“ኡፉ! ሙቀቱ እንዴት ይጨንቃል…” ብለን ከላይ የለበስነው ያስወለቀን ሙቀት፤ በጊዜ ዑደት ቦታውን ለቆ ቆዳን የሚያኮማትር ቅዝቃዜ ይሰማን ጀምሯል። ይሄኔ ቀድመን አውልቀነው የነበረ ልብስ ብንደርብ እንኳን አይበቃንም። ተጨማሪ ከቁምሳጥናችን ፈልገን አልያም ከሌለን ገዝተን እንደርባለን። እንዲህ ሰማይ ሲያስገመግም መሬቱ ርሶ አየሩ ሲቀዘቅዝ ሰውነታችን ሙቀት ይፈልጋል።
በዚህ ወቅት ደረብረብ አድርጎ መውጣት በምቾት መንፈላሰስ ያምረናል። ፋሽን ተከታዮችና ዘመነኞች ሙቀትን ሲፈልጉ ከምቾት ባሻገር የሚያስቡት ጉዳይ አለ። ለእነዚህ የልብሱ ያማረ ዲዛይን፣ ቀለምና ወቅታዊነት ዋንኛ መለኪያዎች ናቸው። ስለዚህም ክረምት ላይ የሚለበስ ፋሽን ለአየር ጠባዩ የሚስማማ ከመሆኑ ባሻገር ተለብሶም የሚያዘንጥ ወይም ሲጫሙት የሚያሳምር መሆን ይጠበቅበታል።
የክረምት ወራት መጀመሪያው የሆነው ሰኔ ይዞት የመጣውን ቅዝቃዜ ለወራት የሚዘልቅ ነውና ቅዝቃዜው እንዴት እንለፈው ማለታችን አይቀርም። በዛሬው የፋሽን ገፃችን ለክረምት የቀረቡ አልባሳት ላይ ትኩረት አድርገን፤ በክረምቱ ወቅት ሙቅትም የሚያላብሱን አልባሳት ምን አይነቶች እንደሆኑና የገበያ ሁኔታ ለመመልከት ወደድን።
ወፈርፈር ያለ ልብስና ከቁርጭምጪሚት ከፍ ያለው የእግር ክፍል የሚሸፍን ጫማ በክረምት ወቅት ፋሽን ከፍ ብሎም ከብርድ መከላከያ ጋሻ ነው። ይህ ደግሞ የመስኩ ባለሙያዎች በደንብ ያውቁታል። ለዚያ ነው፤ በከተማችን ላይ የሚገኙ የተዘጋጁ አልባሳት መሸጫ ሱቆች ወቅቱን ያማከሉ አልባሳት በየመደርደሪያና አልባሳት ማሳያዎቻቸው ላይ የሚያበረክቱት። እኛም ሰውነታችን በብርድ እንዳይጎዳ፤ አካላችን በቅዝቃዜ እንዳይረታ የሰውነታችን ሙቀት የሚጠብቁ አልባሳት መፈለጋችን አይቀርምና ወደ ሱቆቹ ጎራ እንላለን።
ሰኔ መግባቱን ተከትሎ የሰዎች አለባበስ ተቀይሯል። በፊት የነበረው ቀለል ያለ አለባባስ ሙቀት ወደሚሰጡ ሹራቦችና ካፖርቶች ተለውጧል። በከተማዋ የተለያዩ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ የበዙት የተዘጋጀ ልብስ መሸጫ ሱቆች በክረምት አልባሳት ይሞላሉ።
በጋውን በተለያዩ አልባሳት ከፊት አሰልፈው ለተጠቃሚ ሲያቀርቡ የቆዩት የተዘጋጁ ልብሶች መሸጫ ሱቆች በአሁኑ ወቅት የሚፈለጉት የክረም አልባሳት መሆናቸው አሳምረው ያውቁታልና የልብስ መስቀያቸውን በክረምት አልባሳት ሞልተውታል። በሱቆቹ ወቅቱን ያገናዘበ የክረምት ፋሽን አልባሳት በየበራቸው በልብስ ማሳያ አሻንጎሊቶች ተወድረው ለተመልካች አጓጊ ተደርገው ይቀርባሉ።
ዛሬ ላይ የቴክኖሎጂ መመንጠቅ በፋሽኑ ዓለም የፈጠረው ትልቅ ዕድል አለ። በተለያየ ጥናትና ምርምሮች በመታገዝ አልባሳት ለሰዎች የተለየ ውበት እዲያላብሱና ጤንነትን የሚጠብቁበት ማድረግ ተችሏል። ሰዎች በሚፈልጉት መልኩ ላሻቸው ግልጋሎት ይጠቀሙበት ዘንድ አልባሳት በተለያየ ግብዓት ተሰርተው ለገበያ ቀርበዋል።
በእኛ አገር አይለመዱ እንጂ ባደጉትና እጅጉን በዘመኑት አገራት ክረምት ላይ ሙቀትን የሚሰጡና በሚፈለገው መልኩ የሙቀት መጠንን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ልብሶች አሉ። እነዚህ አልባሳት በፈለጉት መልክ ሙቀትን ከፍና ዝቅ ባለ መልኩ እንዲሰጡ ተደርገው የተሰሩ የኤሌክትሪክ ሥርዓት የተገጠመላቸው ዘመናዊ አልባሳት ናቸው።
እኛም አገር ወቅትን መሰረት አድርገው የሚለበሱ አልባሳት ተጠቃሚዎች ይመርጡዋቸው ዘንድ ለዲዛይናቸውም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይዘጋጃሉ። ለክረምት ወቅት የሚዘጋጁ አልባሳት ሙቀት ሊሰጡ ከሚችሉ ግብዓችም ይዘጋጃሉ። የክረምት አልባሳት የሰውነት ሙቀትን ከመጠበቅ ባለፈ እንደ ፋሽን ተወስደው ውበትን የሚያጎናፅፉ አምረንና ሽክ ብለን እድንታይ የሚያደርጉም ናቸው።
በመዲናችን በፋሽን አልባሳት በስፋት ከሚታወቁት ሰፈሮች አንዱ በሆነው ሜክሲኮ መሀል ተገኝተናል። የክረምት አልባሳት አይነቶች፣ ገበያና ተፈላጊነት ምን ይመስላል? የሚለውን ምላሽ ለማግኘት ቅኝት ስናደርግ ሜክሲኮ ላይ ጎልቶ የሚታየው ደብረ ወርቅ ህንፃ ስር በተርታ ተሰልፈው ያገኘናቸው የተዘጋጁ አልባሳት መደብሮች ጎራ አልን።
ብርቱኳን አየለ በአካባቢው ታዋቂ ከሆነው የፋሽን አልባሳት መሸጫዎች ሱቅ ውስጥ በአንዱ ደንበኞችዋን ስታስተናግድ አገኘኋት። በሱቅዋ ውስጥ የተደረደሩት አልባሳት በአብዛኛው የክረምት እንደሆኑ ገልፃ፤ የፋሽን ኢንዱስትሪው ባህሪ መሆኑንና የደንበኞች ፍላጎትም ያማከለ መሆኑን ትናገራለች።
በክረምት ወቅት እጅግ ተፈላጊ የሆኑ አልባሳት በሴቶችም በወንዶችም ወፈር ያሉና የሰውነት ሙቀት የሚጠብቁ እንዲሁም ዝናብን የሚቋቋሙ ልብሶች መሆናቸውን ትገልፃለች። በዋጋቸውም ቢሆን በበጋ ወቅት ከነበረው ከፍ እንደሚል ገልፃ ተፈላጊነታቸው ሲጨምር ዋጋቸውም ከፍ እንደሚል ትናገራለች።
እጅግ የሚማምሩ የሴቶች ፋሽን አልባሳት መሸጫ ሱቅዋ ውስጥ የተሰቀሉ ልብሶች ወቅቱን ያገናዘቡና በተጠቃዎች በተለይም በዘመንኛ ወጣቶች የሚፈለጉ መሆናቸውን የምትገልጸው ብርቱኳን አልባሳቱ ተፈላጊነታቸው ስለሚጨምር በብዛትና በአይነት በስፋት ለደንበኞችዋ እንደምታቀርብ ትናገራለች።
አሁን ላይ ሰዎች በተለይም ሴቶች ልብስ ሲገዙ ሙቀት ብቻ የሚሰጥን ብለው ሳይሆን ፋሽን መሆኑንና በዲዛይን አዲስ መሆኑም ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚገዙም ታስረዳለች። አካባቢው ላይ ባሉ ሱቆች በብዛትን ለገበያ የሚቀርቡት አልባሳት የሰውነት ሙቀት ከመስጠታቸውም ባለፈ ፋሽን የሆኑና በደንበኞች የሚመረጡ በተለያየ ዲዛይን የተዘጋጁ መሆናቸውን ታብራራለች።
ዋጋ በተመለከተ በፊት ከነበረው ሁሉም በሚባል መልኩ የዋጋ ጭማሪ እንዳለው ገልፃ አልባሳቱ እንደተሰሩበት ጥሬ እቃና ተፈላጊነት ዋጋቸው ይለያያል። በሱቅዋ ውስጥ የሚገኙ ቀሚሶች በአማካይ ከ1500 እስከ 4900፣ ጃኬቶች ከ1800 እስከ 3500 ድረስ ዋጋ ተተምኖላቸው ለሽያጭ እንደተዘጋጁ ትገልፃለች።
ተገልጋዮች ወይም ደንበኞች እዚህ ላይ ምን ይላሉ ብለን የሚሉት ለመስማት ወደ ሱቁ አጋጣሚ ለመግዛት የገባቸውን አንዲት ወጣት ተጠግቼ አወራኋት፡ ፡ቤዛዊት አየለ ትባላለች፤ ለክረምት የሚሆን ሹራብ ለመግዛት እንደገባች ነግራኝ፤ ሁሌም ወቅቱን ያገናዘበ አልባበስ እንደሚመቻትና እራስዋንም ከወቅቱ ጋር በአለባበስ ለማስታረቅ እንደሆነ አስረዳችኝ። ገበያውን በተመለከተ “አይቀመስም” በማለት አስተያየትዋን የምትገልጸው ቤዛዊት የአልባሳቱ ዋጋ እጅግ የተጋነነ መሆኑን ትናገራለች።
ከቄራ ታክሲ መጫኛ ፊት ለፊት ባሉት የበዙ የተዘጋጁ ልብሶች መሻጫ ሱቆች ውስጥ የሚገኙ አልባሳት በዋጋ ከሱቅ ሱቅ የሚለያዩ መሆኑን በምልከታዬ ታዝቤያለሁ።
አካባቢው በአማካይ ከ500 እስከ 4500 ድረስ የወንዶችና የሴቶች አልባሳት ሹራቦች፣ ጃኬችና ካፖርች በብዛት ይሸጣሉ። ለዚህ ልዩነት መነሻ የአካባቢው የገበያ ሁኔታና በአካባቢው የሚኖረው ሕብረተሰብ የመግዛት አቅም እንዲሁም የሱቆቹ የኪራይ ዋጋ መብዛትና ማነስ ምክንያት አድርገው የመሸጫ ሱቆቹ ልብሶቹን በተለያየ ዋጋ ያቀርባሉ።
በሱቆቹ ባደረግነው ቅኝት ከሴቶች አልባሳት ይልቅ የወንዶች በዋጋ ከፍ የሚል ወይም የሚወደድ ሲሆን በተጨማሪም የወንዶች አልባሳት ከሴቶች ይልቅ በአብዛኛው የልብስ መሻጫ ሱቆች ውስጥ በርክተው ይገኛሉ። ለወንዶች የሚሆኑ የክረምት ቡትስ ጫማዎች በአማካይ ከ1200 እስከ 3500 ብር የሚጡ ሲሆን ለሴቶች የሚሆኑ ቡትስ ጫማዎች ደግሞ በአማካይ ከ850 እስከ 3500 ድረስ ይሸጣሉ። በእግጥ የአልባሳቱ ዋጋ ከሱቅ ሱቅ የዋጋ ለውጥ እንዳለውም ለመታዘብ ችለናል
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2014