‹‹እኔ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ በመሆኔ እድለኝነቴን ዛሬ አይቻለሁ። ተስፋዬንም ከአሁን ጀምሮ ሰንቄያለሁ። ምክንያቱም ቀጣይ አራት ዓመታት በዲጅታል ቴክኖሎጂው እጠቀማለሁ። የተሻለች ተማሪ መሆንም እችላለሁ። በተለይም ምንም ኮምፒዩተር ነክቼ አለማወቄ ጉጉቴን አግዝፎታል። አዲስ ነገር ለማወቅም ሁልጊዜ እንደምሰራ ለራሴ ቃል እንድገባም አድርጎኛል። በተስፋና በተግባር የተደገፈ ትምህርት ደግሞ የታሰበበት ላይ እንደሚያደርስ አምናለሁ። ስለዚህም ኢትዮ ቴሌኮም ለሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ››ⵆ ኢትዮ ቴሌኮም የዲጅታል ትምህርት ማዕከላትን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት አቋቁሞ ባስመረቀበት ጊዜ በከፍተኛ 23 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምትማረዋ ልጅ ከመድረኩ ላይ ወጥታ የተናገረችው ነው።
ይህ እድል እርሷንና መሰሎቿን ለማንቃት፣ ለማሻሻልና የአገር ጠበቃ ለማድረግ የመጣ በመሆኑ በደስታ ነው ሃሳቧን የገለጸችው። በተመሳሳይ ይህንኑ ሃሳብ የሚጋሩት የቀድሞ የከፍተኛ 23 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪና የአሁኑ የኢትዮ- ቴሌኮም ተፊክስድ ኔትዎርክ ቺፍ ኦፊሰር አቶ ቴዎድሮስ ኃይለመስቀል፤ ይህ ጊዜ ብዙ እድል የሰጠበት ነው። በተለይ ተማሪዎች ከተጠቀሙበት እድለኛ የሆኑበት ወቅት ነው። ቴክኖሎጂውን በኮምፒዩተር ብቻ ሳይሆን በእጅ ሞባይላቸው ጭምር ይዘው የሚዞሩትና ለመረጃ ቅርብ የሚሆኑበትም ነው። እናም እድለኝነታቸው በቃላት የሚገለጽ ካለመሆኑም በላይ የመማር ማስተማር ስራውን በብዙ መንገድ ያሳልጣል ይላሉ።
አቶ ቴዎድሮስ እንደሚሉት እርሳቸው ተማሪ በነበሩበት ወቅት ቤተመጸሐፍት አግኝቶ ለማጥናት እንኳን ከሰዓት በላይ በእግራቸው ይጓዙ ነበር። ኮምፒዩተርማ የማይታሰብ ነበር። እናም ትምህርት ከመጸሐፍት ውጪ የለም። እርሱም ቢሆን እንደልብ ከተገኘ ነው። ስለሆነም ከኮምፒዩተር ጋር የተዋወቅነው ሥራ ላይ ሳለን ነው በማለት ተማሪዎች ይህንን አጋጣሚ በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ መክረዋል። ነገር ግን ይህንን ቀላል መንገድ መጠቀሙ ደግሞ እንዳያዘናጋቸውም ጥንቃቄ ማድረግም ይገባል ባይ ናቸው።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩም በበኩላቸው በእርሳቸው ጊዜ ተማሪዎች የሚገጥማቸው ችግር በቀላሉ የሚገለጽ እንዳልነበረ ያስታውሳሉ። ኮምፒዩተር ሳይንስ ጭምር በዲግሪ የተመረቁ ተማሪዎች ዳግመኛ ካልተማሩ ለመሥራት የሚቸገሩበት ሁኔታ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ይህ ደግሞ ጊዜንና ገንዘባቸውን እንደሚወስደውም ያወሳሉ። ምክንያቱ ደግሞ ከታች ጀምሮ አለመማራቸውና ከቴክኖሎጂው ጋር አለመተዋወቃቸው ነው። ዩኒቨርሲቲ እስኪገቡ ድረስ ብዙዎች ኮምፒዩተርን አይጠቀሙም። ዩኒቨርሲቲም ከገቡ በኋላ ገና ዳዴ ስለሚሉ ቶሎ እውቀቱን ለመጨበጥ ይቸገራሉ። ከወጡ በኋላም ለመቀጠር ወኔ የማይኖራቸው ለዚህ እንደሆነ ያስረዳሉ።
የሚቀጥር ሰው ለማግኘት አቅምና ችሎታ ግድ እንደሆነ የሚያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ ጊዜ ፈጅተው ዳግም ኮምፒዩተር ሴንተር ገብተው ለመለማመድ የሚያስገድዳቸውም ይህ ጉዳይ ነው። ግን ዛሬ ነገሮች አልፈዋል። የአሁን ተማሪዎች በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ብዙ ነገርን የሚያቀሉበትን እድል አግኝተዋል። ትምህርታቸውን ጭምር በቀላሉ ለማጥናትና የፈለጋቸውን መረጃ ለማግኘት ምንም አይቸገሩም። ይህ ደግሞ ተማሪ ሆነውም ቢሆን የመሥራት እድላቸው እንዲሰፋላቸው ያደርጋል። በአግባቡ ከተማሩና ከተመረቁ በኋላም ስለ ቅጥር የሚያስቡት ነገር እንዳይኖር የሚያግዛቸው ነው። ሆኖም ለተጠቀመበት እንጂ ላየው አይደለም ይላሉ።
እንደ ወይዘሪት ፍሬህይወት ገለጻ፤ የቴሌኮም አገልግሎቶችን መጀመር ብዙ ነገሮችን ለተማሪዎች መስጠት ነው። ያልተማረውን ማሕበረሰብ ጭምር ማገዝ ነው። ምክንያቱም አገልግሎቱ በአንድ ቦታ የተወሰነ አይደለም። እንደ አገር የሰፋ ፤ ብዙውን የማሕበረሰብ ክፍል የሚያዳርስ ከዚያም ባሻገር መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት፣ ዘመኑ የደረሰበትን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ ነው። እናም ጅማሮውን በትምህርት ቤት ማድረጉ መሰረቱ የጸና እንዲሆንም ያስችለዋል።
የዲጂታል መማሪያ ማዕከላት (digital learning centers) መስፋት የማሕበረሰብ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ባሻገር አገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ ከምንም በላይ በትምህርት ዘርፉ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋልና ዘመኑን የሚመጥን ትምህርት ለመስጠት ኢትዮ ቴሌኮም ስትራቴጂያዊ እቅዶችን ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ያለንበት ዘመን የዲጂታል ዘመን እንደመሆኑ የመማሪያ ማዕከላትን መገንባት ፤ የቴክኖሎጂና አዳዲስ የመማሪያ አካባቢን መፍጠር ያስፈልጋል። ተማሪዎች ከዲጂታል ቴክኖሎጂው ጋር አብረው እንዲጓዙ መደገፍም የግድ ነው። በተጨማሪም የመረጃ ተደራሽነትን ማሳደግ፣ የበጎ ፈቃደኛ ሠራተኞችን ተሳትፎ በትምህርትና በሥልጠና ማጎልበት፤ እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ለሚኖሩበት ማሕበረሰብ እንዲያካፍሉ ማስቻል እንዲሁም ሙያዊ ትንታኔ እና ችግር ፈቺ ክህሎቶችን ማዳበርም ይገባል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ተቋም ኃላፊነቱን ወስደው ባሉበት ደረጃ ልክ መወጣት ይኖርባቸዋል። በመሆኑም ኢትዮ ቴሌኮም ጀማሪ የመሆን ተግባሩን እንደፈጸመ በምረቃው ወቅት ተናግረዋል።
ሌላው የዲጂታል መማሪያ ማዕከላትን በማቋቋም ተግባራዊ የተደረገው ይህ እድል በአገር አቀፍ ደረጃ በ66 የመንግሥት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆን ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ብሎም የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን በዕውቀት ለማነጽ በሚል ሥራውን እያከናወነ እንደሚገኝም አብራርተዋል። በተለይም ሁለገብ ሀገራዊ ጥረትን ለማገዝና ሀገራዊ እና ተቋማዊ ማሕበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ተማሪዎችን በቴክኖሎጂው ማገዝ ከምንም በላይ አስፈላጊ እንደሆነም አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ ኢትዮ ቴሌኮም ከሚሰራቸው በርካታ ስራዎች ውስጥ አንዱ እንደሆነ የሚያነሱት ኃላፊዋ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ይተገበራል። ከእነዚህ መካከልም 66 የመንግሥት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። ለዚህም አስፈላጊ የሆኑ ኮምፒዩተሮች፣ ልዩ ልዩ የትምህርት ቤት መገልገያ መሳሪያዎችን እና ከፍተኛ ፍጥነት ያለው መደበኛ የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት እንደተሟላላቸው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ተማሪዎች ከሌላ ትምህርት ቤቶች ጋር መረጃ በቀላሉ መለዋወጥ እንዲችሉ፣ ማሕበረሰባዊ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን፣ የመማር ማስተማሩን ሂደት ውጤታማ እና የተሻለ ለማድረግ፣ ተመርቀው ሲወጡ ለዲጂታል አለሙ ራሳቸውን ዝግጁ እንዲያደርጉ እና የዲጂታል ቴክኖሎጂውን በሚጠቀሙ እና በማይጠቀሙት መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስረድተዋል።
በመላ አገሪቱ ለሚገኙ 66 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ 45 ነጥብ 48 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 1 ሺህ 386 ዴስክቶፕ ኮምፒዩተሮች፣ 1 ሺ 386 ጠረጴዛዎችና ወንበሮችን፣ የትምህርት ቤት መገልገያ መሳሪያዎችን በማሟላት የዲጂታል የመማሪያ ማዕከሎቹን አቋቁሟል። በዚህም ከ140 ሺ 596 በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ናቸው። ከእነዚህ 66 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 18 ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ፣ የሚገኙ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 48 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በክልሎች ያሉ እንደሆኑ አንስተዋል።
በአዲስ አበባ እና በክልሎች ያሉ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ቢሮዎቻቸው አማካይነት መመረጣቸውን ገልጸው በኢትዮ ቴሌኮም የሪጅንና የዞን ጽህፈት ቤቶች አማካኝነት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ወይዘሪት ፍሬህይወት ጠቅሰዋል። የትምህርቱ ዘርፍ ለሀገራችን ሁለገብ የልማት እንቅስቃሴ ያለውን ፈርጀ-ብዙ ሚና የሚወጣም መሆኑን አክለዋል።
እንደ ወይዘሪት ፍሬህይወት ማብራሪያ፤ የትምህርት ተቋማትን በቴክኖሎጂ የተደገፈና ጥራት ያለው ትምህርት በቀጥታ ስርጭት እንዲያገኙ ማድረግ፣ ከፍተኛ አቅም ባላቸው የገመድ እና የሳተላይት መገናኛ አማራጮች ማገናኘት (ስኩል ኔት)፣ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በነጻ እንዲሁም እስከ 86 በመቶ በሚደርስ ቅናሽ መስጠት በገንዘብ ሲተመን ከ 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑንም አመልክተዋል። በተጨማሪም በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በሀገር አቀፍ ደረጃ በ665 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ተማሪዎች 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት 50 ሺ ደርዘን የመማሪያ ደብተሮችን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎች ልገሳ መካሄዱንም ገልጸዋል።
በ24 ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ 9 ሺ ተማሪዎች ለትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር የሚውል 23 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር፣ በ 45 ዩኒቨርሲቲዎች ለተመረጡ 5ሺ 500 ተማሪዎች ለአንድ ዓመት የኪስ ገንዘብ የሚሆን 22 ሚሊዮን ብር መድቦ ለእያንዳንዱ ተማሪ በወር 400 ብር ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ያነሱት ኃላፊዋ፤ ከዚህ ባሻገር ሴቶች የመረጃ እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል 54 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በሚገመት ወጪ 70 ሺ የሞባይል ቀፎዎችን ከሲም ካርድ ጋር በአገራችን 846 ወረዳዎች ለሚገኙ ሴቶች በስጦታ ማበርከቱን ተናግረዋል።
ሴት መምህራን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደግፈው በተሰማሩበት የሙያ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ ለመደገፍ 50 ላፕቶና 200 ዘመናዊ የስልክ ቀፎዎችን በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡት መምህራን ሽልማት መስጠቱን ገልጸዋል።
ለትምህርቱ ዘርፍ ልህቀት አሁንም ቢሆን ተቋሙ ቁርጠኛ አቋም አለው የሚሉት ወይዘሪት ፍሬህይወት፤ በቅርቡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ጦርነት ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ውድመት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት መልሶ ለማቋቋምና ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ በአጭር የጽሁፍ መልእክት (9222) እና በቴሌብር መተግበሪያ አማካኝነት ድጋፍ ሰጪዎች አቅማቸው የፈቀደውን የገንዘብ መጠን ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበትን ማመቻቸቱን አስታውሰዋል። እንደ አንድ ሀገራዊ ተቋም የትምህርት ዘርፉን በመደገፍ እና የተሻለ ትውልድ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እንዲሁም በማሕበረሰቡ ሁለንተናዊ የእድገት እንቅስቃሴ ላይ በቀጥታ በመሳተፍ ሀገራዊ አለኝታነቱንና ማሕበራዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም በንግግራቸው አረጋግጠዋል።
ዲጅታል ማዕከሉን በተመለከተም የተቋሙ ሰራተኞች በሚያጋጥሙ ችግሮች ብቻ ሳይሆን በመማር ማስተማሩ ሥራ ጭምር በመግባት እንዲያግዙ ይደረጋልም ብለዋል። ከዚህ ቀደም በትምህርት ቤቱ ቢበዛ አራት ኮምፒዩተር እንደነበር ያንን ለመጠቀም ከባድና ብዙ ሰው በአንዴ መግባት ስለማይችል ተከፋፍሎ መግባት የሚያስገድድ ከዛ በኋላም ያለው አጠቃቀም ውጤታማ እንዳልነበር የምትናገረው ደግሞ የከፍተኛ 23 ሁለተኛ ደረጃ የ 10ኛ ክፍል ተማሪዋ ሰሚራ መሀመድ ናት ፤ አሁን ግን የዚህ እድል ተጠቃሚ በመሆናቸው እጅግ ደስተኛ መሆኗንና አሁን ያለው ብዛቱ ብቻ ሳይሆን ፍጥነቱ የተሻለ ተደርጎ ዲጅታል ማዕከሉ በኢትዮ ቴሌኮም አማካኝነት መከፈቱ ችግራቸው እንደሚፈታ እምነት አላት።
የተከለያዩ ወርክ ሽቶችን አትሞ (ፕሪንት) እያደረጉ ለማጥናት መልካም እድሎችን እንደሚፈጥርላቸውም ተስፋ አድርጋለች። እናም ይህንን እድል ለሰጣቸው ኢትዮ ቴሌኮም ትልቅ አክብሮት እንዳላት ትገልጻለች። ‹‹የኮምፒዩተር ሳይንስና መሰል ቴክኖሎጂውን የሚነካኩ መስኮችን መርጦ ለመማርም ከወዲሁ ያዘጋጀናል›› የምትለው ደግሞ የዚሁ ትምህርትቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪዋ ኢየሩሳሌም መኮንን ነች። እርሷ እንዳለችን፤ እስከ አሁን በነበረው የትምህርት ቆይታ ብዙ ከኮምፒዩተር ጋር የሚያገናኙን ነገሮች ቢኖሩን እድሉ ግን ጠባብ ነው። መረጃዎችን እንኳን ለማግኘት ሌሎች ማዕከላት ጋር መሄድ ግዴታችን ነበር ። በዚህም ወጪያችን ቀላል አይደለም። ከዚያም አልፎ ቤታችን ሆነን በሞባይል ዳታ ለመጠቀም ያልተጠበቀ ወጪ እናወጣለን። እናም ጥቂት ጊዜም ቢሆን እፎይታን ስለሚሰጠን በእድሉ ደስተኛ ነኝ ትላለች።
ለቀሪዎቹ በተለይም ለዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎች እጅግ የሚያስደስት እድል ነው። እናም ጊዜው ሳያመልጣቸው እንዲጠቀሙበት ትመክራለች። እኛም እድሉ የተሰጣችሁ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተጠቀሙበት አገራችሁን አስጠሩበት።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2014