ሰሞኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መግለጫ አውጥቷል፡፡ አዲስ የተወለደው ክልል እስካሁን በዝምታ ስራውን እየሰራ ከሚዲያ ትርኢት ርቆ ስለቆየ መግለጫው ትኩረትን የሚስብ ነበር፡፡ረዘም ያለው መግለጫ ካህዴህ ለተባለ በክልሉ ለሚንቀሳቀስ ፓርቲ መግለጫ የተሰጠ ምላሽ ነበር፡፡
”በህዝቦች መፈቃቀድና መተባበር የተፈጠረ ክልል በተዛባ መረጃና ፕሮፖጋንዳ ሊናወጥ አይገባም!!” በሚል ርዕስ የተሰጠው መግለጫ ከክልሉ ርዕሰ መዲናነት ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ለካህዴህ መግለጫ የተሰጠው የክልሉ ምላሽ እንደሚለው ከሆነ ካህዴህ የክልሉ መመስረት ለከፋ ህዝብ የሚጎዳ ነው ብሎ መግለጫ እንደሰጠ እንዲሁም የክልሉ መዲና ከአንድ ከተማ ወደ ብዙ ከተማ መቀየሩ እንዳልተስማማው የሚያሳይ ነው፡፡
በመጀመሪያ ወደ ሌሎች ዝርዝሮች ከመግባታችን በፊት ጥቂት ማስታወሻዎችን እንያዝ፡፡አንደኛ ጉዳይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሀገሪቱ ላለፉት ሶስት አስርት አመታት ስትከተለው ከቆየችው ብሄርን መሰረት ያደረገ የክልል አደረጃጀት በተለየ ሁኔታ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥን ፤ሶሺዮ ኢኮኖሚን እና ፖለቲካዊ ትንታኔን ተከትሎ የተመሰረተ ክልል ነው፡፡
ይህም ማለት ክልሉ ከሌሎቹ ክልሎች በተለየ ስድስት የተለያዩ ህዝቦች ( ካፋ፣ ዳውሮ፣ ቤንች ሸኮ፣ ሸካ፣ምዕራብ ኦሞ እና ኮንታ) በጋራ ስምምነት የመሰረቱት ክልል ነው፡ ፡ ይህ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት አዲስ ልምምድ ነው፡፡በመሆኑም የዚህ ክልል ስኬትም ሆነ ውድቀት ብዙ አንድምታ ይኖረዋል፡፡
የክልሉ ምስረታ ጉዳይ ከለውጡ ወዲህ ከተከናወኑ ትልልቅ ፖለቲካው እርምጃዎች መሀከል አንዱ ሲሆን በአንድ ጎን የህዝብን ራስን በራስ የማስተዳደር እድል ለሚጠይቁ የፖለቲካ ሀይሎች መሻታቸውን የመለሰ ነው፡፡በሌላ መልኩ አሁን ያለው በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌደራላዊ አወቃቀር ሌላ አማራጭ ያስፈልገዋል ለሚሉም እንዲሁ ሌላኛው አማራጭ በተግባር ሲውል የሚታይበትን እድል የሰጠ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ግን የክልሉ ምስረታ የስድስቱን ህዝቦች የዘመናት የልማት እና የዴሞክራሲ ጥያቄ መልስ የመስጠት ሂደት ያስጀመረ አጋጣሚ ነው፡፡ስለዚህም ክልሉ የውስጡንም ሆነ የውጪውን ሀይል ፍላጎት ያረካ ክልል ነው ማለት እንችላለን፡፡ይህ የካህዴህ መግለጫ መልስ ያስፈለገውም ከዚህ አዎንታዊ መንፈስ የሚቃረን በመሆኑ ይመስላል፡፡
በሌላ መልኩ ይህ አዲስ ክልል አዲስ አሰራርም ይዞ መጥቷል፡፡እሱም ብዝሀ ከተማነት ነው፡፡ይህም በክልሉ ህገ መንግስት የሰፈረ ነው፡፡በህዳር 14/2014 የጸደቀው የክልሉ ህገ መንግስት በስድስተኛ አንቀጹ ላይ “የክልሉ መንግስት ብዝሀ ዋና ከተሞች ይኖሩታል፡፡ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል” ይላል፡፡
ይህም በሌሎቹ ክልሎች ካለው የተለየ እና ለኢትዮጵያ ፖለቲካም አዲስ ልምምድ ነው፡፡እነዚህ ሁለት ምክንያቶች ማለትም ምልክአ ምድርን እና ሶሺዮ ኢኮኖሚን የተከተለ የክልል አመሰራረት እና ብዝሀ ዋና ከተማነት አዲስ እና ምናልባትም ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥንቅጥ ምላሽ ሊሰጡ የሚችሉ ተስፋ ሰጪ ክስተቶች ናቸው፡፡ስለዚህም እነዚህን ፖለቲካዊ እርምጃዎች በጥንቃቄ መምራት ያስፈልጋል፡፡
ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንመለስ ባለ 7 ነጥቡ የካህዴህ መግለጫ መሰረታዊ ጭብጡ አንድ
ነው፡፡ ይሄውም የክልሉ ብዝሀ ከተማነትን መቃወም ነው፡ ፡ እልፍ ብሎም በሶስተኛ ነጥቡ ላይ የክልሉ ርእሰ መዲና መሆን ያለበት የካፋ ዞን ነው ይላል፡፡ሌሎቹ የተቃውም አመክንዮዎች የክልል ርዕሰ መዲና በመሆን ከሚገኝ ከልማት ተጠቃሚነት እንዲሁም የክልሉ ርዕሰ መዲናዎች ብዙ ቦታ መሆናቸው ከሚያመጣው ሎጀስቲካዊ ጣጣ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
በነዚህ መከራከሪያዎች ላይ ብዙ ማለት አይቻልም፡ ፡ምክንያቱም የክልሉ ህዝብ ከ6 ወር በፊት ባጸደቀው ህገ መንግስት ላይ ወስኖባቸዋልና፡፡ይልቁንም ብዙ ማለት የሚቻለው ይህን አዲስ ዴሞክራሲያዊ የሆነ እመርታ ሳይጨናገፍ እንዴት እናስቀጥለው በሚለው ላይ ነው፡፡
ከላይ እንደተገለጸው ይህ ክልል ስድስት ህዝቦች በስምምነት የመሰረቱት የተለየ ክልል ነው፡፡ይህም አዲስ እና ትልቅ እመርታ ነው፡፡እያንዳንዱ ዞን እና ብሄር ክልል ልሁን ብሎ ሀገር በሚያምስበት በዚህ ወቅት በስምምነት በሰላማዊ መንገድ ክልል መሆን መቻል አስገራሚ እና ሊበረታታ የሚገባ የፖለቲካ እርምጃ ነው፡፡
በሌላ መልኩ ቀደም ብለን እንደገለጽነው ክልሉ ዋነኞቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ርእዮቶች የተዋሀዱበት እና የተስማሙበት ነው፡፡ሶስተኛ ባለብዙ ርዕሰ ከተማ መሆኑ በሌላው አለም የተለመደ ቢሆንም በእኛ ሀገር ሆኖ የማያውቅ በመሆኑ ይህም ተስፋ ሰጪ እመርታ ነው፡፡
የተለያዩ ሀይሎች በአንዲት ከተማ ላይ የበላይ ለመሆን በሚተራመሱባት ሀገር ሁላችንም ልማቱንም ውሳኔውንም በጋራ እንካፈል የሚል መንፈስ አስደሳች ነው፡፡ለዚህም ነው እንደ ካህዴህ ያሉ ፓርቲዎችን መግለጫ በጥንቃቄ ማየት የሚያስፈልገው፡፡ በብዙ ተስፋ የተመሰረተ ክልል ወደ ኋላ እንዳይንሸራተት እና ትርምስ ውስጥ እንዳይገባ ሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች እርምጃቸውን ሊጠነቀቁ ይገባል፡፡
የክልል መዲናነትን በተመለከተ እንኳን በክልል ከተማነት ይቅርና በሀገርም ደረጃ ቢሆን ከአንድ በላይ መዲና ያላቸው ከተሞች ብዙ ናቸው፡፡ለምሳሌ ያህል ናይጄሪያ ፤ ታንዛንያ ፤ ቤኒን ፤ አይቮሪኮስት እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከአንድ በላይ መዲና አላቸው፡፡ከአፍሪካ ውጭም ሆላንድ ፤ ቦሊቪያ ፤ እስራኤል እና ሌሎችን መጥቀስ እንችላለን፡፡ስለዚህም በሀገር ደረጃ የሰራ በክልል ደረጃ አይሆንም ማለት አይቻልም፡፡
እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራት ደግሞ ህግ አውጪው፤ ህግ ተርጓሚው እና ህግ አስፈጻሚው አካላት በመዲናይቱ ዋሽንግተን ቢቀመጡም እንኳ የኢኮኖሚ መዲናዋ ኒውዮርክ ናት፡፡ኒውዮርክ የአሜሪካ የኢኮኖሚ ማዕከል የሆነችው በነበራት መልክአ ምድራዊ ብልጫ ነው፡፡ ከተማዋ ያሏት ወደቦች እና ለወደቦች ቅርበት አውሮፓውያን ነጋዴዎች ማረፊያቸው እንዲያደርጓት እንዳስገደዳቸው ታሪክ ይናገራል፡፡
ከዚህ በመነሳት ከደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ከተሞች መሀከል አንዷ ባላት መልክአ ምድራዊ ወይም ሌላ አይነት ብልጫ የክልሉ የኢኮኖሚ ማዕከል ስትሆን ሌላዋ የፖለቲካ ማዕከል ልትሆን እና የክልሉን ምክር ቤት ልትይዝ ትችላለች፡፡ የክልሉ ፌደራል ፍርድ ቤትን ሌላኛዋ ከተማ ልትወስድም ትችላለች፡፡
በዚህ መልኩ የክልሉ የመንግስት ስራ አንድ ቦታ ላይ እንዳይከማች እና ሁሉንም ተጠቃሚ እንዲያደርግ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከዚያ በተለየ የክልሉ መዲና አንድ ቦታ ይሁን ከተባለ ክልሉን ከመሰረቱት ስድስት ህዝቦች አምስቱ የሀዋሳው ጉዞ ቀርቶ ወደ አዲሱ መዲናቸው መሄድ ይቀጥላሉ ማለት ነው፡፡ይህ ደግሞ ከክልሉ የመመስረት አላማዎች አንዱን ብላሽ ያደርገዋል፡፡
ሲጠቃለል ሀሳብን መግለጽ እና ተቃውሞን ማሰማት መብት ነው፡፡ለክልሉ እድገትም
ይጠቅማል፡፡ ነገር ግን ከ6 ወር በፊት ያጸደቁትን ህገ መንግስት ገና በ6ኛው ወር አልተሳተፍኩበትም ማለት አያዋጣም፡፡ እኔ በፈለግኩት መንገድ ነገሮች ካልሄዱ ተነጥዬ ክልል እሆናለሁ ማለት በተጨባጭ የማያስኬድ ሀሳብ ነው፡፡
ብቸኛው መፍትሄ የተገኙ ድሎችን አጠናክሮ በመቀጠል በሰጥቶ መቀበል መርህ መፍትሄዎችን መፈለግ ነው፡፡በዚህ መንገድ የሚመጣ የዚህ ክልል ስኬት ምናልባትም ለኢትዮጵያ አዲስ አማራጭ መስመር ሊፈጥር ይችላል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 ቀን 2014 ዓ.ም