
አዲስ አበባ፡- የሀጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽን የመጀመሪያውን የኪነጥበብ ሽልማት ሊያካሂድ መሆኑን አስታወቀ።
አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ለማስታወስ በስሙ የተቋቋመው ፋውንዴሽን ሰኔ 22 ቀን 2014 ዓ.ም ሃጫሉ ሁንዴሳ የተሰኘ የሙዚቃ ሽልማት (የአዋርድ) መርሐግብር እንደሚያካሂድ ታውቋል።
የሽልማት መርሐግብሩን አስመልክቶ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ባለቤትና የፋውንዴሽኑ የቦርድ አባል ወይዘሮ ፋንቱ ደምሰው ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ፋውንዴሽኑ ደረጃውን የጠበቀ የሙዚቃ ውድድር በማድረግ በኪነጥበቡ ዘርፍ ጠንካራ የፉክክር መንፈስ የመፍጠር ዓላማ አንግቧል።
በመጀመሪያው የሃጫሉ ሁንዴሳ ሽልማት መርሐግብር ከሰኔ 22 ቀን 2012 እስከ መጋቢት 22 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ለሕዝብ የደረሱ ዜማዎችና የዜማ ቪዲዮዎች ለውድድር ይቀርባሉ። ለውድድር የቀረቡት የኪነጥበብ ሥራዎችም ተገምግመው አሸናፊ የሆኑት በዕለቱ በሚዘጋጀው መድረክ ሽልማታቸውን ይረከባሉ ሲሉ አስረድተዋል።
የዘንድሮው የሃጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽን ሽልማቶች በኦሮምኛ የሙዚቃ ሥራዎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን የገለጹት ወይዘሮ ፋንቱ ደምሰው፤ ሽልማቱ ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚዘጋጅና በርካታ የጥበብ ዘርፎችን እያካተተ የሚሄድ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሚቀጥሉት የሀጫሉ ሁንዴሳ የኪነጥበብ ሽልማቶች ላይ ከኢትዮጵያም አልፎ አፍሪካውያን ድምጻውያኖችን ለማካተት መታቀዱን አስታውቀዋል።
እንደ ወይዘሮ ፋንቱ ገለፃ፤ ሀጫሉ ሁንዴሳ አዋርድ ደረጃውን የጠበቀ፣ ግልፅና ለኪነጥበቡ ዘብ በመቆም በአርቲስቶች መሀል ጤናማ የውድድር መንፈስ መፍጠር ይሻል። ፋውንዴሽኑም ደረጃውን የጠበቀ ውድድር በማድረግ በኪነጥበቡ ዘርፍ ለተሻለ ዕድገት መፍጠርን አላማ አድርጓል።
የዘንድሮው የፋውንዴሽኑ የሽልማት ውድድር አስር ዘርፎችን ያጠቃለለ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይ የዓመቱ ምርጥ ዘፈን፣ የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ክሊፕ ፣ የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ግጥም ፣ የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ዜማ፣ የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ አዘጋጅ/አቀናባሪ የሚሉ የውድድር ዘርፎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ክሊፕ ዳይሬክተር፣ የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ክሊፕ ኢዲተር የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ክሊፕ ሲኒማቶግራፊ፣ የዓመቱ ምርጥ ወንድ አርቲስት እና የዓመቱ ምርጥ ሴት አርቲስት የተባሉ ዘርፎችም በውድድሩ መካተታቸውን አንስተዋል።
ፋውንዴሽኑ ላዘጋጀው የሽልማት ውድድር አሸናፊዎች የሚለዩት ውድድሩን በሚመሩት ዳኞች በሚሰጥ የ70 በመቶ ጽምጽ ሲሆን፤ 30 በመቶው ጽምጽ የሚወሰደው ደግሞ ከሙያው አፍቃሪያን በሚላኩ የአጭር የጽሁፍ መልዕክቶች እንደሆነ ወይዘሮ ፋንቱ አስረድተዋል።
ከአጭር የጽሁፍ መልዕክቱ በተጨማሪ ሕዝብ ድምፅ እንዲሰጥበት የተዘጋጀ ድህረ ገጽ መኖሩን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ ባሉት ቀሪ ቀናቶች ለውድድር የቀረቡ የኪነጥበብ ሥራዎች ላይ ድምጽ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
ፋውንዴሽኑ በሃጫሉ ሁንዴሳ ስም የሚሰየም የሙዚቃ ተሰጽኦ ውድድር፤ አርቲስቶች የሚሰለጥኑበት እና ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት ሃጫሉ ሁንዴሳ የጥበብ ማዕከልን ማቋቋም እንዲሁም የፋይናንስ አቅም የሌላቸውን የኪነጥበብ ባለሙያዎች በማወዳደር የስቱዲዮ ሥራ ድጋፍ የማድረግ አላማ እንዳለውም ተገልጿል።
የሀጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽን የኪነጥበብ ሽልማት በየዓመቱ ሰኔ 22 ቀን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚከናወን ተገልጿል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም