በሀገራችን እንደ ወረርሽኝ በስፋትና በፍጥነት እየተዛመተ ስለመጣውና ከግለሰብም፣ ከተቋምና ከመንግስትም ጋር ያለንን ግንኙነት በብርቱ እየፈተነ፤ ወዲህ ደግሞ የዕለት ተዕለት የህይወታችን አካል ስለሆነውና መጠራጠርን እየጎነቆለ ስላለው “የማመን ኪሳራ”ወይም”ትረስት ዴፊሲቲ” አልያም “ትረስት ዲስፕሌስመንት” በቀጣይ ለማጠናቀር ላሰብሁት መጣጥፍ መንደርደሪያ ይሆን ዘንድ በወቅቱ አለምን ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ አነጋግሮ ስለነበር ፤ አለምአቀፍ ሚዲያው ዳር እስከ ዳር ተቀባብሎ ስለዘገበው ፤ በርካታ ዘጋቢ ፊልሞች ፣ ፊልሞች ስለተሰሩለትና አያሌ መጽሐፍት ስለተጻፉለት አንድ ሞልቶ ስለፈሰሰ መታመንና ጽናት እነሆ ብያለሁ። እገረ መንገዳችሁንም ራሳችሁን በባለታሪኩ ስፍራ አስቀምጣችሁ ትገመግማላችሁ። የመታመን ኪሳራችሁንም ትተሳሰባላችሁ ። መቶ አለቃ ኦኖዳ በ2010 ዓም ከአውስትራሊያው ABC ቴሌቪዥን ጋር በነበረው ቃለ መጠይቅ ፤ “ ቆፍጣና መኮንን ነኝ። የተሰጠኝን ግዳጅ እወጣለሁ ። ይሄን አለማድረግ ለእኔ የሞት ሞትና ትልቅ ውርደት ነው ። “ነበር ያለው፤ ኦኖዳ በኋላ ላይ ደግሞ ፤” እጅ አልሰጥም ፦ የ30 አመታት ጦርነቴ ፤ “ በሚል ለንባብ ባበቃው ግለ ማስታወሻ ፤” የአዛዤ የመጨረሻ ትዕዛዝ በጽናት ተዋጋ ! “የሚል ነበር ። እጅ ስጥ የሚለው ትዕዛዝ ከንጉሱ ወይም ከበላይ አዛዦቼ እስኪደርሰኝ ድረስ ለ30 አመት በጽናት ትጥቄን ከወገቤ ሳልፈታ በጽናት ቆይቻለሁ ። በማለት ለሀገሩና ለንጉሱ ያለውን ፍጹም ታማኝነት ያለምንም ማወላዳት ገልጿል ።
ኦኖዳ በሰው ሀገር ጫካ ብቻውን ቀረ ። ጓዶቹን አንድ በአንድ አጣ። ራሱን እንዳያጠፋ የቅርብ አዛዡ ወታደራዊ ትዕዛዝ ትላንት ያዳመጠው ያህል በእዝነ ህሊናው ህያው ሆኖ ይሰመዋል። በስሩ የሚያዝዘው ወታደር እንደሌለው ሲያስብ የሀገሩንና የንጉሱን አደራ የበላ እየመሰለው በጥፋተኝነት አባዜ ከራሱ ጋር ይወዛገባል ። መቶ አለቃ ከ30 አመታት በፊት እጅ መስጠትም ሆነ ራስን ማጥፋት በጥብቅ የተከለከለ ነው ብሎ ወታደራዊ ትዕዛዝ የሰጠው ሻለቃ መልሶ እጅ ስጥ ሲለው መጀመሪያ ክው ብሎ ደነገጠ ከዚያ የሚሰማውን ለማመን ተቸገረ ።
ግራ ተጋባ። ለተወሰኑ ደቂቃዎች ወደ ቀልቡ ለመመለስም ተቸገረ ።
በ1941 ዓም ጃፓን ፤ ሆኖሉሉ ፣ ሀዋይ የሚገኘውን “ፐርል ሀርበር” የተሰኘውን የአሜሪካ የባሕር ኃይል ማዘዣን ድንገት በአየር አጥቅታ ከ2400 በላይ ወታደሮችን መግደሏ ፤ በርካቶችን ቁስለኛ ማድረጓና ተዋጊ መርከቦችንና አውሮፕላኖቹን መደምሰሷ አሜሪካን የ2ኛውን የአለም ጦርነት እንድትቀላቀል ምክንያት ሆኗታል። ለመጀመሪያ ጊዜ የአቶሚክ ቦንብ ለመጠቀሟ እንደ አንድ መግፍኤ ተደርጎም ይወሳል ፡፡ (በነገራችን ላይ ሁሉም የዘመን አቆጣጠሮች እንደ አውሮፓውያን ናቸው ) በዚህም የነጋሳኬና የሔሮሽማ ከተሞች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል ፡፡ ከሁለቱ ከተሞች ወደ 230ሽ የሚጠጉ ነዋሪዎች ሲገደሉ የተረፉት ደግሞ የዘር ሀረጋቸው በአቶሚክ ቦምቡ ጠንቅ ዛሬ ድረስ ጤናቸው እየታወከ መሆኑ ይነገራል፡፡ ለዚህ ነው በአንዳንድ ኃይሎች ዘንድ የአቶሚክ ቦንብ የ2ኛውን የአለም ጦርነት በማስቆም ረገድ አስተዋፆ እንዳለው የሚታመነው ። የወቅቱ የጃፓን ንጉስ ሒሮሂቶ በሀገሩ ነገስታት ታሪክ እንኳን ሊፈጸም በፍጹም ሊታሰብ የማይችል ውሳኔ አሳለፈ ። በሬዲዮ ቀርቦ በአቶሚክ ቦንብ ሒሮሽማና ነጋሳኪ መውደማቸውን፤ ጆሴፍ ስታሊን በጃፓን ላይ ጦርነት ማወጁን ፤ ጦሩም ወደ ማንቹሪያ እየገሰገሰ ስለሆነ በሳምንታት ውስጥ ሰሜናዊ ደሴቷን ሆካይዶ ሊቆጣጠር ስለሚችል ያለን ብቸኛ አማራጭ ለባለቃልኪዳኑ ሀገራት እጃችንን መስጠት ነው በማለት የጃፓንን መራር ሽንፈት ለሕዝቡ አረዳ ።
ጃፓን በ2ኛው የአለም ጦርነት በአሜሪካ ከተሸነፈች ቦኋላ ፤ በ1945 ሙሉ በሙሉ እጇን ለመስጠት ተገዳለች፤ ጥቂት የማይባሉ የጦር ጄኔራሎቿ፣ መኮንኖችና ወታደሮቿም ይህን መሪር ሀቅ ላለመቀበል እጅ ላለመስጠት ለቀናት ፣ ለሳምንታት አንገራግረው ነበር ፡፡ ሂሮ ኦኖዳ የተባለው መኮንን ግን እስከ 1974 ዓም ድረስ ለ30 አመታት የሀገሩን መሸነፍና እጅ መስጠት አምኖ መቀበል አልፈለገም ፡፡ እናም በባዕድ ሀገር ጫካና ተራራ ፋኖ ሆነ ። “ ሶስት ወይም አምስት አመት ሊወስድብን ይችላል ። ምንም ይሁን ምን ተመልሰን እንደርስልሀለን፤ “ ሻለቃ ዮሺሚ ታኒጉኪ ለዛን ጊዜው ወጣት የመቶ አለቃ ሒሮ ኦኖዳ በወርሀ የካቲት መጨረሻ 1945 ዓ.ም ላይ ቃል ገብቶለት ነበር ። ሆኖም ሻለቃው የገባውን ቃል ኪዳን የፈጸመው በቃሉ መሠረት በሶስትና በአምስት አመታት ሳይሆን ከ30 አመታት በኋላ ነው። የለበሰው ወታደራዊ ፋቲግ ወይም የደንብ ልብስ በላዩ ላይ አልቆ ተርዞና ተጎሳቅሎና ገርጅፎ እስከ 1974 ዓ.ም ለ30 አመታት መሽጎ ከነበረበት የፊሊፒንስ ጫካ ፍጹም ተለውጦ ወደ ጠበቀው አዲስ አለም ወጣ ።
በነገራችን ላይ በ1959 ዓ.ም የጃፓን መንግስት የመቶ አለቃ ኦኖዳን ሞት በይፋ ለቤተሰቦቹ አረድቶ ነበር። ይሁንና ኖሪዎ ሱዙኪ የተባለ ገድለኛ ጃፓናዊ ወጣት ከልጅነቱ ጀምሮ ስለ መቶ አለቃ ኦኖዳ ጽናትና ጀብድ እየሰማ ስላደገ፤ በፊሊፒንስ ደሴት በህይወት ሳይኖር እንደማይቀር ሲዘገብ ሲሰማ ይሄን ተአምረኛ ሰውማ አፈላልጌ ማግኘትና ወደ ሀገሩ ማምጣት አለብኝ ብሎ ቃል ገብቶ ፤ አፈላልጎ በማግኘትም ታሪክ ለመስራት ጓዙን ቀርቅቦ ተነሳ። እንደፎከረውም በ1974 ዓ.ም አፈላልጎ ከተደበቀበት የፊሊፒን ጫካ አገኘው ። ኦኖዳ ከሱዙኪ ፊት ለፊት እንደተገጣጠመ አቀባብሎ ግንባሩን ሊፈረክሰው ነበር። ሆኖም ሱዙኪ ኦኖዳን ቢያገኘው ምን ማለት እንዳለበት ቀድሞ ተዘጋጅቶና አጥንቶ ስለነበር ሲገናኙ ፈጥኖ እጁን ወደ ላይ በማንሳት ፤” ኦኖዳ _ሳን የጃፓን ንጉስና ሕዝብ ስለ ደህንነትህ እያሰቡና እየተጨነቁ ነው ፤ “ሲለው ፤ ደግኖበት የነበረውን ጠመንጃ አፈ ሙዝ ዘቀዘቀው ። በማስከተልም ጦርነቱ ከተጠናቀቀ 30 አመት እንደሆነና እሱም ትጥቁን ፈቶና እጁን ሰጥቶ ወደ ሀገሩ መመለስ እንዳለበት ነገረው። ሆኖም የኦኖዳ ለሀገሩ የመታመን ጥግ ከአጽናፍ አጽናፍ የተሻገር ፤ ከአለት የጸና ነውና ፤ ይፋዊ ትዕዛዝ ከሀገሬ ካልደረሰኝ እጅ አልሰጥም ብሎ አሻፈረኝ አለው።
ሱዙኪም ወደ ሀገሩ ተመልሶ ኦኖዳን እንዳገኘው ገልጾ አብሮት የተነሳውን ፎቶም በማስረጃነት አቀረበ። ለሀገሩና ለንጉሱ ምን ያህል ታማኝ እንደሆነ ለሀገሩ ልጆችና ለመላው አለም አሳየ ። በመላ ጃፓንም በአለምም መነጋገሪያም ሆነ። ገድለኛው ሱዙኪ ከወራት በኋላ ከጃፓን መንግስት እጅ እንዲሰጥ የሚያዝዝ መልዕክት የያዘ ልዑክ ጋር ወደ ፊሊፒንስ ተመለሰ ። የመቶ አለቃ ኦኖዳ ታላቅ ወንድምና ከ30 አመታት በፊት እንደርስልሀለን ብሎት የነበረው የቀድሞ አዛዡ ሻለቃ ታኒጉኪ የልዑኩ አባል ነበሩ ። የዚህን ጊዜ አመነ ። ትጥቁን ፈታ ። አሪሳካ 99 ጠብመንጃውን ከእነ 500 ጥይቱ ፣ ሳንጃውንና ቦንቡን አስረክቦ እጁንም ሰጠ ። ወደ መዲናዋ ማኒላ ተወስዶ በወቅቱ የፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት ፈርዲናንድ ማርቆስ ፊት ቀርቦ ሳሙሪ ጉራዴውን ዝቅ አደረገ ። ፕሬዝዳንቱም በምላሹ ምህረት አደረጉለት። ከ2ኛው የአለም ጦርነት እጁን የሰጠ የመጨረሻ የጃፓን መኮንን ሆነ።
መጋቢት 19 ቀን 1922 ዓ.ም ካይናን ውስጥ ዋካያማ ጃፓን ተወለደ ። ሃያ አመት እንደሞላው ኦኖዳ የጃፓንን ጦር ተቀላቀለ ። ከዚያ ተመርጦ በናካኖ የወታደራዊ ደህንነት ትምህርት ቤት ስልጠናውን ተከታተለ። በቆይታው የሽምቅ ውጊያ ፣ ፍልስፍና ፣ ታሪክ፣ ማርሻል አርትና ድብቅ ዘመቻን ተማረ ። ይህ የተሟላ ስልጠና ነው በጽናት ፈተናዎችን እንዲያልፋቸው ያስቻለው። ብሂሉስ ላብ ደምን ያድናል እማይደል ። እሱና ሶስት ባልንጀሮቹ በፊሊፒንስ ሉባንግ ከአካባቢው ሰዎችና ከአሜሪካ ተላላኪዎች ጋር በተደጋጋሚ የሽምቅ ውጊያ አድርገዋል። በጦርነቱ የመጨረሻዎቹ ወራት አካባቢ አሜሪካ ከወግ አጥባቂ የጃፓን ወታደሮች ጋር ፊት ለፊት እስከመፋጠጥ ደርሰው ነበር ።
ሆኖም በመስከረም 1945 ዓ.ም ጃፓን በቃል ኪዳኑ ሀገራት ተሸንፋ እጇን ብትሰጥም እነ ኦኖዳ ግን ይሄን ማመንና እጅ መስጠት አልፈለጉም ። መቶ አለቃ ኦኖዳ ከፍ ብዬ ለጠቀስሁት የአውስትራሊያ ቴሌቪዥን ፤ “ጦርነቱ እንደአበቃና ጃፓንም ተሸንፋ እጇን እንደሰጠች የሚገልጹ በራሪ ወረቀቶች ከአየር እየተጣሉ ቢደርሱኝም ጹሑፎቹ የመረጃ ግድፈት ስለነበረባቸው አምኜ አልተቀበልኋቸውም። ይልቁን በአሜሪካ የተቀነባበረ ደባ ሊሆን ይችላል በሚል አላመንኋቸውም “ ብሏል።
ለ 30 አመታት የጫካ ሙዝ ፣ የዘንባባ ገውዝና የሩዝ ቃርሚያ በመብላት ህይወታቸውን አቆይተዋል። በሽፍትነት ዘመናቸው ከፊሊፒንስ ወታደሮችና ከደሴቷ ነዋሪዎች ጋር በተደጋጋሚ ተታኩሰዋል። በዚህም 30 ሰዎችን ገድለዋል። ሆኖም መቶ አለቃ ኦኖዳ በ1974 ዓ.ም ብቸኛ ተቅበዝባዥ ሽፍታ ነበር ። ከባልጀራዎቹ አንዱ በ1950 ዓ.ም ለፊሊፒንስ ጦር እጁን ሰጠ ። ሁለቱ በ1954 እና በ1972 ዓ.ም ከደሴቷ ፓሊሶች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ሞተዋል ። የወቅቱ የፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት ፈርዲናንድ ማርከስ በሸፍትነቱ ዘመን ለፈጸማቸው ወንጀሎች ምህረት አድርገውለት ወደ ሀገረ ጃፓን ተመለሰ። የ52 አመቱ ጎልማሳ መቶ አለቃ የጀግና አቀባበል ተደረገለት። አለም ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ገድሉን ተቀባበለው። ሆኖም ጃፓን እጅግ ተለውጣ ዜጎቿም ብልጭልጭ ቁሳቁስ አምላኪዎች ሆነው ስላገኛቸው ራሱን ከዚህ ጋር ማላመድ ቸገረው ። በቀጣዩ አመት ግርግርና ትርምስ ከበዛበት የጃፓን የከተማ ህይወት በመሸሽ የሀገሩ ቅኝ ግዛት ወደነበረችው የብራዚሏ ሳው ፓውሎ በመሔድ ከብት አርቢ በመሆን ጸጥ ያለና የተረጋጋ ህይወት በመኖር የህሊና እረፍት አደረገ ። ወዲያው የጃፓን ሻይ አፈላል ስነ ስርዓት አስተማሪ የነበረችውን ማቼ ኦኑኩን ውሃ አጣጭው አደረገ ። አገባ።
በ1984 አንድ ወጣት ከፈተና በመውደቁ ተበሳጭቶ ወላጆቹን መግደሉን ጋዜጣ ላይ ሲያነብ ፤ ወጣቱ ፈተናዎችን የማለፍ የህይወት ክህሎት ቢኖረው ኖሮ ለውድቀቱ ቤተሰቦቹን ተጠያቂ አያደርግም ነበር በሚል እልህና ቁጭት ፤ እንደኔ በፈተና የማይበገር ትውልድ መቅረጽ አለብኝ በሚል ኦኖዳ በዚሁ አመት ወደ ጃፓን በመመለስ ወጣቶች ችግርንና ፈተናን እንዴት ተቋቁመው ማለፍ እንደሚችሉ የሚያስተምር የ”ኦኖዳ የወጣት ካምፕ”ን አቋቋመ ። እንደ ዮሬው ሳሙራይስ መቶ አለቃ ኦኖዳ ከጥንቱ የጃፓን ወግ ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ነበር ። የጃፓንን ባህላዊ እሴቶችና የመስዋዕትነትን ዋጋ በተግባር ኖሮ ያሳየ ጀግና ነበር ። በ1974 ዓ.ም ለመቶ አለቃ ፤” 30 አመታት ሙሉ ጫካ ስትኖር ምን ነበር የምታስበው ? “ ተብሎ ሲጠየቅ ፤”ግዳጄን ከመወጣት ውጭ ምንም አላስብም። “የሚል አስገራሚ መልስ ሰጥቷል።
ሒሮ ኦኖዳ ሀገሩ ጦሯን እንዲቀላቀል ጥሪ ስታደርግለት የ20 አመት ወጣት ነበር ። በታጂማ ዮኮ የንግድ ኩባንያ የሀንኮ ወይም ውሃን የቻይና ቅርንጫፍ ባልደረባ ነበር ። የጤና ምርመራ ተደርጎለት ብቁ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ስራውን ለቆ ጦሩን ተቀላቀለ ። በጃፓን ጦር በመቶ አለቅነት ሰለጠነ። ከዚያም ተመርጦ የወታደራዊ ስለላ ትምህርት ተከታተለ ። ወታደራዊ መረጃ እንዴት እንደሚሰበስብና ስለ ሽምቅ ውጊያም ሰለጠነ። በታህሳስ 1944 ዓ.ም በፊሊፒንስ የሚገኘውን የሱጊ ብርጌድን ተቀላቀለ። በቅርብ አዛዦቹ የሉባንግ ምድብ የሽምቅ ውጊያ መሪ ሆነ። ለግዳጅ ከመሰማራታቸው በፊት ከክፍለ ጦሩ አዛዥ ዘንድ ቀረበው የሚከተለውን መመሪያ ተቀበሉ ። ምንም አይነት ፈተናና መከራ ቢያጋጥም የገዛ ህይወትን ማጥፋት በፍጹም የተከለከለ ነው። የሚበላ ጠፍቶ የዘንባባ ገውዝ ለመብላት ብትገደዱ እንኳ እሱን እየበላችሁ ህይወታችሁን ማቆየት አለባችሁ። በዕዝህ ሁሉም ተሰውቶ አንድ ወታደር ብቻ ቢተርፍ እንኳ እስከ መጨረሻው በጥብቅ ዲሲፕሊን የመምራት ወታደራዊ ግዴታ አለብህ። ለመቶ አለቃ ኦኖዳ ግን ይህ ወታደራዊ መመሪያ በልቡ ታትሞ የኖረ የህይወት ዘመን ቃል ኪዳን ነበር።
መቶ አለቃ ትጥቅ ፈቶ እንጂ ስለሰጠባት ክፉ ቀን ሲጠየቅ፤ ሁሉም ነገር ጨለመብኝ። ዙሪያው ገደል ሆነብኝ። በውስጤ ማዕበል ሲነሳ ተሰማኝ። የተሞኘሁ ያህል ተሰማኝ። ማኒላ እስክደርስ የሆነው ሁሉ አምኖ መቀበል ተቸገርሁ። እየቆየ በውስጤ የተቀሰቀሰው ማዕበል እየቀነሰ ሲመጣ ታወቀኝ። የሆነውን ነገር መገንዘብ ጀመርሁ። ለ30 አመታት ለሀገሬ ጃፓንና ንጉስ ጦር ስል ሳካሂደው የነበረ የሽምቅ መጠናቀቁን አምኜ ተቀበልሁ ። መቶ አለቃ አኖዳ በ1996 ዓ.ም ለ30 አመታት የሸመቀባትን ጓደኞቹንና የዕድሜውን ሲሶ የገበረባትን የፊሊፒንሷን ሉባንግ ደሴት ተመልሶ ጎበኘ። እገረ መንገዱንም ተሰናበታት። ዙሮ ዙሮ ከቤት ኑሮ ኑሮ ከሞት አይቀርምና በ91 አመቱ በ2014 ዓ.ም ይቺን መልቲ አለም ተሰናበታት። በሀገሩ ብሔራዊ የጀግና የቀብር ስነስርዓት ተካሄደለት። ሞቱን ታዋቂ የአለማችን ብዙኃን መገናኛዎች ተቀባበሉት።
ለሀገራችንና ለሕዝባችን የምንታመንበትን ዘመን ፈጣሪ ያቅርብልን !አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም