በዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና የተሳተፈው ቡድን ሽልማት ተበረከተለት

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ20ኛው የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳትፎ ስኬታማ ለሆነው ቡድን የማበረታቻ ሽልማት አበርክቷል። የወጣቶቹ የአትሌቲክስ ቡድን በፔሩ ሊማ በተካሄደው ሻምፒዮና ተሳትፎ በሰበሰባቸው ሜዳሊያዎች ቁጥር ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ወደ ሀገሩ ተመልሷል።

ትናንት በተካሄደው የሽልማት መርሐ ግብርም የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገቡ አትሌቶች 40ሺ ብር ሲበረከትላቸው፤ የብር ሜዳሊያ ያስመዘገቡ 25ሺ እንዲሁም የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤቶች 15ሺ ብር ተሰጥቷቸዋል። ዲፕሎማ ላገኙ እንዲሁም ተሳትፎ ላደረጉ አትሌቶችም የማበረታቻ ገንዘብ ተበርክቶላቸዋል።

ቡድኑን በመምራት ስኬታማ ተሳትፎ ያደረገችውና ከ20 ዓመታት በፊት ጣሊያን ላይ በተካሄደው በዚሁ ሻምፒዮና ተሳትፋ ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበችው አንጋፋ አትሌት መሰለች መልካሙ፤ ቡድኑ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥታለች። በዚህም ቡድኑ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ያደረገው የሃገር ፍቅር ስሜት መሆኑን ገልፃለች። በቡድን ስሜት ስህተትን በቶሎ አርሞ በአልሸነፍ ባይነት 10 ሜዳሊያዎችን ማስመዝገቡም የሚያስመሰግነው መሆኑን ተናግራለች።

የቡድኑ የቴክኒክ መሪ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ በበኩላቸው፤ ቡድኑ ከዝግጅቱ አንስቶ እስከ ተሳትፎው በሃገር ፍቅር እና በኅብረት መሥራቱ ውጤታማ እንዳደረገው ጠቁመዋል። በአሠልጣኞች በኩልም ልምድ ያላቸውና አዳዲስ አሠልጣኞች በጥምረት ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልፀው፣ ቡድኑ ከዚህም በኋላ በውጤታማነት እንዲቀጥል ካሁኑ ክትትልና ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ አሁንም ተተኪ አትሌቶች እንዳሉ የታየበት መሆኑን የተናገረችው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ አትሌቶቹ ያደረጉት ተሳትፎና ያገኙት ውጤት ሊያስመሰግናቸው ይገባል ብላለች። ቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት 2025 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚካሄድበት በመሆኑም ወጣቶቹ አትሌቶች ሃገራቸውን በድጋሚ መወከል እንዲችሉ ዝግጅታቸውን ከወዲሁ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠቁማለች።

ቡድኑ በተሳተፈባቸው ውድድሮች 6 የወርቅ፣ 2 የብር እና 2 የነሐስ በጥቅሉ 10 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብም ተሳትፎውን አጠናቋል። 134 ሃገራት በተሳተፉበት ሻምፒዮና 34 ሃገራት የሜዳሊያ ሰንጠረዡን የተቀላቀሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያ አሜሪካን ተከትላ በዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ልትቀመጥ ችላለች። ይህም ውጤት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚውን ደረጃ ይዛ እንድታጠናቅቅ ያደረገ ነው።

በሻምፒዮናው የመጀመሪያው የውድድር ዕለት በአትሌት መዲና ኢሳ የተጀመረው የ5ሺ ሜትር ድል በሲምቦ ዓለማየሁ 3ሺ ሜትር መሰናክል የቀጠለ ሲሆን፤ ባልተለመደው የወንዶች 800 ሜትር ደግሞ በአትሌት ጄነራል ብርሃኑ አስደናቂ አሸናፊነት ሊጠናከር ችሏል። በቀጣይም በ3ሺ ሜትር ሴቶች አለሽኝ ባወቅ ስትረታ፣ ሳሮን አበበ እና አብዲሳ ፈይሳ ደግሞ በሁለቱም ፆታ በ1ሺ500 ሜትር ተጨማሪዎቹን የወርቅ ሜዳሊያዎች በማስመዝገብ የኢትዮጵያን ሰንደቅ በመድረኩ በተደጋጋሚ በኩራት አውለብልበዋል። ሁለቱ የብር ሜዳሊያዎችም በ5ሺ ሜትር ሴቶችና ወንዶች በአትሌት መቅደስ አለምሸት እና አብዲሳ ፈይሳ የተመዘገቡ ሲሆን፤ ማርታ ዓለማየሁ በ3ሺ ሜትር እንዲሁም ኃይሉ አያሌው በ3ሺ ሜትር መሰናክል ተጨማሪዎቹን የነሐስ ሜዳሊያዎች አስመዝግበዋል።

አትሌት አብዲሳ ፈይሳ ደግሞ በ1ሺ500 ሜትር እንዲሁም በ5ሺ ሜትር የወርቅና የብር ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ በሻምፒዮናው ስኬታማ ቆይታ ያደረገ ወጣት አትሌት ሊሆን ችሏል።

በሊማ በአጠቃላይ የተመዘገበው የሜዳሊያ ቁጥር ከሁለት ዓመት በፊት በኮሎምቢያ ከተካሄደው ሻምፒዮና በ2 ሜዳሊያዎች ያነሰ ቢሆንም በደረጃ ሰንጠረዡ ግን መሻሻል ታይቷል። ኢትዮጵያ በውድድሩ የተካፈለችው በ19 አትሌቶች ሲሆን፤ ውድድር ያደረገችባቸው ርቀቶችም 800 ሜትር፣ 1ሺ500 ሜትር፣ 3ሺ ሜትር፣ 3ሺ ሜትር መሰናክል፣ 5ሺ ሜትር እንዲሁም 10ሺ ሜትር ርምጃ ናቸው። በዚህም 9 አትሌቶች የሜዳሊያ ሲያገኙ፤ 10ሺ ሜትር ርምጃ ሜዳሊያ ያልተገኘበት ብቸኛው ርቀት ሆኗል። በሌላ በኩል በሴቶች የ5ሺ ሜትር እና 3ሺ ሜትር መሰናክል የውድድሩን ክብረወሰን መስበር እንዲሁም በ800 ሜትር ሴቶች ወንዶች የታየው አስደናቂ ፉክክርም የሻምፒዮናው ድምቀት እንዲሁም የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ በተለይ መግዛት የቻሉም ነበሩ።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You