ሁሌም ሲባል እንደሚሰማው፣ እንደሚነገረውና እኛም እንደምናውቀው ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ በጎ አድራጎት ተቋማትና ማህበራት የምን ጊዜም የልማት አጋሮች ናቸው። ንቁና ተሳትፎ አሳታፊ ሲቪክ ማህበረሰብ ከመፍጠር አኳያም የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም። ይህ ማለት በጤናማው አመለካከትና ተገቢ በሆነው በእነሱ ሰብአዊ ተግባር ላይ የተመሰረተ ድምዳሜ ሲሆን፤ ከአላማው ውጪ ውሎ ከተገኘ ግን ምላሹ ተቃራኒ ነው፡፡ ምድቡና ትርጓሜውም ሌላ ይሆናል፡፡
የበጎ አድራጎት ተቋማትን ታሪክ በሀገራችን የሚነሳው ከ1965 ዓ.ም ነው፡፡ በወሎና ትግራይ ከፍተኛ ድርቅ በመከሰቱ ምክንያት ቁጥራቸዉ በርከት ያሉ መንግሰታዊ ያልሆኑ ዕምነት ተኮር ድርጅቶች ተፈጥረዋል፡፡ በዚህም ቀላል የማይባል ሰብአዊ ድጋፍና ተሳትፎ መደረጉን በድርሳናት ሰፍሮ እናገኘዋለን። ይህ ደግሞ በሺህ ለሚቆጠሩ፣ ለዛሬዎቹ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መፈጠር ምክንያት ሆኗል። ከአስር ዓመት በኌላም እንዲሁ እንደገና በ1977 ዓ.ም ድርቁ በተመሳሳይ በወሎና ትግራይ አካባቢ በስፋት ሲከሰት እነዚህ ድርጅቶች ደርሰው በድጋፋቸው ችግሩን አቅለውታል፡፡ ለመቋቋምም አስችለዋል።
በአገራችን አጠቃላይ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች መፈጠርና ወደ ተግባር መግባት ታሪካዊው መነሾ ይሄው ነው። በተለይም ከደርግ ዘመን በኌላ ወደ ስራ በገባው ሕገመንግስት የመደራጀት መብትን በመጠቀም በርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት መፈጠር ችለዋል:: ይህን ስንል ግን የመረዳዳት ባህል፣ የመደጋገፍና በጋራ ችግርን ተጋፍጦ በጋራ መፍትሄ ማምጣት ወዘተ በአገራችን አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ አለ፤ ነበርም። በመኖሩም ነው በተለይ በአሁኑ ወቅት ”አገር በቀል እውቀት”ም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ”አገር በቀል ኢኮኖሚ” የሚሉት ጽንሰ-ሀሳቦች እንደ ገና ልዩ ትኩረትን አግኝተው የሁሉም መነጋገሪያና ርእሰ ጉዳይ ሊሆኑ የበቁት። ችግሩ ተግባራዊነቱ ካልሆነ በስተቀር ማለት ነው።
ሁሌም ”በኢትዮጵያ አገር በቀል እውቀቶች ተጠብቀውና ዳብረው ለትውልዱ እየተላለፉ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ምሁራን በሚፈለገው ደረጃ ሚናቸውን እየተወጡ እንዳልሆነ›› ጥናቶች የሚያመላክቱ ሲሆን፤ በቅርቡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአምቦ ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት አካሂዶት በነበረው ኮንፈረንስ ላይም የተረጋገጠው ይኸው ነው። መፍትሄውም ”መስራት፣ ዘርፉን ማልማት ይገባል” የሚል ነው፡፡ ይህ አገር በቀል እውቀትን ወደ ተግባር ከመቀየር አኳያ ችግር መኖሩ የተገለፀው በጥናትና ምርምር ስራዎች ብቻ አይደለም፡፡ አዲስ ዘመን ከአነጋገራቸው የተለያዩና በየደረጃው ከሚገኙ አካላትም ነው፡፡
በኦሮሚያ ክልል የቡሶ ጎኖፋ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ገረመው ኦሊቃ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደ ገለፁት፤ እኛ አገር በቀል እውቀትን ተጠቅመናል፤ ወደ ተግባር ቀይረነዋል ማለት አንችልም። እንደ አገር ካየነውም ምንም የተሰራ ስራ የለም። በመሆኑም በዚህ ዘርፍ ጠንክረን ልንሰራ ይገባል። ሁሉም በየክልሉ ያለውን አገር በቀል እውቀት ለይቶ በማውጣትና በማልማት ወደ አገራዊ ተጠቃሚነት ማምጣት አለበት።
አክለውም፣ በኦሮሚያ ክልል በጉዳዩ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን፤ አንዱም የገዳ ስርኣት አካል የሆነውን ”ቡሶ ጎኖፋ”ን ወደ ዘመናዊ ተቋምነት የመቀየሩ ስራ ነው፡፡ እሱም ተከናውኗል። (ባለፈው ሳምንት በዚሁ አምድና ገጽ ላይ የወጣውን ጽሑፍ ይመልከቱ።)
ያለንበት ሁኔታ
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ”የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የፕሮጀክት አፈጻጸምና ክትትልን በተመለከተ የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት” (ጥር 2006 ዓ.ም)፤ ”በኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር ሕግና ስርዓትን በተከተለ መልኩ በጎ አድራጎት ድርጅቶችንና ማህበራትን መመዝገብ፣ ማስተዳደርና መቆጣጠር የተጀመረው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሲሆን፣ በወቅቱ የአገር ግዛት ሚኒስቴር ተብሎ ይጠራ የነበረው መንግስታዊ ተቋም በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐብሔር ሕግ ከቁጥር 404እስከ 549 ባሉት ድንጋጌዎችና በዝርዝር ለማስፈፀም በ1952 ዓ.ም በወጣው የማህበራት ምዝገባ ደንብ ቁጥር 321/1959 መሠረት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራትን ሲመዘግብ ቆይቷል፡፡” በማለት ከገለፀ በኋላ፤ ከወታደራዊው መንግስት (ደርግ) በኋላ ባለቤት አጥቶ እዚያና እዚያ ሲል መቆየቱን፤ በተለያዩ ጊዜያትም በተለያዩ ተቋሟት ሲተዳደር መኖሪን ይናገራል። ከዛስ?
በዚሁ አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 621/2001) አንቀጽ 8 መሠረት በመንግስት በተሰየሙ ሰባት አባላት በሚመራ ቦርድ የሚተዳደር የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ እንደ አንድ የፌደራል የመንግስት መስሪያ ቤት ለፍትህ ሚኒስቴር ተጠሪ ሆኖ በመቋቋም ከመስከረም 2002 ዓ.ም ጀምሮ በአዋጁ የተቀመጡትን ተልዕኮዎች ለመፈጸም እየሰራ ይገኛል፡፡ የፌደራል አስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 የኤጀንሲው ተጠሪነት ለፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እንዲሆን ተደረገ፡፡ ከዚህ በኋላስ?
በፈረንጆቹ በ2019 የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በሃገራችን ከ3ሺህ፤ በክልል ደግሞ ከ1ሺህ የሚልቁ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አሉ። የበጎ አድራጎት ድርጅቶቹ ባላቸው አደረጃጀትና የሚሰማሩባቸውን አላማዎች መሠረት በማድረግ፤ ተመሣሣይና ተቀራራቢ አላማ ያላቸውን በመለየት፣ በአዋጅ 621 /2001 መሠረት የተቋቋመው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ”የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራትን የዓላማ ማስፈፀሚያና አስተዳደራዊ ወጪዎችን መወሰን የወጣ መመሪያ ቁጥር 2/2003” በሚል ርእስ ባረቀቀውና ”ይህ መመሪያ ከጥር 15 ቀን 2002 ዓ.ም ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡” በሚለው ሰነድ መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ በሚከተሉት አስር ዘርፎች የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲንቀሳቀሱ ተደረገ፡፡ ዘርፎቹም:-
በሴቶችና ህፃናት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፤ በኤች.አይቪ.ኤድስ መከላከል እና ጤና ማስፋፋት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፤ በግብርና፣ ምግብ ዋስትና፣ ሕይወት ማዳንና አካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ፤ በትምህርት ማስፋፋት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ፤ በአካል ጉዳተኞች፣ ጎዳና ተዳዳሪዎችና አረጋዊያን በመደገፍ ስራ የሚንቀሳቀሱ፤ በባህል፣ ቅርስ፣ ወጣቶችና ስፖርት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ፤ በሰብዓዊና ዴሞክራሲያው መብቶች ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ፤ በግጭት አፈታት፣ የፍትህና የሕግ አፈጻጸም ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ፤ በአቅም ግንባታ፤ ምርምርና ጥናት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ፤ በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ናቸው::
ኤጀንሲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በአገሪቱ 3ሺህ 115 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ተመዝግበው በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 416 የውጭ አገር በጎ አድራጎት ድርጀቶች፣ 2ሺህ 646 በኢትዮጵያ ውስጥ የተደራጁ (አገር በቀል) በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት፤ እንዲሁም 53 ኅብረቶች ናቸው በማለት ያስነበበን ሪፖርተር ጋዜጣ (17 ኦገስት 2016) ነው፡፡
በሃገራችን ያሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጤና፤ የህጻናት ልማት፤ ትምህርት፤ ማህበራዊ ድጋፍ፡ አቅም ግንባታ፤ ገቢ ማስገኛ አካባቢ ጥበቃ እና እርሻ ስራና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ከዚሁ ከበጎ አድራጎት ወይም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች (ኤንጂኦ) ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ የሚሰማው ነገር ድርጅቶቹና ማህበራቱ ለህብረተሰቡ ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ይልቅ የግለሰቦች የሀብት ምንጭና መጠቀሚያ ተደርገዉ የመታየታቸው ጉዳይ ሲሆን፤ ይህ ጽሑፍ በአሁኑ ሰዓት የዚህ አይነቱ አተያይ እየከሰመ፣ በጎ አድራጎት ድርጅቶቹም ወደ ሰብአዊ ተግባራቸው በማተኮር ህብረተሰብን በማገልገል ላይ ናቸው በሚል ታሳቢ የቀረበ ነው።
በአንድ ወቅት ሲነገርለት የነበረው (አሁን አለ?) ”የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት መድረክ” የድርሻውን ይወጣል የሚለውም እንደ ታሳቢ ተወስዷል። ”መንግስት ለምን የመቆጣጠሪያ አሰራርን ዘረጋ?” የሚለው ቅሬታም ተወግዷል ተብሉ ይታሰባል። ያም ሆኖ ግን ኤጀንሲው ወደ ስራ እንደ ገባ ባደረገው ምርመራና የማጣራት ስራ መሰረት፤
”የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ከታዩባቸው ችግሮች መካከል ከተቋቋሙለት ዓላማ ውጪ መንቀሳቀስ፣ ያለኤጀንሲው ፈቃድ የባንክ አካውንት መክፈት፣ የገቢ ምንጫቸውን አለማሳወቅ፣ ዓመታዊ የሥራና የኦዲት ሪፖርት በወቅቱ አለማቅረብ፣ የቋሚ ንብረት ዝርዝር አለማሳወቅ፣ የፕሮጀክት ስምምነት ሳይፈራረሙ መሥራት፣ አስተዳደራዊ ወጪዎችን ከዓላማ ማስፈጸሚያ ወጪዎች ጋር መቀላቀል፣ አስተዳደራዊ ወጪ ከ30 በመቶ በላይ መጠቀም፣ ልማትን ከሃይማኖት ጋር ቀላቅሎ መሥራት፣ ያለፈቃድ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ መሰማራት ለአብነት የሚጠቀሱ ግኝቶች ናቸው፡፡ [… በመሆኑም] በ2008 በጀት ዓመት 122 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ተዘግተዋል፡፡
[…] ባክነር አዶፕሽን ኤንድ ማተርኒቲ ሰርቪስ፣ ግሎባል ኢንፋንቲልና ሜዲስን ዱሞንድ የተባሉ ሦስት የውጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በፈጸሙት የሕግ ጥሰት ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ያሉባቸውን ችግሮች ባለማስተካከላቸው ተዘግተዋል፡፡ […] መሥፈርቱን ያሟሉ 187 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ተመዝግበዋል፡፡ ለ803 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የፈቃድ እድሳት ተሰጥቷል፡፡” በማለት ያሰፈረውን ሪፖርት መጥቀሱ ተገቢ ይሆናል።
ወደ አገር በቀሎቹ እንምጣ
”ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው።” በሚል መርህ የሚመራው ሜቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ዛሬ የደረሰበትን ደረጃና እየሰጠ ያለውን ማህበራዊ አገልግሎት በተመለከተ በማእከሉ ማደግና መስፋፋት መገረም ብቻ ሳይሆን፤ በ”ይቻላል!!!” ሁሉ እንደሚደመም ምንም ጥርጥር የለውም።
በታህሳስ 2002 ዓ.ም የቤተሰቦቻቸውን ቤት መነሻ አድርገው በ10 ተረጂዎች የተጀመረው ይህ ማእከል በመስራቹና ተግባሩን ”የሕይወቴ ጥሪ ነው” ሲሉ በሚገልፁት አቶ ቢኒያም በለጠ የሚመራ ሲሆን፤ ከተቋቋመበት አላማ ሌላ ሌሎች በርካታ መሰል ድርጅቶች እንዲፈጠሩ አርአያ ለመሆን የበቃ የአሁኑ ትልቅ፣ የወደ ፊቱ ግዙፍ ተቋም ነው።
ተቋሙ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማንን ከጎዳና በመሰብሰብ የላቀ ሰብዓዊነት ያለው፤ ከላይ በጠቀስነው መርህ የሚመራ ዓመታትን ያስቆጠረም ነው። አሁንም አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያንና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በክልሎች እየተዘዋወረ፤ የግንባታ ስፍራዎችን እየተረከበና እየገነባም ይገኛል። በባህር ዳር፣ ድሬ ዳዋ፣ ኢሉ አባቦራ፣ ጎሬ … ቦታዎችን ተረክቧል፤ ወደ ግንባታ የተሸጋገረባቸው አካባቢዎችም አሉ።
እኤአ ኤፕሪል 11፣ 2021 ይፋ በሆነ ዜና እንደ ተነገረው፤ ማዕከሉ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተረጂዎችን ቁጥር በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ወደ 10ሺህ ለማድረስ እየሰራም ይገኛል። አረጋውያንንና አዕምሮ ህሙማንን መሰረታዊ ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር አምራች ዜጋ በማድረግና እና ከተረጂነት ተላቀው እንዲኖሩ በማስቻል ረገድ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ነው። ለዚህ ሁሉ ስኬቱ፣ የህዝቡን ድጋፍ ለማግኘቱ፣ የህብረተሰቡ ተሳትፎና የእርዳታ ፈላጊዎቹ ተጠቃሚነት ዋናውን ድርሻ የተጫወተው የማእከሉ አገር በቀልነት መሆኑ በብዙ መልኩ ተረጓግጧልና ሌሎች ይማሩበታል ተብሎም ይታሰባል።
ተስፋ አይነ ስውራንና አካል ጉዳተኞች ማቋቋሚያ ማዕከል፣ ፍቅር ለሕፃናትና ለእናቶች የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ ሙዳይ፣ ኢንስፓየርድ ኢትዮጵያ ዩዝ አሶሲየሽን፣ ሀገር ፍቅር በጎ አድራጎት ማህበር፣ የኮቪድ-19 መከሰትን ተከትሎ የተፈጠሩ በርካታ ማህበራትና ድርጅቶች (ለምሳሌ ዱብቲ በጎ አድራጎት ማህበር) ወዘተ እያለ የሚቀጥል የበርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ፤ አገር በቀል እርዳታ ድርጅቶችና ማህበራት ተቋቁመው ሰብአዊ ድጋፎችን በማድረግና ሀላፊነታቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ።
ይህ በየትኛውም መልኩ የሚበረታታ ሲሆን፤ ችግሩና አሳሳቢው ጉዳይ የት ይደርሳሉ የሚባሉት እነዚህ ማህበራዊና ሰብአዊ ተቋማት ብቅ ጥልቅ የማለታቸው፣ እየታዩም የመክሰማቸው ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ብዙዎቹ ከእነ ሜቄዶኒያ ትምህርትንና ልምድን ሊወስዱ ይገባል የምንለው። ወደ ማሳያችን እንዝለቅ፤
”መሠረት በጎ አድራጎት ድርጅት” ይባላል። የተመሰረተው ቅን ልቦና ካላቸው ዜጎች አንዷ በሆኑት ወይዘሮ መሰረት አዛገ ነው። ታዳጊ እናቶች እና ልጆቻቸውን ከጎዳና ላይ አንስቶ ከመርዳት ባለፈ ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን በመስጠት እራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ይህ አገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅት፤ በአንድ ወቅት ”መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት 15ሺህ ለችግር የተጋለጡ ህፃናትና ሴት ተማሪዎችን ለትምህርት ለማብቃት የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አደረገ” የሚል ተስፋ ሰናቂ ዜና ሲነገርለት እንደነበረ የሚታወስ ነው።
በለጋ እድሜ የልጅ እናት መሆን የሚያመጣውን ችግር ለመቅረፍ በጎዳና ላይ የወደቁ እናቶችን በመሰብሰብ እና መጠለያ በመስጠት የተሃድሶ መርሃግብር እንዲያገኙና በኋላም ቤት ተከራይተው እራሳቸውን ችለው እንዲወጡ ለመርዳት እራሷ እየመራች የምትገኘው መሰረት፤ በአሁኑ ሰዓትም አንዳንድ የሚደርሱባትን ጫናዎች ቢኖሩም ችግሩን ተቋቁማ ተግባሯን አስቀጥላለች፡፡ በዚህም ከበርካቶች ”እናታችን” የሚል መጠሪያን አትርፋበታለች።
ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ካደረጉት፣ በ”መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት” እየታገዙ ከሚገኙትና ልዩ እንክብካቤን እያገኙ ካሉት መካከል አንዷ የሆነችውና የልጅ እናቷ እመቤት ከበደ እንደነገረችን፤ ሁሉ ነገር ልዩ ነው። እናትና አባት የማያደርገው ሁሉ ይደረግላታል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም መንጃ ፍቃድ ለመያዝ እየሰለጠነች ሲሆን፤ ስትጨርስም ባጃጅ ለመያዝና እራሷን ለመቻል እቅድ አላት፡፡
ሌላዋ፣ የልጅ እናትዋና የልብስ ስፌት ማሽን ስልጠና እየወሰደች ያለችው ሀረግ አለሙ ትባላለች፡፡ ከድርጅቱ ተጠቃሚ እንደሆነችና ድርጅቱ ከቤተሰብም በላይ እየተንከባከባቸው እንደሚገኝ ነግራናለች። በአጠቃላይ በየትም አገር በጎአድራጎት ድርጅቶች ያስፈልጋሉ። በመሆኑም በብዛት ሊኖሩ፣ ከሚመለከታቸው አካላትም አስፈላጊው ሁሉ ሊመቻችላቸው፤ እነሱም የሚጠበቅባቸውን በአግባቡ ሊያደርጉ …. ይገባል። ይህንን ሁሉ ስንልም፣ ለአንድ አገር ሁለንተነዊ እድገት የአገር በቀል ተቋማት ሚና የሚተካ አለመሆኑን፤ በብዛትም ሊፈጠሩ የሚገባ መሆኑን ከስሩ በማስመር ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3 /2014