ብዙዎቻችን ደግመን ደጋግመን ሰላም ለኢትዮጵያ፤ ሰላም ለአገራችን ይሁን በማለት ሰላም ውለን ሰላም እንድናድር እንመኛለን፤ እንናፍቃለን። ከምኞት ባለፈ ግን እጅግ ውድ የሆነውን ዋጋ ለሰላም ስንሰጥ አንስተዋልም።እኛ ኢትዮጵያውያን ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችለን የመጨረሻና ቀላሉ የሆነውን መነጋገር እንኳ ባህል ማድረግ አልቻልንም። ከመነጋገር ይልቅ መደነቋቆር፤ ከመደማመጥ ይልቅ መጯጯህ ላይ ቆመናል፡፡ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋጋጥ ሁነኛ መፍትሔ የሆነውን ሰላማዊ ውይይት ወደ ጎን በማድረግ ምርጫ መሆን የማይችሉ አማራጮችን አጀንዳ በማድረግ ሰላማችንን አደፍርሰናል፡፡
በአገራችን አሁን የተፈጠረው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሰላም ዕጦት ችግር ያመጣብን መዘዞች ናቸው ፡፡ እያንዳንዳችንም ለደፈረሰው ሰላማችን በአንድም ይሁን በሌላ የነበረን አበርክቶ የጎላ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን “ሳይቃጠል በቅጠል” ነውና የሰላም ሐዋሪያ በመሆን ከየትኛውም ጉዳያችን በፊት ሰላማችንን ቀዳሚ አጀንዳችን ማድረግ ይገባናል።የሁሉም ነገር መሰረት ሰላም ሲኖር ነውና ከሰላም የሚቀድም አጀንዳ ሊኖረ አይገባም፡፡
ሰላም ከሌለ እንኳንና ሰርቶ መብላት፤ ወጥቶ መግባት ይቅርና የበሰለ ምግብን ለአፍ ማድረስ የማይቻል ይሆናል።ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዛሬ አንድነታችንን በመሸርሸር ሰላማችንን ለማደፍረስ አጀንዳ እየሰጡን ላሉ የውስጥና የውጭ ጠላቶች መሳሪያ ባለመሆን የድርሻችንን የምንወጣበትና የሰላም ሐዋሪያ የምንሆንበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡
ሰላም በሌለበት ሁሉ ጦርነት፤ ጦርነት ባለበት ደግሞ ብዙ የሕይወት ምስቅልቅሎሽ ይከተላል። መተኪያ የሌላትን ውድ ሕይወት ከመገበር ባለፈ ጦርነት ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። በተለይም ህጻናትና ሴቶች እንዲሁም አረጋውያን ሰላም በሌለበት ቀዳሚ ተጎጂዎች የሆኑበትን አጋጣሚ በየዘመኑ ተመልክተናል፡፡ እንደአለመታደል ሆኖ ዛሬም በኢትዮጵያ ምድር ጦርነት፣ ስደትና ረሃብ እየተፈራረቀ ተዝቆ የማያልቅ መከራን ሊያስታቅፈን ከእያንዳንዳችን ደጅ ደርሷል፡፡
የሁሉም ነገር መሰረት የሆነውን ሰላም ገንዘባችን ለማድረግ ችግሮቻችንን በውይይትና በመደማመጥ ለመፍታት መነሳት ይህንንም ባህል አድርገን ማስቀጠል ይጠበቅብናል። ዜጎች ፍጹም ሰላማዊ የሆነ ኑሮን መምራት እንዲችሉና በምድራችን የተረጋጋ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር እያንዳንዳችን ለሰላም ድርሻ ሊኖረን ይገባል፡፡ በተለይም ከመሪዎቻችን የምንናፍቃቸውን ቀና መንገዶች እንመልከት፡፡
በየአቅጣጫው ለሚሰማው ኮሽታ ጆሮ ዳባ ልበስ ከማለት ይልቅ መፍትሔ በመስጠት ኮሽታው ቀጣይነት እንዳይኖረው እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ በተለይም የመኖር ዋስትና የኢኮኖሚ መሰረት የሆነው ግብርናችን በሚዘወርበት በዚህ ወሳኝ ወቅት መቋጫ ያልተገኘለት የሰሜኑ ጦርነት ስጋት ከመሆን ባለፈ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያጠላው ጥላ ወደፊት ሊያራምደን ስለማይችል መቋጫ ሊበጅለት ይገባል፡፡
መንግሥት ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በተለይም የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ፈጣን ምላሽ መስጠት ይኖርበታል፡፡ በሰሜኑ ጦርነትም ሆነ በሌላ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስና ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ ሰላም ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል። ከዚህ በኋላ የሚኖረው እልህ መጋባትና ግብዝነት ለማንም የማይበጅ ከመሆን ባለፈ አንዲት እርምጃ እንኳን ሊያራምድ አይችልም፡፡
ጦርነት በተለይም ደሃ በሆኑ አገራት ላይ የሚያጠላው ጥላ ከባድ ከመሆኑም ባለፈ ጥሎ የሚያልፈው ጥቁር ጠባሳው የጎላ በመሆኑ ይህው ላለፉት 17 ወራት ያሳለፍነው ጦርነት ባስከተለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎሽ በሕይወትና በንብረት ላይ ካደረሰው ጥፋት በላይ በቀጣይ የሚኖረው ጠባሳ ይበልጥ ያማል፡፡
ነገሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ ኢትዮጵያ ዛሬም ጦርነትን መሸከም በማይችል ኢኮኖሚዋ ጦርነትን ማስተናገድ ዕጣ ፈንታዋ ሆኗል፡፡ እርግጥ ነው ከጦርነት ውጭ ህልውናውን ማስቀጠል የማይችል የሚመስለው የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ከአፋር ክልል ወጥተናል ማለቱን ተከትሎ መረጋጋት ያሳየ ቢመስልም ከሰሞኑ ዳግም ግጭቶች ሊያገርሹ እንደሚችሉ መረጃዎች ያሳያሉ።
በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተካሄደው ይህው ጦርነት ታዲያ እንደ ማንኛውም ጦርነት በቀዳሚነት የበርካቶችን ሰላማዊ ኑሮ አናግቶ መተኪያ የሌላትን ሕይወት ነጥቋል፤ ረሃብና ጥሙን፣ ስደትና እንግልትም አስከትሏል፤ የሰው ልጅ ይፈጽመዋል ተብሎ የማይታሰቡ መጥፎ ድርጊቶች ሁሉ በአሰቃቂ ሁኔታ ተፈጽመውበታል፡፡ ለዚህ ሁሉ ጥፋት ማርከሻ መድሃኒት የሆነው ሰላም ከምድራችን የራቀ ቢመስልም የቱንም ያህል ርቀት ተጉዘን ሰላምን ማረጋገጥ ግን ምርጫ የሌለው የመጨረሻው አማራጫችን ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሁሉም ነገር መፍትሔና መሰረት የሆነው ሰላም አሁን ያሻታል፡፡ እርግጥ ነው አሁን ላይ ረገብ ያለ የሚመስለው የሰሜኑ ጦርነት ይበልጥ እንዲረግብና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በፌዴራል መንግሥት በኩል በርካታ ጥረቶች መደረጋቸው ይታወቃል። ይህ የመንግስት የተናጠል ጥረት በራሱ የተፈለገውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም። ያመጣል ብሎ መገመትም የዋህነት ነው።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በተጠናወተው የጥፋት መንገድ ሊመለስ የሚችልበትን የአስተሳሰብ መሰረት ሆነ እየተጓዘበት ካለበት የሽብር መንገድ ሊመለስና ለሰላምና ለሰላም አማራጮች እራሱን ሊያስገዛ ይገባል። እወክለዋለሁ የሚለውን የትግራይ ህዝብ እራሱ ከፈጠረበት ችግርና መከራ ለመታደግ ከከንቱ ጀብደኝነት ወጥቶ ለሰላም መስራት ይጠበቅበታል።
ኢትዮጵያውያን ለውስጥ ችግራችን እራሳችን መፍትሄ እንድንሆን የሚያስችሉ የቆዩና የካበቱ ባህሎች ባለቤቶች፤ ለዚህ የሚሆን ከእኛ አልፎ ዓለምን የሚያስደምም አኩሪ ባህል ያለን ህዝቦች ነን ።
ወደ ቀደመው ገናናነታችን እንመለስ ዘንድ ወደ አንድነታችን በመመለስ መነጋገርና መደማመጥን ቀዳሚ ባህላችን እናድርግ፡፡ በተለይም ዛሬ በአገሪቷ በአራቱም ማዕዘናት የሚሰሙና የሚስተዋሉ ጸያፍ ተግባራትን በማውገዝ የሁሉም ነገር መሰረት የሆነውን ሰላም ለማስፈን እያንዳንዳችን የሰላም ሐዋሪያ እንሁን።ስለ ሰላም ከማዜም ባለፈ ስለ ሰላም ዋጋ ለመክፈል እራሳችንን ማዘጋጀት፤ ስለ ሰላም የሚከፈል ዋጋ ከፍያለና ውድ መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም