በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን፤ 1957 ዓመት የታተሙትን ጋዜጦቻችንን አይተናል። በአዋሽ ሰባት ኪሎ ያለፈቃድ ሣላ ስለገደለው ጣልያናዊ ቱሪስት፤ በወቅቱ ግማሽ ሚሊየን የተባለው የአዲስ አበባ ነዋሪ በቀን 20 ሺህ ሜትር ኩብ ውሃ እንደሚጨርስ እና በቦርከና ወንዝ ላይ የተሠራ ድልድይ ለትራፊክ ክፍት ስለመሆኑ የሚያካትት ዜና ይዘናል።
ጣልያኑ ያ ለ ፈቃድ በማደኑ ፫፻ ብር ተቀጣ
ናዝሬት፤ ሲኞር ዳኮር ጆርጅ የተባለ ኢጣሊያዊ ተወላጅ ፤ሚያዝያ ፲፯ ቀን አዋሽ ሰባት ኪሎ መንገድ ሔዶ የአደን ፈቃድ ሳይኖረው፤ አንድ ሳላ ገድሎ ቀንዱን ይዞ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ፤ በወለንጪቲ ፖሊሶችና በደን ዘበኞች ተቆጣጣሪነት ስለተያዘ፤ የየረርና ከረዩ አውራጃ ግዛት ፍርድ ቤት በዓቃቤ ሕግ ሻምበል ተፈራ ደነቀ አማካይነት ተከሶ፤ ፫፻ ብር መቀጫ ከፍሏል። የተያዘውም የሣላ ቀንድ ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን ተወስኗል።
( ሰኔ 3 ቀን 1957 ዓ.ም
የታተመው አዲስ ዘመን)
፻፹፫ሺህ፫፻፶፭ ብር የፈጀው የቦርከና ወንዝ ድልድይ ሥራውን ጀመረ
በወሎ ጠቅላይ ግዛት ኮምቦልቻ አጠገብ የሚገኘው የቦርከና ወንዝ ድልድይ ተፈጽሞ ለትራፊክ አገልግሎት የተከፈተ መሆኑን የአውራ ጐዳና ባለሥልጣን የማስታወቂያ ክፍል ገልጧል።
ይኸው አዲስ የተሠራው ድልድይ ፶ ሜትር ርዝመትና ሰባት ሜትር ስፋት ሲኖረው፤ ፩፻፹፫ሺህ፫፻፶፭ ብር ፈጅቷል። በሥፍራው የነበረው የቀድሞ ድልድይ ባለፈው ክረምት በጐርፍ ኃይል መፍረሱ ይታወሳል። ይህንኑ ድልድይ እንደገና ለመሥራት የአምስት ወር ጊዜ የፈጀ ሲሆን እስከዛሬ ከተሠሩት ዘመናዊ ድልድዮች አንዱ ነው ሲል ይኸው የማስታወቂያ ክፍል በድጋሚ አረጋግጧል።
( ሰኔ 3 ቀን 1957 ዓ.ም
የታተመው አዲስ ዘመን)
የአዲስ አበባ ሕዝብ በቀን ፳ ሺህ ሜትር ይጨርሳል
በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነው ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ በየወሩ ፳ ሺህ ሜትር ኩብ ውሃ የሚጠጣ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የውሃ ክፍል ዳይሬክተር በሰጡት ወሬ ለመረዳት ተችሏል።
ውሃ ቤታቸው እንዲገባላቸው የሚጠይቁት ሰዎች ብዛት በወር ከ፪፻ እስከ ፬፻ ይደርሳል። የጠያቂዎቹ ብዛት እየጨመረ በመሄዱ የውሃ ክፍሉ ቆጣሪ አልቆበት ከውጭ አገር ለማስመጣት አስቧል። ቆጣሪው እስከ ሐምሌ ወር መጨረሻ ድረስ ስለሚመጣ፤ ሕዝቡ ቅሬታ ሊሰማው አይገባውም። የውሃ ክፍል የሕዝቡን ፍላጐት አሟልቶ ለመያዝ የሁልጊዜ ጥረቱ ስለሆነ ቅሬታ መፈጠር የለበትም ሲሉ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሕንፃ ለሚሠሩ ሁሉ አሸዋ ለሚያጠጡት ሸክላ የሚሠሩትና ከባድ ሥራ የሚያከናውኑት በዚሁ በተጣራ ንጹሕ ውሃ በመሆኑ ዳይሬክተሩ ቅር ተሰኝተዋል። ሕንፃ ሠሪዎች የሆኑ ሁሉ በጉድጓድ ውሃ ቢሠሩና የቧንቧን ውሃ ለመጠጥ ብቻ ቢያደርጉ ከፍ ያለ ዕርዳታ መሆኑን ገልጠዋል። በአሁኑ ጊዜ የአዲስ አበባ የውሃ ደንበኞች ከ፴፩ሺህ በላይ ደርሰዋል።
በገፈርሳ ውሃ ላይ ተጨማሪ እንዲሆን የታሰበው ሁለተኛው ገፈርሳ ሥራውን ከሁለት ዓመት በኋላ እንደሚጀምር ተገልጧል። ይኸውም አዲሱ ገፈርሳ ፲ሚሊዮን (አሥር ሚሊዮን)ሜትር ኩብ የሚይዝ ሲሆን፤ ከአሁኑ ገፈርሳ ጋር ፲፯ ሚሊዮን(አሥራ ሰባት ሚሊዮን) ሜትር ኩብ ፤የከተማውን የውሃ ችግር ከመቼውም የበለጠ ሊያቃልል እንደሚችል ተነግሯል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን በከተማው ሕዝብ ላይ ምንም ዓይነት የውሃ እጦት አይታይም።
የአዲሱ ገፈርሳ ግድብ ማጣሪያ ፲፮ ሚሊዮን ፹፫ሺህ ፰፻፭ (አሥራ ስድስት ሚሊዮን ሰማንያ ሦስት ሺህ ስምንት መቶ አምስት ብር) ይፈጃል። በጨረታውም የጀርመን፤ የኢጣልያ፤ የእንግሊዝና የፈረንሳይ አገር ሰዎች እንደሚወዳደሩ በወሬው ተመልክቷል።
የአዲሱ የገፈርሣ ውሃ ግድብ ቢበዛ እስከ መስከረም ፶፰ ዓ.ም ድረስ ከቆየ በኋላ ከዚያ ለጨረታው አሸናፊ ሥራው የሚሰጥ መሆኑን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
በየቦታው ውሃ በእንሥራ ለሚቀዱ በአንድ ሣንቲም ሒሳብ ያስከፍላል። አንዱን ሜትር ኩብ በ፴ ሣንቲም ሒሳብ ያስከፍላል። በየቤቱ ያሉት ግን ለአንድ ሜትር ኩብ ውሃ ፶ ሳንቲም የሚከፈል መሆኑ ታውቋል።
አዲሱ የገፈርሣ ሥራ እስካለቀ ድረስ ለሕዝቡ የሚያገለግል አንድ በጣም ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ በቅርቡ ይቆፈራል።
( ሰኔ 5 ቀን 1957 ዓ.ም የታተመው
አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7 /2014