሼህ ሙሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ያገኙት::በእድሜው ትንሽነትና በድምጹ ማማር የተደነቁት እነዚህ ባለሀብቶች ወደወዳጃቸው ወይዘሮ ጽጌ ባዩ ቤት ወስደው “ትንሽ አዝማሪ አምጥተንልሻል” ብለው አስተዋወቁት:: “እስኪ ዝፈን” ተባለና ያችን የሚያውቃትን ብቸኛ ዜማ “ኧረ ገዳሙን” ሲዘፍን ከድምጹ በላይ ልጅነቱ አሳዘናቸውና “ከዛሬ ጀምሮ ከዚህ ቤት አትወጣም! እዚሁ እንደልጄ ትኖራለህ፤ ትምህርት ቤትም ትገባለህ” ተባለ::
ከወይዘሮ ባዩ ውቤ ቤት ትንሽ እንደቆየም በ1972ዓ.ም ላይ አምባሳደር ቴአትር ቤት ሙዚቀኛ ይቀጥራል ተብሎ ሲሄድ ከነድምጻዊ ፀሐዬ ዮሐንስና ድምጻዊት አበበች ደራራ ጋር “እቴ ጥበብ ሸማ ጥበብ ሸማ ያገር ልጅ አይናማ” የምትለውን ዜማ በማዜም በድምጻዊነትና በማሲንቆ ተጫዋችነት ተቀጠረ::
ለድምጻዊ ሻምበል በላይነህ ያ ዘመን ከጎንደሬነት ወደ ኢትዮጵዊነት የተቀየረበት ምርጡ ዘመን ነበር:: ምክንያቱ ደግሞ የብዙ ብሔር ብሔረሰብ ሙዚቃዎችን፣ ባህልና ቋንቋዎችን በማወቁ ኢትዮጵያ የገዘፈችበት ጊዜ እንደነበር ያስታውሳል::
አምባሳደር ቴአትር ቤት እንደተቀጠረ የመጀመሪያዬ የሚላትን ሙዚቃ ከድምጻዊ ንዋይ ደበበ ጋር ቢሰራትም በማስታወቂያ ሚኒስቴር ግምገማ እንዳትደመጥ ተደረገች:: ተስፋ ያልቆረጠው ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ ከነ ጋሽ ሙላቱ አስታጥቄና ድምጻዊ ማህሙድ አህመድ ጋር በኢትዮ ስታር ባንድ አማካኝነት በአረብ አገራት እየዞሩ ይዘፍኑ እንደነበር ያስታውሳል::ከዛም ወደ አሜሪካ ጥሪ መጥቶለት ሰርቶ ተመልሷል:: ከዛም “አንች ባለድሪ… አብረሽኝ አደሪ” የተሰኘችውን ዜማ ከድምጻዊት ራሄል ዮሐንስ ጋር ሲዘፍን በትክክልም ድምጻዊነቱን አረጋግጦ በመላው አገሪቱ ተወዳጅነት እና ተቀባይነትን አገኘ:: በመቀጠልም “አሞራ በሰማይ ሲያሽ ዋለ” የተሰኘውን ካሴት አወጣና በመላው ኢትዮጵያ ተወዳጅነትን ይበልጥ አተረፈ::
ጥበብን በስደት
በወቅቱ ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ በስራዎቹ ተወዳጅነትን ቢያተርፍም የወቅቱ የአገሪቱ ሁኔታ ያሳስበው እንደነበር ያስታውሳል::የ1983 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ በነበረው ጦርነት ነገሮች ጥሩ ባለመሆናቸው ባህር ማዶ ተሻግሮ ኑሮውን አሜሪካ ላይ ይመሰርታል::በአሜሪካ ቆይታውም ከይልማ ገብረአብ እና ከተስፋ ብርሃን ጋር በርካታ ስራዎችን ሰርቷል::በተለይም “ዜሮ ለዜሮ”፣ “ታሪክ ይፍረደው” እና “ኢትዮጵያ” የተሰኙ አልበሞቹ የወቅቱን ሁኔታ ያንጸባረቁና የሕወሓትን ስውር አላማ የሚያጋልጡ በመሆናቸው በመንግስት ጥርስ ተነከሰበት::ተቃዋሚ ተብሎ ተፈረጀና ወደ አገር ውስጥ መግባቱ ቀርቶ በአውሮፓና በአሜሪካም ስራዎቹን እንዳያቀርብ ወከባዎችም ጠነከሩበት::
“አሞራ በሰማይ ሲያይሽ ዋለ” የተሰኘውና በተወዳጅነቱ በብዙ ድምጻውያን የሚዜመውን ሙዚቃ አስመራ ውስጥ በኤርትራውያን ባንድ ነበር የሰራው::አሞራ በሰማይ ሲያይሽ ዋለን ብዙ ሰዎች ከመስራታቸው የተነሳም የመጀመሪያው ዘፋኝ ማን እንደ ሆነ መዘንጋቱን የሚናገረው ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ፣ ብዙዎቹ ሙዚቃዎቹ በሌሎች ድምጻውያን በመዜማቸው ቅሬታ ባይኖረውም ስሙን በመጥቀስ አሻሽለው ቢሰሩት መልካም ነበር ይላል::
በመቀጠልም የስደት ፍሬዎቹ የሆኑት “ሳብየ ኧረ ነይ ሳብየ”፣ “አሞግሱት አሉ” እና “የአባይ ዳር እንኮይ ሎሚ” የተሰኙት ሙዚቃዎቹ በመላው ዓለም ይበልጥ ተወዳጅ ሆኑለት::
“ከአባይ ዳር እንኮይ ሎሚ፣
ከወሎ ልጅ ከዳሚ፣
የለም የሚለኝ ማነው፣
አላምነው::
እጥፍ ዘርጋ እያለች የልቤ ሰላይ፣
መጣች የወሎ ልጅ በገራዶ ላይ” በማለት በምናቡ የሳላትን የወሎ ጉብል የገለጸበት ሙዚቃ ዛሬም ድረስ ምስል ከሳችና ለወሎዬዎች ያለውን ፍቅር የገለጸባት እንደሆነ ይሰማዋል::
አብዮተኛው ድምጻዊ
በሕወሓት አገዛዝ ዘመን ይደርስ የነበረውን አፈና ቀድሞ የተቃወመው ሻምበል በላይነህ፤ ሕወሓት የኢትዮጵያዊነት ጸር መሆኑን በመረዳቱ፤ በፖለቲካዊ ትግል እንደማይወድና፤ የትጥቅ ትግል ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ አምኖ ኤርትራ በረሃ ድረስ ገብቶ የትጥቅ ትግሉን ተቀላቅሎ እንደነበርም ይናገራል:: ሰራዊቱን በሙዚቃ ከማነቃቃት ባለፈም ስልጠና ወስዶ ብረት አንስቶ ለመፋለም ቆርጦ የተነሳበት ጊዜም ነበር::ወደ ወልቃይት በመምጣትም “ወልቃይት ጎንደር እንጂ ትግራይ ሆኖ አያውቅም” የሚለውን ሙዚቃ ቦታው ድረስ በመሄድ ታሪክ አጣቅሶና በመረጃ አስደግፎ በሰራው የሙዚቃ ክሊፕ ሙያውን ለእውነቱ አበርክቶታል::
ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ በዚህ ሁሉ ትግሉ፤ በውጭ አገር የሚገኙ አፍቃሪ ወያኔዎች የሙዚቃ ኮንሰርቶችንና በምሽት ቤቶች እንዳይሰራ ያላደረጉት ጥረት አልነበረም:: “የቀረው ይቅር እንጂ አገር አፍራሹን ወያኔን ደግፌ አልቆምም” በማለት የራሱን ጥቅም ጥሎ ለአገሩ ነጻነት ከ30 አመታት በላይ ሲታገል ቆይቷል::
“የወያኔ ደጋፊዎች 30 አመታትን ያለስራ ቢያስቀምጡኝም ጠንካራ ኢትዮጵያውያንም ነበሩና ድጋፋቸው አልተለየኝም” የሚለው ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ፤ በቅርቡ በነበረው የህልውና ዘመቻ እንደሌሎቹ ዲያስፖራ በገንዘቡ ብቻ አልነበረም የዘመተው:: በአካል ግምባር ድረስ ገብቶ በሙያው ለመፋለም በማሰብ ቤተሰቦቹን ሳያሳውቅ ወደ ኢትዮጵያ መጣ::በትክክል ግንባር ድረስ ገብቶ ለመታገል የሚያመቸውን መንገድ ሲፈልግ በራስ ተነሳሽነት ወደ ግንባር የዘመቱ “ዜማዎችን ለኢትዮጵያችን ዘማች ኪነት” የሚባል ስብስብ እንዳለ ሲሰማ እነርሱን አፈላለገ::በግጥምና ዜማ ደራሲው ተስፋ ብርሃን አማካኝነት ቡድኑን ተቀላቅሎ ከአንድ ወር ላላነሰ ጊዜ በግምባር የሚገኘውን ሰራዊት በማነቃቃት አገራዊ ሚናው ተወጥቷል::
በተለይም በጋሸና እና በላሊበላ ከተማ በነበረው ወሳኝ ግንባር ተገኝቶ ከሰራዊቱ ያገኘውን አድናቆት መቼም እንደማይዘነጋው ይናገራል:: በወረታ፣ በመራዊ፣ በመቄት በጋሸናና በላሊበላ መድረኮቹ ሙያዊ አበርክቶው የታዘበውን ሲናገር፤ “ከወታደሩ ወኔ በላይ ከሰራዊቱ ጎን በመሆን ግንባር ድረስ አብረው የዘመቱ ባለሀብቶችን ተግባር የሚደንቅ ነበር:: ብዙ ባለሀብቶች ጠፍተው ወደሌላ አገር መሄድ እየቻሉ ከሰራዊቱ እኩል ቀድመው በመገኘት ሰራዊቱን ሲያበረታቱና ሲመግቡ የነበሩትን በአካል አግኝቼ አድንቄያቸዋለሁ ኮርቸባቸዋለሁም” ይላል::
ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ ዘመቻውን ለታይታ ያደረገው ባለመሆኑ ወታደር ጋር ሂደው ፎቶ እየተነሱ የሚመለሱት አርቲስቶች እውቅና ሲሰጣቸው እርሱ አስታዋሽ በማጣቱ አላኮረፈም::ለአገር የሚደረግ ማንኛውም ተግባር ሽልማቱና እውቅናው የህሊና እርካታ እንደሆነ ይናገራል:: “በዛን አስቸጋሪ ወቅት በሙያዬ ማድረግ የሚገባኝን ባላደርግ ኑሮ የዕድሜ ልክ ጸጸት ይሆንብኝ ነበር፤ ግን ደግሞ በአስቸጋሪው ወቅት ግንባር ድረስ ተገኝቼ ከሰራዊቱ ያገኘሁት ምላሽ ከእውቅናና ሽልማት በላይ ሆኖልኛል” በማለት በኩራት ይናገራል::
ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ ህዝብ ለህዝብ ላይ የነበረው ሚና ጉልህ እንደነበር ብዙዎች ይመሰክሩለታል::በወቅቱ ለህዝብ ለህዝብ ቡድን የሚሆን አልባሳት መግዣ 80ሺ ብር ጠፍቶ ጉዞው ሊሰረዝ ሲል እሱና ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ አዋጥተው እንዲገዛ አድርገዋል:: አልባሳቱ ከተገዛ በኋላ ጓድ መንግስቱ ኃይለማሪያም ስራውን እንዳዩ ባስቸኳይ ሁሉም ነገር እንዲደረግና ጉዞው እንዲካሄድ በማዘዛቸው ገንዘባቸው እንደተመለሰላቸውም ያስታውሳል::
ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ በህዝብ ለህዝብ ጉዞ የታየው ኢትዮጵያዊ አንድነት ዛሬም እንዲመለስ ይፈልጋል:: በወቅቱ አሜሪካኖች ጉዞው እንዲሰናከል በገንዘብ ከማማለል ጀምሮ መኖሪያ ፍቃድ በመስጠት ለማስከዳት ያደረጉትን የመበተን ጥረት ሳይሳካ የህዝብ ለህዝብ አንግቦ የተነሳው ዓላማ መሳካቱን ሲያሳብ ይደነቃል::
ጥበብን ለበጎነት
ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ በበጎነቱም ይታወቃል::በአሜሪካን አገር ቆይታው 30 አመት ሙሉ ለአገሩና ለህዝቡ ነው የኖረው:: ለራሴ የሚለው ጊዜና ገንዘብ አልነበረውም፤ ይህን የሚመሰክሩለት አስተባብሮና ለምኖ ካሳከማቸው በላይ አሜሪካን አገር የሚኖሩ የሙያ አጋሮቹ ናቸው::
የአምባሰሏ ንግስት ድምጻዊት ማሪቱ ለገሰ በታመመችበት ወቅት ማሲንቆውን ይዞ እየዞረ ለምኖ እንድትታከም አድርጓል::ድምጻዊ አክሊሉ ስዩም፣ ድምጻዊት ዘሪቱ ጌታሁን፣ ድምጻዊ ታምራት ሞላ ታመው ህክምና ባስፈለጋቸው ጊዜ ጀርመንና ለንደን ድረስ በመሄድ ገንዘብ አሰባስቦ ህክምና እንዲያገኙ አድርጓል:: ኮቪድ-19 (ኮረና) ወደ ኢትዮጵያ የገባ ጊዜ ስራ ያቆሙ አርቲስቶችን ለመደገፍ የሙያ አጋሮቹን በማስተባበር ገቢ ሰብስቦ በአቻሬ ጫማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ልኮ ድጋፍ አድርጓል::
አገሩ በችግር ላይ ሆና ገንዘብ ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግ ከሰማ እንቅልፍ አይወስደውም:: በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር በኩል በሚቀርብለት ጥሪ ሁሉ ቀድሞ ከተፍ ይላል፤ ከሙያዊ አስተዋጽኦ ባለፈ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላሮችን አሰባስቧል::
ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ ስሜተ ስሱ ነው::ያለውን ክህሎት በሙሉ ለሰዎች ሲያውለው ይበልጥ ይደሰታል:: ያኔ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በታሰረበት ወቅት እንደማናችንም ስሜቱን በከንፈር መምጠጥ አልነበረም የገለጸው፤ በዜማው ነበር በግፍ መታሰሩን የተቃወመው:: “ወትሮም የካሳ ልጅ ቴዲ ሞት አይፈራም” በማለት አሞግሶ አዚሞለታል:: ሰዎች ፍትህ ሲጓደልባቸው አይወድም::በቴዲ አፍሮ መታሰር ከማዘን ባለፈ ከአሜሪካ ተነስቶ እንግሊዝ ለንደን ድረስ በመሄድ ሰላማዊ ሰልፍ አስተባብሮ ድርጊቱን ሲቃወም የቀደመው አልነበረም:: የአሁኗ ምርጫ ቦርድ ኃላፊ ብርቱካን ሚዴቅሳ ያኔ ከወያኔ የእስር ቤት ስቃይ በኋላ ወደ አሜሪካ ስትመለስ “የሴቶች አንበሳ ብርቱካን ሚዴቅሳ” በተሰኘው ዜማ ደማቅ አቀባበል አድርጓል::ለታማኝ በየነም ቢሆን ጀግንነቱን፣ አገር ወዳድነቱን እያየ ዝም ለማለት አልደፈረምና፤
“ብን ብሎ ቢጠፋ ሁሉም እየጣለህ፤
ከሺ መንገደኛ ታማኝ ትበልጣለህ” ብሎ አሞግሶ አዚሞለታል::በአሜሪካን ቆይታው ሶስት ልጆችን አፍርቷል::የሱን ሙያ የተከተለ ልጅ የለውም::ምክንያቱ ደግሞ በታዋቂነቱ ሲጠቀም፤ እንደ ሌሎቹ አሜሪካዊ ድምጻውያን ሀብት ባላማካበቱና የተረጋጋ ሕይወት ሲያሳልፍ ባለማየታቸው እንደሆነም ይናገራል::
“እንቁናት ኢትዮጵያ”
ከ33ዓመት በኋላ ወደአገሩ የመጣው ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ “እንቁናት ኢትዮጵያ” የተሰኘ የሲዲ ምርቃትና የሙዚቃ ኮንሰርትን አካቶ በስካይ ላይት ሆቴል ሰኔ 16/2014 ዓ.ም ከአድናቂዎቹ ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ይዟል:: በዚህ መርሃግብር ከአድናቂዎቹ ጋር ከመገናኘት ባለፈ “የድሮ ዘፈኖቼን ሰብስቤ በአዲስ መልኩ የማሳተሜ ዋናው አላማ ዘፈኖቼ የኔ መሆናቸውን እንዲታወቅልኝ ነው” በማለት የመርሃ ግብሩን አላማ ተናግሯል::
በድምጻዊ ሻምበል በላይነህ የአልበም ምርቃት ላይ ከአንጋፋዎቹ ጀምሮ አዳዲሶቹ ሙዚቀኞችን ጋብዟል::ሁሉም ድምጻውያን በነጻ እንዲታደሙ አድርጓል::ሊደግፉት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ብቻ ናቸው የመግቢያ ከፍለው የሚታደሙት ብሏል::
ወደፊትም በርካታ ግጥምና ዜማዎች እጁ ላይ ስላሉት ዘመኑን የሚዋጁ ጥሩ ጥሩ ስራዎችን ከግጥም ደራሲው ተስፋ ብርሃን እና ከዜማ ደራሲው አበበ ብርሃኔ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል::አሁን ለአድማጭ በሚደርሰው አልበም ሁለት አዳዲስ ዜማዎች የተካተቱበት ሲሆን ቀሪዎቹ ተወዳጅ የሆኑ የቀድሞ ስራዎቹን አካቶበታል::
መልዕክት
በመጨረሻም “የአገራችን ችግር እንደ ባህል ሆኖ እየቀጠለ ነው:: 30 ዓመት ሙሉ ብቻዬን ታገልኩ ለውጥም አምጥቻለሁ ብዬ አስባለሁ፤ የተሳሳትኩትም ነገር ይኖራል ብዬ አምናለሁ:: ይሁን እንጂ አሁን የተጠናወተን የዘር ፖለቲካ ለልጅ ልጆቻችን አልፎ ሊያጫርሰን አይገባም:: አንድ ቦታ ላይ ሊቆም ይገባል:: ዓለም በኢኮኖሚ እየጠነከረ ባለበት ዘመን እኛ እርስ በእርስ እንጋጫለን::ጦርነት ለማንም አይጠቅምም፣ ለልጅ ልጅ እያስተላልፈን የምናስጨርስበት መሆን የለበትም” በማለት ይናገራል::
“ጠንካራ መሪ ጠንካራ ህዝብ ይፈጥራል፤ ጠንካራ ህዝብም ጠንካራ መሪ ያወጣልና በ ”ፌስ-ቡክ” የሚመራ ህዝብ የትም አይደርስምና ህዝቡ በእውቀት ይመራ፤ አንድነቱን ያስቀድም” በማለት መልእክቱን አስተላልፏል::
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2014