የካንሰር ህመም በታዳጊ አገራት እየጨመረ እንደሆነ በመስኩ የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ። እንደነዚሁ መረጃዎቹ ከሆነ፣ በተለይም ቅባት የበዛባቸውና ኃይል የሚሰጡ ምግቦችን አዝወትሮ መመገብ፣ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ተገቢ ያልሆነ ውፍረት፣ አልኮል አብዝቶ መውሰድና የአማካኝ እድሜ ጣሪያ መጨመር ለካንሰር ህመም ተጋላጭነታችን ቀዳሚ መንስኤዎች ናቸው።
አገራት የካንሰር ህመም መከላከል እቅድና ስትራቴጂ መርሃግብሮችን ነድፈው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ዋል አደር ቢሉም ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረጉ በኩል ግን ክፍተቶች አሉ። ይህ ደግሞ ችግሩን ካለመፍትሄ እንድንጋፈጥ በማድረጉ አሁን ላይ በመላው አለም፤ እንዲሁም በአገራችን ዜጎች ለተለያዩ የካንሰር ህመሞች ተጋልጠው ይገኛሉ።
በመሆኑም ካንሰር እንዳይዘን ከተፈለገ ልናደርጋቸው የሚገቡን ተግባራት ያሉ ሲሆን፤ ቀድመን መከላከል፣ ከተያዝን በአነስተኛ ደረጃ ላይ እያለ ህመሙን ማወቅ፣ ምርመራና ህክምና ማድረግ፤ እንዲሁም፣ ህመሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ የህመምተኛውን ስቃይና የአስታማሚውን እንግልት መቀነስ የሚሉት ናቸው። እነዚህ አራት ጉዳዮችም በመንግስት ብቻ ሳይሆን፤ ታማሚውን ጨምሮ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ተግባራዊ ሊደረጉ ይገባል።
ህብረተሰቡ ጤናውን እንዴት መጠበቅ እንዳለበትና ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን በተመለከተ ትምህርት እንዲያገኝ ማድረግም ሌላው ከመከላከያ መንገዶቹ መካከል የሚጠቀሰው ጉዳይ ነው። እንቅስቃሴ ማድረግ ከተለያዩ ህመሞች ራስን ለመከላከል የሚጠቅም በመሆኑ ከተማ ሲለማ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችም አብረው ሊታሰቡ እንደሚገባም መታወቅ አለበት ።
በተለይም በእኛ አገር ምንም እንኳን ችግሩ ስር የሰደደ ቢሆንም የካንሰር ህክምና ባለሙያዎች እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ይታያል። በአገር አቀፍ ደረጃ ቁጥራቸው ትንሽ የሆኑት የዘርፉ ስፔሻሊስቶች ካለው የችግሩ ስፋት አንጻር ተገቢውን የመከላከል፤ ብሎም ህክምናውን በአግባቡ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት ውጤቱ የዘገየ እንዲሆን አድርጎታል።
ዛሬ ላይ የእነዚህን ባለሙያዎች ቁጥር ለማሳደግ በአገር ውስጥ ሳይቀር ትምህርቱ የሚያገኙበትጅ እድል የተመቻቸ ቢሆንም አሁንም በቂ የዘርፉ ባለሙያዎች አሉን ለማለት አያስደፍርም። ከእነዚህ ጥቂትና ፈር ቀዳጅ ከሆኑት የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት ባለሙያዎች መካከል አንዱ የዛሬ የህይወት ገጽታ አምዳችን እንግዳ የሆኑትን ዶክተር ቦጋለ ሰለሞን ሲሆኑ፤ ዶክተር ቦጋለ የመጀመሪያው የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት፤ እንዲሁም፣ የጥቁር አንበሳ ካንሰር ህክምና ማዕከልን ያቋቋሙ አንጋፋ የዘርፉ ባለሙያ ናቸው።
ዶክተር ቦጋለ ሰለሞን የተወለዱት ባሌ ሲሆን፣ ከጎባ ከተማ 40 ኪሎ ሜትር ወጣ ብላ በምትገኝ የገጠር መንደር ውስጥ ነው። ለቤተሰባቸው ሁለተኛ ልጅ የነበሩት ዶክተር ቦጋለ በወቅቱ ከእድሜ እኩዮቻቸው ጋር የገጠርን ህይወት ከመኖራቸውም በላይ ለትምህርት እንደደረሱ ያመሩት ወደ ቄስ ትምህርት ቤት ነበር። እዛም ከፊደል ጀምረው የቃል ትምህርት፣ ንባብ፣ ወንጌል፣ ዳዊት፤ እንዲሁም ቅዳሴ ተምረዋል። በወቅቱም ለትምህርት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ፤ እንዲሁም፣ ካሉት ተማሪዎች ሁሉ በእድሜ ትንሹ እሳቸው ስለነበሩ እሁድ ሳይቀር የኔታ ጋር በመሄድ ይውሉ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በወቅቱ ዘመናዊ ትምህርትን ለመቅሰም ወደ ከተማ ማለትም ወደ ጎባ ከተማ መምጣት ነበረባቸውና ቤተሰቦቻቸውም እንዲማሩላቸው ከነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ እዛው ጎባ ከተማ ላይ ያሉ ዘመዶችን በመለመንና ከልጃቸው ጋር በማገናኘት አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ሆነ። ነገር ግን ይህ አካሄድ ብዙም አዋጭ ስላልነበር ዶ/ር ቦጋለ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ቤት ተከራይተው ቀለብ ከቤተሰባቸው እየተጫነላቸው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጥሩ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ቻሉ።
ታዳጊው ቦጋለ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው እዛው ጎባ ከተማ “አዝማይ ደግላ” በሚባል ትምህርት ቤት ቀጠሉ። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉበት የአዝማይ ደግላ ትምህርት ቤት በወቅቱ በክፍለ ሃገሩ የመጀመሪያውና ብቸኛው ሲሆን እሳቸውን ጨምሮም ብዙ ጎበዝ ተማሪዎችን ያፈራ፤ ዛሬም ድረስ አገራቸውን በተለያየ መልኩ እየጠቀሙ ያሉ ጓደኞቻቸው የተማሩበት ስለመሆኑ ይናገራሉ።
“…. ምንም እንኳን የገጠር ልጅ ብሆንም አንደኛ ደረጃም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴ ላይ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት አድርጌ ነው የተማርኩት። በዚህም ጥሩ ከሚባሉት እንደውም የደረጃ ተማሪዎች መካከል ነበርኩኝ። በዚህም ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ ይደሰቱብኝ ነበር። በተለይም ቤተሰቦቼ በትምህርቴ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ እንድደርስላቸው ከፍተኛ የሆነ ማበረታታት ያደርጉልኝ ነበር” ይላሉ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተማሩ አስረኛ ክፍል ላይ ሲደርሱ የሙያ ምርጫ ማድረግ የቻሉት ወጣቱ ቦጋለ ለመሆን ወይም ለመማር የፈለጉት የህክምና ትምህርት ነበርና ምርጫቸውን “የጤና ተቆጣጣሪ” አደረጉ። ይህንንም ትምህርት ለመማር ወደ ጎንደር ተጓዙ።
ነገር ግን በዲፕሎማ ደረጃ ለመማር ያቀዱትን የጤና ተቆጣጣሪነት ትምህርትት አንደጀመሩ የእድገት በህብረት ዘመቻ መጣና እሳቸውም እንደ መላው የኢትዮጵያ ተማሪ ሁሉ ዘመቻውን ተቀላቀሉ።
“… እድገት በህብረት ዘመቻን የተቀላቀልኩት ከጎንደር ከተማ ነው። እንደ አጋጣሚም የደረሰኝ የዘመቻ ጣቢያ የዛሬው ሲዳማ ክልል ውስጥ ነበር። ነገር ግን ከባሌ ከወጣሁ በኋላ ለረጅም ጊዜ ቤተሰቦቼን የማየት እድሉን አግኝቼ አላውቅም። አዲስ አበባ መጥቼ የዘመቻውን አስተባባሪዎች ወደ ባሌ እንዲያዘዋውሩኝ ለመንኳቸው። እነሱም ፍቃደኛ ሆነው ወደ ትውልድ መንደሬ ዝውውር አደረኩ። በዛም ጎባ ምደብ ጣቢያ በመመደብ በአካባቢው ላይ ላሉ የጤና ሰራተኞች የቡድን አባል ሆንኩ ከቡድን አባላቶቼ ጋርም እየተዘዋወርን ለህብረተሰቡ የጤና ትምህርት አገልግሎት እንሰጥ ነበር “ይላሉ ዶ/ር ቦጋለ።
የእድገት በህብረት ዘመቻቸውን እንደጨረሱ በቀጥታ ያመሩት ያቋረጡትን የህክምና ትምህርት ለመቀጠል ወደ ጎንደር ከተማ ነበር። ጎንደር ከተማ ገብተውም ወደ ትምህርት አለሙ በመቀላቀል በእድገት በህብረት ዘመቻ ምክንያት ዳር ሳያደርሱ የተውትን ትምህርት ቀጠሉ። ለትምህርቱ ፍላጎት ስለነበራቸውም በጥሩ ውጤት አጠናቀው ለመመረቅ መቻላቸውን ይናገራሉ።
ያው ተማሪ ለፍቶ፣ ተምሮ፣ ተመርቆ መጨረሻው ስራ ማግኘት፤ በዛም በሚያገኘው ደመወዝ ለትምህርት ያወጣውን ላብ መተካት፤ አልፎም ለነገ ህይወቱ ስንቅ የሚሆኑ ነገሮችን መያዝም አይደል!? አዎ፣ ወጣቱ ቦጋለም የህክምና ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ፣ ወይም ከተመረቀቁ በኋላ በቀጥታ ያመሩት ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ወደ መደባቸው የጤና ጣቢያ ሲሆን፤ ሄዶም መስራት ነበር። ግን በዚህ አገልግሎት ብዙም አልቆዩበትም።
ዶ/ር ቦጋለ ያልቆዩበትንም ምክንያት “… እንግዲህ የእድገት በህብረት ዘመቻ ዘርፈ ብዙ መልክ ያለው ነው። እኔም በሙያዬ ላገለግል በሄድኩበት አካባቢ ላይ ሌሎች ግብረ ሰናይ ደርጅቶች ደግሞ ፈንጣጣን (Smallpox) የማጥፋት ስራ ይሰሩ ነበር። በወቅቱ እኔም ከእነዚህ አካላት ጋር የመስራትን እድል አግኝቼ ነበርና አውቃቸዋለሁ፤ ያውቁኛልም። ዘመቻው ተጠናቆ እኔም ወደ ትምህርቴ ተመልሼ ተምሬ፤ ተመርቄ ስራ እየሰራሁ ባለሁበት ወቅት አብሬያቸው አንድሰራ ጠየቁኝ። የጠየቁት እኔን ብቻ አይደለም፤ ጤና ጥበቃንም ነበር። የጤና ጥበቃም ፍቃድ ስለሰጠኝ የጤና ጣቢያ ስራዬን አልቀጠልኩበትም” በማለት ነው የገለፁት።
ጤና ጥበቃም ስለፈቀደ ችግሩን የማስወገድ ስራ ላይ መግባታቸውን ይናገራሉ።
ምንም እንኳን ወቅቱ ፋንጣጣ ከኢትዮጵያ እየወጣ ያለበት ወቅት ቢሆንም፤ ኦጋዴን አካባቢ ግን ችግሩ ስለነበር እሱን ለማስወገድ ነው አብረው እንዲሰሩ የተጠየቁት። ዶክተርም ባላቸው የስራ ልምድ ፈንጣጣን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት ኦጋዴን ድረስ በመሄድ ሊወጡ ተቋሙን ተቀላቀሉ። ስራውንም በሚገባ ሰርተው ፈንጣጣም ዳግመኛ ኢትዮጵያ ላይ እንዳይከሰት አደርገው ግዳጃቸውን በሚገባ ከተወጡ በኋላ ጉዟቸውን ወደ አዲስ አበባ ስለማድረጋቸው አጫውተውናል።
“…. በወቅቱ እድገት በህብረት ላይ የሰራሁት ስራ ፈንጣጣን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት ላይ እንድሳተፍ አስመረጠኝ። በእርግጥ እኔም በዚህ ስራ በመሳተፌ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። ጥሩ ክፍያ ከአበልና መኪና ጋር ሰጥተውኝ በጥሩ ሁኔታ ነው ስራውን የሰራሁት። አጋጣሚውም የተሳካ ስለነበር ስራውን በአጭር ጊዜ ለመጨረስ በቅተናል” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
ፈንጣጣን የመዋጋት ስራው እንደተጠናቀቀ በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሜዲካል ትምህርት ቤት ነበር ያቀኑት። በዛም ለጠቅላላ ሀኪምነት የሚያበቃውን የህክምና ትምህርታቸውን (ጀነራል ፕራክቲሽነር) ለሰባት ዓመታት ያህል ለመከታተል ገቡ። በወቅቱ መልካም የሚባል የትምህርት ጊዜን ማሳለፋቸውንና ከብዙ ምርጥ መምህራን እስከ ዛሬ ድረስ የሚያስታውሱትና የሚጠቀሙበት እውቀትንም ስለማግኘታቸው ይመሰክራሉ ።
የህክምና ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም በቀጥታ ስራ የጀመሩት የኢትዮጵያ አየር ሃይል ውስጥ ሆነ። እዛም በነበሩበት ወቅት ሃኪምም፣ አባልም ለመሆን የቻሉት ዶ/ር ቦጋለ በዚህም እስከ ሻምበልነት ድረስ የዘለቀ ወራደራዊ ማዕረግን ለማግኘት በቅተዋል።
የህክምና ትምህርት ”በቃ፣ ተምሬያለህ፤ እዚህ ላይ ይበቃኛል” የሚባል አይደለም የሚሉት ዶክተር ቦጋለ ተምረው የህክምና ሙያን ቢያገኙም ጥሩ ስራ ኖሯቸው፤ ህዝባቸውን እያገለገሉ የነበረ ቢሆንም፤ ይበልጥ ተምረው፣ አውቀው፤ በተለይም ደግሞ አንድ የህክምና አይነትን በደንብ አጥንተው አገርና ህዝብ የጣለባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት በማሰብ እንቅልፍ አልተኙም። ይህንንም ህልማቸውን ለማሳካት የአየር ሃይል ስራቸውን አቋርጠው ዳግም ትምህርትቸውን ለመቀጠል ወሰኑ። በዚህም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የህክምና ትምህርት ቤት ተመልሰው ገቡ።
“… በወቅቱ እድለኛ ነኝም ማለት እችላለሁ፤ የህክምና ትምህርቴን ተምሬ እንደ ጨረስኩ አየር ሃይል ውስጥ ስራ ተመደብኩ። እዛም ከተራ ሰራተኝነት ጀምሮ አባል እስከ መሆንና ማዕረግም እስከ ማግኘት ደረስኩ። ቀጥሎም ትምህርቴን ”ስፔሻላይዝድ” አደርጋለሁ ብዬ ስጠይቅ መስሪያ ቤቴ ”ትችላለህ” ብሎ ደመወዝ እየከፈለኝ ልማር ትምህርት ቤት ገባሁ” በማለት ሁኔታውን ወደ ኋላ ያስታውሳሉ።
ነገር ግን በወቅቱ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ባለበት ጊዜ ሆስፒታሉ የካንሰር ህክምናን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማቋቋም የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ከጤና ጥበቃ ጋርም እቅድ ይዞ ስለነበር ከነበሩት የስፔሻላይዜሽን (በአንድ የህክምና (ለምሳሌ የዐይን) ዘርፍ ላይ የበለጠ መሰልጠን) ተማሪዎች መካከል እርሳቸው የመመረጥ እድልን አገኙ።
“… በወቅቱ እኔ ምንም ያማውቀው ነገር አልነበረም። ነገር ግን፣ ሆስፒታሉ ከጤና ጥበቃ ጋር ባዘጋጀው እቅድ መሰረት የካንሰር ህክምና ማዕከል ሊከፈት ሆነ። ለዚህ ደግሞ ሃኪም ትሆን ዘንድ ለትምህርቱ፤ እንዲሁም ለስራው ተመርጠሃል ተባልኩ። እኔ በወቅቱ ያስተምረኝ የነበረው አየር ሃይል ስለነበር፤ ይህ ነገር አይሆንም፣ እቸገራለሁ አልኩና መልስ ሰጠሁ። አይ አንተ ፈቃደኛ ሁን እንጂ ፕሮጀክቱ አገራዊ ስለሆነ ቀጣሪዎችህን እናነጋግራለን፤ እንጨርሳለን አሉ፤ አይ እንደዛማ ካደረጋችሁልኝ ለእኔ ትልቅ እድል ነው በማለት ፈቃደኝነቴን ገለጽኩ” ይላሉ።
በወቅቱ አየር ሃይል የጉዳዩን አስፈላጊነት ወደ ፊትም ለአገር የሚኖረውን ተስፋ በማየት ችግር የለውም፤ ይሰልጥን በማለት ፍቃድ ሰጣቸው። እርሳቸውም በካንሰር ህክምና ላይ ስፔሻላይዝድ ለማድረግ ጉዟቸውን ወደ ግብጽ ዋና ከተማ፣ ካይሮ አደረጉ። በወቅቱ ካይሮ በመሄድ የካንሰር ህክምና ስልጠናን የወሰዱት ብቸኛው ሰውም ሆኑ። ከዛ በኋላ ግን ነጻ የትምህርት እድል በመሰጠቱ ሌሎች ሃኪሞች፣ ቴክኖሎጂስቶች፣ ሜዲካል ፊዚስቶች፣ መሰልጠናቸውን ይናገራሉ።
ካይሮ ትምህርታቸውን እየተማሩ ብዙ ነገሮችን ”አገሬ ላይ ቢሆን” ብለው የሚመኟቸውን የህክምና ጥበቦች፤ በተለይም ደግሞ በካንሰር ህክምና በኩል እንዳዩ ይናገራሉ። ትምህርታቸውን በተያዘላቸው ጊዜ ሰሌዳ መሰረት አጠናቀው ወደ አገራቸው እንደተመለሱም በቀጥታ ያመሩት ወደ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የካንሰር ህክምና ክፍል ነበር። ወደ’ዛ ያምሩ እንጂ በወቅቱ የመጀመሪያው ሃኪምም ሆነው የሰለጠኑት እሳቸው ብቻ ናቸው። የህክምና ማዕከሉም ገና አልተደራጀም ነበር። ስለዚህ ህክምና ክፍሉን ከማደራጀት ጀምሮ ህክምናውን መስጠትም የእርሳቸው ሃላፊነት ሆነ። የተሰጣቸውንም ሃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ብቸኛው ሀኪም እሳቸው ሆነው የህክምና ክፍሉ እውን ሆነ።
“…. በወቅቱ በሽታው እንደአሁኑ ስር የሰደደና ብዙ ሰዎች ላይ የሚታይ ባይሆንም በአገራችን የካንሰር ህመምተኞች ነበሩ። ህክምናው ግን አይታወቅምም፤ አይሰጥምም ነበር። በሌላ በኩልም በሰዎች ዘንድ ስለ ህመሙ የነበረው ግንዛቤ አናሳ ስለሆነ ህመሙ የሚታይባቸው ሰዎች ወደ ህክምና ተቋም የሚመጡት ዘግይተው፣ በሽታው ወደ መላ ሰውነታቸው ከተሰራጨ በኋላ ነበር። ይህ ደግሞ የተሟላ ህክምናም ካለመኖሩ ጋር ተደማምሮ ብዙዎቹ ቀናቸውን እየጠበቁ ያልፉ ነበር” ይላሉ ያንን ክፉ ጊዜ ከሙያ አኳያ እያስታወሱ።
ወደ ካንሰር ህክምና ትምህርት ሲገቡ የፈቀደላቸው አየር ሃይል አሁን በቃ በተማረበት ሙያ ያገልግል በማለት ሙሉ በሙሉ ለቀቃቸው። ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲዘዋወሩም መልካም ፍቃዱ ሆነ። በመሆኑም ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ገብተው የህክምና ቦታውን መምረጥ፣ ቤቱን ማሰራት፣ የህክምና ግብዓቶችን፤ እንዲሁም መድሃኒት እንዲሟላ ማድረጉ ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራታቸውን ቀጠሉ።
“… ከትምህርት ከመጣሁ በኋላ የህክምና ስራዬን ከመስራት ባሻገር ዋና ስራዬ የነበረው የህክምና ቤቱን ማስገንባት፣ የህክምና እቃዎችን ማሟላት ነበር። ይህንንም በሚገባ በመስራት የህክምና ማዕከሉ መስራት በሚችልበት ቁመና ላይ እንዲገኝ አድርጌዋለሁ”በማለት ስራቸውንና በመስራታቸው የተሰማቸውን እርካታ ይገልፁታል።
ይህንን ስራም በሚገባ የተወጡት ዶ/ር ቦጋለ ቤቱ ተሰርቷል፤ እቃው ከሞላ ጎደልም ቢሆን ተሟልቷልና በቃ ብለው አልተቀመጡም። ይልቁንም ህመምተኞች ከመላው አገሪቱ የሚመጡ ከመሆናቸው አንጻር፣ እንዲሁም በሽታው ስለሚጎዳቸውም አብዛኞቹን ስቃያቸውን ከማስታገስ የዘለለ ህክምና መስጠት አለመቻሉም በጣም ይረብሻቸው ነበር። ይህ እንዳለ ሆኖ ደግሞ በሽታው እንደታየባቸው ለመጡት ሰዎች ከኦፕሬሽን ጀምሮ የጨረር ህክምናን ሰጥቶ ተገቢውን ድጋፍ እስከማድረግ የደረሰ ከፍተኛ ስራንም ያከናውኑ ነበር ።
“… አሁን ላይ እኛ የካንሰር ሃኪም ሆነን ስራ ከጀመርንበት ጊዜ ጋር የማይነጻጸሩ ብዙ ለውጦች አሉ። በወቅቱ እንዳልኩሽ በበሽታው ላይ ህብረተሰቡ የነበረው አረዳድ ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋም መሄድ ላይ የነበረው ችግር፤ ከዛም ወደ ጤና ተቋም ሲመጣ ህክምናው በአንድ ሆስፒታል በጥቂት ባለሙያዎች ብቻ መሰጠቱ ከፍተኛ የሆነ ችግር ነበር። ዛሬ ላይ ግን ብዙ የተሻሻሉ ነገሮች ከመኖራቸውም በላይ አሁን ህክምናው በአብዛኞቹ የግልና የመንግስት ሆስፒታሎችም ይገኛል። ለእኔ ይህንን ማየቴ ደግሞ ትልቅ ነገር ነው። ትልቅ ደስታ ነው የሚፈጥርብኝ” ይላሉ።
ይህም ቢሆን የበሽታው መስፋፋት፣ ፍጥነትና ሌሎችም ነገሮች ተደማምረው፤ እንዲሁም አለም የደረሰብትን የቴክኖሊጂ ደረጃ ሲያዩት አገራችን ገና ብዙ መስራት ይቀራታል ይላሉ። በመሆኑም የካንሰር በሽታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ እንጂ የሚቀንስ ባለመሆኑ ፖሊሲ አውጪዎችም፤ ጤና ሚኒስቴር አካባቢ ያሉ ሰዎችም ትልቅ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ስለመሆኑም አበክረው ይናገራሉ።
እንደው የችግሩን ውስብስብነትና ህመሙ ከሚያስከትለው ከፍተኛ ስቃይ አኳያ ሲያዩ፤ እንዲሁም ሰዎች ሲረዱሲ ቆይተው ህይወታቸው ሲያልፍ ”ምነው ባልተማርኩ” አላሉም ነበር? በማለት ላነሳንላቸው ሃሳብም፤
“… አይ እንደውም ካይሮ ትምህርት ላይ በነበርኩበት ጊዜ በአገሪቱ ያለው የህክምና አማራጭ፣ የመድሃኒቱ ብዛት ሰዎች በበሽታው ላይ ትልቅ ግንዛቤ ያላቸው በመሆናቸው ምልክት እንዳዩ መጥተው፣ ታክመውና ድነው ሲሄዱ ሳይ ’መቼ ነው እኔም አገር ይህን መሰሉ የህክምና አሰጣጥ ተፈጥሮ እንደ ካይሮ ነዋሪዎች ሁሉ ኢትዮጵያዊያንም ከህመማቸው ድነው የማይበትን ቀን?’ በማለት ነበር የምመኘውም። ምንም እንኳን የወገኖቻችን ችግር ሰፊና ውስብስብ ቢሆንም የግንዛቤ ችግሩም አለ። አሁን ላይ ህክምናው እየተሰጠ ብዙዎችም እየዳኑ መሆኑን ሳይ ’እንኳንም ተማርኩት’ ነው የምለው” ይላሉ።
ዶክተር ቦጋለ በስራ ምክንያት በበርካታ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ እንዲሁም የእሲያ አገራት ተዘዋውረዋል። በእነዚህ አገሮች ደግሞ ብዙ ተሞክሮዎችንም ቀስመው ነው የመጡት። ካዯዋቸውና እርሳቸው አስፈላጊና ጥሩ ነው ከሚሉት ነገር አንዱ ደግሞ ሰዎች ለካንሰር ህመም እንዳይዳረጉ ቅድመ መከላካል ላይ መስራቱን ነው። ሌላው በሽታው በአነስተኛ ደረጃ ላይ እያለ ተገኝቶ ማከመን ነው። እነዚህን ልምዶች ወደ አገራችን ለማምጣት የህክምና ማዕከላቱ ጉዳይ በዚህ ደረጃ ፈጣንና ቀልጣፋ ህክምናን ለመስጠት ያስችላል ባይባልም ቅሉ፤ ወደ ፊት ግን ሌሎች አገራት በሚሄዱበት መንገድ ተጉዘን ወገናችንን ከበሽታው እንታደጋለን የሚል ተስፋ አላቸው።
“… እኛም እንደሌሎቹ አገሮች ካንሰርን አክመን የምንድንበት ጊዜ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ። አሁንም ከበፊቱ የተሻለ ደረጃ ላይ ነን ብዬ ለመናገር እደፍራለሁ” ይላሉ።
ዶክተር ቦጋለ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የካንሰር ስፔሻሊስት ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚገኘውንም የካንሰር ህክምና ማዕከል አደራጅተው ለስራ ያበቁ ምሁር ናቸው። ከዚህ ጎን ለጎንም የህክምና ባለሙያ ከሆኑት ባለቤታቸው ጋር ትዳር መስርተው የሁለት ወንዶችና የአንዲት ሴት ልጅ አባትም ናቸው።
በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ የእናትና አባታቸውን ፈለግ ተከትለው ሶስቱም ልጆቻቸው የህክምና ባለሙያ በመሆን ነው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት። ዶ/ር ቦጋለ በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያ ልጃቸው ትዳር መስርቶ የልጅ ልጅ አሳይቷቸዋል።
በካንሰር ህክምናው ዘርፍ ቢሆን …..
የካንሰር ህክምና ከፍተኛ የሆነ ትኩረትን የሚፈልግ ነገር ነው። አሁን ባለው ሁኔታ በሽታውን መከላከል የምንችልበት ቁመና ላይ ነን ለማለት አያስደፈርም። የህክምና አገልግሎቱ ዝቅተኛ ከመሆኑ አንጻር ህመምተኞቻችንን እንኳን በአግባቡ የሚገባቸውን ህክምን እንዲያገኙ ማስቻል ላይ አልደረስንም።
ከዚህ ቀደም ካንሰር ያደጉ አገራት በሽታ ሆኖ ቆይቷል። ዛሬ ላይ ግን ያ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል። እንደውም፣ የእኛ የደሀ አገራት ትልቅ ችግር ሆኖ ነው ያለው። በመሆኑም በሽታው ከዚህ በኋላም ቢሆን በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የሚሄድ በመሆኑ መጠንቀቁ በጣም አስፈላጊ ነው።
በነገራችን ላይ ያደጉት አገራት ከእኛም በፊት ህመሙን ስለሚያውቁትና በቂ ዝግጅትም ያደረጉ በመሆናቸው አክሞ ማዳኑ ለእነሱ ከባድ አልነበረም። እኛ ግን የህክምና ሁኔታችን በቂ ካለመሆኑ አንጻር፤ እንዲሁም፣ ክልሎችም ላይ በበቂ ሁኔታ ያላዳረስነው የህክምና አሰጣጥ ሁኔታ ስላለ፤ ሰዎችም ህመሙ ሲጠናባቸው ስለሆነ ወደ ህክምና ተቋሟት የሚመጡት አክሞ ማዳኑ ፈታኝ ይሆናል።
ወደ ፊት ግን እነዚህ ሁኔታዎች እየተሻሻሉ በአነስተኛ ደረጃ ህመሙን አግኝቶ ማከሙም ሆነ መከላከሉ ላይ የሚሰራው ስራ እየተሻሻለ ከሄደ፤ በካንሰር የሚሞቱ ህሙማን ቁጥር እየቀነሰ እንደሚሄድ ተስፋ አለኝ። ያደጉት አገራት ተሞክሮም የሚያሳየው ይህንን ነው። በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም