ኢትዮጵያ ከውጭው ዓለም ጋር ፖለቲካል፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ግንኙነት ማድረግ የጀመረችው ከአክሱም ሥርዎ መንግስት በፊት እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ። በዚህ ወቅት የነበረው የኢትዮጵያ ግንኙነት ሁለንተናዊ ጥቅሟን ማስከበር ብቻ ሳይሆን የውጭውን ዓለም ተፅዕኖ ጭምር መመከት የቻለ እንደነበርም ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ከአክሱማይት ሥርወ መንግስት መዳካም ጋር ተያይዞ ብዙ ነገሮች እንዲቀየሩ ሆነዋል። አንዱ በአውሮፓ የተፈጠረው የአውሮፓዊያን ተሃድሶ (EUROPIAN RENASSANCE) ሲሆን፤ ሌሎች አገራትን ለመርገጥ የሚያስችላቸውን ስትራቴጂ የቀየሱበት ነው። ቀድመው ይዘውት የነበረውና ለዘመናት ሲከተሉት የቆየው በሃይማኖት እና በባህል ላይ ያተኮረው ተግባር አዋጭነት ያለው አልነበረም። ስለዚህም ወደ ሰውኛ ሥራ (humanistic activity) እንዲቀይሩት አድርጓቸዋል። ይህ ደግሞ ፍላጎታቸውን እንዲያሰርጹ ያገዛቸው እንደሆነም ይታመናል።
ይህ አስተሳሰባቸው ደግሞ ከአውሮፓ ውጭ ያሉ ዓለማትን ጭምር እንዲያውቁ ያጓጓቸውና ፍላጎታቸውን ያሰፋላቸው ሆኗል። በዚህም አውሮፓዊያን መላ ዓለምን ለማሰስ በቁ። እነአሜሪካን የመሰሉ አዲስ አህጉር የመገኘታቸው ምስጢርም ይኸው ነው። እነኚህ በአሳሽነት ስም በየአገራቱ የሚዘዋወሩ አውሮፓዊያን በንጉሳቸው እና በንግስታቸው ድጋፍ እንዲሁም በአሳሾ ፍላጎት የሌሎችን አገራት ጥቅም እየደፈጠጡ እንዴት የራሳቸውን አገር ጥቅም ማስከበር እንደሚችሉ በትጋትም ሰርተዋል። በዚህም በቀረው ዓለም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። በዚህ ዘመን ሃይማኖትን ሽፍን ተደርጎ በኢትዮጵያ የተፈጠሩ አገራዊ አንድነታችንን የሚፈታተኑ ጦርነቶች ዋና ተዋናኞችም እነሱም ስለመሆናቸው የሚሞግቱ የታሪክ ሰዎች አሉ ።
ከአጼ ፋሲለደስ ንግስና በኋላ ሸፍጠኞቹ አውሮፓዊያን ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ተደርገው ነበር። ሆኖም ሥራቸው እንዳይጠፋና እንዲቀጥል የተከሉት ነገር ነበር። አንዱ ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሲሆን፤ እንደ ቅባት፣ ጸጋ፣ የስጋ ልጅ ወዘተ የሚባሉት ተተክለው የቀሩት በዚህ ምክንያት እንደሆነም ይነገራል።
ከተሃድሶ ዘመናቸው ቀጥሎ የተፈጠረው ደግሞ አውሮፓዊያን በዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ ጫና እንዲያደርጉ መጓዝ ሲሆን፤ ለዚህ ማሳያው በፈረንሳይ የተጀመረው የምሁራን ንቅናቄ (Enlightenment) እና በእንግሊዝ ተጀምሮ በኋላም በመላ አውሮፓ የተዛመተው የኢንዱስትሪ አብዮት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። እነኚህ ሁለት ነገሮች የዓለምን ሁለንተናዊ ቁመና ቀይረውታል። በተጨማሪም የአውሮፓዊያንን ኃያልነት አሳይተዋል። በተለይም የኢንዱስትሪ አብዮት አውሮፓዊያኑ አፍሪካን እንዲቀራመቱ ያስቻለ እንደነበር ይገለጻል።
አውሮፓዊያን በበርሊን ኮንፈረስ ተስማምተው አፍሪካን ለመቀራመት ሲመጡ ከአውሮፓዊያን የቅርጫ ዝርዝር ውስጥ በግንባር ቀድምትነት የገባቸው ኢትዮጵያ ነበረች። በመካከለኛው ዘመን በኢትዮጵያ ላይ ያደረሱት ግፍ አልበቃ ብሏቸው የኢንዱስትሪ አብዮትን ተከትሎ ጣሊያን የተባለች በቅጡ እንኳን ያልተዋሀደች አገር በእንግሊዝ መንገድ ጠራጊነት ኢትዮጵያን የወረረችውም ለዚህ ነበር።
ለውጭ ጫና አይበገሬዎቹ ኢትዮጵያዊያን ጣሊያን በመጣችበት እግሯ አሳፍረው መልሰዋታል። በዚህም ቂም ያረገዙ ጣሊያውያንን በአንድ በኩል ሌሎች የአውሮፓ አገራት ደግሞ የአገሪቱን አንድነት አደጋ ውስጥ ለመጣልና ለጥቅማቸው ሲሉ በሌላ በኩል እየተጓዙ አጋጣሚዎች ሲጠብቁ ቆይተዋል። የ1906 ዓ.ም የንጉሰ ነገስት ምኒልክ መታመምና ንጉሰ ነገስቱ አልጋ ወራሽ የሚሆን ወንድ ልጅ ያለመኖራቸው የአገሪቱ ክፍተት ነው ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል።
ክፍተቱን ለመጠቀምም ሶስቱ የአውሮፓ አገራት ማለትም እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን የሶስትዮሽ ስምምነት (Tripartite treaty) ተፈራረሙ። የስምምነቱ ዓላማም ኢትዮጵያን በማተራመስ ለሶስት መቀራመት ነበር። ነገር ግን የአውሮፓዊያን ሴራ የገባቸው ንጉሰ ነገስቱ ክፋታቸውን የሚያሽር ሁነኛ መድሃኒት አበጁ። አንደኛው አልጋ ወራሼ ልጅ እያሱ ነው ብለው ያስነገሩት ሲሆን፤ ሁለተኛው ዘዴ ደግሞ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ማቋቋማቸው ነበር። በዚህም የአውሮፓዊያን ፍላጎት ድባቅ ተመታ።
ቀን ከሌሊት ለኢትዮጵያ የማይተኙት አውሮፓውያኑ አሁንም ሌላ ሴራ አሴሩ። ይህም በአዲስ አባባ ቆንስላ ጽህፈት ቤታቸውን በመክፈትና በቆንስላዎቻቸው አማካኝነት የኢትዮጵያን ስም በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ዘንድ ማጠልሸት ነው። በርካታ ቆንስላዎች እና ዲፕሎማቶችም ተግባሩን ፈጽመውታል። ከእነኚህ መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ‹‹ኢትዮጵያ የባሩድ በርሜል›› የተሰኘ መጽሐፍ ደራሲው የኦስትሪያው ዲፕሎማት ሮማን ፕሮቻዝካ አንዱ ነው። ይህ ሰው ከዲፕሎማሲያዊ ተግባሩ ባፈነገጠ መልኩ ኢትዮጵያን ሊያጠፋ የሚችል ሥራ ሲሰራ በመገኘቱ ከጣሊያን ወረራ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በ1927 ዓ.ም ከኢትዮጵያ የተባረረ ነው። በመጽሐፉም አውሮፓዊያን ኢትዮጵያን መበታተን/ ማጥፋት እንዳለባቸው አጥብቆ የመከረም ነበር። ይህን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ ኢትዮጵያ አፍሪካን አስተባብራ ለአውሮፓዊያንን ቀጣይ ስጋት ልትሆን እንድምትችልም አስጠንቅቋል።
መጽሐፉ በተጻፈ በዓመቱ በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን እንድትወር ሆነ። ኢትዮጵያን ለማጥፋትም የመርዝ ጋዝ እስከመጠቀም ተደረሰ። በዚህ ጊዜ የዓለም ማህበር አባል አገር የሆነችው ኢትዮጵያ የደረሰባትን በደል ለማሰማት ወደጀኔቭ ብትሄድም ነገሮችን ከራሳቸው ጥቅም አንጻር የሚያዩት አውሮፓዊያን ሊሰሟት አልወደዱም። እንደውም ይባስ ብለው በኢትዮጵያዊያን ቁስል ላይ ተሳለቁባት።
ይህን ጊዜ እጅ መስጠት የማያውቁት ኢትዮጵያዊያን በጋራ ተነሱ። ስላቃቸውን አስውጠውም አስጎነበሷቸው። በእብሪት የተወጠረ ልባቸውንም አፈነዱት። ማንም እንደማይደፍራቸው አስመሰከሩም። በአንድነታቸው አገራቸውን ታድገው ቀና ማለትን ለጥቁር ሁሉ አስተማሩም።
እነዚህ ሀይሎች ይህ ሁሉ አልበቃ ሲላቸው ኢትዮጵያንን በመከፋፋል የአገሪቱን አንድነት ፍጽም አደጋው ውስጥ ሊጨምሩ በሚችል መልኩ ወደ ውጭ ለትምህርት አውሮፓ እና አሜሪካ የሚሄዱ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ግማሾቹን በገንዘብ በመደለል ግማሹን ደግሞ በማታለል ኢትዮጵዊያን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ሰላም በመንሳት መከፋፋል የሚያስችላቸውን አውዳሚ የፖለቲካ መርዝ በፖለቲካ ቤተሙከራቸው ውስጥ ፈጥረዋልም። ይህም የብሔር ብሔረሰቦች መብት የሚል ሽፋንን የያዘ ሲሆን፤ በአሸባሪው ሕወሓት አስፈጻሚነት ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል። አሁንም ድረስ ለአገሪቱ ተግዳሮት ሆኖ የቀጠለ የፖለቲካ ነቀርሳ ሆኗል። ተግባሩ ሲፈጸም በፖለቲካ መርዙ የተበከሉት ኢትዮጵያዊያን አገር ውስጥ በመግባት ሌሎችን እንዲከትቡ በማድረግ ነው።
በዘመነ ደርግ ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን እርስ በእርስ የተበላሉት በዚህ ተክል ምክንያትም ነው። ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን ሕይወት መቀጠፍም ምክንያትም ነበር። ኤርትራን ከእናት አገሯ እንድትገነጠል ያደረገውም ይኸው ምስጢር ነው። ኢትዮጵያንም ያለ ባህር በር እንድትቀርም ያደረጋት ይኸው ጉዳይ እንደሆነ ነጋሪ አያሻውም።
በእርግጥ ከጥንት እስከዛሬ ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ የሚደግሱትን የጥፋት ድግስ በአንክሮ ስንመለከተው ለምን አይተውንም ያስብላል። መቼ ነውስ ከኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን የሚያነሱት እንድንል ያደርገናል። ይሁን እንጂ ኃያልነት ሁሉም የሚፈልገው ነውና መነካካቱ አይቀሬ ነው። እናም እንደአገር አይበገሬና አልደፈርም ባይነታችንን ለማስቀጠል ከፈለግን አንድነታችን ከምንም በላይ ማስቀደም ያስፈልገናል። መፈለጋችንንም ልንጠላው አይገባም።
ሌላው ከእኛ የሚፈልገው ትልቅ ማንነት አለን። ያንን ደግሞ አለማስነካት የእያንዳንዳችን ድርሻ ነው። ብርታታችን፤ ሀብታችንና ጀግንነታችን ዘላለማዊ እንጂ የአንድ ዘመን እንዳልሆነም ማመንና መተግበር አለብን። በአባቶቻችን አይበገሬነት እንዲሁም በሕብረ ብሔራዊነት የምዕራባዊንን የጥፋት ድግስ ማክሰምና ወደፊት መጓዝ ይጠበቅብናል። ለዚህ በጎ አሳቢነት ቀዳሚ ነውና እርሱን እንያዝ በማለት ለዛሬ አበቃን። ሰላም !!!
ክብረ ነገስት
አዲስ ዘመን ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም