በአገሪቱ ሁለት ተጠባቂ ምርጫዎች አሉ። የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትና አገር አቀፍ ምርጫ። ምርጫዎቹ መቼና እንዴት እንደሚካሄዱ እስካሁን የተባለ ነገር ባይኖርም ተፎካካሪ ፓርቲዎች እራሳቸውን እያዘጋጁ ይገኛሉ። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለመጪዎቹ ምርጫ አባላትን ከማደራጀት አንስቶ ተዋህዶ እስከመስራት የሚስችላቸውን ሥራዎች እያከ ናወኑ ይገኛሉ። ከምርጫዎቹ በፊት ግን አገሪቱ የገባችባቸው የስጋት ሁኔታዎች መቀረፍ እንዳለባቸው አስተያየታቸውን የሰጡ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ይናገራሉ።
ከአዲስ አበባ ይገባኛል ጥያቄ አንስቶ በክልሎች መካከል የሚታዩት መጎሻሸሞች የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት የሚያናጉ መሆናቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ይጠቅሳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በአገሪቱ የሚገኙ አብዛኞቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ብሄርን መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው ተደራሽነታቸው አነስተኛ መሆኑም ተጠቅሷል። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበባው መሀሪ እንደሚናገሩት፤ ድርጅታቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ አባላት አሉት።
ለዚህ የሚሆን መዋቅርም በሁሉም ወረዳዎች ላይ አለው። ድርጅቱ በአግባቡ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ድርጅት ነው። በቀጣይ ስለሚኖረው ምርጫ ለመወያየትም ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ ነው የሚወስነው። በጉባዔው በምርጫው ስለሚኖረው ሂደት በምን አይነት መንገድ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ውሳኔ ይሰጥበታል የሚሉት አቶ አበባው፤ ፓርቲያቸው አሁን ያለውን ለውጥ እንደሚደግፈው የሚና ገሩት አቶ አበባው አገሪቱ በአሁኑ ወቅት አስጊ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝም ይጠቅሳሉ። በመሆኑም ለአገሪቱ ሰላም ለውጡ ጠንክሮ እንዲጓዝ ማድረግ ተገቢ ነው ይላሉ።
ሆኖም ግን በአሁኑ ሰዓት ያሉ የተወሰኑ አመራሮች ለለውጡ የሚመጥኑ አለመሆናቸውን ያነሳሉ። ቀደም ብሎ ሲዘርፉና ህዝቡን ሲበድሉ የነበሩ ሰዎች አሁንም ድረስ በስልጣን ላይ እንዳሉ ይጠቅሳሉ። ገዢው ፓርቲ ከፓርቲው ውጭ ያሉ ሰዎችን ስልጣን ላይ አላስቀምጥም ማለቱም አግባብ አለመሆኑንና ለአገሪቱ ይጠቅማሉ የተባሉ ሰዎች እንዲሰሩ መደረግ እንዳለበት ያመለክታሉ። እንደ አቶ አበባው ገለፃ፤ በአዲስ አበባ ጉዳይ የተጀመሩት ጉሽሚያዎችም መቆም አለባቸው። በከተማዋ ጉዳይ እየወጡ ያሉ ሀሳቦች እንዲረግቡ በማድረግ ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሁኔታ ለውይይት ሊቀርብ ይገባል። በኃይልና በሁከት መብት ማስጠበቅ አይቻልም። ሁከትና ብጥብጥ ለአገሪቱ የሚጠቅም ነገር አይደለም።
አዲስ አበባ የኗሪዎቿ እንጂ የአንድ ብሄር አይደለችም። ከአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚፈናቀለው አርሶ አደርም እንዴት ተደርጎ ካሳ መከፈል እንዳለበት በጥልቅ መወያየት ያስፈልጋል። አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ትግስቱ አወሉ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት በየቦታው ያለው ግጭትና እርስ በርስ መጠራጠር አባላትና ደጋፊዎችን ለማወያየት እንቅፋት ፈጥሯል። ይሄ ባልተስተካከለበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም። ፓርቲው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በትብብርና በቅንጅት ለመንቀሳቀስ ጅምር ሥራዎች አሉ። ፓርቲው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋርም ወደፊት በአገሪቱ ስለሚፈጠሩ ሁነቶች ምን መምሰል አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ውይይት እያደረገ ይገኛል።
አሁን ያለው የአገሪቱ ሁኔታ ሁለት መልክ ነው ያለው የሚሉት አቶ ትግስቱ፤ የመጀመሪያው ተስፋዎቹና መልካም ነገር ይዘው የሚሄዱበት ሁኔታ ነው። በሌላ በኩል የነበረውን ተስፋ የሚያመክኑ ነገሮች አሁን አሁን መታየታቸውን ይጠቅሳሉ።በዚህም አስቸጋሪ ነገር ውስጥ መገባቱንና ለውጡን የሚመራው ኃይል መዳከሙን ይጠቁማሉ። የለውጥ ኃይል የሚባለው እየሄደበት ያለው መንገድ አሳታፊነት ስለጎደለው የፓርቲ ስልጣን አላቸው የሚባሉ ሰዎችን ብቻ እያቀረበ እንደሚገኝም አቶ ትግስቱ ይናገራሉ። በተደራጀ ሃሳብ ያለመመራት፣ በክልሎች ያለው ኩርፊያ ጎልቶ እየወጣ መምጣትና የህግ የበላይነት በየቦታው መጣስ እየተስተዋለ መሆኑን ይገልፃሉ።
በሁሉም አቅጣጫ የሚታየው በተለይ ክልሎች የአንድ አገር ነዋሪነታቸው ቀርቶ የእርስ በርስ ጦርነት ለማድረግ የሚዘጋጁ የሚመስልበት ሁኔታ ላይ መደረሱ ስጋት መፍጠሩን ያመለክታሉ። በነዚህ ሁኔታዎች መገናኛ ብዙኃንም በተለይ የክልል መገናኛ ብዙኃን ተሳታፊነት መጨመሩን ያስረዳሉ። እንደ አቶ ትግስቱ ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት አራት የለውጥ ኃይል ነን የሚሉ አካላት አሉ። እነዚህም የማንነት ኃይል፣ የአንድነት ኃይል የለውጥ ኃይሉና የተደራጁ ወጣቶችን ያሳተፈ ኃይል ናቸው።አገሪቱም በነዚህ ኃይሎች ተቃርኖ ውስጥ ትገኛለች። በዚህ የተነሳ አገር ለመገንባት ብዙ ጥረት እየተደረገ አይደለም። የተመዘገቡና ያልተዘገቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም አሉ። ወደ ምርጫ ለመግባት እነዚህ መጥራት አለባቸው።
በዚሁ ከቀጠለ ቀድሞ ከነበረው የበለጠ አዳጋች ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ እምቢአለ በየነ እንደሚናገሩት፤ በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ አብዛኞቹ ፓርቲዎች የተደራጁት ብሄርን መሰረት በማድረግ ነው። በብሄር መደራጀታቸው እንደ አገር በሁሉም አቅጣጫ ተደራሽ እንዳይሆኑ ያደርጋል። ለተደራሽነት ችግር ደግሞ ዋነኛ ምክንያት አደረጃጀታቸው ነው።
አባል ማፍሪያ መንገድ ብሄርን መሰረት ያደረገ ከሆነ ተደራሽነቱም ይቀንሳል። በአገሪቱ የሚገኙ ፓርቲዎች ምርጫ ሊደርስ ሲል የመብዛት ነገር አለ የሚሉት አቶ እምቢአለ፤ በምርጫም ሲሸነፉ የመጥፋት ነገሮች እንደሚበዙ ያመለክታሉ። አብዛኞቹ ፓርቲዎች በብሄር ላይ ያተኮሩ በመሆናቸውም አማራጭ ሃሳባቸውን ማወቅ አለመቻሉን ይናገራሉ። በሌላ በኩል ፓርቲዎቹ በጥምር የሚሰሩ ባለመሆኑ በአገሪቱ የተበታተኑና የማይጨበጡ አስተሳሰቦች እንዲፈጠሩ ምክንያት መሆናቸውን ያስረዳሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011
መርድ ክፍሉ