የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የስትራቴጂ ሰነድ የግብርና ዘርፍ 32 ነጥብ 8 በመቶ፣ አጠቃላይ አገራዊ ምርት 85 በመቶ የአገሪቱን የሰው ኃይል፣ እንዲሁም 90 በመቶ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠቁማል። እንደ ስትራቴጂ ሰነዱ መረጃ ከሆነ፣ በአገሪቱ የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂ እንቅስቃሴዎች ሲኖሩ፤ በዋናነት የሚጠቀሱት በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ እና በአጋሮቹ የሚመሩት እንደሆኑ ይገልፃል።
የዲጂታል ግብርና ስርአት/ ሲስተም/ መገንባትና የግብርና ቴክኖሎጂ ስራ ፈጠራን መደገፍ እና ማበረታታት አስፈላጊ መሆኑን የሚጠቅሰው ይሄው ሰነድ፤ በመጀመሪያው በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠትና ለመተግበር የሚያስችል የተቀናጀ ስርዓት መፍጠር፤ ሁለተኛው ደግሞ ፈጠራን፣ የስራ እድል ማስገኘትን እና አካታችነትን የሚያበረታታ የግብርና እና ተዛማጅ ዘርፎች ለውጭ ገበያ በማቅረብ ብቃት አስፈላጊነት ላይ ያወሳል።
የሰለጠኑትና በኢኮኖሚ የበለፀጉት አገራት በተለይ የግብርና ዘርፋቸውን በቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ የምርምር ውጤት ማገዝ አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸው ይነገራል። ከዚያ ባለፈ ግለሰቦች እውቀትና የፈጠራ ክህሎታቸውን ተጠቅመው የሚያስተዋውቋቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና የፈጠራ ሃሳቦችም እንዲሁ ዘርፉን በእጅጉ ካዘመኑና ዓለም የደረሰበትን የእድገት ደረጃ ከበየኑት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል እንደሆኑም ይገለፃል። በዚህ ምክንያት ለወጣቶችና ግለሰቦች የመፍጠር አቅም ልዩ ትኩረት ድጋፍ ይደረጋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም “በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” የስትራቴጂ ዶክመንት ላይ የፈጠራና አዳዲስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሃሳቦችን የሚያፈልቁ ባለሙያዎችን ማበረታታት አንዱ ግብ መሆኑን አስምሮበታል። በመሆኑም የአገሪቱን የግብርናና መሰል ተያያዥ ፖሊሲዎች ከዚህ አንፃር እንዲቃኙ በመስራት ላይ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተለይ ከስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ጋር በተገናኘ ወጣቶች ግብርናን ጨምሮ ልዩ ልዩ ዘርፎች ላይ ያላቸውን የፈጠራ ሃሳብ እንዲያሳድጉና ለማህበረሰቡ እንዲጠቅሙ ድጋፍ እንደሚደረግ እየወጡ ያሉት መረጃዎች ያመለክታሉ።
የህሊና መንገድ
የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አምድም ከዚህ ከፈጠራና አዳዲስ ሃሳቦች ጋር በተያያዘ በግብርናው ዘርፍ ለየት ያለና ያልተለመደ የቴክኖሎጂ ሃሳብ ይዛ ብቅ ያለች ወጣት አዲስ ቴክኖሎጂ ሊያስተዋውቃችሁ ወድዷል። ይህቺ ወጣት በዓለማችን ላይ ከሚተገበሩ ሳይንሳዊና በቴክኖሎጂ የተደገፉ የግብርና ዘዴዎች መካከል “ሲድቦል ቴክኖሎጂ” አሊያም ዘርን ባልተለመደ መንገድ (ፍሬውን በኳስ አሊያም ልጆች በሚጫወቱበት ብይ መልክ በአፈርና በማዳበሪያ መልክ በማዘጋጀት) የመትከል ፅንሰ ሃሳብን በተግባር ላይ እያዋለች የምትገኝ ነች።
በሙያዋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርክቴክቸር (ንድፍ) ትምህርት (በተለይ በቤት ውስጥ ዲዛይን ላይ ትኩረቷን አድርጋ) የተከታተለች ሲሆን፣ የማህበረሰቡን የአኗኗር መንገድ የሚቀይሩ የቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ የፈጠራ ሃሳቦች ላይ በስፋት በመሳተፍ ትታወቃለች። በተለይ ዓለማቀፍ ንቅናቄዎችና በተፈጥሮና የስራ ፈጠራ ዙሪያ ላይ በሚሰሩ ተቋማት ላይ “young african leaders initiative alumni”፣ “The Women Entrepreneurship for Africa (WE4A)”፣ “Connect4Climate” በመሳተፍም ትታወቃለች፤ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በምትሰራቸው ስራዎች የ“climate change for east africa earth champions” ነች። የዛሬ እንግዳችን ወጣት ህሊና ተክሉ “የሲድቦል ኢትዮጵያ” መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ።
ወደ ራዕይ የሚደረግ ጉዞ
ህሊና የከፍተኛ ትምህርቷን እስክትጀምር ድረስ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታዋ በፈጠራና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሃሳቦች ላይ እምብዛም ተሳትፎ አልነበራትም። ከዚያ ይልቅ ትማርበት በነበረው ስኩል ኦፍ ቱሞሮው ትምህርት ቤት የድራማና ቲያትር ክለብ ውስጥ መሳተፍን ትመርጥ ነበር። ይሁንና የረጅም ጊዜ ፍላጎቷ ወደሆነው የአርክቴክቸር ትምህርት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህንፃ ኮሌጅ ስትቀላቀል አዳዲስ ሃሳቦችና የፈጠራ ስራ ላይ ያተኮሩ ዝንባሌዎችን ታዳብር ጀመር። በተለይ “sustainable architecture” ማለትም የአየር ንብረት ተፅእኖን የሚቀንሱና በትንሽ ወጪ ለበርካታ ዜጎች መኖሪያ ቤት መገንባት የሚያስችሉ ሃሳቦች ትኩረቷን ይስቡት ጀመር። በተለይ ከሶስተኛ እስከ አምስተኛ ዓመት ተማሪ በነበረችበት ወቅት ከጭቃ፣ ከኮንቴይነር፣ ከአሸዋና ከቀርከሃ በቀላሉ የመኖሪያ ቤት ለመስራት በሚደረጉ አዳዲስ ሃሳቦች ላይ ተሳታፊ ትሆን ጀመር። ይህ ተሳትፎዋ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥን በሚገቱ ሃሳቦች ላይ ይበልጥ እንድትሳብና በዚያ ዙሪያ ላይ እንድትሰራ መንገዱን ጠረገላት።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቃ እንደወጣች የአየር ንብረት ችግርን የሚቀርፉ ሃሳቦችን ለማመንጨትና አዳዲስ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ስራዎች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያድርባታል፤ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን ትሳተፍ ነበር። በዋናነትም ከ“Young African Leaders Initiative (YALI)” የአየር ንብረት ተፅእኖን ለመቀነስ በሚደረጉ ሃሳቦች ላይ ስልጠና በመውሰድ የእውቀት አድማሷን አስፍታ ሰርተፍኬት መውሰድ ቻለች።
ወዲያው “climate change Africa” የሚል ኩባንያ አቋቋመች። በዚያም ኤክስፖዎችን ከማዘጋጀት ባለፈ በመላ ኢትዮጵያ በመዞር ኢትዮጵያውያን በጉዳዩ ላይ የእውቀት ሽግግር በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ሃሳቦችን እንዲደገፉ እድሉን በማመቻቸት ልዩ ልዩ ስራዎችን ታከናውን ጀመር። በመሃል ግን በውጪ አገር ከሚኖር የምታውቀው ሰው በምትመካከርበት ወቅት በኢትየጵያ ውስጥ አዲስ ስለሆነና የአየር ንብረት ተፅእኖን ከመቀየር ባለፈ ለአርሶ አደሩ፣ ለመንግስትም ሆነ በግብርናውና ደን ልማት ላይ ለሚሰሩ ሁሉ ቀላልና ለአሰራር ምቹ የሆነ የዘር አዘገጃጀትና አተካከል ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ ውጥን (ሃሳብ) ተከሰተላት። ይሄ ሃሳብ ግብርና ላይ ያተኮረ ሲሆን “ሲድቦል ኢትዮጵያ” ኩባንያ ቴክኖሎጂን እንድትመሰርት ያስቻላት ነበር።
“ሲድቦል” ምንድን ነው?
“ሲድ ቦል ምንም አይነት ኬሚካል ሳይገባበት የዶሮ ኩስን እንደ ማዳበሪያ በመጠቀም የሚዘጋጅ አነስተኛ ክብደት ያለው በአፈር ዘሩን እንደ ኳስ በማድቦልቦል የሚዘጋጅ ነው” የምትለው የሲድ ቦል ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ህሊና፤ ዋናው አላማ ችግኝ ማፍላት አሊያም ረጅም ጊዜ የሚወስደውን የዘር ማፍላት ሂደት ለማስቀረት ያለመ ቴክኖሎጂ እንደሆነ ትናገራለች። በተለይ ለአረንጓዴ ልማት የሚውለውን ችግኝ አፍልቶ እስከ መትከል ያለውን ሂደት ለማድረስ ጊዜ፣ ቦታና ሌሎች ረጅም ሂደቶች እንዳሉት በመግለፅም “ሲድቦል” ይህንን የሚያስቀር እንደሆነ ትገልፃለች።
እንደ ህሊና ገለፃ፤ የሲድቦል ቴክኖሎጂ ብዙ ሂደቶችን የሚያስቀር ነው። በተለይ በችግኝ ተከላ ወቅት የሚጠይቀውን ቁፋሮ፣ የመትከል ሂደት እንዲሁም በሰው ሃይል ሊደረስባቸው የማይችሉ ተራራማና የሸለቆ ቦታዎችን በደን በቀላሉ ለመሸፈን በድሮንና በአውሮፕላን ተጠቅሞ ለመዝራት የሚያስችል ነው።
በአፈርና ማዳበሪያ ተጠቅሎ በኳስ መልክ የተዘጋጀው ዘር አሊያም “ሲድቦል” በማብቀል ሂደቱ ከመሬቱ በላይ የሚቀመጥ ሲሆን የሚሸፈንም አይደለም። አጠቃላይ ክብደቱ 2ነጥብ2 ግራም ሲሆን ማንኛውም ዘር ያለው ችግኝም ሆነ አትክልት በቀላሉ ቴክኖሎጂ እንደሚዘጋጅ ትናገራለች። ከዚህ ቀደም ሰፊ ሽፋን የሚይዘው ከአየር ላይ ዘርን የመዝራት ሃሳብ በብዙ ምልኩ አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልፃ በተለይ 50 በመቶ ብቻ የሚሆነው መሬት ላይ እንደሚደርስ ቀሪው በአእዋፋት እና በንፋስ እንደሚወሰድ ትናገራለች። ሲድቦል ቴክኖሎጂ ግን ክብደት ባለው አፈርና ማዳበሪያ የሚጠቀለል በመሆኑና ወፎችም ሆኑ ማናቸውም እንስሳት በቀላሉ ሊያገኙት ስለማይችሉ ብክነት እንደሌለውና በልዩ ሁኔታ ተመራጭ እንደሚያደርገው ታነሳለች።
ሲድቦል ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት
ህሊና ላለፉት አራት ዓመታት በቴክኖሎጂው ላይ ከማጥናቷም ባሻገር የሲድቦል ፅንሰ ሃሳብን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ጥረት እያደረገች ነው። ፍቃድ አውጥታና ለተወሰኑ ሰዎች የስራ እድል ከፍታ በርካታ ዘሮችን በሲድቦል መልክ በማዘጋጀት ገበያ ላይ በውስን መልኩም ቢሆን (በዞማ ሙዜም የሳርቤት ቅርንጫፍና በአንድነት ፓርክ ውስጥ በሚገኘው) እያቀረበች ትገኛለች።
አሁን ደግሞ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ የግብርና ምርምር ቴክኖሎጂ ላይ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር ለመስራት ጥረት እያደረገች ነው። በተለይ ይህ ቴክኖሎጂ ለአርሶ አደሮች መቅረብ ስላለበትና በሰፊው መተዋወቅ ስለሚኖርበት በዚያ ጉዳይ ከግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አብራ ለመስራት ለመነጋገር ጥረት እያደረገች መሆኗን ትገልፃለች።
ዋና ስራ አስፈፃሚዋ “ኢትዮጵያውያን በምግብ ራሳችንን እንድንችል ብዙ ፀጋዎችና በረከቶች የታደልን ነን። ያንን ግን መመልከት አልቻልንም” ትላለች። ይህ እንዲቀር ወጣቶች የፈጠራና አዳዲስ ሃሳቦችን የማስተዋወቅ አቅማቸውን ተጠቅመው እውን ሊያደርጉት ይገባልም ትላለች። እሷም በአጭር ጊዜ ውስጥ ፕሮጀክቱ በመላው ኢትዮጵያ እንዲስፋፋና የአገሪቱን ኋላቀር የግብርና ስራ በቴክኖሎጂና በሳይንሳዊ መንገድ እንዲቀየር የበኩሏን ማበርከት እንደምትፈልግ ትናገራለች። ህሊና በአሁኑ ሰዓት የሲድቦል (የዘርኳስ) ዘዴን ለኢትዮጵያ የግብርና ዘዴ እንዲመች በማድረግና አዳዲስ የምርምር ስራዎችን በማከናወን በመላው አገሪቱ እንዲተዋወቅ በመስራት ላይ ትገኛለች።
የዘር ኳሶችን “ሲድቦል” በጥንት ግብፃውያን የዓባይ ወንዝ ከዓመታዊ የጎርፍ መጥለቅለቅ በኋላ በወንዙ ዳርቻዎች ላይ ባሉ ደለል የሚተኛበት ስፍራ ላይ ለመዝራት ይጠቀሙባቸው እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳናል። በእስያ እና በሌሎች አካባቢዎች በተለይም በደረቃማ አካባቢዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውንም መረጃዎች ያመለክታሉ።
በዋናነት ዘሮቹ ለመብቀል ምቹ ሁኔታ እስኪፈጠርላቸው ድረስ ደህንነታቸው የተጠበቀ እና በቀላሉ እንዳይጎዱ ይጠብቃቸዋል። በ1700ዎቹ በካሮላይና የምዕራብ አፍሪካ ባሮች፣ በአፍሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለውን የዘር ኳስ ዘዴ በመጠቀም ሩዝ ያመርቱ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህም ዘርን ከአእዋፍ በመጠበቅ እና ማሳው በሚጥለቀለቅበት ጊዜ እንዳይንሳፈፍ በማድረግ ረገድ የሲድቦል ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ጠቀሜታ ነበረው። አሁንም ምእራባውያንና የበለፀጉ አገራት በሲድቦል ቴክኖሎጂ ሰፊ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ እንዲሁም የተሻሻሉ ዘዴዎችን በማስተዋወቅ ይጠቀሙበታል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7 /2014