ከሳሽ ፍርድን በመሻት ስኳር ኮርፖሬሽንን ችሎት አቁመዋል:: ግራ ቀኝ ሙግት በመግጠም በሥር ፍርድ ቤት የተወሰነውን አልፈፅምም በሚል እሳቤ እስከ ሰበር ደርሷል:: የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ውሳኔዎች የሚያሳትም ሲሆን፤ በቅፅ 15 በሰነድ መለያ ቁጥር 84661 መጋቢት 27 ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት ዳኞች ተሰይመው እና አመልካች አቶ ዳዊት ሸዋቀና በአካል ሳይቀርቡ እና ተጠሪው ስኳር ኮርፖሬሽን ነገረ ፈጅ አቶ ጌታቸው አክሊሉ ቀርበው መዝገቡ ተመርምሮ ፍርድ ተሰጥቷል:: የዝግጅት ክፍላችንም የክርክሩን ሂደት በዚህ መንገድ አቅርቦታል::
የክሱ ጭብጥ
ለእዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ የሰበር አመልካች ከሳሽነት የተጀመረው በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን ተጠሪው ደግሞ ተከሳሽ ነበር:: ክሱም በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ የኦዲት ክፍል ኃላፊ ሆኜ እየሠራሁ የሥራ አፈጻጸምህ ዝቅተኛ ነው፤ እንዲሁም በሥራ ላይ ቸልተኝነት አሳይተሃል በሚል ያለማስጠንቀቂያ ሐምሌ 11 ቀን 2003 ዓ.ም የሥራ ውሌን ያቋረጠብኝ በመሆኑ ወደ ሥራ እንዲመልሰኝ ካልሆነም ካሳ፣ የስንብት ክፍያ፣ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ፣ ክፍያ በዘገየበት እና የዓመት ዕረፍት ወደ ገንዘብ ተለውጦ እንዲከፍል ይወሰንልኝ የሚል ነው::
ተከሳሽ ምን አለ?
ለክሱ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያና በአማራጭ በፍሬ ጉዳዩ ላይ መልስ ሰጠ:: ከሳሽ ከሥራ የተሰናበቱበት ምክንያት በተሰጣቸው የስንብት ደብዳቤ ላይ የተገለጸላቸው ሲሆን፤ ወደ ሥራ ለመመለስ ያቀረቡት ጥያቄም ተቀባይነት የሚኖረው አይደለም፤ እንዲሁም እንዲከፈላቸው ከጠየቁዋቸው ክፍያዎች ውስጥ የዓመት ዕረፍት ወደ ገንዘብ ተለውጦ ተከፍሏቸዋል:: ሌሎች ክፍያዎች ዳግሞ ሊከፈሏቸው አይገባም ሲል ተከራከረ::
የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔ
የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ተከሳሽ ያቀረበውን መቃወሚያ ቀደም ሲል በብይን ውድቅ ማድረጉን በመግለጽ በሰጠው ፍርድ፤ ተከሳሽ ለከሳሽ በጻፈው የስንብት ደብዳቤ የሥራ አፈጻጸማቸው ሲገመገም ዝቅተኛ ስለመሆኑ የተመዘኑበትን ማስረጃ ካለመቅረቡም ሌላ በሥራቸው ቸልተኝነት አሳይተዋል ቢልም በምን ምክንያት ቸልተኝነት እንዳሳዩ አልዘረዘረም በማለት የሥራ ውሉ በሕገ ወጥ መንገድ ተቋርጧል ሲል ወስኗል::
ከሳሽ በአማራጭ ያቀረቡትን የዳኝነት ጥያቄ ማለትም የሥራ መሪ ያለበቂ ምክንያት ከሥራ አሠሪው ቢያሰናብት ወደ ሥራ የመመለስ መብት እንዳለው በፍትሐብሔር ሕጉ፣ በኅብረት ስምምነቱም ሆነ በሥራ መሪዎች የመተዳደሪያ ደንብ ስላልተገለጸ ተቀባይነት የለውም ሲል ወድቅ አድርጓል:: ከሳሽ እንዲከፈላቸው የጠየቁትን ክፍያዎች በተመለከተም የስንብት ክፍያ እንዲከፈላቸው ሲወስን፤ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ግን ከሳሽ የሚሠሩበት ሥራ የእምነት ሥራ እና ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ ማስጠንቀቂያ አለመስጠት በፍትሐብሄር ቁጥር 2577(2) መሠረት ኪሣራ የሚያስከትል አይሆንም ሲል አልተቀበለውም::
ካሳ እንዲከፈላቸው ያቀረቡት ጥያቄንም የሕግ መሠረት ያለው አይደለም በሚል ውድቅ ሲያደርግ፤ የዓመት ዕረፍት ወደ ገንዘብ ተለውጦ የተከፈላቸው መሆኑንም በቃል ክርክር ወቅት ከሳሽ ስላመኑ በድጋሚ ሊከፈላቸው አይገባም ብሏል:: እንዲሁም ክፍያ በዘገየበት የጠየቁትን ክፍያ በተመለከተም የሚከፈላቸው ክፍያ አይኖርም ሲል ሳይቀበለው ቀርቷል::
ወደ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት
ከሳሽም በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የይግባኙን መዝገብ በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ቁጥር 337 ዘግቶ በማሰናበቱ የሰበር አቤቱታቸውን ለችሎት አቅርበዋል:: አመልካች በሰበር አቤቱታቸውም በዋናነት ያቀረቡት የቅሬታ ነጥብ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያና ካሳን ፍርድ ቤቶቹ በአዋጅ ቁጥር 377/1996፣ በኅብረት ስምምነቱና በሥራ መሪዎች የመተዳደሪያ ደንብ አግባብነት ባላቸው ድንጋጌዎች መሠረት መወሰን ሲገባቸው ሳይወስኑ ማለፋቸው አግባብ አይደለም ብሏል::
ተጠሪው በበኩሉ በሰጠው መልስ፤ ኮርፖሬሽኑ በደንብ ቁጥር 192/2003 የተቋቋመ ሆኖ እያለ አመልካች የተሻሩትን የሥራ መመሪያዎች ደንብና የኅብረት ስምምነት መሠረት በማድረግ የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈሏቸው ያቀረቡት ክርክር ተቀባይነት የለውም ሲል ተከራክሯል::
አመልካች ተጠሪው ላቀረቡት መልስ የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክረዋል:: የጉዳዩ አመጣጥ አመልካች ከሥራ የተሰናበቱት በሕገ ወጥ መንገድ ነው በሚል የሥር ፍርድ ቤቶች ከወሰኑ በኋላ ካሳና የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ሊከፈላቸው አይገባም ያሉት በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? በሚል መዝገቡ ለሰበር ያስቀርባል ሲባል በተያዘው ጭብጥ መሠረት ክርክሩ ምርመራ ተደርጎበታል::
ተጠሪው ድርጅት በአዲስ መልክ በደንብ ቁጥር 192/2003 የተቋቋመ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የሥር ፍርድ ቤቶች ፍርድ ለመስጠት መሠረት ያደረጉት የሥራ መሪዎች ደንብና የኅብረት ስምምነት ስለተሻሩ አግባብነት የላቸውም ሲል ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት ያለው መሆን አለመሆኑ ሊመረመር የሚገባ ሆኖ አግኝተናል ይላል ፍርድ ቤቱ::
በደንብ ቁጥር 192/2003 ተፈጻሚ የሆነው ከጥቅምት 19 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ስለመሆኑ በደንቡ አንቀጽ 12 የተደነገገ ሲሆን፤ አመልካችም ክሱን ያቀረቡት ጥር 27 ቀን 2004 ዓ.ም በመሆኑ ክሱ የቀረበው ደንቡ ጸንቶ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ነው:: በዚህ ደንብ ቀደም ሲል በየራሳቸው የማቋቋሚያ ደንብ ተቋቁመው የነበሩት አራት የስኳር ፋብሪካዎች የስኳር ኮርፖሬሽን በሚል መቋቋማቸውን ከደንቡ መገንዘብ የሚቻል ነው::
ይሁን እንጂ ተጠሪው ቀደም ሲል በደንብ ቁጥር 122/1998 እንደተሻሻለው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በሚል ሲጠራ የነበረ ሲሆን፤ የራሱ የሆነ የኅብረት ስምምነት እና የሥራ መሪዎች የመተዳደሪያ ደንብ ያለው ነው:: ተጠሪው የኅብረት ስምምነቱና የሥራ መሪዎች የመተዳደሪያ ደንቡ ተሽረዋል በሚል ክርክር ስለማቅረቡ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የማያመላክት ሲሆን ክርክር አቅርበዋል ቢባል እንኳን ፍርድ ቤቱ ባለመቀበል በተሻሩ የሥራ መመሪያዎች ደንብና የኅብረት ስምምነቱ መሠረት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሰጥቶ ከሆነ ጉዳዩን ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በማቅረብ ፍርዱን ማስለወጥ ሲገባው ይግባኝ አቅርቦ አላስለወጠም::
በዚህ በሰበር ደረጃ ባደረገውም ክርክር የኅብረት ስምምነቱ እና የሥራ መሪዎች የመተዳደሪያ ደንብ መሻራቸውን ከመግለጹ በስተቀር በየትኛው የኅብረት ስምምነትና የሥራ መሪዎች ደንብ እንደተተኩ አልጠቀሰም:: ስለሆነም የኅብረት ስምምነቱና የሥራ መመሪያዎች መተዳደሪያ ደንብ የተሻሩ ናቸው ሲል ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም::
ዳኞች እንደሚሉት፤ ወደ ጭብጡ ስንመለስ ተጠሪው የሥራ ውሉን ለመቋረጥ የጠቀሳቸው ምክንያቶች የአመልካች የሥራ አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ ነው፣ እንዲሁም በሥራ ላይ ቸልተኝነት አሳይተዋል በሚል እንደሆነ ለሥር ፍርድ ቤቶች በማስረጃነት ከቀረበው የስንብት ደብዳቤ የተረጋገጠ ሲሆን፤ ተጠሪውም አመልካች በሥራ አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ ስለመሆኑ የተመዘኑበትን ማስረጃ ባለማቅረቡ እንዲሁም በሥራ ላይ ቸልተኝነት አሳይተዋል ላለውም ምክንያቱን በመዘርዘር ማስረዳት ባለመቻሉ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ወደሚለው ድምዳሜ የስር ፍርድ ቤቶች ደርሰዋል::
በመሆኑም የሥራ ውሉ በሕገ ወጥ መንገድ መቋረጡ የተረጋገጠ ፍሬ ነገር እስከሆነ ድረስ ተጠሪ ካሳና የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ሊከፍል የሚገባ መሆን አለመሆኑን አግባብነት ካላቸው ሕጎች ጋር አገናዝቦ መመልከት ይገባል:: ከክርክሩ መገንዘብ እንደተቻለው አመልካች ሥራ መሪ ናቸው:: አሠሪው የሥራ ውሉን ቀሪ በማድረግ ወይም አላድስም በማለት ይህን ውሳኔ በግልጽ የሚያረጋግጥ በቂ ምክንያት የሌለው እንደሆነ ሠራተኛው ተገቢ የሆነ ኪሳራ የማግኘት መብት ያለው ስለመሆኑ በፍትሐብሔር ቁጥር 2573 ከተደነገገው መገንዘብ የሚቻል ነው::
በዚህ መልኩ በሕጉ የሥራ ውሉ በቂ ባልሆነ ምክንያት የተቋረጠ ከሆነ አሠሪው ኪሳራ የመክፈል ግዴታ ያለበት ስለመሆኑ በግልጽ ተደንግጎ እያለ የስር ፍርድ ቤቶች አመልካች የተሰናበቱት ያለበቂ ምክንያት መሆኑን በፍሬ ነገር ደረጃ ካረጋገጡ በኋላ ኪሳራውን ሳይወስኑ ማለፋቸው ሕጉን የተከተለ አይደለም:: ኪሳራ መክፈል ተገቢ መሆኑ ከታመነ ደግሞ ስለሚከፈልበት ሁኔታም አግባብነት ያላቸውን ሕጎች መመልከት የሚገባ ነው::
አመልካች በክሳቸው የስድስት ወር ደመወዝ ካሳ እንዲከፈላቸው ዳኝነት የጠየቁት አዋጅ ቁጥር 377/1996 መሠረት በማድረግ ነው:: አንድ የሥራ መሪ የሥራ ውሉ ያለ በቂ ምክንያት ሲቋረጥ ሊከፈል የሚገባው የኪሳራ ልክ ሠራተኛው ባለፈው ሶስት ወር ከተቀበለው ደመወዝ ሊበልጥ እንደማይችል በፍትሐብሔር ቁጥር 2574 (2) የተደነገገ ሲሆን ይህንኑ የሕግ አነጋገር በመያዝ በታኅሳስ ወር 2002 ዓ.ም ወደወጣው የተጠሪ የሥራ መሪዎች የመተዳደሪያ ደንብ ስንመለስ በአንቀጽ 51(1) በዚህ ደንብ ውስጥ የተደነገጉት እንደተጠበቁ ሆነው በሌሎች ሕጎች ፣ደንቦች ወይም በሌላ አኳኋን ተለይቶ የተወሰነው የተሻለና የበለጠ ጥቅም የሚያስገኝ ሆኖ በዚህ ደንብ ውስጥ ባልተጠቀሱም ሆነ በተጠቀሱ ጉዳዮች፣ በኅብረት ስምምነት የተደነገጉት፣በአሠራር ደንብ የተወሰኑትና የሚታወቁት ስለሥራ ሁኔታ፣ የሙያ ደህንነትና ጤንነት፣ የሥራ አካባቢ፣ ጥቅሞች፣ ግልጋሎቶች፣ ሥልጠና፣ የሥራ ውጤት መለኪያ ዘዴ እንዲሁም ይህን ደንብ የማይቃረኑ አግባብ ያላቸው ሌሎች የሥራ ውል ግንኙነቶች የሚመለከቱ ዝርዝር ድንጋጌዎች የሥራ መሪው የሥራ ውል አካል ሆነው ይቆጠራሉ በሚል ተደንግጎ እናገኛለን::
በዚሁ ድንጋጌ መሠረትም በፍትሐብሔር ሕጉ ከተመለከተው የኪሳራ መጠን ይልቅ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 43(4)(ሀ) የተመለከተው የካሳ መጠን የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝ በመሆኑ ለአመልካችም ተጠሪው ካሳ ሊከፍላቸው የሚገባው በዚሁ የአዋጁ አንቀጽ መሠረት ሊሆን ይገባል::
ሌላው አመልካች የጠየቁት የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ነው:: ተጠሪው የአመልካችን የሥራ ውል ሲያቋርጥ ቅድመ ማስጠንቀቂያ አለመስጠቱ የተረጋገጠ ጉዳይ ሲሆን የስር ፍርድ ቤቶችም የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ለአመልካች አይገባቸውም በሚል የወሰኑት አመልካች የሚሰሩት የሥራ ባህሪ በመግለጽ ሲሆን ለዚህም መሠረት ያደረጉት የፍትሐብሔር ቁጥር 2577(2) ድንጋጌን ነው::
በዚህ ድንጋጌ በንዑስ ቁጥር (1) የሥራው ውሉ ልዩ የሆኑ ችሎታዎችን የሚጠይቁ፣የእምነት ሥራዎች እንደሆኑ አሠሪው ውሉን ቀሪ የሚያደርግበትን ወይም የማያድስበትን ምክንያት ለማስታወቅ የማይገደድ መሆኑ የተደነገገ ሲሆን ኪሳራ ለመክፈል የሚገደደው ግን ውሉ እንዲቀር የተደረገው በማይገባ ጊዜና አንደኛውን ወገን ለመጉዳት ወይም ሊደርስበት የሚችለውን ጉዳት ባለማሰብ መሆኑ ሲረጋገጥ ነው:: ከዚህ ውጪ ግን የውሉ ያለ ማስጠንቀቂያ ቀሪ መሆን አሠሪው ለሠራተኛው ኪሳራ እንዲከፍል የሚያስገድድ አይሆንም::
በዚህ ጉዳይ ግን ውሉ ቀሪ የተደረገው በማይገባ ጊዜ ወስጥ ስለመሆኑ፣ ወይም ተጠሪው አመልካችን ለመጉዳት ወይም ሊደርስበት የሚችለውን ጉዳት ባለማሰብ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ውሉን ቀሪ ስለማድረጉ የተረጋገጠ ፍሬ ነገር የለም:: አመልካች በተጠሪው ደርጅት የኦዲት ክፍል ኃላፊ የነበሩ እንደመሆናቸው መጠን የሥራ ውሉ ልዩ ችሎታን የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ ሥራውም በእምነት የሚሠራ በመሆኑ አስቀድሞ የሥራ ውል የሚቋረጥ ስለመሆኑ ማስታወቅ የአሠሪውን ጥቅም ሊጎዳ የሚችልበት አጋጣሚ ሊፈጥር ስለሚችል ማስጠንቀቂያ አለመሥጠቱ በፍትሐብሔር ቁጥር 2577(2) እንደተመለከተው ኪሳራ እንዲከፍል የሚያስገድደው አይሆንም::
በመሆኑም የስር ፍርድ ቤቶች ተጠሪው ለአመልካች ከሚሠሩት የሥራ ባህሪ የተነሳ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ የሥራ ውሉን በማቋረጡ ምክንያት የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ለመክፈል አይገደድም ያሉት የሚነቀፍበት ምክንያት የለውም::
በመሆኑም ሃሳቡ ሲጠቃለል፤ የስር ፍርድ ቤቶች ለአመልካች የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ሊከፈላቸው አይገባም ያሉት ከዚህ በላይ በተገለጹት ምክንያቶች የተነሳ ተገቢ በመሆኑ የማስጠንቀቂያ ክፍያ ሊከፈላቸው አይገባም በሚል ፍርድ ቤቶቹ የወሰኑት ተገቢ ቢሆንም የሥራ ውሉ በሕገ ወጥ መንገድ የተቋረጠ ስለመሆኑ ተረጋግጦ ባለበት ሁኔታ ግን ካሳ እንዲከፈላቸው ሳይወስኑ ያለፉት መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በማግኘታችን ተከታዩን ውሳኔ ሠጥተናል ብሏል -ፍርድ ቤቱ
ው ሣ ኔ
የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመለያ ቁጥር 03537 በ15/10/2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሠጠውን ፍርድ እና የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመለያ ቁጥር 126268 በቀን 17/12/2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሠጠው ትዕዛዝ ተሻረ ፡፡ በተጨማሪ የሥር ፍርድ ቤቶች የሥራ ውሉ በተጠሪው ሕገ ወጥ ድርጊት ተቋርጦ እያለ ለአመልካች የካሳ ክፍያ እንዲከፈላቸው ሳይወስኑ ማለፋቸው ተገቢነት የሌለው መሆኑ ተጠቅሶ፤ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 43(4)(ሀ) መሠረት የአመልካች የቀን አማካይ ደመወዝ በ180 ተባዝቶ እንዲከፈላቸው ተወሰነ፡፡
የስር ፍርድ ቤቶች ከካሳ ክፍያ በስተቀር የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያም ሆነ ሌሎች ክፍያዎችን በተመለከተ የሠጡትን ውሳኔ የፀና ሲሆን፤ የካሳ ክፍያ አፈጻጸም ክሱን የያዘው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይጻፍ የተባለ ሲሆን፤ የፍርድ ቤት ወጪና ኪሣራ የየራሳቸውን ይቻሉ በማለት መዝገቡ ተዘጋ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 /2014