ክረምት ሲመጣ ብርድ ያንሰፈስፋል፤ ባዶ ሆድ ሲሆኑ ቅዝቃዜው ይበልጥ ይበረታል። በዚህ ጊዜ የሚበላው ያለው እያሟሟቀ ትኩስ ትኩሱን ይበላል። የሌለው ደግሞ አይኑን ጨፍኖ ‹‹ ዳቦ የለም እንጂ ወተት በነበረ በርሱ ማግ እያረግን እንበላ ነበረ ›› እያለ ከመመኘት አልፎ ትኩስ ትኩሱን የሚበላውን በማጣቱ እየተበሳጨ ይብሰከሰካል። አዋቂዎች ብቻ አይደሉም፤ ህፃናትም ሲርባቸው ስለምግብ ይመኛሉ፤ ያስባሉ፤ ባይብሰከሰኩም እየተነጫነጩ እየተጣሉ ረሃባቸው እስኪታወቅባቸው ያለቅሳሉ።
ሕፃናት በጋ ላይ በሞቀ ፀሐይ ጊዜ ያገኙት የነበረውን ምግብ ክረምት ላይ ሲያጡት ሕይወት ቀላል አትሆንላቸውም። ከብስጭት እና ከእንባቸው አልፎ ለብርድ (ለሳንባ ምች) እና ለሌሎችም በሽታዎች መጋለጣቸው አይቀርም። ይሄኔ የተወዳጁ ድምፃዊ የጥላሁን ገሠሠ ዘፈን በአዕምሮ ውስጥ መምጣቱ አይቀርም። ‹‹ ዋይ ዋይ ዋይ ሲሉ፤ የረሃብን ጉንፋን ሲስሉ ›› እንግዲህ ክረምትና ረሃብ ተያይዘው የጉንፋን ሳል ማምጣታቸው አይቀሬ ይሆናል።
ክረምት ሲመጣ የልጆች መታመም እና መሰቃየት የተለመደ ይሆናል። እዚህ ላይ ማረጋገጫ ለማግኘት የአሁኑን ክረምት ተከትሎ በአዲስ አበባ የተለያዩ ጎዳናዎች ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች ዞር ዞር በማለት ሕፃናትን ማየት ተራ ነገርን እንደመመልከት ይቆጠራል።
ክረምት እና ረሃብ ሲነሳ ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ ሕፃናት፣ ልጆቻቸውን በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መመገብ የማይችሉ እና በቂ ገቢ የሌላቸው ወላጆች ልጆች በረሃብ እየተሰቃዩ በመማሪያ ክፍል ውስጥ ራሳቸውን ስተው እየወደቁ ስለመሆኑ በአዲስ አበባ መወራት ከጀመረ አሥር ዓመታት ተቆጠሩ። ከወሬው አልፎ በ2006ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮና የሴቶችና ህጻናት ቢሮ በጋራ ያደረጉት የዳሰሳ ጥናት በማስረጃ ተደግፎ እንደቀረበው ከ20ሺ በላይ የሚሆኑ ህፃናት በዛ ዓመት በቂ ምግብ ባለማግኘት የተነሳ የከፋ ደረጃ ላይ እንደደረሱ ይፋ ተደርጓል።
ተማሪዎች በረሃብ ትምህርታቸውን ለመከታተል ስለመቸገራቸው መገለፁን ተከትሎ ሕፃናትን በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመመገብ መርሐ ግብር መጀመርን በሚመለከት በብዙዎች ዘንድ ሃሳቡ መጉላላት ጀምሯል። በተለይ የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ የነቃ ተሳትፎ የሚዘነጋ አይደለም።
ይህ ሃሳብ ምንም እንኳን ቀድሞ ሰብዓዊነትን ተከትሎ የተነሳ ሃሳብ ቢሆንም በተጨማሪነት ህፃናት እንክብካቤ የማግኘት መብት ስላላቸው የትምህርት ቤት ምገባ መኖር አለበት የሚል ሃሳብ መሰንዘር ቀጠለ። በአንዳንድ በጎ ፈቃደኞች በጥቂቱ ይካሔድ ከነበረ ምገባ በተጨማሪ በ220 የቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ከ22ሺህ በላይ የሚሆኑና የከፋ ድህነት ላለባቸው ተማሪዎች በእናት ወግ በጎ አድራጎት ማህበር እንዲሁም በመምህራንና በትምህርት ቤት ማህበረሰብ፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት፣ ግለሰቦች እንዲሁም የተለያዩ በጎ አድራጎት ሥራ ላይ በተሰማሩ አካላት ደግሞ ከ10ሺህ 119 በላይ የሚሆኑና በቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ለሚማሩ የመንግሥት ተማሪዎች በምገባ መርሐ ግብር ተጠቃሚ መሆን ቻሉ።
ጤናማና የተማረ ማህበረሰብ መፍጠር ለአንድ አገር ህልውና መሰረት በመሆኑ ለትምህርት ቤቶች የሚውለው በጀት ለኢንቨስትመንት እና ለግንባታ ብቻ ሳይሆን፤ ለምገባም መዋል እንዳለበት ሙሉ ለሙሉ ታመነ። ተማሪዎች በቂ ምግብ ባለማግኘታቸው ምክንያት የነበረውን የተማሪ መቅረት፤ የክፍል ደረጃ መድገም እና ትምህርት ማቋረጥ ላይ የነበሩትን ከፍተኛ ችግሮች ማቃለል ተቻለ። በተጨማሪ በቂ ምግብ ሳያገኙ ተርበው ሲማሩ የሚውሉ ልጆች ትምህርቱን ለመረዳት የሚያዳግታቸው በመሆኑ በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስላለው ይመገቡ ከማለት በተጨማሪ በቂ፣ ጤናማ እና የተመጣጠነ የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር በተገቢው መልኩ መካሔድ እንዳለበት ታምኖ በመንግሥት ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት እስከ አሁን ቀጠለ።
ይህ እጅግ በጣም ብዙዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ያለ የምገባ መርሐ ግብር አሁን ደግሞ ከትምህርት አንፃር ብቻ ሳይሆን ከሰብዓዊነት እና ልጆች በቂ ምግብ የማግኘት መብት ያላቸው በመሆኑ በክረምትም ምግብ የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበት ብዙዎች ሃሳብ በመሰንዘር ላይ ናቸው። እንደበጋው የተማሪዎች ምገባ ሁሉ የክረምት ምገባ አስፈላጊነትን ስናነሳ በእርግጥም ባዶ ምሳ ዕቃ ይዘው የሚሔዱ፤ አንዳንዴም ከጓደኞቻቸው የሚወድቅ ፍርፋሪን ለቅመው ይበሉ የነበሩ ልጆች የትምህርት መዘጋት ሆዳቸው ባዶ ሆኖ ቀናትን እንዲገፉ ያስገድዳቸዋል።
ክረምት ላይ ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ የሚያጋጥማቸውን ርሃብ መገመት አያዳግትም። ከትምህርት አንፃርም ከታየ በአንድ ወቅት ብቻ በቂ ምግብ ማግኘት ውጤታማ አያደርግም። በክረምት በረሃብ እና በበሽታ ሲሰቃዩ የነበሩ ልጆች በጋ ላይ ምግብ ስላገኙ ብቻ ጤናማ ይሆናሉ ብሎ ማመን ችግሩን ማገናዘብ አለመቻል ነው።
በትክክል ከሰብዓዊነትም ሆነ ከትምህርት ጥራት እንዲሁም ልጆች ካላቸው በቂ ምግብ የማግኘት መብት አንፃር ከታየ የበጋ ወይም የትምህርት ጊዜ ምገባ ብቻ ሳይሆን የክረምት ወቅት ምገባም ያስፈልጋል። የክረምት ምገባ ከሌለ በረሃብ ምክንያት ራሳቸውን ስተው ትምህርት ቤት ውስጥ ይወድቁ የነበሩ ልጆች ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን ቤታቸውም ያለማንም ተመልካች ራሳቸውን ስተው የሚወድቁበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ነጋሪ አያሻም።
የበጋው ምገባ ከትምህርት ቤት ይቀራሉ፤ትምህርት ያቋርጣሉ፤ ክፍል ይደግማሉ በማለት እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ቢሆንም የሌሎች ተማሪዎችን ትርፍራፊ በመልቀም ይበሉ የነበሩ ሕፃናት በክረምትም ከቤታቸው ወጥተው ምግብ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ወደ ሌላ ተግባር ማለትም ወደ ስርቆት ሊገቡ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። ይህ ሲቀጥል በጋ ላይ ትምህርታቸውን እንዳይቀጥሉ ሊገደዱ ይችላሉ። ምክንያቱም በአንድ በኩል የስርቆት ተግባርን የሚቀጥሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። ወይም ወደ ማረሚያ ቤት የሚገቡበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። በሌላ በኩል ስርቆታቸው ከታወቀ የመገለልና የበታችነት ስሜት ይሰማቸዋል። ይህ ልጆቹን ቁጡና ተናዳጅ ስለሚያደርጋቸው ሌሎች ተማሪዎች ላይም ሆነ መምህራን ላይ ጫና ይፈጥራል። ይህም ተያይዞ የትምህርት ጥራት ላይ የራሱን አሉታዊ ጫና ይፈጥራል።
ይህንን ችግር ለማቃለል በተለይም በዋናነት በቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በበላይ ጠባቂነት ሴት መምህራንን የቦርድ አባል በማድረግ በ2007 ዓ.ም በተቋቋመው የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማህበር በይፋ የተጀመረው የትምህርት ቤት ምገባ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ሲቀጥል የክረምት ጉዳይ ብዙም ትኩረት ያላገኘ በመሆኑ አሁን ግን ተገቢውን ትኩረት ማግኘት አለበት።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በ2011ዓ.ም የትምህርት ቤት ምገባ በ241 ትምህርት ቤቶች ከ311 ሺህ 523 በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ሆነዋል። በአዲስ አበባ የመንግሥት አንደኛ ደረጃና ቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በአጠቃላይ በሙሉ ተደራሽ የተደረገው የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር ለ6ሺህ 969 ለሚሆኑ ሥራ አጥ እናቶች የሥራ እድል ፈጥሮላቸዋል። ይሁን እንጂ የክረምት ምገባ የለም። ይህ በተማሪዎች ፣ በወላጆች፣ በመምህራን እና ብሎም በትምህርት ጥራት ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ከወዲሁ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም