በኢትዮጵያ እንደ ክሪፕቶከረንሲ፣ ቢትኮይንና የመሳሰሉት ዲጂታል መገበያያ ገንዘቦች ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ያልተሰጠው ድርጊት በመሆኑ ኅብረተሰቡ ከመሳተፍ እንዲቆጠብ ባንኩ አስጠንቅቋል።
ኢትዮጵያውያን በዲጂታል መገበያያ ገንዘብ እንዳይጠቀሙ ባንኩ ማሳሰቡ አገሪቱ ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ራሷን እንደማላቀቅ የሚቆጠር መሆኑን ደግሞ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ተናግረዋል።
ቢትኮይንና የመሳሰሉት ዲጂታል መገበያያ ገንዘቦችን አስመልክቶ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ግርማ እንደሚሉት፤ ክሪፕቶከረንሲ በስሩ እንደቢትኮይን የመሳሰሉትን የሚይዝ ሲሆን፣ ስሙ ኪሪፕቶግራፊ እንደማለት ነው። ክሪፕቶግራፊ ደግሞ የኦንላይ ደህንነት ስርዓት ነው። አንድን ዳታ ክሪፕቶ ማድረግ ምስጢራዊነቱን ጠብቆ ለማቆየት የምንጠቀምበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስርዓት ነው። ክሪፕቶግራፊ የሚባል ስርዓትን ተከትሎ የሚፈጠር ገንዘብ ነው።
መረጃዎችም እንደሚያመለክቱት፤ ቢትኮይኖችም ሆኑ ሌሎች ክሪፕቶከረንሲዎች የኢትንተርኔት ወይም የበይነ መረብ ላይ መገበያያ ናቸው። በቢትኮይን ግብይት ውስጥ ያሉት የተወሰኑ ኮዶችና የምስጢር ቁጥሮች ብቻ ናቸው እንጂ ምንም አይነት የሚጨበጥ ገንዘብ የለም። ቢትኮይን የተሰራው ማንነታቸው ላልታወቁ ግብይቶች እንደ ገለልተኛ ያልተማከለ ስርዓት ነው። በተጨማሪም ይህ ምንዛሬ ባለቤቶች የሉትም። ምናልባትም፣ የመንግስት አካላትም ሆኑ ትላልቅ ኮርፖሬሽኖች በመረጋጋት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር አይችሉም።
ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ገንዘብ አንድ ዋናው ባህሪው ደህንነቱ ወይም ምስጢራዊነቱን ለመጠበቅ እያንዳንዱ ኖት ላይ የየራሱ የሆነ ቁጥር ይደረግበታል ይላሉ። ይህን ቁጥር ባንኩ የሚያውቀው ሲሆን፣ ከዚህ ባለፈ ደግሞ በምሲጢራዊ ህትመት ውስጥ ያለፉ የማይታዩ ቁጥሮችም ይኖሩታል። ይህ ስምምነት ነውና ገንዘብ ተብሎ ሰው እንዲገበያይበት ስለሚደረግ አንዱ ባህሪው ተቀባይ መኖሩ ነው።
ወደክሪፕቶከረንሲ ስንመጣ ደግሞ ማዕከላዊ ባንክም ስለሌለው በዛ ስርዓት ውስጥ ላሉ ሰዎች ተዓማኒነቱን ለመጨመር የሚሰጥ ማስተማመኛ አለ። ያ ማስተማመኛ ‹ማይኒግ› በሚባል ቴክኖሎጂ ስርዓት ውስጥ የሚያልፍ ነው። በዓለም ላይ እንዲመነጩ የተደረጉ ቢትኮይኖች እስከ 2019 እኤአ 17 ሚሊዮን ነበር። ቢትኮይኑን እንዲመነጭ ያደረጉት በከፍተኛ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ነው።
ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ገንዘብ ማተም ሲባል የሚታተመው ወረቀት ነው፤ የሚጠይቀው መስማማትን ብቻ ነው፤ ስለሆነም መንግስት የቱንም ያህል ማተም ይችላል። ክሪፕቶከረንሲ ላይ ግን እንደርሱ አይደለም፤ የኮምፒዩተር ስርዓት ነው። እዛ ደረጃ ላይ ለመድረስ ደግሞ ብዙ ሂደት ስላለው ዝም ብሎ እንደወረቀቱ ብር የሚታተም አይደለም፤ አንዱም ተመራጭ ያደረገው ልክ የወርቅ ያህል የሚያልፈው መንገድ ፈታኝ በመሆኑ ነው ይላሉ። ከዚህም የተነሳ በጣም ጥረትን የሚጠይቅ ነው። ስለዚህም ክሪፕቶከረንሲ፤ ሳይንቲስቶች፣ የሒሳብ ቀመር አዋቂዎች፣ የሶፍትዌር ኢንጂነሮች በከፍተኛ የዘመኑ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሚፈጥሩት እንደሆነ ነው የተናገሩት።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ቢትኮይንን የፈጠረው ሰው ማንነት በግልጽ አይታወቅም። የሚጠራበት ስም የሐሰት ስም እንደሆነ ይነገራል። በእርግጥ የፈጠረው ግለሰብ አሊያም በቡድን ሊሆን እንደሚችልም ይገመታል። ቢትኮይንን ፈጠረ የተባለው ሰው እንዲኖሩ የፈቀደው እስከ 21 ሚሊዮን ቢትኮይኖችን ነበር። ማይኒንግ በሚባል ሂደት ውስጥ የተፈጠረው ቢትኮይን፣ የተፈቀደው 21 ሚሊዮን ቢሆንም እስከ እኤአ 2019 ድረስ 17 ሚሊዮን ቢትኮይን ተሸጧል። ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንግስት ባለ ሁለት መቶ ብር ይህን ያህል፣ ባለመቶ ደግሞ ይህን ያህል ነው ያተምኩት ሊል ይችላል፤ ልክ እንደዛ ሁሉ 21 ሚሊዮን ቢትኮይኖች መታተም አለባቸው ተብሎ ተወስኖ ከ21 ሚሊዮኑ 17 ሚሊዮኑ ሊሸጥ ችሏል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የቢትኮይን ፍላጎት ደግሞ ቀንሷል። ምክንያቱም ለምሳሌ የክሪፕቶከረንሲ የዋጋቸው ባህሪ በጣም ተለዋዋጭ ነው። አንዴ እኤአ በ2018/19 ገደማ አንድ ቢትኮይን አስር ሺ የአሜሪካ ዶላር ነበር። በዓመቱ ደግሞ በሶስት እጥፍ ቀንሶ ወደ 3 ሺ 500 ዶላር ገደማ ወርዷል። ተለዋዋጭነቱ ከፍተኛ በመሆኑ ፍላጎቱ በጣም እየቀነሰ መጣ። ዋጋውን የሚጨምረውና የሚቀንሰው በዛ የገንዘብ ስርዓት ውስጥ ያሉ ሰዎች ፍላጎት በመሆኑ ነው። አንድ ቢትኮይንን ውድ የሚያደርገው ለማመንጨት የሚወስደው ጊዜ ነው። ክሪፕቶከረንሲ ተለዋዋጭ የሚሆንበት ምክንያት በጅምር ላይ ያለ ኢንቨስትመንት በመሆኑ ነው። ራሱ የንግድ ስርዓቱ በየቦታው ባሉ ወኪሎች ፍላጎት የሚካሄድ ስለሆነ የተገደበ ጣራ የለውም።
ገንዘብ ማለት መተማመን ማለት እንደመሆኑ ቢትኮይን ላይ እምነት እንዲኖር በዳታ ዝውውር ወይም ኮድ ሲሰተም ነው ማምጣት የፈለጉት። ኩባንያዎች ደግሞ የሚፈልጉት ዋስትናን ነው። ምክንያቱም አንድ ኩባንያ ገንዘቡን እንደሚፈልገው አይነት ከዶላር ወደ የን ወይም ከየን ወደ ብር መቀየር ግድ ሊለው ይችላል። ከዚህም የተነሳ ኩባንያዎች ወዲህና ወዲህ ማለት ትርፉ ድካም ነው ብለው ስለሚያስቡ ወደቢትኮይን መግባት አማራጭ ነው ብለው ይወስዳሉ። ለዛም ነው ቢትኮይንን የፈጠሩት።
አሜሪካ ውስጥ ማይክሮሶፍትን ጨምሮ 14 የሚሆኑ ትልልቅ ኩባንያዎች ናቸው ተብሎ የሚታሰቡት። ከእነዚህ ኩባንያዎች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪም ያለ አበዳሪም ሆነ ወይም በባንክ ስርዓት ውስጥ ያለ ወይም እቃ የሚገዛ አሊያም ደግሞ ግብዓት የሚያቀርብ ሁሉ ተያይዟል ተብሎ የሚነገረው። ክሪፕቶከረንሲ በስሩ ብዙ ጉዳዮችን የያዘ ነው። የኮምፒዩተር ሶፍትዌሮች ኢንጂነሮች፣ በፋይናንስ ስርዓት ውስጥ ያሉ አካላት አሉ። በመሃል ደግሞ ስርዓቱን የሚመሩ ደላሎች አሉ።
ታዲያ ይህ ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ እኛ አገር ላይ እንዳይሰራ የተከለከለው ለምንድን ነው ሲባል በአገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታ፣ የፋይናንስ ዝውውሮችና ግኝቶች ሲመጡ የደህንነት ጉዳይ ነው የሚሆኑት። ገንዘብ ነውና ሰው ማግኘት የሚፈልገው ዋስትና አለ። እኛ ደሃ አገር ነን፤ ለምሳሌ አንድ ሰው አንድ ባንክ ላይ ያስቀመጠውን ገንዘብ መውሰድ ፈልጎ ቢከለከል መላ ህዝብ ገንዘቡን ከባንኩ ያወጣል። ባንኮች ላይ ተቀማጭ ገንዘብ አይኖርም ማለት ነው ይላሉ።
ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ እንደሚሉት፤ ሌላው ምሳሌ ኤቲኤምን (Automatic Teller Machine) በአገራችን ለማስተዋወቅ ምን ያህል ጊዜ ፈጅቶ እንደነበር ይታወቃል። በዚህ ደረጃ ያለን የፋይናንስ ስርዓት ክሪፕቶከረንሲ ሲመጣበት ሌላ ዱብ እዳ ነው የሚሆንበት። ሌላው ቀርቶ መንግስት የማይቆጣጠራቸው የገንዘብ ስርዓቶች ተብለው ቀርቶ መንግስት የሚያውቀውና የሚቆጣጠረው ላይ እንኳ ያለው ነገር ይታወቃል። ትልቁ ነገር ይህ ነው እንጂ ክሪፕቶከረንሲ ለሌብነት ይዳረጋል የሚባለው ነገር አንገብጋቢው ሆኖ ሳይሆን እሱ ለእኔ ሁለተኛው ምክንያት ነው።
በእርግጥ ፌክ ክሪፕቶከረንሲን መስራት እጅግ በጣም ከባድ ነው። ስለዚህ የውሸት ነገር ውስጥ እንገባለን የሚባለው ነገር ዋና ሆኖ አይደለም። ስለዚህ ዋናው ነገር ነባራዊ ሁኔታውን ያላገናዘበ፤ ማለትም አሁን ያለንበት የፋይናንስ እድገት ደረጃ ወቅቱ አይደለም የሚል እምነት አለኝ ይላሉ።
ሁለተኛው ደግሞ ቢሆን እንኳ ክሪፕቶ ከረንሲዎች በጣም ተለዋዋጭ ናቸው፤ ዛሬ አንድ ሺ ዶላር ሆኖ ነገ ሁለት መቶ ዶላር ሊሆን ይችላል። በነጋታው ደግሞ 50 ዶላር ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በጣም ተለዋዋጭ ስለሆነ እሱን መቀበል የሚችል የሕዝብ ስነ ልቦና አለ ወይ የሚል ጥያቄ የሚያጭር ነው። በውጭ አገር ያሉ አካላት ከዚህ የተነሳ ራሳቸውን እስከማጥፋት ደርሰዋል። ምክንያቱም በልጽገናል በሚሉ አገሮች ራሱ ተለዋዋጭነቱ ከፍ ያለ ተጽዕኖ አድርሷል።
ወደእኛ አገር ሲመጣ ደግሞ ያለችንን ሀብት ሙሉ በሙሉ ወደእዛ አሻገርን እንዲህ አይነት ተለዋዋጭ ባህሪ የሚያሳየን ከሆነ ይህን ቀውስ ሊሸከም የሚችል የስነ ልቦና ጽናት ይኖረናል ወይ የሚያሰኝ ነው። ስለዚህ የዚህ አይነት አደጋዎች ስላሉ አይመከርም ሲሉ ተናግረዋል።
ለእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ የማይመከርበት ሌላው ነገር የፋይናንስ ቁጥጥር ስርዓቱ እንኳን በቢትኮይን እየተመራ በማዕከላዊ ባንክ እንኳ እየተመራ ለገንዘብ ማጭበርበር እየተጋለጠ ነው። በአሁን ወቅት እንኳ ዶላር እየሸሸ ስለመሆኑ ማሰብ ያስፈልጋል። ስለዚህ በመደበኛ የገንዘብ ስርዓት ውስጥ እንዲህ አይነት ክፍተት ከተፈጠረ በማይታዩ ሰዎችና ስርዓት በሚተላለፍ ገንዘብ ደግሞ ምን ያህል አደጋ ሊደርስ እንደሚችል መገመት ይቻላል። እንዲህ ሆኖ እንኳ በእኛ አገር ውስጥ ክሪፕቶከረንሲን ለመግዛት ገንዘብ የሚያፈላልጉ አካላት እንዳሉ እየተነገረ ነው።
በእኛ አገር ውስጥ ጥቂት ባለሀብቶች በዚህ ጉዳይ የተቸገሩ አሉ፤ ንብረታቸው ብዙ አገሮች ላይ ያለ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች አሉ። ለምሳሌ ቢትኮይን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ምን ያህል ሊሸከም ይችላል ቢባል ዓለም አቀፍ ኢንቬስተሮቻችን እንዳሉበት መጠን ነው። ዓለም አቀፍ ደረጃ የደረሱ ኢትዮጵያውያን ኢንቨስተሮች ካሉ ቢትኮይንን የሚፈልጉት እነዚሁ ሰዎች ናቸው እንጂ ተራው ህዝብ አይደለም። ምክንያቱም ዓለም አቀፍ ላኪዎችና አስመጪዎች በግብይቶቻቸው መሃል የሚያጋጥማቸው ስለሆነ ነው። እነዚህ ሰዎች በቁጥር ጥቂቶች ቢሆኑም በኢኮኖሚ ደግሞ ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች በዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር ስርዓት ውስጥ ይቸገራሉ። ያንን ፈተና ለማለፍ ሲሉ ቢትኮይኖችን ገዝተው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውሩን ለማለፍ ይፈልጋሉ።
በዓለም ላይ ካሉ 190 ያህል አገራት መካከል በአሁኑ ጊዜ 113 አገራት ቢትኮይንን ይጠቀሙበታል። ስለዚህም በርካታ አገራት አጽድቀውታል ማለት ይቻላል። በእርግጥ የመገበያያ ስርዓትነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። እኛ ደግሞ ሌሎች አገራት የሚጠቀሙበትን የገንዘብ ዝውውር ማሳለጫ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በአብዛኛው እየተጠቀምንበት አይደለም።
ከዚህ ሌላ ደግሞ የቢትኮይን የገንዘብ ስርዓቱ የውጭ ምንዛሬ ሽሽትን እንዲያውም ያቀለዋል እንጂ እንዲቆም አያደርገውም። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ሁለት በመቶ አጠቃላይ አመታዊ ገቢዋን ከልማቱ የምታጣው በውጭ ምንዛሬ ገንዘብ ሽሽት ነው፤ በተለይ ይህ የሚታጣው በሚላኩና በሚገቡ እቃዎች አማካይነት ነው። በአሁኑ ሰዓት ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው እንደ አገሪቱ የመከላከያ ኃይል እኩል ለፋይናንስ ስርዓቱም ጥንቃቄ ማድረጉ ተገቢና አስፈላጊም ጭምር ነው።
ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ በአሁን ሰዓት ኢትዮጵያ እየተጠቀመችበት ያለው የዶላር ስርዓትን ነው ይላሉ። በዚህ ስርዓት ውስጥ ያለው ስምምነት ነው። ብዙ አገሮች ዶላርን ዓለም አቀፍ መገበያያ ስላደረጉት ከዚህም የተነሳ ዶላር ዓለም አቀፍ ገንዘብ ሆኗል። ለምሳሌ የዶላር ባለቤት አሜሪካ ናት፤ ብሔራዊ ባንኳ ያትማል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ደግሞ ዶላርን ለማግኘት አፈር ከድሜ ይበላሉ። ስለዚህ ለዓለም አቀፍ የገንዘብ ብዝበዛ መጋለጥ ይሆናል።
ምናልባት የምናገረው ሐሳብ ከዓለም የኢኮኖሚ ስርዓት ጋር ሊቃረን ይችላል፤ ምክንያቱ እነርሱ የዓለም የኢኮኖሚ ስርዓትንና ንግድን ያሳያል ይላሉ። ነገር ግን እኔ ከኢኮኖሚው በላይ የደህንነት ጉዳይ ስለሚታየኝ ነው። በእርግጥ የዓለም ኢኮኖሚ አንድ የመገበያያ ገንዝብ ቢኖርለት ምቹ ይሆናል። ነገር ግን ፍትሃዊ የሆነ የንግድ ስርዓት በሌለበት ዓለም ላይ እንዲህ አይነት የገንዘብ ዝውውር ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ስለዚህ ቢትኮይን የሚባለው ተጨማሪ የገንዘብ ዝውውር ያውም ማንነቱ በማይታወቅ አካል እየተዘወረ ስለሆነ ተጨማሪ ስጋት ነውና ለእኛ አደጋ ነው የሚሆነው። ወደፊት ጊዜ ብሎም ቴክኖሎጂ የሚፈታው ነገር ነው።
በአሁን ሰዓት ቢትኮይን ትልቅ አስደንጋጭ ክስተት ነው። ምክንያቱም ክሪፕቶከረንሲን በአሁን ሰዓት ለመቆጣጠር አስቸግሯቸዋል። እነርሱ ቴክኖሎጂያቸው የመጠቀ፤ የህግ ማዕቀፋቸውም ጠንካራ ሆኖ ባለበት ሁኔታ እንኳ እየተቸገሩ ነውና ልብ ማለቱ ይበጃል ባይ ነኝ።
ምናልባት አንዳንድ ኢንቨስተሮች ኢንቨስትመ ንታቸውን በሚያካሄዱበት አገር ላይ እየተጠቀሙ እንደሆነ እየታየ ነው። ይህም ለራሳቸው የሚመቻቸው ከመሆኑም በተጨማሪ በቀላሉ ገንዘብ ለማሸሸ እንዲያመቻቸውም ጭምር ነው። እኛ አገርም በቀላሉ ገንዘብ ለማሸሸ ነው በሚል ጥርጣሬው አለ። ስለዚህ የቀረው ይቅር ብለን ብሔራዊ ባንክ የወሰደው እርምጃ ተገቢነቱ ላይ ብናተኩር መልካም ነው።
ከምንም በላይ ኢኮኖሚክ ናሽናሊዝም ላይ እነ ራሽያ፣ ቻይና እና ኢራንን፤ ዓለም አቀፍ የሆነ የራሳቸው ባንክ ለማቋቋም እያጣሩ ባለበት በዚህ ጊዜ ይህንን ነገር መጠቀም ማለት አደጋ ውስጥ እንደመግባት ይቆጠራል። ይህን የእነርሱን ቢትኮይን መጠቀም ማለት ራስን ለውጭው አካል ለቅኝ ግዥነት እንደማመቻቸት ይቆጠራል። እኛ እነርሱ ያላቸውን የፋይናንስ ስርዓትና ቴክኖሎጂ እስካልታጠቅን ድረስ ያንን እንተግብር ብለን የምንነሳ ከሆነ ቅኝ ግዛትን በላያችን ላይ እንደማወጅ ነው የሚቆጠረው። ሌላው ቀርቶ ዶላር ራሱ እጥረት እንዲከሰትብን ምን ያህል እንደሚሰሩ እውን ነው። ከዛ ውጭ እንዲህ እንደቢትኮይን አይነት ቴክኖሎጂዎች ሲመጡ ዲዛይን የሚያደርጉት ለራሳቸው እንዲመች አድርገው ነው። ከኢኮኖሚም በላይ ደህንነታችንን በእጃቸው መዳፍ ውስጥ ለማድረግ ነው የሚጥሩት። እኛ ደግሞ የራሳችንን ቴክኖሎጂ ተጠቅመንና ሌሎች ላቅ ያሉ ነገሮች ኖረውን እንጂ እንዲሁ የምንቀላቀለው አይደለም። በእርግጥ አሁን ሊኖረን የሚገባ የፋይናንስ የድጂታል ስርዓቱም አለን ይላሉ።
የዩኤስ ብሔራዊ ደህንነት ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያ ሳየው፤ እኤአ 2009 የመጀመሪያው ብሎክ እና የመጀመሪያዎቹ 50 ቢትኮይኖች ተፈጠሩ። የመጀመሪያው የቢትኮይን ግብይት የተከሰተው 2009 ሲሆን፣ የመጀመሪያውም የቢትኮይን ገንዘብ ልውውጥ የተደረገው በዚሁ ዓመት መሆኑ ይታወሳል።
ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፤ የቢትኮይን አድራጊ ፈጣሪዎቹ ፈጠርነው የሚሉት ናቸው። ኢትዮጵያ ዶላርን እንኳ የግብርና ምርቷን እንዲሁም ማዕድኗን ሽጣ እንዴት እንደምታገኝ ይታወቃል። አሁን ደግሞ ተጨማሪ የሆነ ሌላ የገንዘብ ስርዓት ቢትኮይን የምንል ከሆነ ሌላ የእጅ አዙር የቅኝ ገዢን ቀንበር በራሳችን ጫንቃ ላይ እንደማስቀመጥ ይቆጠራል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7 /2014