የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እአአ በ2025 በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የምድቡን የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታ ከሜዳ ውጭ አድርጎ በአቻ ውጤት ተለያይቷል። ቡድኑ ከታንዛኒያ አቻው ጋር የመጀመሪያውን ጨዋታ ያለ ግብ በመለያየት የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞውን ጀምሯል።
በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች በምድብ 8 የተደለደለችው ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የምድብ ጨዋታ ከትላንት በስቲያ ነሐሴ 28/2016 ዓ.ም ከሜዳዋ ውጭ አድርጋለች። በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ቤንጃሚን ምካምፓ ስታድየም በተካሄደው ግጥሚያ 0 ለ 0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይታለች። ቡድኑ ለማጣሪያው በሀገር ቤት ከ15 ቀናት በላይ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቢቆይም፣ በጉዳት እና በተጫዋቾች አካል ብቃት መውረድ እንደፈለገ አልተንቀሳቀሰም። አሁንም የግብ ማስቆጠር ችግሩ ያልተቀረፈው ቡድኑ የአቡበከር ናስር እና አቤል ያለው አለመኖር የአጥቂ መስመሩ እንዲሳሳና የግብ እድሎች እንዳይፈጥር አድርጓል።
በመጀመሪያው ጨዋታ ብልጫ ወስዶ ሶስት ነጥብ በማሳካት ለቀጣይ ጨዋታ የሥነ-ልቦና ስንቅ የሚይዝበትን እድልም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ምንም እንኳን የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ቡድናቸው ተጭኖ ለመጫወት ወደ ሜዳ እንደሚገባ አስቀድሞ ቢገልጹም ወደ ተቀራኒ ሜዳ ሰብሮ የመግባት እንቅስቃሴ እምብዛም አልታየም። በኳስ ቅብብል ከታንዛኒያ ብሔራዊ ቡድን የተሻለ ቢመስልም ተቃራኒ ቡድን ላይ ጫና የማይፈጥርና ትርጉም አልባ ቅብብሎች በማድረግ ያለ ሶስት ነጥብ ከሜዳ ወጥቷል። የቡድኑ የቅንጅት እና የፈጠራ ችግሮች ጎልቶ የታዩና የግል እድሎች ብዙም ያልተፈጠሩበት የመጀመሪያ ጨዋታም ነው። አሰልጣኙ አሁንም የጨራሽ አጥቂ (9 ቁጥር) እጥረት እንዳለ ቢጠቅሱም ቡድኑ የሚያስቆጭ የጎል ሙከራ አላደረገም።
ቡድኑ በኳስ ቁጥጥር የተሻለ ቢሆንም የተቃራኒ ቡድን የግል ክፍል ሰብሮ ከመግባት አንጻር ከፍተኛ የሆነ ችግር ታይቶበታል። በመሃልና በሁለቱ መስመሮች ሰብሮ ለመግባት አልፎ አልፎ የሚደረጉ ሙከራዎችም በቀላሉ በታንዛኒያ ተጫዋች ከሽፎ ወደ ውጤት ሳይቀየር ቀርቷል። ዋልያዎቹ በጨዋታው ትርጉም አልባ የኳስ ቅብብሎችን ያለ ተጋጣሚ ጫና ሲያደርጉ፤ በአንጻሩ የታንዛኒያ ብሔራዊ ቡድን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ፈጣን ሽግግሮችን በማድረግ አደገኛ ሙከራ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል። ከኳስ ጋራ ምቾት የማይሰማቸው ተጫዋቾች መኖራቸውና ሽመልስን በፈጠራው ረገድ የሚተካ ተጫዋች አለመኖሩ ብሔራዊ ቡድኑን አሁንም ከበፊቱ የበለጠ ዋጋ እንዲከፍል እያደረገውም ይገኛል።
ዋሊያዎቹ ምንም እንኳን የሜዳቸውን ጨዋታዎች ከሀገር ውጭ ለማድረግ ቢገደዱም መሠረታዊ የሆኑ የቡድኑን ቴክኒካልና ታክቲካል ችግሮች ተረድቶ መፍታት የአሰልጣኙ ኃላፊነት ይሆናል። ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ጨምሮ ባለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ድል ከተቀዳጀ ደግሞ የአሁኑን ጨምሮ ስድስት ጨዋታዎች አልፈውታል። ብሔራዊ ቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ያሸነፈው የግብጽ ብሔራዊ ቡድንን ነበር። በ2025ቱ የሞሮኮ አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያም የውጤት ቀውሱ በመጀመሪያ ጨዋታ የቀጠለ ሲሆን ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ለመመለስ ለሚያደርገው ጉዞ ቀጣይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ የሚያሳካው ውጤት ይጠበቃል።
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በሰጡት አስተያየት ጨዋታው ጠንካራ እንደሆነና ለማሸነፍ ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ቡድናቸው በመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረጉ ማሸነፍ እንደሚገባውም ጠቅሰዋል። ታንዛኒያዎች በሜዳና ደጋፊዎቻቸው ፊት እንደመጫወታቸው ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ነው ቀርበዋል። በጨዋታው ሂደት ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል የመድረስ ችግር እንዳልነበረበት ጥሩ የሆነ 9 ቁጥር ተጨዋች ባለመኖሩ የአጨራረስ ችግር እንዳለበት በመጥቀስ አነጋጋሪውን አስተያየት ደግመውታል። ሃሰተኛ ዘጠኝ ቁጥርን በመጠቀም እንደ ቡድን ለመጫዋት ጥረት መደረጉን እና በኢትዮጵያ አሁንም የውጤት መጥፋት ችግር መኖሩን አምኖ ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነም አክለዋል።
ዋልያዎቹ ከቀናት እረፍት በኋላ ሁለተኛውን እና የሜዳቸውን የመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ታንዛኒያ ዳሬሰላም በሚገኘው ቤንጃሚን ምካፓ ስታድየም ሰኞ ጳጉሜን 4 ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር የሚያደርጉ ይሆናል። ብሔራዊ ቡድኑ ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ከሁለተኛው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ነጥብ ይዞ ወደ ሀገሩ እንደሚመለስም ይጠበቃል።
ሁሉም ቡድኖች ለ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለማለፍ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን በሜዳና ከሜዳ ውጭ ያካሂዳሉ። በ12 ምድቦች 48 የአፍሪካ ሀገራት ለ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚያደርጉት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በምድብ 8 ተደልድላለች። ታንዛኒያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ጊኒ ከኢትዮጵያ ጋር የተደለደሉ ሀገራት ናቸው። 35ኛ የአፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ አስተጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን አዘጋጇን ሀገር ጨምሮ ከየምድቡ አንደኛና ሁለተኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ 24 ሀገራትን በማሳተፍ ይካሄዳል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 1 /2016 ዓ.ም